>

የአማራና ኦሮሞ ትብብር ሕወሃቶችን ለቁጭትና ቅዠት የሚዳርገው ለምንድነው? (ስዩም ተሾመ)

አንድ ነገር ልጠይቃችሁ? የሁለት ሕዝቦች ትብብርና አንድነት እንዴት ለአንድ የፖለቲካ ሳይንስ መምህር “ቅዠት” ሊሆንበት ይችላል? የኦሮሞ ወጣቶች የጣና ሃይቅን ከእንቦጭ አረም ለመታደግ በሚደረገው ርብርብ አጋርነታቸውን ለማሳየት ወደ ባህር ዳር መሄዳቸው መሃሪ ዮሃንስ የተባለውን መምህር ለምን አሳሰበው?፣ የወጣቶቹን ተግባር ለምን አጣጣለው? እንደው በአጠቃላይ የአማራና ኦሮሞ ሕዝብ የጋራ ትብብርና አንድነት ለምንና እንዴት ሆኖ የሕወሃት/ኢህአዴግ ደጋፊ የሆኑ የፖለቲካ ልሂቃንን ሊያሳስብ ይችላል።

የአብዛኞቹ የፖለቲካ ልሂቃን ሃሳብና አስተያየት “አህያና ጅብ” በሚሉት ቃላት ላይ ትኩረት ያደረገ ነበር። ከእነዚህ ውስጥ የተወሰኑት ብቻ ነገሩን ከቀድሞ የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ፅ/ቤት ኃላፊ ከነበሩት አቶ ጌታቸው ረዳ ንግግር ጋር ለማያያዝ ጥረት አድርገዋል።በእርግጥ የአቶ ጌታቸው “ኦሮሞና አማራ እንዴት በአንድ መፈክር ስር ሊሰለፉ ይችላሉ? እሳትና ጭድ እንዴት በጋራ እንዴትስ በጋራ ሊቆሙ ይችላሉ?” የሚለው በቁጭት የተሞላ ንግግር እና የመሃሪ ዮሃንስ “አህያ እና ጅብ” የሚለው ቅዠት በአንድ ዓይነት የፖለቲካ አመለካከት የተመሰረቱ እሳቤዎች ናቸው።

አብዛኞቹ የአማራና ኦሮሞ የፖለቲካ ልሂቃን መሰረታዊ ችግር ደግሞ ይህን የፖለቲካ አመለካከት ሥረ-መሰረት እና አሁን በሀገራችን ያለውን የፖለቲካ ስርዓት ትክክለኛ ባህሪ በግልፅ የተረዱ አይመስለኝም። በመሆኑም፣ ከላይ በማሳያነት የተጠቀሰውን ዓይነት ሃሳብና አስተያየት እንደ ጤናማ የፖለቲካ አመለካከት ወስደው ተቀብለውታል።

አንድ ሰው የሁለት ሕዝቦች ትብብርና አንድነት ለአስፈሪ ቅዠት እና ለከፍተኛ ቁጭት የሚዳርገው ለእነዚህ ሕዝቦች የጠላትነትና ጥላቻ ስሜት ሲኖረው ነው። ነገር ግን፣ መ/ር መሃሪ ዮሃንስ ሆነ አቶ ጌታቸው ረዳ የአማራና ኦሮሞ ሕዝብን እንደ በጠላትነትና በጥላቻ ይመለከቱታል የሚል እምነት የለኝም። ምክንያቱም የሀገሪቱን 2/3 ሕዝብ በጠላትነትና በጥላቻ የሚመለከት የፖለቲካ መሪ ሆነ አስተማሪ ይኖራል ብዬ ማሰብ አልችልም።

ታዲያ በአማራና ኦሮሞ ሕዝብ ትብብርና አንድነት ምክንያት አቶ ጌታቸው ለቁጭት፣ መ/ር መሃሪ ደግሞ ለቅዠት የተዳረጉበት ምክንያት ምንድነው? እነዚህ የሕወሃት/ኢህአዴግ የፖለቲካ ልሂቃን “አያውቁም” እንዳይባል ሀገርና ሕዝብ ይመራሉ፥ ያስተምራሉ። “ያውቃሉ” እንዳይባል ደግሞ በአማራና ኦሮሞ ሕዝብ ትብብርና አንድነትን ሲመለከቱ ይቆጫሉ፥ ይቃዣሉ።

ይሄን ግራ-መጋባት ለመፍታት የእነዚህን ሰዎች ሃሳብና አስተያየት፣ ሥራና ተግባር እያነሱ መከራከር ይቻላል። ነገር ግን፣ በዚህ ዓይነት አካሄድ ከአንድ መቋጫ ላይ መድረስ አይቻልም። ችግሩን በግልፅ ለመረዳት ከሰዎቹ ከተናገሩት ሃሳብ፥ ይዘት (content) ይልቅ በፖለቲካ አመለካከታቸው፥ ቅርፅ (form) ላይ ትኩረት ማድረግ ያስፈልጋል።

ፈረንሳዊው ሊቅ “Ernest Renan” በብዙ የታሪክ መፅሃፍት ላይ ተጠቃሽ የሆነ “ሀገር ምንድነው?” (What is a Nation?) የሚል ፅሁፍ አለው። በዚህ መሰረት፣ ሀገር መምራት የሚቻለው የሕወሃት/ኢህአዴግ አመራሮችና ደጋፊዎች ከሚከተሉት ፍፁም በተለየ መንገድ ነው። ምክንያቱም፣ እንደ “Renan” አገላለፅ፣ ሀገር የሚመሰረተው ከቀድሞ ታሪክ ጥሩን በማስታወስና መጥፎን በመዘንጋት የወደፊት አብሮነትን በማጠናከር ላይ ነው፡-

 “A nation is ‘a daily referendum’, and that nations are based as much on what the people jointly forget, as what they remember.” Qu’est-ce qu’une nation?¨, conference faite en Sorbonne, le 11 Mars 1882.

በመሰረቱ የሕወሃት/ኢህአዴግ መንግስት መስራቾችና ከፍተኛ አመራሮች፣ እንዲሁም ቀንደኛ ደጋፊዎች፣ ሁሉንም ነገር የሚመለከቱት በብሔር ምንፅር ነው። ለምሳሌ የፖለቲካ ድጋፍና ተቃውሟቸው በብሔር ነው። ሥራና አሰራራቸው በብሔር የተመሰረተ ነው። ከራሳቸው አልፈው የሁሉም ሰው ሥራና አሰራር በብሔር ላይ የተመሰረተ እንዲሆን ይፈልጋሉ። ከዚህ በተጨማሪ፣ ላለፈው ሩብ ክ/ዘመን እንደተመለከትነው፣ በተለይ በሀገሪቱ አብላጫ ድምፅ ባላቸው የአማራና ኦሮሞ ሕዝቦች መካከል የነበረውን የታሪክ ልዩነትና ቁርሾ በመቆስቆስ ቂምና ጥላቻ ለማስፋፋት ጥረት አድርገዋል። በዚህ ረገድ የቂም ሃውልት እስከ ማቆም ደርሰዋል።

ሁለቱ ሕዝቦች በታሪክ የነበራቸውን ልዩነትና ተቀናቃኝነት ወደ ጎን በመተው የወደፊት አብሮነት እና አንድነትን ሲያስቀድሙ ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው፣ የሕወሃት/ኢህአዴግ ከፍተኛ አመራሮች በቁጭት ይነዳሉ፣ ቀንደኛ ደጋፊዎቻቸው ደግሞ ሲቃዡ ያድራሉ። ይህ ቁጭትና ቅዠት ከምን የመጣ ነው? በመሰረቱ እንዲህ ያለ አመለካከት በሁለቱ ሕዝቦች መካከል ከትብብር ይልቅ መለያየትን ማየት፣ ከወደፊት አብሮነታቸው ይልቅ የትላንት ልዩነታቸውን መስማት ከመፈለግ የመጣ ነው።

በአማራና ኦሮሚያ ክልል ለተቃውሞ አደባባይ የወጡ ሰልፈኞች አንዱ ለሌላው አጋርነቱን ሲገልፅ ጌታቸው ረዳ “እሳት እና ጭድ” ያለው፣ እንዲሁም የእንቦጭ አረምን ለማስወገድ ሲተባበሩ መ/ር መሃሪ ዮሃንስ “አህያ እና ጭድ” ያለው፣ የፖለቲካ ስርዓቱ የአማራና ኦሮሞ ሕዝቦችን በመለያየት (separateness) ላይ የተመሰረተ ስለሆነ ነው። “መለያየት” (separateness) የሚለው ቃል የደቡብ አፍሪካ ነጮች በሚናገሩት የ“Afrikaan” ቋንቋ “Apartheid” (አፓርታይድ) የሚል ፍቺ አለው።

ስለዚህ በሕወሃት መሪነት የተዘጋው መንግስታዊ ስርዓት ትክክለኛ መጠሪያ ስሙ “አፓርታይድ” የሚለው ነው። አብዛኞቹ የሕወሃት/ኢህአዴግ አመራሮችና ደጋፊዎች የአማራና ኦሮሞ ሕዝብ ትብብርና አንድነት ሲመለከቱ ለቁጭት እና ቅዠት የሚዳረጉበት መሰረታዊ ምክንያት የዚህ አፓርታይድ ስርዓት ተጠቃሚ፥ ጠበቃ ስለሆኑ ነው። በአጠቃላይ የአማራና ኦሮሞ ትብብር ሕወሃቶችን ለቁጭትና ቅዠት የሚዳርገው ፖለቲካዊ ስርዓቱ “አፓርታይድ” ስለሆነ ነው።

Filed in: Amharic