>
5:13 pm - Sunday April 18, 6799

የኢትዮጵያ የብሔር ፓለቲካ አያያዝ አነር ድመትን ለማላመድ እንደመሞከር፤ (በውብሸት ሙላት)

ከታች የሚቀርበው ጽሑፍ የሐሳቡ መነሻ የማርጋሬት ካኖቫን “Sleeping Dogs, Prowling Cats and Soaring Doves: Three Paradoxes in the Political Theory of Nationhood” የሚለው ጽሑፍ ነው፡፡ ካኖቫን ጽሑፍ ፍሬ ሐሳቡ በአጭሩ እንዲህ ነው፡፡ እ.አ.አ. ከ1950ዎቹ ጀምሮ እስከ 2000 ዓ.ም.ድረስ ብሔር፣ ብሔርተኝነትና ብሔርነትን የፖለቲካ ፈላስፋዎች እስከ ቀዝቃዛው ጦርነት ማብቂያ ድረስ እንዴት የሐቲታቸው ማጠንጠኛ ሳያደርጉት እንደቀሩ እና “በተኛ ውሻ” (Sleeping Dog) በመመሰል ብሎም እሷን በማንቃት የቡድናዊ የሥልጣን ምንጭ ስትሆን የተፈጠረውን ፣ ከዚያ በኋላ ደግሞ ከፍልስፍና ምህዋር ውጭ ሆና ስትንከራተት የነበረችውን ብሔርተኝነትን “በአነር ድመት” (Prowling Cat) በመመሰል እና እሷን ለማላመድ የሚደረገውን የንድፈ-ሐሳብ ትግል እና አላማጆቿ ይዘው የሚመጡትን ጦሶች፤ ብሎም በምዕራባዊያን የሊበራል አስተሳሰብ ላይ በመመርኮዝ በመፍትሔነት የቀረበውን ከዓለማ አቀፋዊው እና አገራዊው ነባራዊ ሁኔታ “በርግብ” (Soaring Dove) በመመሰል የሌሎች ፈላስፋዎችን ሥራ ቅርጽ በማስያዝ የቀረበ ትችት ነው፡፡

የ20ኛው ክፍለ-ዘመን ሁለተኛ አጋማሽ በምዕራቡ የፖለቲካ ንድፈ-ሐሳብ ውስጥ የብሔር ጉዳይ መጮህ እየተገባው እንቅልፉን እንደሚለጥጥ ውሻ በመሆን አለፈ፡፡ የሚገባውን ትኩረት አልተሰጠውም፤ አላገኘምም፡፡

የፖለቲካ ፈላስፋዎች የውሻውን መተኛት ምክንያት በማድረግ ኮሽታ ሳያሰሙ ማለፍን መረጡ፤ይሁን እንጂ ውሻው እንቅልፉን ሲጨርስ ወይንም ኮሽታ ሲሰማ ሊነሳ እንደሚችል የዘነጉት ይመስላል፡፡

የሶቭየት ኅብረት መፈራረስ የብሔርተኝነት ጥናት ላይ ታላቅ የመነቃቃት ሒደት አሳየ፡፡ በ1990ዎቹ መጀመሪያ ላይ ብዙዎች የሊብራሊዝም ሐሳብን ምርኩዝ በማድረግ ስለብሔርተኝነትና ስለብሔራዊ የራስን ዕድል በራስ መወሰን መጻፋቸውን አጧጧፉት፡፡ ይሁን እንጂ ለአብዝኃኛዎቹ የብሔርተኝነት ማዳወሪያና ማጠንጠኛው ብሔሮች ሳይሆኑ ግለሰቦች ናቸው፡፡

ከፖለቲካ ንድፈ-ሐሳብ ውጭ በመሆን ዱር ለዱር ስትንከራተት የነበረችውን አነር ድመቷን፣ ብሔርተኝነትን፣ ለማዳ ማድረግ እንደሚቻል ተፈላሰፉ፡፡ ሌሎች ደግሞ ፍጹም ለማዳ ማድረግ እና አገርን ለማስተዳደር የማትመች እንደሆነች ጻፉ፡፡

የፖለቲካ ፈላስፋዎቹ ምንም ይበሉ ምን፣ በተለያዩ አገራት ብሔርን መሠረት ያደረግ አዲስ የአገር አስተዳደር ዘይቤ ተከተሉ፡፡ የአገር አስተዳደር መሠረት ባየደርጓትም እንኳን እንደው በአግባቡ ሊያላምዷት ባለመቻላቸው፣ ትክክለኛ መኖሪያዋን ስላላመቻቹላት ሌሎችን ወደጠላትነት በመቀየርና እያነቀች መብላት በመጀመሯ ወደዘር ጠረጋ አመራች፡፡ ሩዋንዳ፣ ዩጎዝላቪያ፣ ቦስኒያና ኮሶቮ ዐቢይ ምሳሌዎች ናቸው፡፡

ብሔርተኝነትን እንደ አነር ድመቷ የማላመድ እና ቤተኛ የማድረግ ንጽጽሮሽ ሲነሳ የኤዞጵ ተረቶች ውስጥ ያለው የአይጦችና የድመቶችን ታሪክ ያስታውሰናል፡፡ አይጦች ከዋና ጠላታቸው ከድመት ለማምለጥ አንድ ስልት መዘየድ ነበረባቸው፡፡ በመሆኑም የአይጦች ጠቅላላ ጉባኤ ተጠራና ምክክር ተጀመረ፡፡ በጉባኤው ላይ የተለያዩ ሐሳቦች ተነሱ፡፡ አንድ የአይጥ ጎረምሳ በአስደማሚ የንግግር ጥበቡ የመፍትሔ-ሐሳብ አቀረበ፡፡

“ማንኛውም አይጥ ከድመቶች ጥቃት ለመዳን እያንዳንዱ ድመት አንገት ላይ ከሩቅ የሚሰማ ቃጭል በማሰር ድመቶች ቃጭላቸውን እያቅጨለጨሉ ሲመጡ በመስማት ወደጉድጓድ ጥልቅ በማለት ማምለጥ ነው” ሲል አቀረበ፡፡ አዳራሹን በአይጥኛ ጭብጨባ አናጉት፤ለጎረምሳው አይጥም አድናቆት ጎረፈለት፡፡ ወደውይይታቸው መጨረሻ ላይ ከጥግ አካባቢ ተቀምጦ የነበረ የአይጥ ሽማግሌ የቀረበውን መፍትሔ አድንቀው፣ “ነገር ግን የድመቶቹ አንገት ላይ ቃጭል አሳሪው ማን ነው? ለማሰር መሰማራት ውጤቱ ለድመት ቀለብ መሆን ስለሆነ ጭብጨባ አያስፈልግም” ሲሉ ተናገሩ፡፡

ብሔርተኝነትን በአንድ አገር የፖለቲካ ምህዳር ውስጥ ምሰሶ ለማድረግ መሞከር አይጦች ከጠላቶቻቸው ከድመቶች ለመከላከል የድመቶች አንገት ላይ ቃጭል ለማሰር እንደመሞከር ይመስላል፤ ብሔርተኝነትን ለማላመድ መሞከር አገርን ቀረጣጥፋ ልትበላ ትችላለች፡፡ ብሔርተኝነት ላይ ቃጭል በማሰር ሊመጣ የሚችል መጥፎ አደጋን ከርቀት መስማት ከተቻለ ቀድሞ ጉድጓድ ውስጥ በመግባት (መፍትሔ በመዘየድ) ስጋትን መቀነስ ይቻላል፤ ይህ ሳይሳካ ቢቀር ደግሞ ዘርጠራጊ ዴሞክራሲን ልታሰፍን ትችላለች፡፡

ከዚህ በተቃራኒው ደግሞ የብሔርን ጣጣ ፈጽሞ በመርሳት የግለሰብ መብት ላይ ብቻ ጥብቅ ማለትም ችግር የለውም ባይባልም ግለሰባዊ መሠረት ላይ ሙጭጭ የሚሉ መኖራቸውን መዘንጋት የለበትም፡፡ በተለይም ዓለምአቀፍ ተቋማትና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች አንድ-ብሔር-አንድ-ሀገር ከሆነባቸውና የፖለቲካ ፍልስፍናቸውም ሊብራሊዝም፣ ማኅበራዊ መሠረታቸው ግለሰብ የሆኑ አገራት ዜጎቻቸውን በተለያዩ ተቋማት አማካይነት ወደተለያዩ አገራት እንደ እርግብ በመልቀቅ የራሳቸውን የፖለቲካ ጃኬት ለተለያዩ አገራት ለማልበስ ትልቅ ትግል እንደሚካሔድ እሙን ነው፡፡ ይህንን የሚደግፉም በርካታ ንድፈ-ሐሳቦችም ፈልቀዋል፡፡

ይሁን እንጂ በምዕራባውያን ቁመትና ውፍረት የተሠራው ጫማና ጃኬት ርሃብና ድርቅ ላደቀቀው፣ ሀሩር ቁመቱን ላሳጠረው አፍሪካዊ ላይሆን ይችላል፤ ለሲውዲናውያን ወይም ሩሲያውያን ብርዳማና ቀዝቃዛ የአየር ፀባይ የሚሠራው ካፖርት ለአፍሪካ ሀሩር ወበቅ ከመጨመር ያለፈ ጥቅም የሚያበረክተውም ፋይዳ የለውም፡፡ እንደሁኔታው ማስተካከል ግድ ይላል፡፡ ልክ እንደዚሁ ሁሉ እንደነአሜሪካ ባሉ በጣም ድብልቅልቅ ያለ ማኅበረሰብ ባለበትና የፖለቲካና የማኅበራዊ መሠረቱም ግለሰብ የሆኑባቸው አገራትን ብሔር፣ ነገድ፣ ጎሳ እጅግ ከፍተኛ ዋጋ በሚሰጥባቸው እንደ ኢትዮጵያ፣ ናይጀሪያ፣ ሶማሊያ ወዘተ ባሉት አገራት ያለምንም ለውጥ እንዳለ እንዲተገበር መጣር አበሳ መጥራት ነው፡፡

አንድ ብሔር የራሱን ብሔርነት ከሌሎች ጋር ማጣጣም ካልቻለ፣ አስታርቆ መኖር አዳጋች ከሆነበት፣ የልዩነት ማማው ቁመቱ መጨመሩን ከቀጠለ ተለይቶ መኖር ተመራጭ ሊሆን ስለሚችል መገንጠል አይቀሬ ይሆናል፡፡ የብሔር መሪዎች ከዚህ ሂደት ለመጠቀም ሲሉ ጥርጣሬ ማንገሥንና ራሳቸውን ተጠቃሚ ሊያደርጋቸው የሚችሉ መፈክሮችን ያዘጋጃሉ፤ይነዛሉም፡፡

በመቀጠልም ሌላውን የብሔሬ ልጅ አይደለም የሚሉትን ማግለል፣ መለየትና ማስወጣት ይጀምራሉ፡፡ እንደዩጎዝላቪያና ሩዋንድ በጭፍጨፋ አሊያም አካባቢውን ለሌሎች ሠርቶ መኖሪያ እንዳይሆን በእሾሃማ ሕጎችና ተግባራት ማጠር የዘወትር ሥራቸው ማድረጋቸውን ይተጉበታል፤ ብሔር ላይ ብቻ የተመሠረቱ የክልልና የአካባቢ ፖለቲካ ፓርቲዎችን በማቋቋምና ሌሎችን እንዳያቅፍ በማድረግ፣ ከአስፈጻሚውምና ከዳኝነቱም በማግለል ሌሎች በባይታወርነት ስሜት እንዲሞሉ ማድረግ፣ የብሔሩን ቋንቋ የማይችሉትን ከመንግሥታዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማት ተቀጣሪ እንይዳሆኑ በሕግ መደንገግን የመሳሰሉትን በማከናወን ተሰበጣጥሮና በአንድነት ከመኖር ይልቅ አንድ ብሔር ብቻ የአካባቢውን ሁለመና የራስ ማድረግ ይቀጥላል፡፡

በነገራችን ላይ ብሔርን መሠረት ያደረጉ ፖለቲካ ፓርቲዎችን መመሥረት በብዙ ሀገራት ክልክል ብቻ ሳይሆን ወንጀልም ነው፤በተቃራኒው ብሔር ዘለል በመሆን ግለሰቦችን/ዜጎችን መሠረት ያደረገ ፖለቲካ ፓርቲ በኢትዮጵያ አይበረታታም፤ሕገ-መንግሥቱ የቆመበት መሠረትም ይሁን አገሪቱ በሕግ የተዋቀረችበት ዋልታና ማገር ብሔር እንጂ ጅምላው ኢትዮጵያዊ ሕዝብ አይደለምና!

ከላይ እንደተገለጹት ዓይነት አስቸጋሪ ሕግጋት፣ተቋማት፣የልማት ጎዳና፣የፓርቲ አወቃቀር፣ አድሏዊ የሥልጣን መጋራት ወዘተ ማስተካከል ካልተቻለ ብሔርን መሠረት ያደረገው የፌደራል ሥርዓት አደጋ መጥራቱ አይቀሬ ነው፡፡ እንደ አነር ድመቷ ዱር ለዱር ስትሔድ የነበረችው ብሔርተኝነትን በአግባቡ ማለማድ ያስፈልጋል፡፡ በአግባቡ ማላመድ አለመቻላችንን የሰሞኑ ሁኔታ ምስክር ነው፡፡

Filed in: Amharic