>

የዋልድባ መነኮሳት ጥሪ!

“እኛ ውጊያችን ከህዝብና ከፈጣሪ ጠላት ጋር ነው !”

ካላፉት ቀናት መካከል በአንዱ በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ታስረው ያሉትን የዋልድባ በተለየ መጠሪያው የአብረንታት ገዳም መነኮሳት የኾኑት አባ ገ/ሥላሴ ወልደ ሃይማኖት ገ/መድኅን እና አባ ገብረ ኢየሱስ ኪዳነ ማርያም ካሣዬን ለመጠየቅ ሄጄ ነበር፡፡ መነኮሳቱ በማዕከላዊ ከ ፬ ወራት ስቃይ በኃላ ወደ ቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ተዘዋውረው በማረሚያ ቤቱ ውስጥ ይገኛሉ፡፡
መነኮሳቱ የተከሰሱት በሽብር ክስ ሲኾን ሟቹ ጠ/ሚኒስቴር በነበረበት ጊዜ ከዋልድባ ድረስ
በመምጣት በፅህፈት ቤታቸው ካነጋገሯቸው መነኮሳት መካከል እነዚህም አባቶች ይገኙበታል፡፡ መለስም ምላሹ ተገቢ ባለመኾኑም በፀሎት ብቻ ሥራቸውን ከተወጡት
መካከል ናቸው፡፡
ኹለቱ መነኮሳትን በእስር ቆይታቸው የተለያየ ሰው ሰራሽ መከራ አጋጥሟቸዋል፡፡ በማዕከላዊ
እስር ቤት ቶርቸር ተገርፈዋል፤ የአንዱ አባት እጅም በድብደባ ተሰብሯል፡፡ በማዕከላዊ ከኹሉም የከፋ የሚያስለቅስ መከራ ያጋጠማቸው በክርስትና አስተምህሮ ላይ እንደታዘዘው አንድ ሰው ወደ ምንኩስና ሲገባ ሞተ ማለት ስለኾነ በቀጭን ቆዳ ወይም ጧፍ ሰውነታቸውን በግንዘት ልክ ታስረው እድሜ ልካቸውን ከሰውነታቸው ሳይፈቱ ይኖራሉ፡፡ መነኮሳቱም በማዕከላዊ “ይሄን ፍቱ!” ሲባሉ “እምነታችን አይፈቅድም! አንፈታም!” በማለታቸው ድብደባው ፀንቶባቸው ነበር፡፡ “በተለይ አንዲት ሴት ያረገችብን መቼም አንረሳውም! ይህቺ ሴት፡- እምነት ባይኖራት፤ ቤተሰብ የላትም? እንዴ? እንኳን የሀገራችን ሴት፤ ነፍሰ በላ፣ አግድም አደግ ወንድ እንኳን የማያረግውን ነው፡፡” ብለው ኹለቱም ፊታቸውን በማንገሽገሽ ጭፍግግ አደረጉት ከእዛ በኃላ ያረገችውን እኔ መንገሩ ልቤ አልፈቀደወም፡፡…… “እኛ ውጊያችን ከህዝብ እና ከፈጣሪ ጠላት ጋር ነው! በሚደርስብን፡- መከራ፣ እንግልት፣ እስር ምንም አንከፋም! እግዚአብሔርም ለእዚህ እድል ስለመረጠን እናመሰግናለን፡፡” ብለዋል፡፡
አሁን ስላሉበት ኹኔታ አንድ እስረኛ ስጠይቅ “እውነት ክርስትና እንዲህ ናት? ምንም
እንደማላውቅ ነው የተረዳሁት፤ የሚገርመኝ ማታ ኹሉም ሲተኛ እነሱ ሲያነበንቡ ሲፀልዩ ነው
የሚያድሩት ሌሊት በነቃሁ ቁጥር እነሱ ሲፀልዩ ነው የማያቸው፤ መቼ እንደሚተኙ እንኳን
አላውቅም በጣም ይገርማሉ” ብሎኛል፡፡
እስር ቤቱ ውስጥ ኹሉንም ቀርበው የሚያወሩት መነኮሳቱ ብቻ በመኾናቸው የማይስማሙ፣
የተጣሉ እስረኞችን በማስታረቅ፤ የሚመጣላቸውን ምግብ ለሌሎች ጠያቂ ለሌላቸው
በመስጠታቸው፤ ባሉበት ዞን ውስጥ ሰላማዊ አየር በመፍጠራቸው በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት
ኃላፊዎች ዘንድ ጥርስ ተነክሶባቸው፤ በተደጋጋሚ ጨለማ ቤት እንዲታሰሩ ተደርገዋል፡፡
በዛሬው ዕለትም ለፍርድ ቤቱ አቤቱታ ያቀረቡ ሲኾን ካቀረቡት መካከል፡-
1. ከሰው እንድንገለል ተደርገናል፤
2. አብረን እንዳንመገብ ተከልክለናል፤
3. ፀሎት እንዳናደረስ ተፅዕኖ እየተደረገብን ነው፤
ፍርድ ቤቱም ለኅዳር 15 ቀን 2010ዓ.ም ቀጠሮ ሰጥቷቸዋል፡፡መነኮሳቱን የዋልድባ ገዳም መነኮሳት እና አበመኔት ጨምሮ እየመጡ ይጠይቋቸዋል፡፡በአዲስ አበባ ውስጥ ያለን የክርስትና እምነት ተከታዮች እንዲኹም ፍትህ ፈላጊዎች በሙሉ፡-እነዚህ አባቶች የታሰሩት ለታመነችው ኦርቶዶክስ እና ለቅፅረ ቤተ ክርስቲያንዋ መጠበቅ፣መከበር ሲሉ በመኾኑ ማረሚያ ቤት በመሄድ እንጠይቃቸው፤ ፍርድ ቤትም በቀጠሯቸው ቀን በመገኘት አጋርነታችን እናሳያቸው፡፡ የቤተ ክርስቲያን ጉዳይ ይመለከተናል የሚለው # ቤተ_ክህነትም ከታሰሩት ከአባቶች ጎን ሊቆም ይገባዋል። ሁሉም ክርስቲያን ከእኒህ አባቶች ጎን በመቆም፣ በመተባበር ከእስር እንዲፈቱ የበኩሉን አስተዋፅኦ ያድርግ፡፡ መነኮሳቱም “እኛ ስለ እምነታችን እና ስለገዳማችን ለመሞት ዝግጁ ነን!” ብለዋል፡፡ የእነሱ ብርታትና ጥንካሬ ለእኛም ያድለን!

Gebrial Gizachew
Filed in: Amharic