>

«ባባ ዛሬ ሻይ አትጠጡም ካለን በፍፁም ሻይ አንጠጣም!! ...» የኪሱሙ ነዋሪ (በዮናስ ሃጎስ)

አሁን 11 ሰዓካባቢ ላይ ነው። የጁቢሊ ፓርቲ (ገዢው ፓርቲ) ተወካይ ሴናተር ጄምስ ሙር ፓርቲውን ወክሎ መግለጫ እየሰጠ ነው።
«ቅድም የናሳ ተወካዮች የሰጡትን መግለጫ አዳምጠናል። ኬንያውያን የመምረጥም ሆነ ያለመምረጥ መብታቸው የተጠበቀ ሆኖ ሳለ የናሳ መሪ ራይላ ኦዲንጋ ግን የኪሱሙ ወጣቶችን በመደለል ብጥብጥ እንዲያስነሱና በዚያ ካውንቲ ምርጫ እንዳይደረግ እንዲከላከሉ አድርጓል። ለነዚህ ወጣቶች የማስተላልፈው መልዕክት ቢኖር ራሳቸውን ለፖለቲከኞች ሲሉ ችግር ውስጥ መክተት እንደሌለባቸው ነው። ፖለቲከኞች ዞረን ዞረን እንገናኛለን። አሁን እንኳ እኔ እዚህ መግለጫ ከመስጠቴ በፊት ከናሳ ተወካዮች ጋር ሻይ እየጠጣን ነበረ። እኔ ነኝ የጋበዝኳቸው። እንዲያውም ሒሳቡን እንድከፍል እየጠበቁኝ ነው። ስለዚህ እኛ ዞረን ዞረን ልንገናኝ ለማይረባ ፖለቲካ ሲባል ሕይወታችሁን አታበላሹ…»
***
ቀጥሎ የተፈጠረው ነገር በፍፁም ያልተጠበቀ ነው። ልብ በሉ ይህ መግለጫ በሐገሪቷ አራት የቴሌቭዥን ጣቢያዎች በቀጥታ እየተላለፈ ነው።
***
የናሳ ተወካዮች ከግራ በኩል እየተንጫጩ ሲመጡ በድንገት ታዩ። ተወካዮቹ ሴናተሩንና ሌሎቹን የገዢውን ፓርቲ ተወካዮች ከመናገርያው እንዲርቁ አደረጓቸው። የማታሬ የፓርላማ ተወካይ ማይክራፎኑን ተቀብሎ «ይህ ሰውዬ ውሸታም ነው። አይደለምና ሻይ ሊጋብዘን ቀርቶ ይህን አሁን መግለጫ እየሰጠበት ያለውን ቦታ ራሱ የከፈልንበት እኛ ነን። ስለዚህ እኛ በከፈልንበት ሆቴል ተቀምጦ መሪያችንንና እኛን የሚያንቋሽሽ ነገር ሲናገር መስማት ስለማንችል ካሁን በኋላ መግለጫ የሚባል ነገር የለም! መግለጫ መስጠት ከፈለጉ ቤተ መንግስቱ የነርሱ ስለሆነ እዛ ሄደው ይስጡ» ሲል በቁጣ ለጋዜጠኞች ተናግሯል። የጁቢሊ ተወካዮች ወደ መግለጫቸው ለመመለስ ያደረጉት ጥረት ጥቂት የቡጢ ምልልሶችን ቢያስተናግድም በማታሬው የፓርላማ ተወካይ እንቢተኝነት መግለጫውን አቋርጠው ለመውጣት ተገድደዋል።
***
ኪሱሙ አይደለምና ምርጫ የሚባል ነገር ልታስተናግድ ቀርቶ ነዋሪዎቿ በቪድዮው ላይ በምትመለከቱት መልኩ ከወታደሮች ጋር ተፋጥጠው ነው የዋሉት። እኔ ባለሁበት ኪቢራ ከጠዋት አንድ ሰዓት ጀምሮ መተኮስ የጀመረው አስለቃሽ ጭስ እና ጥይት አሁን 12 ሰዓት ካለፈ በኋላ ነው በረድ ያለው። በኪሱሙ ጋዜጠኞች ያነጋገሯቸው ነዋሪዎች የሚከተለውን ብለዋል።
«ኡሁሩ ኬንያታ ካለፈው ነሐሴ ጀምሮ ፈላጭ ቆራጭ ወታደራዊ መንግስት ሆኗል። ስለዚህ እንደጀመረው በጉልበት መግዛቱን ይቀጥል እንጂ ዴሞክራሲያዊ መንግስት ነኝ ዓይነት ድራማ ለመስራት የውሸት ምርጫ በዚህ ግዛት ውስጥ እንዲያካሂድ አንፈቅድም። በካርድ የተመረጠ መንግስት ሳይሆን በመሳርያ እየገዛ ያለ መንግስት ነውና በዚያው ይቀጥል..»
***
ሌላኛዋ ተናጋሪ ለተቃዋሚው መሪ ራይላ አሞሎ ኦዲንጋ ያላቸውን ክብርና ፍቅር ለመግለፅ አንድ ዓረፍተ ነገር ብቻ በቅቷታል።
«ባባ ዛሬ ሻይ አትጠጡም ካለን በቃ ሻይ ሳንጠጣ መዋላችን ነው!»
Filed in: Amharic