>
5:13 pm - Saturday April 19, 5180

የዳግማዊ አጤ ምኒልክ መታሰቢያ ሀውልት (አምደ ጽዮን ሚኒሊክ)

የዳግማዊ አጤ ምኒልክ መታሰቢያ ሀውልት የቆመው/የተተከለው ከዛሬ 87 ዓመታት በፊት (ጥቅምት 22 ቀን 1923 ዓ.ም) ነበር፡፡

ንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ ምኒልክ የአባታቸውን የዳግማዊ አጤ ምኒልክን ስራና ውለታ ቀጣዩ ትውልድ ያስበውና ይዘክረው ዘንድ … ማስታወሻ የሚሆን የመታሰቢያ ሐውልት ለማሰራት አሰቡ፡፡

ሐውልቱንም በጀርመናዊው መሃንዲስ ሙሴ ሄንትል አማካኝነት አስጠንተው፤ ከጀርመን ተቀርፆ እንዲመጣ አዘዙ፡፡ ሀውልቱ የተመደበለት ቦታ ተደልድሎ ከተዘጋጀ በኋላ ገና ሳይተከል/ሳይቆም ንግሥቲቱ መጋቢት 22 ቀን 1922 ዓ.ም አረፉ፡፡

በመሆኑም የንግሥቲቱን እረፍት ተከትሎ ንጉሰ ነገሥት ለመሆን እየተዘጋጁ የነበሩት አልጋ ወራሽ ንጉሥ ተፈሪ መኮንን፣ ከዛሬ 87 ዓመታት በፊት (ጥቅምት 22 ቀን 1923 ዓ.ም) ሐውልቱ በታላቅ ክብረ በዓል እንዲተከል አደረጉ፡፡

በሐውልቱ ላይ አፄ ምኒልክ ካባ እንደለበሱ አንባር አጥልቀው በእጃቸው ጣምራ ጦር ይዘው በፈረሳቸው በ‹አባ ዳኘው› ላይ ተቀምጠው በግርማ ሞገስ ይታያሉ፡፡ የሐውልቱ ቁመት ከተፈጥሮ አካላዊ መጠን በላይ ሲሆን ‹አባ ዳኘው› ፊቱን ወደ ሰሜን መልሶ በኋላ እግሮቹ ቆሞ፣ የፊት እግሮቹን ወደላይ አንስቶ ይታያል፡፡

‹‹ከትልቅ ወይንም ከትንሽ መወለድ ሙያ አይደለም፤ ራስን ለትልቅ ታሪክ መውለድ ግን ሙያ ነው›› የሚል ጽሑፍ የያዘው ሐውልቱ፣ ፋሺስት ኢጣሊያ ኢትዮጵያን በወረረችበት ወቅት በ1929ዓ.ም ወድቆ/ፈርሶ ነበር፡፡

ብርሃኑ ድንቄ ‹‹የአምስቱ የመከራ ዓመታት አጭር ታሪክ›› በሚለው መጽሐፋቸው ጣሊያኖች የአፄ ምኒልክን ሐውልት እንዴት እንዳፈረሱት እንደሚከተለው ገልፀውታል፡፡ ‹‹ … በቅድሚያ ሐውልቱ ያለበትን አካባቢ ረጅም እንጨት እየማገሩ በቆርቆሮ ሲያጥሩ ሰነበቱ …. ይህንን ያየው የአዲስ አበባ ሕዝብ ‹‹ሊያፈርሱት ነው›› ብሎ እርስ በእርሱ በሐዘን መነጋገሩን ቢሰሙ ‹‹ልናድስ›› ነው ብለው አስወሩ፡፡ ሁሉንም ነገር ካመቻቹ በኋላ ግን በየበሩ በታንክ ጭምር ጥበቃ አጠናክረው … ወደ ማታ የአራዳን አካባቢ በታንክ አጥረው በባውዛ ሌሊቱን ከተማውን እየተቆጣጠሩ በሌላ ኃይል ደግሞ ሐውልቱን ሲያፈርሱ አድረው ሲነጋጋ ወደ አልታወቀ ቦታ ወስደው ቀበሩት፡፡ ሕዝቡ እድሜና ፆታ ሳያግደው ሐዘኑን ይገልጽ እንደነበር አዛውንቶች ይመሰክራሉ …

በጊዜው የአዲስ አበባ ነዋሪ የነበረው የሃንጋሪው ዶክተር ላዲ ስላስ ላቫ እንደፃፈው፣ ሐውልቱ ከፈረሰበት ቦታ ቆመው ያለቅሱ የነበሩትን ሰዎች የጣሊያን ወታደሮች በኃይል ይበትኑ እንደነበር ገልጿል፡፡

በሌላ ዘገባ ደግሞ አንድ ሕፃን ልጅ ሲያለቅስ ጣሊያኖች ደርሰው ለምን እንደሚያለቅስ ቢጠይቁት ‹‹የንጉሱን ምልክት ስላወረዳችሁ ነው›› ብሎ እንደመለሰላቸውና ጣሊያኖችም ከሙሶሊኒ ሌላ ንጉሥ እንደሌለው በመንገር ልጁን ገርፈው እንዳባረሩት ተገልጿል፡፡ ጣሊያኖች ሐውልቱን ካፈረሱ በኋላ ሰው ሳያይ ሸፍነው በመውሰድ በታላቁ ቤተ-መንግሥት አዳራሽ ጀርባ ቀበሩት …››

የፋሺስት ወራሪ ኃይል ከኢትዮጵያ ከተባረረ በኋላም፣ ሐውልቱ ከተቀበረበት ቦታ ወጥቶ እንደገና ታድሶና ተጠግኖ ሚያዝያ 27 ቀን 1934 ዓ.ም ቀድሞ በነበረበት ቦታ እንዲቆም ተደረገ፡፡ ከዚህ በተጨማሪም፣ በ1988 ዓ.ም የአድዋ ድል መቶኛ ዓመት ሲከበር ሐውልቱ ጥገና ተደርጎለት እንደነበር መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

Filed in: Amharic