>

‹‹ኢትዮጵያን በዛሬ መልኳ የፈጠራት ድንጋጤ ነው›› ሰሎሞን ዴሬሳ (በዘላለም ክብረት)

ሰሎሞን ደሬሣ የመጀመሪያውን ግጥሙን የጻፈው ለአንዲት ልጅ የሚላክ የፍቅር ደብዳቤ አስር ሳንቲም ተከፍሎት ነበር፡፡ የዩንቨርስቲ ትምህርቱን አቋርጦ እንደገና በነፃ የትምሕርት እድል አውሮፓ የገባው ሶሎሞን ከደራሲነት እስከ ሐያሲነት፤ ከጋዜጠኝነት እስከ ፍልስፍና መምሕርነት … ብቻ ያልሰራው ሥራ አልነበረም፡፡ ‹‹በፓሪስ እንደ ጄምስ ባልድዊን ካሉት ታላላቅ ጸሐፊዎች ጋር አብሮ መዋል እኔንም ጸኃፊ ያደረገኝ መስሎኝ ነበር›› የሚለው ሰሎሞን፤ አያይዞም ‹‹ያሳደጉኝ እነ [ባልድዊን] እንጅ የፈረንሳይ ዩንቨርስቲ አልነበረም›› ባይም ነው፡፡ … እንዲህ እንዲህ እየተባለ የሰሎሞን ሕይወት መዘከሩ አይቀርም፡፡

Inline image 1
ሰሎሞን ዼሬሣ

ከዛ ይልቅ ግን ሰሎሞን በሕይወት ላይ የነበረው ሕልዋዊ (existentialist) እሳቤ፣ ኢትዮጵያን የሚረዳበትን መንገድ፤ ስለ ማንነት ያለውን ግንዛቤ ሰሎሞን ከ19 ዓመታት በፊት በታሕሳስ 1991 ለሪፖርተር መጽሔት የሰጠውን አንድ ቃለ-ምልልስ ላይ አምስት አንቀፆች መዝዘን ብናየው የሰሎሞንን ብዙም ያልተነገረ ምሉዕ ምስል ለማየት ያስችለናልና እንዲሁ እናድርግ::

ሰሎሞን የኢትዮጵያን የአምስት መቶ ዓመታት የሥልጣን ሽኩቻ ታሪክ ‹የፈረቃ የበላይነት› በማድረግ ልኂቃኑ ሲወጡና ሲወርዱ ተርታው ብዙሃን ያለው የቀን ተቀን ግንኙነት ብቻ ቀሪ መሆኑን በመናገር ይጀምራል፡

የኢትዮጰያን ታሪክ ያየህ እንደሆን በአንድ በኩልም ያስገርማል ያሰኛል፤ ባንድ በኩል ደግሞ ያሳዝናል:: ስልጣኗን ተፈራርቀውባታል:: ጎንደርን ኦሮሞዎች ገብተው ንጉስ አንግሰው የሚገዙበት ጊዜ ነበር:: አፄ ቴዎድሮስ ከነገሱ በኋላ ግዛቱ ወደ ጎንደር ተመለሰ:: አጼ ዮሀንስ ሲመጡ የትግራይ ዘመን ሆነ:: ምኒሊክ ሲመጡ የመሃል አገር ያማራው ግዛት ሆነ:: አሁን ደግሞ ስልጣኑን የያዙት ከውጭ እንደሚታየው ከትግራይ የመጡ ሠዎች ይመስላሉ:: ሁሉም አላፊዎች ናቸው:: መፈራረቅ አይቀርም:: ነገ ማን እንደሚመጣ አላውቅም:: ወይ አማራው ይሆናል ወይ ኦሮሞው የሚመጣበትን መንገድ ደግሞ ልገምት አልችልም:: የማያልፈው ይህ ግንኙነት ነው …

አስከትሎም ‹‹በሴት አያቶቻችን በራፍ ላይ ማን እንዳለፈ ስንቶቻችን ነን የምናውቀው?›› በሚል መጠይቃዊ መልስ የማንነትን ተቀያሪ-ተከላሽነት (the fluidity of identity) በጠንካራ፤ ነገር ግን አጭር አንቀፅ እንዲህ ሲል ጠይቆ ይመልሳል፡

በአንድ በኩል ስታስበው ኢትዮጰያ ውስጥ ተቀምጦ ‹‹እኔ የትግራይ ሰው ነኝ››፤ ‹‹እኔ አማራ ነኝ››፤ ብሎ አፍ ሞልቶ መናገሩም አለማወቅ ይመስለኛል:: በሴት አያቶቻችን በራፍ ላይ ማን እንዳለፈ ስንቶቻችን ነን የምናውቀው? የኔን ጥሩ ኦሮሞነት እግዚአብሔርና የሴት አያቶቼ ብቻ ናቸው የሚያውቁት:: የሁሉም እንዲሁ ጦር ባለፈ ቁጥር በመዋለድ በንግድ በመገናኘት ተቸግሮ ከአገር ወጥቶ ሌላ ቦታ በመኖር ይቀላቀላል ነው … ከዚህ ባለፈ ግን ስንት ኦሮሞ ከብት በነዳበት አገር ‹‹እኔ የጠራሁ አማራ ነኝ›› ወይም ‹‹ንፁህ ትግሬ ነኝ›› ቢለኝ አነጋገሩ ‹‹ለማያውቁሽ ታጠኝ›› ነው::

ሰሎሞን በኢትዮጵያዊያን ዘንድ የታዘበውን (ነገሩ በሁሉም የዓለም ክፍሎች ተመሳሳይ ነው) የመንደራቸውን ነገር መውደድ፤ የራሳቸውን ሸንተረር ማድነቅ፤ ያደጉበትን ምንጭ ከሌሎች ወንዞች የበለጠ አድርጎ የማቅረብ አባዜ (obsession with self) በክፋት አያየውም፡፡ ‹‹እና ምን ያድርጉ?›› ነው የሱ ጥያቄያዊ መልስ፡፡ የጭቆና ተረክን በመንቀፍ ጀምሮ እንዲህ ይለናል፡

የኢትዮጰያ ታሪክ የመጣው ሁሉ ‹‹አማራ የገዛ እንደሆነ ሌላውን ቁልቁል ይዞ››፤ ‹‹ትግሬው የመጣ እንደሆነ ሌላውን ቁልቁል ይዞ›› … እያልን ይህንን ስንት ሺህ አመት ነው የምንደጋግመው? ምን ያህል እንለያያለን ዘር በመቁጠር ደረጃ? እኔ ምንም ችግር አይታየኝም:: ምክንያቱም በራስህ ለመኩራት መጀመሪያ በአባትህና በእናትህ መኩራት አለብህ:: እሱን እንደምግብ በልተኸው ነው ያንተ በራስህ መተማመን የሚመጣው:: ለምሳሌ እኔ ከትግራይ ሰው ጋር ተገናኝቼ ‹‹የማጫውትህ የትግራይን ትልቅነት ነው›› ቢለኝ፤ ‹‹በል ቁጭ በልና አጫውተኝ›› ነው የምለው:: ከዚህ በላይ ምን ያጫውተኝ? የወለጋውን እንዳያጫውተኝ የሱ አይደለም:: ከጎንደር የመጣ ሠው ‹‹የጎንደርን ትልቅነት ላጫውትህ›› ሲለኝ ሌላ ምን ያጫውተኝ? ጎንደር የሄድኩት የዘመዶቸን ትልቅነት ለመስማት አይደለም [እንዴ]? የነሱን ትልቅነት ለማየትና ለመስማት ነው፡፡ በባህል በኩል በጥበብ በኩል ምንም ዋጋ ያለው አይመስለኝም::

ለሕልዋዊው ሰሎሞን የኢትዮጵያ የጭቆና ታሪክ መሠረቱ የሕዝቦቿ ሁሌም በፍርሃትና ድንጋጤ ውስጥ መኖር ነው፡፡ ሰው አላፊና ጠፊ መሆኑን (the absurdism of life) ካለመረዳትና ዘላለማዊነትን ከመሻት አንጻር እኛን የማይመስሉንን የመጠራጠርና እነሱን የመግዛት መንፈስ አለ ባይ ነው፡፡ ሰሎሞን ሐሳቡን እንዲህ ያስረዳል፡

አንዱ አንዱን መጫን ከየት ነው የመጣው ያልከኝ እንደሆን ከድንጋጤ ነው የመጣው:: ሁልጊዜ ጠዋት ተነስተን ‹‹ዛሬ ምን እበላለሁ?››፣ ‹‹ምን ለብሼ አድራለሁ?›› ብለህ መወራጨቱ ነው:: በኢትዮጵያ ውስጥ ደግሞ በታሪካችን ሲጻፍ ያየኸው እንደሆነ ሁልጊዜ እንደ ጀግንነት የሚታየው ጦርነት ብቻ ነው:: እኔ ደግሞ የጦረኝነት ድፍረት ከድንጋጤ የሚመጣ ነው የሚመስለኝ:: የጦርነት ጀግንነት ከድንጋጤ ሞትን ከመሸሽ የተነሳ ነው:: ወደፊት ለኢትዮጵያ የምመኝላት ካለ የማይደነግጡ የሚያልፉ መሆናቸውን የሚቀበሉ ሰዎችን ነው:: ለራሴ የምመኝውን ነው ለኢትዮጵያ ወይም ለኢትዮጵያዊ የምመኝው:: ለራሴ የማልመኝውን አልመኝም:: ለራሴ የምመኝው ፍርሃቴን አላፊ መሆኔን ምንም አለመሆኔንና መሬት አፈር መሆኔን መቀበል መቻሌ ነው:: የሰውን ልጅ የሚመራው ፍርሃትና ድንጋጤ ነው:: እድገት ደግሞ ከዚያ ማለፍ ነው:: በእኛ በኢትዮጵያዊያን ታሪክ ጀግንነት ከጦርነት አልፎ በሕይወቴ ባየው ደስ ይለኝ ነበር:: ግድ ከሆነ ጊዜዬና እድሜዬ ቢሆንም እዚያ ውጭ እንደተሰለፉት (በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት የዘመቱትን ወጣቶች መሆኑ ነው) ልጆች መሰለፍና መሞት እችላለሁ:: ይህ አንድ አይነት ግዴታን መቀበል ነው:: ከዚያ የባሰ ጀግንነት ወይም አለመፍራት የኔን አላፊ መሆን መቀበል ነው:: በደራሲነትም ሆነ የሰው ልጅ በመሆን::

በመጨረሻም ‹አለመተዋወቅን የመሰለ ጠላት የለንም› በሚል ሐሳቡ ስለሰዎች መልካምነት እንዲህ ይለናል ሰሎሞን፡

በዚህ በእስካሁኑ ሕይወቴ ቁልቁልም ሆነ ወደላይ የማየው፤ ከቀረብኩት ደግሞ የማላፈቅረው ሰው እንደሌለ ተረድቻለሁ:: በተጨማሪ ሰው ሳትዳኝው ስለራሱ ሲያወራ ባታደምጠው ስላንተ እያወራ ነው የሚመስልህ:: ሲሆን የሰራሁትን፤ አለዚያ ባልሰራውም ያሰብኩትን ነው የሚያወራኝ::

ሰሎሞን በእንግሊዝኛ ቋንቋ ከጻፋቸው ጥቂት ግጥሞች መካከል ‹ለራስ ውዳሴ› — ‘Ode to Myself’ የተሰኝች ግጥሙ ፍላጎቱን ትገልፃለችና በእርሷው እንሰናበተው፡፡

Shall I someday be forgiven

My unrelaxing obsession

With the tone of silence

ሰሎሞን እንግዲህ ወደሚጓጓለት ዘለማለማዊ ጸጥታ ሒዷል፡፡ ታዲያ ወደሚናፍቁት ሠላምና ጸጥታ እንደመሸጋገር ምን ደስ የሚያሰኝ ነገር አለ? እናመሰግንሃለን ኢልማን ዼሬሳ፤ ሰሎሞን፡፡

Filed in: Amharic