>

ጀግናው ሻምበል አበበ ቢቂላ ‹‹ሮምን የወረረው ብቸኛው ወታደር›› (በአምደጽዮን ሚኒሊክ)

ለኢትዮጵያና ለአፍሪካ የመጀመሪያውን የኦሊምፒክ ማራቶን የወርቅ ሜዳልያ ከዓለም ክብረ ወሰን ባለቤትነት ክብር ጋር ያስገኘው ጀግናው ኢትዮጵያዊ ሯጭ ሻምበል አበበ ቢቂላ የሞተው ከዛሬ 44 ዓመታት በፊት (ጥቅምት 15 ቀን 1966 ዓ.ም) ነበር፡፡

አበበ ቢቂላ አበበ ቢቂላ ነሐሴ 30 ቀን 1925 ዓ.ም በሸዋ ጠቅላይ ግዛት በደብረ ብርሃን አውራጃ፣ ደነባ ልዩ ስሟ ጃቶ በምትባል ሥፍራ ላይ ከአባቱ አቶ ቢቂላ ደምሴና ከእናቱ ከወይዘሮ ውድነሽ መንበሩ ተወለደ።

ወጣቱ አበበ እንደአካባቢው ልምድ በእረኝነትና በትምሕርት ተሰማርቶ በአሥራ ሁለት ዓመቱ የቄስ ትምሕርቱን አጠናቀቀ። በዚህ በጨቅላ ዕድሜው ስመ ጥር የገና ተጫዋች እንደነበር ይነገርለታል። በ1944 ዓ.ም ወደ አዲስ አበባ በመሄድ በክብር ዘበኛ ሰራዊት በወታደርነት ይቀጠርና በገና ጨዋታ እና በስፖርት እየዳበረ ቆየ።

ወዲያው በ1946 ዓ.ም ደግሞ የአራት ልጆቹ እናት መሆን የቻለችውን ወይዘሪት የውብዳር ወልደጊዮርጊስን አገባ።

በኅዳር ወር 1948 ዓ.ም በአሥራ ስድስተኛው የሜልቦርን ኦሊምፒክ ላይ የተሳተፈውን የኢትዮጵያን ቡድን ለመቀበል በተደረገው ሰልፍ ላይ ከጀርባቸው ላይ የአገራቸው ስም የተጻፈበትን መለያ ልብሳቸውን ለብሰው አገራቸውን ወክለው የተወዳደሩትን ወጣቶች ባየ ጊዜ ምን ያህል የኩራት ስሜት እንደተሰማውና ያን ጊዜ እሱም እንደነሱ ለመሳተፍ እንደወሰነ ይነገራል።

በዚሁ ወቅት አበበ በብሔራዊ የሠራዊቱ እርስ በርስ ውድድር ላይ ተሳተፈ፡፡ በ5000 ሜትር እና በ10,000 ሜትር ሩጫ የብሔራዊውን ክብረ ወሰን የያዘው የጊዜው የስፖርት ጀግና ዋሚ ቢራቱ እና አበበ በማራቶን ውድድሩ ሲገጥሙ ተመልካቹ ሕዝብ ‹‹ዋሚ ያሸንፋል›› ብሎ ነበር ጠብቆ ነበር።

ከጥቂት ኪሎሜትሮች በኋላ አበበ ቢቂላ የተባለ ከዚያ ቀደም በሰው ዘንድ ታዋቂ ያልነበረ ወጣት ቀድሞ ሩጫውን እየመራ እንደሆነ ሕዝቡ በራዲዮ ሰማ። ውድድሩንም በቀላሉ አሸነፈ። የዋሚን የአምስት ሺ እና አሥር ሺ ሜትር ክብረ ወሰን በመስበርም እየታወቀ መጣ።

ታዲያ በዚህ ሁኔታ ነበር አበበ ለ1952 ዓ.ም የሮም ኦሊምፒክ በተወዳዳሪነት የተመረጠውና ያንን የአገሩን መለያ ልብስ በዓለም አቀፍ ውድድር ላይ ለብሶ ለመሳተፍ ከአራት ዓመታት በፊት ያለመው ሕልሙን እውን ያደረገው።

በጦር ካምፕ ውስጥ አበበ የሚያደርጋቸውን ልምምዶች እና ውድድሮች በጥሞና ይከታተሉ የነበሩት ስዊድናዊ አሰልጣኝ ኦኒ ኒስካነን፣ የአበበን ችሎታ በመገንዘባቸው ከሌሎቹ አትሌቶች ጋር ተቀላቅሎ እንዲለማመድና፣ የሮም ኦሎምፒክ እስኪቃረብ ድረስም ከ2000 ሜትር በላይ ከፍታ ባላቸው ተራራማ ቦታዎች ላይ የመሮጥና የ1500 ሜትር ተደጋጋሚ የፍጥነት ሩጫ ልምምዶችን እንዲሠራ አደረጉት።

በሮም ኦሊምፕክ ኢትዮጵያን ወክለው ለመሳተፍ ከአሰልጣኙ ጋር ወደ ሮም ካመሩት የኢትዮጵያ ተወዳዳሪዎች መካከል ለማራቶን ሩጫ የተመረጡት አበበ ቢቂላ እና አበበ ዋቅጅራ ነበሩ።

አሰልጣኙ ኒስካነን የሞሮኮው ራህዲ ቤን አብዴሰላም ፣ የኒውዚላንዱ ባሪ ማጊ፣ የሶቪዬት ኅብረቶቹ ኮንስታንቲን ቮሮብዮቭ እና የወቅቱ የማራቶን ክብረ ወሰን ባለቤት የነበረው ሰርጌይ ፖፖቭ (2:15:17.0) እንዲሁም የብሪታንያው ዴኒስ ኦጎርማን የጊዜውን ምርጥ ማራቶን ተወዳዳሪዎች እንደነበሩ ለሁለቱ ኢትዮጵያውያን ሯጮች በጥብቅ ነግረዋቸዋል።

ይሁን እንጂ የሞሮኮው ራህዲ ይለብሳል የተባለው የመለያ ቁጥሩ 26 የነበረ ቢሆንም የለበሰው መለያ ግን በ10ሺህ ሜትር ውድድር ላይ ለብሶት የነበረው መለያ ነበር፡፡ ስለሆነም አበበ የሞሮኮው ሯጭ የትኛው እንደሆነ አላወቀም ነበር፡፡

የአበበ ፍላጎትና ሃሳብ ራህዲ እስከሚያጋጥመው ድረስ ጉልበቱን ለመቆጠብ ነበር፡፡ በዚህ ምክንያት ባይሆን ኖሮ ክብረ ወሰኑን በተሻለ ውጤት ይሰብር እንደነበር ኒስካኒን ጥርጣሬ እንዳልነበራቸው ገልጸዋል።

ሆኖም አበበ ቢቂላ ውድድሩን በሁለት ሰዓት፣ ከአሥራ አምስት ደቂቃ፣ ከአሥራ ስድስት ነጥብ ሁለት ሴኮንድ (2:15:16.2) በማጠናቀቅ የዓለምን ክብረ ወሰንን ሰብሮ የወርቅ ሜዳሊያ አገኘ። ራህዲ ሁለተኛ፣ ባሪ ማጊ ደግሞ ሦስተኛ ደረጃን አገኙ።

በውድድሩ ማግሥትም፣ የኢጣሊያ ጋዜጦች ‹‹ኢትዮጵያን ለመውረር የኢጣሊያ አገር ወታደር ሁሉ አስፈልጎ ነበር፤ ኢትዮጵያ ግን አንድ ወታደር ብቻ ልካ ድፍን ሮምን ወረረችው›› የሚል ጽሁፍ ይዘው ወጡ፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ በኦሊምፒክ ውድድር አሸንፎ የወርቅ ሜዳሊያ የወሰደ ጥቁር አፍሪካዊ አበበ ቢቂላ ነው።

ይህም አጋጣሚ ብዙ ጥቁር አፍሪካውያን በዓለም አቀፍ ውድድሮች እንዲሳተፉ በር ከፍቷል። የአበበ ቢቂላ ዝናም ከዓለም ጫፍ እስከ ጫፍ ተዳረሰ።

ከዚህ ውድድር በኋላ አበበ ወደ ኢትዮጵያ በተመለሰ በሁለት ወሩ በክብር ዘበኛ ሠራዊት ዋና አዛዥ ብርጋዴር ጄነራል መንግሥቱ ንዋይ እና በወንድማቸው ገርማሜ ንዋይ ጥንሰሳ የተካሄደው የታኅሣሥ 1953 ዓ.ም የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ሲከሽፍ፣ የሠራዊቱ አባል የነበረው አበበም ከሌሎች ወታደሮች ጋር በመጠርጠር ለጥቂት ጊዜ ታስሮ እንደነበር ይነገራል።

ከታኅሣሡ ግርግር በኋላ እስከ ጥቅምት 1954 ዓ.ም ድረስ አበበ በግሪክ፣ በጃፓን እና በቼኮዝሎቫኪያ በማራቶን ተወዳድሮ በሁሉም አንደኛ በመውጣት አሸንፏል።

ሐምሌ 3 ቀን 1956 ዓ.ም አዲስ አበባ ላይ የተካሄደው የኢትዮጵያ የኦሊምፒክ ማጣሪያ ውድድር በአበበ አሸናፊነት፤ በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ማሞ ወልዴ እና ሦስተኛ የወጣው ደምሴ ወልዴ ወደ ቶኪዮ እንደሚጓዙ ሲረጋገጥ በመላው ዓለም ኢትዮጵያ አንድ ብቻ ሳይሆን ሦስት ኃይለኛ ተወዳዳሪዎች እንዳሏት ተሰማ።

የቶኪዮ ኦሊምፒክ 40 ቀናት ሲቀሩት አበበ በልምምድ ላይ እያለ በህመም ራሱን ስቶ ወደቀ፡፡ ቀዶ ጥገና ተደረገለትና ልምምዱን ቀጠለ፡፡ ማንም ያሸንፋል ብሎ የገመተ ሰው ሳይኖር ጀግናው የኢትዮጵያ ልጅ ግን ከዓራት ዓመታት በፊት ሮም ከተማ ላይ የሰበረውን የዓለም ክብረ ወሰን ጭምር በማሻሻል የቶኪዮውን ውድድር አሸነፈ፡፡

በቶኪዮው ድሉ የኦሊምፒክን ብቻ ሳይሆን የዓለምን ክብረ ወሰን ጭምር መስበር ችሏል። ከእርሱ በፊት ማንም ያልፈጸመውን፣ ከእርሱ በኋላም ለ16 ዓመታት ማንም ያላደረገውን የኦሊምፒክ ማራቶን ሁለት ጊዜ አከታትሎ የመውሰድ ገድልንም ፈጸመ። ይኸም ብቻ አይደለም፤ በአሻናፊነት የገባበት ሰዓትም እጅግ በጣም ፈጣንና በእንግሊዛዊው ባዝል ሔትሌይ በ2 ሰዓት 13 ደቂቃ 55 ሰኮንድ ተይዞ የነበረውን የዓለም ክብረወሰን በ1 ደቂቃ 43 ሰከንድ፣ 8 ማይክሮ ሰከንድ ያሻሻለበት ነው፡፡

ሁለተኛውን ወርቅ ይዞ ወደ ኢትዮጵያ ሲመለስ፣ መላው የአዲስ አበባ ሕዝብ ወጥቶ የጀግና አቀባበል ካደረገለት በኋላ ንጉሠ ነገሥቱ የሻምበልነት ማዕረግና አዲስ ቮልስ ዋገን ቢትል መኪና ሸለሙት።

የሜክሲኮ ኦሊምፒክ በተደረገበት ዓመት እግሩ ላይ በደረሰበት ጉዳት ልምምዱን ለማቋረጥ ተገዶ ነበር፡፡ ይባስ ብሎም ከውድድሩ ጥቂት ቀናት በፊት አበበ የእግር አጥንቱ ስብራት ደርሶበት እንደነበር ይነገራል፡፡ ሜክሲኮ ሲገባም በእግሩ ላይ የደረሰው ጉዳት አልተሻለውም ነበር። ውድድሩ የሚካሄድበት ቦታ ከፍታው አበበ ቢቂላ ከለመደው በ1000 ጫማ ከፍታ ያለም ነበር፡፡

ውድድሩ ተጀመረና እስከ አስራ ሰባተኛው ኪሎሜትር ድረስ ከሮጠ በኋላ የእግሩ ሕመም ስለጠናበት ‹‹አይዞህ ታሸንፋለህ፤ እኔ አልቻልኩም፤ የ ግሬ ወለምታ በጣም ተሰምቶኛል፤ ሌላም የማላውቀው ስሜት እየተሰማኝ ነው። ስለዚህ አደራዬን ተቀበለኝ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ይጠብቀናል፤ እኔ ስላልቻልኩ አንተ ቀጥል፤ የኢትዮጵያ አምላክ ይከተልህ» በማለት ለማሞ ወልዴ አደራ ሰጥቶት አስፋልት ዳር ወደቀ። ወዲያውኑም ወደ ሆስፒታል ተወሰደ።

ጀግናው ማሞ ወልዴም የአቤን አደራ ፈፀመ፤ አሸንፎ ለኢትዮጵያ ሦስተኛውን የማራቶን ወርቅ ተቀበለ። አበበ ቢቂላም ከዚህ በኋላ ውድድር ሳያደርግ ቀረ።

ሻምበል አበበ ቢቂላ በሽልማት የተሰጠውን ቮልስ ዋገን መኪና አዲስ አበባ ውስጥ ሲነዳ (በ1961 ዓ.ም) አደጋ ደርሶበት ከወገቡ በታች ተጎዳ። ንጉሠ ነገሥቱ ለሕክምና ወደ እንግሊዝ አገር ልከውት በታወቀው የስቶክ ማንደቪል ሆስፒታል (Stoke Mandeville Hospital) በሕክምና ሲረዳ ቢቆይም ጉዳቱ ከተሽከርካሪ ወንበር የማያላቅቀው በመሆኑ ወደሚወዳት ሀገሩ ኢትዮጵያ በቃሬዛ ተመለሰ። አዲስ አበባ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርስ ቤተሰቡ፣ ወዳጆቹና ደጋፊዎቹ ሲቀበሉት በበዙ ሺ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንም በየመንገዱ ዳር ተሰልፈው እያጀቡ ተቀበሉት። ከአደጋው በኋላ እነኛ ዓለምን ያስደነቁ እግሮች ሁለተኛ አልተራመዱም።

በወቅቱም ‹‹መልካም ውጤት የሚያመጡ ሰዎች አሳዛኝ አደጋም ይገጥማቸዋል። በእግዚአብሔር ፍቃድ የኦሊምፒክ ማራቶንን ለማሸነፍ በቃሁ፤ እንዲሁም በእግዚአብሔር ፍቃድ የመኪና አደጋ ደረሰብኝ። ድሉን እንደተቀበልኩ ሁሉ መከራውንም መቀበል አለብኝ። ሁለቱንም የሕይወት ሁኔታዎች ስለሆኑ በጸጋ ተቀብዬ ሕይወቴን በደስታ መኖር ነው ያለብኝ›› ብሏል።

በ1964 ዓ.ም በተካሄደው 20ኛው የሙኒክ ኦሊምፒክ ውድድር ላይ በልዩ እንግዳነት ተጋብዞ በተሽከርካሪ ወንበሩ ላይ ተቀምጦ ውድድሩን ተመልክቷል። የወቅቱን የማራቶኑን ውድድር ያሸነፈው አሜሪካዊው ፍራንክ ሾርተር ሽልማቱን ከተቀበለ በኋላ በቀጥታ ወደ አበበ ቢቂላ ሄዶ እጁን በመጨበጥ ያለውን ፍቅር እና አክብሮት ገልጾለታል።

ከተወዳደረባቸው አስራ አምስት የማራቶን ውድድሮች አስራ ሁለቱን በአንደኛነት የጨረሰው ኢትዮጵያዊው ጀግና ጥቅምት 15 ቀን 1966 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ፡፡

የጀግናው ሻምበል አበበ ቢቂላ አስክሬን አዲስ አበባ በቅዱስ ዮሴፍ ቤተ ክርስቲያን ሲቀበር ቀዳማዊ አጤ ኃይለሥላሴ በተገኙበት ዘመዶቹ ወዳጆቹ እና አድናቂዎቹ ጋር ከ75 ሺህ በላይ የሚሆን ሕዝብ ተሰብስቦ እየተላቀሰ የመጨረሻ ስንብት አድርጎለታል። ዕለቱም በመላ ኢትዮጵያ የሐዘን ቀን ሆኖ እንዲውል ተደርጓል።

ከጀግናው የክብር መታወሻዎች መካከል የሚከተሉት ይጠቀሳሉ

• አዲስ አበባ ውስጥ አባ ኮራን ሰፈር የሚገኘው የቀድሞው የአሜሪካ ሕብረተሰብ ት/ቤት ስታዲየሙን በአበበ ስም ሰይሞለታል፡፡

• አምስተርዳም ከተማ የአበበ ቢቂላ መንገድ አላት፡፡

• ሮም አበበን የዘከረችው በሩጫ ብቻ ሳይሆን ከከተማዋ 25 ኪሎ ማትር ርቀት ላይ በምትገኘው ላዲስፖሊ ከተማ የሚገኘውን አዲስ የእግር ድልድይና መንገድ በአበበ ቢቂላ ስም (ፖንቴ አበበ ቢቂላ) በመሰየም ነው፡፡

• የሴኔጋል መዲና ዳካር በ1971 ዓ.ም. የመጀመሪያውን የአፍሪካ አትሌቲክስ ውድድር ምክንያት በማድረግ ወደ ‹‹ዴምባ ዲዮፕ›› ስታዲየም የሚያስገባውን መንገድ የአበበ ቢቂላ መንገድ ብላ ሰይማዋለች።

• ‹‹ቶኪዮ ኦሊምፒያድ›› በተባለው የትረካ ፊልም ላይ የአበበ ቢቂላ የቶኪዮ ድል ተጨምሯል። ከዚሁ ፊልም የተወሰደ ክፍልም በ1968 ዓ.ም በተሠራው ‹‹ማራቶን ማን›› በተባለው ፊልም ላይ ይገኛል።

• ‹‹ቪብራም›› የተባለ የአሜሪካ የጫማ አምራች ድርጅት በ2002 ዓ.ም ‹‹ፋይቭ ፊንገርስ ቢቂላ” (FiveFingers Bikila) የተባለ ጫማ ለገበያ አቅርቧል።

• ሮቢን ዊሊያምስ የተባለው አሜሪካዊ ቀልደኛ ‹‹የራስ ማጥፊያ መሳሪያዎች››በተባለው ዝግጅቱ ላይ የአበበን በባዶ እግር መሮጥ ይጠቅሰዋል።

• ነሐሴ 1 ቀን 2005 ዓ.ም ቀን ለሕዝብ እይታ የቀረበው የ’ጉግል’ (Google) ሰሌዳ የአበበን 80ኛ ልደት በመዘከር በሮም ውድድር ላይ በባዶ እግሩ የመጨረሻውን መስመር በጥሶ ሊያልፍ ሲል የነበረውን ገጽታ የሚያሳይ ምስል አቅርቧል።

ከጀግናው ንግግሮች መካከል፡

• ‹‹እኔ ዓለም ሁሉ እንዲያውቀው የምፈልገው አገሬ ኢትዮጵያ ሁል ጊዜ የምታሸንፈው በቆራጥነት እና በጀግንነት ነው፡፡›› ሮም ኦሊምፒክ ላይ ካሸነፈ በኋላ

• ‹‹መልካም ውጤት የሚያመጡ ሰዎች አሳዛኝ አደጋም ይገጥማቸዋል። በእግዚአብሔር ፍቃድ የኦሊምፒክ ማራቶንን ለማሸነፍ በቃሁ፤ እንዲሁም በእግዚአብሔር ፍቃድ የመኪና አደጋ ደረሰብኝ። ድሉን እንደተቀበልኩ ሁሉ መከራውንም መቀበል አለብኝ። ሁለቱንም የሕይወት ሁኔታዎች ስለሆኑ በጸጋ ተቀብዬ ሕይወቴን በደስታ መኖር ነው ያለብኝ፡፡›› በደረሰበት ጉዳት የተሽከርካሪ ወንበር ተጠቃሚ ከሆነ በኋላ

• ‹‹እኔ የዓለም አንደኛ፣ የኢትዮጵያ ግን ሁለተኛ ሯጭ ነኝ፡፡›› ለዋሚ ቢራቱ ያለውን ፍቅር ክብር እና አድናቆት ሲገልጽ

• ‹‹ለምወዳት አገሬ ኢትዮጵያ እና ሕዝቧ የሺህ ዓመት መኩሪያ እና መከበሪያ ታሪክ በእግዚአብሔር ፈቃድ ስለሠራሁ ከእንግዲህ በኋላ የምመኘው ነገር የለም።››

• ‹‹እኛስ ኢትዮጵያውያን ለሀገራችን ለኢትዮጵያ ምን አደረግንላት?››

• ‹‹እኔ በባዶ እግሬ ለመሮጥ የመረጥኩበት ዋናው ምክንያት ጫማ አጥቼ ሳይሆን ኢትዮጵያ አገሬ ከጥንትም ጀምራ የጀግንነትን ሙያ በድፍረትና በቆራጥነት የምትፈፅም መሆኑን ለዓለም በይፋ ለማሳወቅ ነው››

ቻርሊ ሎቬት ‹‹ማራቶን በኦሊምፒክ›› በሚለው መጽሐፉ ላይ፣ አበበ ቢቂላን ‹‹ወደር የማይገኝለት እውነተኛ የማራቶን ሯጭ ምሳሌ ነው›› ይለዋል።

ሪቻርድ በኔዮ ደግሞ ‹‹የማራቶን ጌቶች›› በሚለው መጽሐፉ፣ ‹‹አበበ ቢቂላ ሩጫውን ምንም አይነት ጥረት የማያስፈልገው ያስመስለዋል፤ አበበ ቢቂላን ሲያዩት ረጅም ቀጠን ያለ በቀላሉ ተሰባሪ ይመስላል፤ ነገር ግን ከሚገባው በላይ ጠንካራ አትሌት ነው፡፡ አበበ የማንኛውም ዓይነት የማራቶን ሩጫ ተወዳዳሪ ሊሆን የሚገባው ሰው ነው፤ ብሏል። አበበ ቢቂላ ተፈጥሮ ካፈራቻቸው ምርጥ የዓለማችን አትሌቶች አንዱ ነው›› በማለት ይገልፀዋል።

(ምንጭ ፡ ዊኪፒዲያ አማርኛ)

Filed in: Amharic