>

መሪ-አልባ ሕዝብ እርስ-በእርስ ይጋጫል! (ስዩም ተሾመ)

የትኛውም የፖለቲካ እንቅስቃሴ መሪ ያስፈልገዋል። እንቅስቃሴው አብዮታዊ (revolutionary) ከሆነ የለውጥ መሪ ያስፈልገዋል። ፀረ-አብዮታዊ (reactionary) ከሆነ ደግሞ የስርዓት መሪ ያስፈልገዋል። ለስኬት ብቻ ሳይሆን ለውድቀትም መሪ ያስፈልጋል። ምክንያቱም፣ ከስኬታማ ለውጥ በስተጀርባ ውጤታማ አወዳደቅ አለ። በእርግጥ በውድቀት ውስጥ ሽንፈት ነው ያለው። ነገር ግን፣ ውድቀትን አውቆ ሽንፈትን ለመቀበል ዝግጁ የሆነ አመራር ከሌለ ፖለቲካዊ ቀውስ ይከሰታል። የቀድሞ ስርዓት ወድቆ-አይወድቅም፣ አዲሱ ስርዓት አይመሰረትም። ይህን ተከትሎ የቀድሞ ስርዓት ሳይወድቅ በቁሙ ይፈራርሳል፣ ሕዝባዊ ንቅናቄው ግቡን ይስታል። ይህ ሲሆን የብዙሃንን መብት፥ ነፃነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተጀመረ ንቅናቄ አቅጣጫውን ስቶ ወደ ሁከትና ብጥብጥ፣ የእርስ-በእርስ ግጭትና ጦርነት ይወስዳል። ይህ በምናባዊ እሳቤ ላይ ሳይሆን በመሰረታዊ የኃይል ፅንስ-ሃሳብ ላይ የተመሰረተ ነው። ይህንንም የደቡብ አፍሪካ የአፓርታይድ ስርዓት አወዳደቅን እንደ ማሳያ በመውሰድ በዝርዝር እንመለከታለን።

በመሰረቱ፣ “ኃይል” (power) ማለት አንድን ነገር ለማድረግ ወይም ለመለወጥ የሚያስችል አቅም ነው። የኃይል ፅንሰ-ሃሳብ ለሁለት ይከፈላል። የመጀመሪያው አንድን ነገር ለማድረግ ወይም ለመለወጥ የሚያስችል ቀጥተኛ ኃይል (Active power) ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ተግባሩን ወይም ለውጡን ለመቀበል የሚያስችል ቀጥተኛ ያልሆነ ኃይል (Passive power) ነው። ይህን ጽንሰ-ሃሳብ ለማስረዳት እንግሊዛዊው ፈላስፋ ቶማስ ሆብስ እሳት እና ወርቅን እንደ ማሳያ ይጠቅሳል። እሳት ወርቅን ከጠጣርነት ወደ ፈሳሽነት ለመቀየር የሚያስችል ኃይል አለው። በሌላ በኩል፣ ወርቅ በሙቀት አማካኝነት ከጠጣርነት ወደ ፈሳሽነት ለመቀየር የሚያስችል ኃይል አለው። እሳት ወርቅን የማቅለጥ ወይም ቀጥተኛ ኃይል ሲኖረው ወርቅ ደግሞ በእሳት የመቅለጥ ወይም ቀጥተኛ ያልሆነ ኃይል አለው። ወርቅ እንደ አፈር እሳት ሲነካው የሚፈረካከስ ቢሆን ኖሮ የወርቁ ቅርፅ መለወጥ ወይም መቀየር አይቻልም ነበር። ስለዚህ፣ የወርቅ ጌጥ የሚሰራው የእሳት ሙቀት ከወርቅ የመቅለጥ ባህሪ ጋር በመጣመር ነው። ለውጥ ለማምጣት የሚያስችለው ቀጥተኛ ኃይል ለዉጥን መቀበል ከሚያስችለው ቀጥተኛ ያልሆኑ ኃይል ጋር ካልተጣመረ የሚፈለገው ለውጥ ሊመጣ አይቻልም።

በተመሣሣይ፣ አንድን ፖለቲካዊ ስርዓት በተሳካ ሁኔታ መቀየር የሚቻለው በስርዓቱ በደጋፊና ተቃዋሚ ጎራ ያሉ የፖለቲካ መሪዎች የለውጡን አስፈላጊነት እና አይቀሬነት ተገንዝበው በጥምረት መንቀሳቀስ ሲችሉ ብቻ ነው። ይህን ማየት ከመጀመራችን በፊት ግን “ኃይል”ከፖለቲካ አንፃር ያለውን ትርጉምና ፋይዳ በግልፅ መገንዘብ ያስፈልጋል። ከላይ እንደተጠቀሰው፣ “ኃይል” (power) ማለት አንድን ነገር ለማድረግ ወይም ለመለወጥ የሚያስችል አቅም ነው። ከዚህ አንፃር፣ የፖለቲካ ኃይል (political power) ማለት ደግሞ የአንድን ሀገርና ሕዘብ ለማስተዳደር ወይም ፖለቲካዊ ስርዓቱን ለመቀየር የሚያስችል አቅም፥ ስልጣን ነው። ለፖለቲካዊ አስተዳደር ወይም ለለውጥ የሚያስችለው አቅም ምንጩ የብዙሃኑ አመለካከት (public opinion) ነው።

የአንድ ሕዝብ በመንግስታዊ ስርዓቱ ላይ ያለውን በጥቅሉ የመንግስት ደጋፊና ተቃዋሚ በማለት ለሁለት ከፍሎ ማየት ይቻላል። “የመንግስት ደጋፊ” በሚለው ጎራ ያለውን ማህብረሰብ በቀጥታ የመንግስት ደጋፊዎች እና መንግስትን በይፋ ባይደግፉ-የማይቃወሙ ናቸው። በተመሳሳይ፣ “የመንግስት ተቃዋሚዎች” የሚባሉት ደግሞ በቀጥታ የመንግስት ተቃዋሚዎች እና መንገስትን በይፋ ባይቃወሙ-የማይደግፉ ናቸው። በዚህ መሰረት፣ በስልጣን ላይ ያለ መንግስት ሀገሪቷንና ሕዝቡን መምራት የሚችለው አብዛኛው የሕብረተሰብ ክፍል የመንግስት ደጋፊ ወይም መንግስትን በይፋ ባይደግፍ እንኳን የማይቃወም ከሆነ ነው። ነገር ግን፣ አብዛኛው የሕብረተሰብ ክፍል መንግስትን የሚቃወም ወይም በይፋ ባይቃወም እንኳን የማይደግፍ ከሆነ ፖለቲካዊ ስርዓቱ መቀየር ወይም መሻሻል አለበት።

አብዛኛው የሕብረተሰብ ክፍል መንግስትን የሚቃወምበት፣ በይፋ ባይቃወም እንኳን የማይደግፈበት መሰረታዊ ምክንያት የእኩልነት ጥያቄ ነው። የሰው ልጅ ፖለቲካዊ አመለካከትና ተግባራዊ እንቅስቃሴ የሚመራው በእኩልነት መርህ ነው። እያንዳንዱ ሰው ከሌሎች ሰዎች ጋር በእኩል አይን መታየት ይሻል። በመሆኑም፣ እያንዳንዱ ዜጋ ከሌሎች እኩል መብት፥ ነፃነትና ተጠቃሚነት ሊኖረው ይገባል። “እኩልነት” (equality) የዴሞራሲያዊ ስርዓት መርህና መመሪያ የሆነበት ምክንያት ከሰው-ልጅ ተፈጥሯዊ ባህሪ ጋር የተቆራኘ ስለሆነ ነው። በመሆኑም፣ ዴሞክራሲ የብዙሃንን መብት፥ ነፃነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ላይ የተመሰረተ ፖለቲካዊ ስርዓት ነው። በተቃራኒው፣ ጨቋኝ ወይም አምባገነን የሆነ መንግስታዊ ስርዓት የተወሰነ የሕብረተሰብ ክፍልን የበላይነትና ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ላይ የተመሰረተ ነው። እንዲህ ያለ መንግስታዊ ስርዓት ባለበት ሀገር ዜጎች ያለማቋጥ የእኩልነት ጥያቄ ያነሳሉ።

በእርግጥ ገና ከአመሰራረቱ ጀምሮ ዴሞክራሲያዊ የሆነ መንግስት የለም። ይሁን እንጂ፣ ዴሞክራሲያዊ መንግስት በየግዜው ከሕዝብ ለሚነሳው የመብት፥ ነፃነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጥያቄ ምላሽ ይሰጣል፤ ሥራና አሰራሩን ያሻሽላል። ጨቋኝና አምባገነን መንግስት ግን በተለያየ ግዜ ከዜጎች የሚነሳውን የእኩልነት ጥያቄ በኃይል ለማፈን ጥረት ያደርጋል። ሆኖም ግን፣ የእኩልነት ጥያቄ ከሰው-ልጅ ተፈጥሯዊ ባህሪ እንደመሆኑ በሰው-ሰራሽ ኃይልና ጉልበት ማስቆምና ማስቀረት አይቻልም። ስለዚህ. የብዙሃኑን መብት፥ ነፃነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችል ለውጥና መሻሻል ከማምጣት ይልቅ የዜጎችን ተፈጥሯዊ ፍላጎት በኃይል ለማፈን የሚሞክር መንግስት በራሱ ላይ ውድቀት እየደገሰ ነው። በመጀመሪያ በአመፅና ተቃውሞ የተጀመረ እንቅስቃሴ ቀስ-በቀስ ወደ ሁከትና ብጥብጥ ያመራል። ከዚያ ቀጥሎ የእርስ-በእርስ ግጭትና ጦርነት ይከተላል። በመጨረሻም፣ በጉልበት ላይ የተመሰረተ መንግስት በተመሳሳይ ኃይል ከስልጣን ይወገዳል። በዚህ መልኩ፣ የሕዝቡ ንቅናቄ ከተቃውሞ ወደ አመፅ፣ ከአመፅ ወደ ሁከትና ብጥብጥ ተሸጋግሮ በመጨረሻ ስርዓት-አልበኝነትና ጦርነት እንዳያስከትል የፖለቲካ መሪዎች የሚጠበቅባቸውን ሚና በአግባቡ መወጣት አለባቸው።

በብዙሃኑ አመለካከት ላይ ካላቸው ተፅዕኖ ወይም ኃይል አንፃር የፖለቲካ መሪዎችን ሚና ለሁለት ከፍሎ ማየት ይቻላል። ቀደም ሲል እንደተገለፀው፣ የፖለቲካ ኃይል (political power) ቀጥተኛ እና ቀጥተኛ ያልሆነ በሚል ለሁለት ይከፈላል። በዚህ መሰረት፣ የዜጎችን መብት፥ ነፃነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ መሪዎች መንግስታዊ ስርዓቱን ለመቀየርና መምራት የሚያስችል ቀጥተኛ ኃይል (Active power) ያላቸው ሲሆን የስርዓቱ መሪዎች ግን ቀጥተኛ ያልሆነ ኃይል (Passive power) አላቸው። ቀጥተኛ ያልሆነ ኃይል መንግስታዊ ስርዓቱን በቀጣይነት ለመምራት ወይም ለመቀየር የሚያስችል አይደለም። ከዚያ ይልቅ፣ የፖለቲካ ስርዓቱን ለመቀየር የሚደረገውን እንቅስቃሴ መቀበል ወይም አለመቃወም (Passive) ነው። ስለዚህ፣ የተቃዋሚ መሪዎች ኃይል የፖለቲካ ስርዓቱን ለመቀየር የሚያስችል ሲሆን የጨቋኝ ስርዓት መሪዎች ኃይል ግን የለውጡን እንቅስቃሴ መደገፍ ነው። ይሁን እንጂ፣ የሚፈለገው ለውጥ ለማምጣት ቀጥተኛና ቀጥተኛ ያልሆነ ኃይሎች እኩል አስፈላጊና ጠቃሚ ናቸው።

በተለያየ ግዜና ቦታ ዜጎች የመብት፥ ነፃነትና ተጠቃሚነት ጥያቄ ያነሳሉ። በየትኛውም ግዜና ቦታ ቢሆን የመንግስት ድርሻ የሕዝብን ጥያቄ በተገቢ ሁኔታ ተቀብሎ ምላሽ ለመስጠት ጥረት ማድረግ ነው። የሕዝቡን የለውጥና መሻሻል ጥያቄ በተገቢ ሁኔታ ለመመለስ የተቃዋሚ መሪዎች ንቅናቄውን ከፊት ሆነው መምራት ያለባቸው ሲሆን የስርዓቱ መሪዎች ደግሞ የለውጡን አይቀሬነት አውቀውና ተቀብለው ከዚህ ተፃራሪ የሆኑ ተግባራትን ከመፈፀም መታቀብ ይኖርባቸዋል። ነገር ግን፣ የተቃዋሚ መሪዎች ለሞት፥ እስራትና ስደት በማድረግ ሕዝባዊ ንቅናቄውን መሪ-አልባ ካደረጉት፣ እንዲሁም ለውጡን የማይቀበሉና ለእንቅስቃሴው እንቅፋት የሚሆኑ ከሆነ የሀገሪቱ ፖለቲካ ሚዛኑን ይስታል።

የዜጎችን ጥያቄ በጉልበት ለማፈን መሞከር ውድቀትን ከማፋጠን የዘለለ ፋይዳ የለውም። ምክንያቱም፣ የእኩልነት ጥያቄ በየግዜው የሚለኮስ እሳት ነው። እሳቱ በተለኮሰ ቁጥር እንደ ወርቅ መቅለጥ የተሳነው መንግስት እንደ አፈር ተፈረካክሶ ይወድቃል። ይህ ሲሆን የብዙሃኑን መብት፥ ነፃነትና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በሚል የተጀመረው ሕዝባዊ ንቅናቄ አቅጣጫውን በመሳት ወደ ሁከት፥ ብጥብጥ፥ ግጭትና ጦርነት ያመራል። ይህ እንዳይሆን ቀጥተኛና ቀጥተኛ ያልሆኑ ኃይሎች እኩል አስፈላጊና ጠቃሚ ናቸው። የለውጡ መሪዎች ሕዝባዊ ንቅናቄው አቅጣጫውን እንዳይስት፣ ተግባራዊ እንቅስቃሴያቸው ከበዳይ-ተበዳይ ስሜት ይልቅ በእኩልነትና ነፃነት መርህ መመራት አለበት። በሌላ በኩል፣ የስርዓቱ መሪዎች የለውጡን አይቀሬነት፥ የስርዓቱን ውድቀት አምኖ መቀበል፣ እንዲሁም ከለውጡ መሪዎች ጋር ያለ ቅድመ-ሁኔታ ለመወያየት ፍቃደኛና ቁርጠኛ መሆን አለባቸው። በዚህ መልኩ፣ ጨቋኝ ስርዓትን በዘላቂነት ማስወገድና በእኩልነት መርህ የሚመራ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት መዘርጋት ይቻላል።

ከዚህ አንፃር፣ በደቡብ አፍሪካ የነበረው አፓርታይድ ስርዓት የወደቀበትና በምትኩ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት የተዘረጋበትን አግባብ እንደ ማሳያ መጥቀስ ይቻላል። ብዙውን ግዜ ስለ አፓርታይድ ሲነሳ ቀድሞ ወደ አዕምሯችን የሚመጣው የቀድሞ ፕረዜዳንት ኔልሰን ማንዴላ እና የ”ANC” ፓርቲ ናቸው። ነገር ግን፣ በደቡብ አፍሪካ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እንዲዘረጋ በወቅቱ የአፓርታይድ መንግስት ፕረዜዳንት የነበሩት “ከዲ ክለርክ” (F. W. de Klerk) እና ፓርቲያቸው “National Party” ከኔልሰን ማንዴላ እና “ANC” ተነጥሎ ሊታይ አይችልም። ምክንያቱም፣ ሁለቱም ወገኖች የአፓርታይድ ስርዓትን ለማስወገድ በጋራ ጥረት ባያደርጉ ኖሮ በደቡብ አፍሪካ የጥቁሮችን እኩልነትና ነፃነት ማረጋገጥ አይቻልም ነበር።

በኔልሰን ማንዴላ መሪነት ሲካሄድ የነበረው የለውጥ ትግል በዋናነት የአፓርታይድ ስርዓትን ለማስወገድና የጥቁሮችን መብትና ነፃነት ለማረጋገጥ ነው። የጥቁሮችን መብትና ነፃነት እስካልተረጋገጠ ድረስ አመፅና ተቃውሞ በሂደት ወደ ሁከትና ብጥብጥ፣ ብሎም ወደ እርስ-በእርስ ግጭትና ጦርነት ማምራቱ አይቀርም። በመሆኑም፣ በሀገሪቱ የተከሰተው ግጭትና አለመረጋጋት ከቁጥጥር ውጪ ከመውጣቱ በፊት የአፓርታይድ ስርዓትን ማስወገድና በምትኩ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት  መዘርጋት የግድ ነበር። ፕ/ት ዲ ክለርክ ደግሞ ይህን እውነት አምኖ ተቀብሎ ኔልሰን ማንዴላና ሌሎች የፀረ-አፓርታይድ ትግል መሪዎችን ከእስር በመፍታት በደቡብ አፍሪካ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ስለሚዘረጋበት ሁኔታ መወያየት ነበር። ለዚህ ደግሞ ዲ ክለርክ የአፓርታይድ መንግስት ፕረዜዳንት ሆነው ከተመረጡ ከጥቂት ወራት በኋላ እ.አ.አ. በ1990 ዓ.ም (ለነጮች) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው ባደረጉት ንግግር እንዲህ ብለው ነበር፡-

“…only a negotiated understanding among the representative leaders of the entire population is able to ensure lasting peace. The alternative is growing violence, tension and conflict. That is unacceptable and in nobody’s interest. The well-being of all in this country is linked inextricably to the ability of the leaders to come to terms with one another on a new dispensation. No-one can escape this simple truth.” Transition (1990 – 1994) – Documents and Reports – 1990

አሁን በሀገራችን ካለው ነባራዊ ሁኔታ አንፃር በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ ዜጎች የመብት፥ ነፃነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጥያቄ  በማንሳት ላይ ይገኛሉ። የኢህአዴግ መንግስት የለውጡን አይቀሬነት አውቆና ተቀብሎ ለሕዝብ ጥያቄ ተገቢ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ በኃይል ለማፈን ጥረት እያደረገ ነው። ይህ የኢህአዴግ መንግስት የለውጡን አይቀሬነት አውቆና ተቀብሎ አስፈላጊውን ለውጥና መሻሻል ለማምጣት የሚያስችል አመራር እንደሌለው በግልፅ ይጠቁማል። ከዚህ በተጨማሪ፣ የፖለቲካ መሪዎችን፣ ጋዜጠኞችንና የመብት ተሟጋቾችን በሽብርተኝነት ወንጀል እየከሰሰ በማሰር ሕዝቡን መሪ-አልባ እያደረገው ይገኛል።

የኢትዮጲያ ፖለቲካ በዚህ ሁኔታ ከቀጠለ በተለያዩ አከባቢዎች የሚታየው ሕዝባዊ ንቅናቄ ወደ ሁከትና ብጥብጥ፣ ብሎም ወደ የእርስ-በእርስ ግጭትና ጦርነት የማምራት እድሉ ከፍተኛ ነው። በእስር ላይ የሚገኙት ዶ/ር መረራ ጉዲና “የሚበላው ያጣ ሕዝብ መሪዎቹን ይበላል” ነበር ያሉት፡፡ መሪ-አልባ ሕዝብ ግን እርስ-በእርስ ያባላል (ይጋጫል)! ስለዚህ፣ ሀገሪቷን ከእርስ-በእርስ ግጭትና ጦርነት ለመታደግ ሲባል  የኢህአዴግ መንግስት ሁሉንም የፖለቲካ እስረኞችን መፍታት እና የፀረ-ሽብር ሕጉንና ሌሎች አፋኝ ሕጎችን ማስወገድ አለበት፡፡ በመቀጠል፣ በአሸባሪነት የተፈረጁ ድርጅቶችን ጨምሮ ከሁሉም የፖለቲካ ድርጅቶችና ሲቭል ማህበራት፣ እንዲሁም ሌሎች የሕብረተሰብ ክፍሎች ጋር ያለ ምንም ቅድመ-ሁኔታ መወያየት አለበት።

Filed in: Amharic