>

‹ዳውን ዳውን ኬንያታ!› እያሉ በአደባባይ መጮህ የለም (ዮናስ ሃጎስ)

የኬንያ ምርጫ እንደተጠበቀው በጣም አስጊ ሳይሆን አብቅቶለታል። አዲሱ ተመራጭ ኡሁሩ ኬንያታ ቃለ መሐላ ለመፈፀም ገና 24 ቀናቶች ይቀራቸዋል። ከምርጫው ሁለት ወራት በፊት በምርቻው ሰበብ ተቃዋሚዎች የሚያስነሱባቸውን ሕዝባዊ ዓመፅ በማንኛውም መስዋዕትነት ለመመከት መቁረጣቸውን ዘመናዊ የሆኑ የአድማ መበተኛ መሳርያዎችን በመግዛትና ከዚያም በኋላ 56 ሰልፈኞችን በጥይት እስከመግደል ድረስ እርምጃ ወስደው ዓመፁን መግታትና ማቆም ቢችሉም አሁን ተቃዋሚው ናሳ ይዞባቸው የመጣውን ጣጣ ግን እንዴት እንደሚወጡት ፍፁም ግራ ተጋብተዋል።
***

ናሳ ሕዝባዊ ዓመፅ በመጥራት ደጋፊ ወጣቶቼን አላስፈጅም በማለት አዲስ ወደሆነ ሕዝባዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ተሰማርቷል። በዚህ ሕዝባዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ከፖሊስ ጋር መሯሯጥ የለም። በፖሊስ መገደል የለም። ‹ዳውን ዳውን ኬንያታ!›

እያሉ በአደባባይ መጮህ የለም። ግን ይህ እንቅስቃሴ እንደታሰበው ከተቀናጀ ኡሁሩ ኬንያታ ከ24 ቀናት በኋላ ቃለ መሐላ የሚፈፅምባት ሐገር ሁሉ ላትኖረው ትችላለች።

***
የናሳ አዲሱ እንቅስቃሴ ሕዝባዊ እንቢተኝነት የሚሰኝ ሲሆን ይህ ንቅናቄ የመጀመርያ ዒላማው ያደረገው በኬንያታ ቤተሰቦች የተያዙና በምርጫው ጊዜ ለገዢው ፓርቲ ድጋፍ ሰጥተዋል ያሏቸውን የንግድ ተቋማት በሙሉ ቦይኮት ማድረግ ነው። የሐገሪቷ ግዙፉ የቴሌኮም ኩባንያ ሳፋሪኮም ዒላማ ከተደረጉት ድርጅቶች አንደኛው ሲሆን በዛሬው እለት የተቃዋሚው ፓርቲ ተመራጭ የሆኑ የፓርላማ አባላት የሳፋሪኮም ሲምካርዳቸውን በሌላ ቴሌኮም ኩባንያ ለማስቀየር ሰልፍ ይዘው ታይተዋል። የንግድ ተቋማቱ ዝርዝር በጣም ረዥም ሲሆን ንብረትነቱ የኬንያታ የሆነው የወተት ተዋፅዖ አምራች ብሩክሳይድና በመላው ኬንያ ቅርንጫፎች እንዳሉት የሚነገረው የኢኩዊቲ ግሩፕ ባንክ ይገኙበታል።
***
ሕዝባዊ እንቢተኝነቱ በጠረፍ አካባቢ ደግሞ በባሰና ጫን ባለ ሁኔታ ነው የተከሰተው። ሞምባሳን ጨምሮ የኬንያ ጠረፍ ክልሎች ሕብረት ነሐሴ ላይ የተደረገው ምርጫ የተጭበረበረ እንደነበረና የኦክቶበር 26 ምርጫ የምርጫ ቦርድ ሳይስተካከል የሚካሄድ ከሆነ የመገንጠል ትያቄ እንደሚያቀርቡ አስጠንቅቀው እንደነበረ ባለፈው አስነብቤያችኋለሁኝ።
እነሆ ዛሬ ቃላቸውን ጠብቀው ከታች በምትመለከቱት ቪድዮ ላይ በሰጡት መግለጫ የጠረፍ ክልሎች በአምባገነን መንግስት መተዳደር ስለማይፈልጉ ከኬንያ ለመገንጠል የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ከጠበቆቻቸው ጋር ሆነው በሕገ መንግስቱ መሰረት እንደጀመሩ አሳውቀዋል። ይህ የመገንጠል ትያቄ ከተሳካ ኬንያ ከኢትዮጵያ ቀጥሎ በግንጠላ ምክንያት የባህር ወደቦቿን የምታጣ ሐገር ልትሆን ትችላለች።
***
ምክትል ፕሬዝዳንቱ ዊልያም ሩቶ በናሳ በተጠራው ቦይኮት ስማቸው ለተካተተ ድርጅቶች ዛሬ ባስተላለፉት መልዕክት ድርጅቶቹ ምንም እንዳልተፈጠረ ስራቸውን እንዲቀጥሉና መንግስት ከጎናቸው እንዲቆም እንደሚያደርጉ ቃል ገብተዋል።
Filed in: Amharic