>

የበፍቃዱ ሞረዳ እውነት (ሃብታሙ አያሌው)

በአንዱ ይሁን በሌላ ምክንያት በዛሬዉ የኦሮሚያ ክልል ዉስጥ ከሚገኙት አካባቢዎች ኢሉአባቦርን ያህል የስብጥር (diversity) አብነት የሚሆን አካባቢ ያለ አይመስለኝም፡፡ ተከባብሮ፣ተቻችሎ፣ ተፋቅሮ የመኖር ተምሳሌት ነዉ ኢሉአባቦር፡፡
ያደግነዉ ከሕንዶች፣ከአረቦች፣ ከሱዳኖች፣ከአማሮች፣ ኤርትራ ተወላጆች፣ ከጉራጌዎች፣ ከትግሬዎች፣ ከካፍቾ…ልጆች ጋር በፍቅርና በመከባበር ነዉ፡፡ ከኢሉ ማርና ወተት ተጋርተን፡፡
ከአባቴ ልጆች አንዷ ሙስልም ባል አግብታ የሰለመች ናት፡፡ የአንዷ ባል ጉራጌ ነዉ፡፡ሰባት ቤት ያሉ ጉራጌ ዘመዶቹን ረስቶ፣ እኛን ዘመድ አድርጎ ኖሮ አሁን ለእርጅና ዕድሜ የደረሰ፡፡ መለሰ እግር ጥሎት ወደእኛ የገጠር መንደር ሲመጣ የአካባቢዉን ቋንቋ እንኳን መናገር አይችልም ነበር፡፡ የኢሉ የፍቅር ኃይል ግን ጠልፎ አስቀረዉ፡፡ ዉሎ አድሮ የእኛን ቋንቋ ለምዶ፣ የእርሱን ቋንቋ የማትችለዉን እህቴን አግብቶ፣ ልጆች አፍርቶ እኛን ሆኖ ኖሮ አረጀ፡፡
አንዷ እህቴ ከአንዱ የከፋ ሰዉ ሁለት ልጆች ወልዳለች፡፡ ትዳሯ ባይሆንላት ከእሱ ተፋታ፣ የአማራ ሰዉ አግብታ ሌሎች ልጆች ወልዳ ትኖራለች፡፡
ይህ በእኛ ቤት ዉስጥ ያለዉ እዉነት በአብዛኛዉ በኢሉአባቦር ሰዉ ቤትና መንደር ያለ እዉነት ነዉ፡፡ጊዜና ሁኔታ ያልለወጠዉ እዉነት፡፡
አንዳንድ ወገኖች በበጎነት ባይቀበሉትም በዚያን ዘመን በድርቅ ከተጎዱት አካባቢዎች በተለይም ከወሎና ከትግራይ ተነስተዉ ሌላ ቦታ ከሰፈሩት ሰዎች መሐከል ኢሉ አብዛኛዉን ተቀብላ ዛሬም ድረስ ተፈጥሮ ከቸራት ፀጋ እያጋራች ፣ጥላና ከለላ በመሆን በሰላምና በፍቅር እያኖረቻቸዉ መሆኑ እዉነት ነዉ፡፡ ሰፋሪዎችም ‹‹ ሀገሬ ›› ብለዉ፣ ነባሩ ሕዝብም ‹‹ ወገኔ›› ብሎ፡፡
ላለፉት ሰላሳ ዓመታት ‹‹ አንተ ሰፋሪ ነህ›› ብሎ የተናገራቸዉና ያገለላቸዉ የኢሉ ሰዉ የለም፡፡ሰፋሪዉም በሰፋሪነቱ ባይተዋሪነት ተሰምቶት ሀገሩን ጥሎ አልሄደም፡፡ የኢሉ ተፈጥሮዉ ብቻም ሳይሆን የሰዉም ፍቅር ኃይለኛ ሙጫ ነዉና፡፡
ባለፉት ሃያ ምናምን ዓመታት የኢሉአባቦርን ሀብት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ሲዘርፍ የኖረዉ ‹‹ ወያኔ›› የተሰኘዉና በትግራይ ሕዝብ ስም የሚነግደዉ የጥፋት ኃይል ተፈጥሯዊ መሞቻዉ ባልጠበቀዉ ሁኔታ ሲቃረብ በእጁ የቀረዉን የመጨረሻ የአጥፍቶ መጥፋት ካርድ መጠቀም ይዟል፡፡

በዚህም የሞት ሽረት መፍጨርጨር ዉስጥ ሰሞኑን በየዋሁና በደጉ የኢሉ አባቦር ሕዝብ ጉያ ሥር ተደብቀዉ የኖሩ ነቀዞች ፣በተለይም በኦሮሞና በአማራ መሀከል ግጭትን በመፍጠር እየነደደባቸዉ ያለዉን እሳት የሚያበርዱ መስሏቸዉ እንደለመዱት አረመኔያዊ ግድያ ፈፅመዋል፡፡ በዚህ ግድያ ሰለባ የሆኑት አማሮች ብቻ ሳይሆኑ አሮሞ ወንድሞቻቸዉም ጭምር ናቸዉ፡፡
ይሁን እንጂ፣በድርጊቱ የኦሮሞን ሕዝብ ለመወንጀል በየሶሻል ሚዲያዉ ላይ ወያኔዎች ባሰማሩዋቸዉ ሚሊሺያዎቻቸዉ አማካይነት የተሳሳቱ መረጃዎችን በማሰራጨት፣ ለበለጠ ግጭትና መቃቃር ከበሮ ድለቃ ይዘዋል፡፡ አንዳንድ የዋህዎችም ይህንኑ ፕሮፓጋንዳቸዉን እየተቀበሉ ሲያስተጋቡላቸዉ ይታያሉ፡፡ ስለአማራ የተቆረቆሩም በመምሰል የአዞ እምባ ለማፍሰስ ይሞክራሉ፡፡
ይህን አሳፋሪ የወንጀል ተግባር የፈፀሙ ሰዎች ማንም ይሁኑ ማን፣ መቼም ቢሆን ለታሪክ ፍርድ መቅረባቸዉ የማይቀር ነዉ፤ ይገባልም፡፡ ለዚህ ደግሞ ከማንም በላይ ተግቶ የሚሠራዉ የኢሉ አባቦር ሕዝብ ነዉ ፡፡በፍቅርና በሰላም ላጌጠዉ መልካም ስሙና ክብሩ ሲል፡፡
እስከዚያዉ ግን ፣እዚያም እዚህም ያላችሁ መልካምና ቅን ሰዎች በስሜታዊነት ተገፋፍታችሁ በወያኔ ወጥመድ ዉስጥ ላለመግባት ተጠነቀቁ ዘንድ ጊዜዉ ይጠይቃል፡፡ በኦሮሞ ስም የሚያለቃቅስ ሁሉ የኦሮሞ ተቆርቋር ሊሆን እንደማይችል ሁሉ ፣ በአማራ ስም ስለአማራ የሚያለቃቅስ ሁሉም እዉነተኛ የአማራ ተቆርቋሪ ሊሆን አለመቻሉን ብልህ ልብ አይስተዉም፡፡
የአሁኑ የወያኔ ጥረት እንደዚህ ዓይነት ግጭቶችን በየቦታዉ በማባባስ ሀገሪቱን በወታደራዊ አገዛዝ ሥር ለማስገባትና ተጨማሪ ዕድሜ ለመሸመት መሆኑን እየገመቱ ካሉ ወገኖች ጋር እስማማለሁ፡፡ ያስባሉ፤ የታሰበዉ ሁሉ ግን የሚሳካ አይደለም፡፡
ይህን ከፋፋይና ገዳይ ሥርዓት በተባበረ ክንድ በመጣል የሰዉ ልጅ ሰብዓዊ ክብር የተረጋገጠበትን ፣ ለሁላችንም የሚሆን ሕዝባዊ ሥርዓት ለመገንባት በአንድነት እንቆም ዘንድ አስተዋይ ልቦና ይስጠን፡፡

Filed in: Amharic