>

የተፈናቃይ ዜጎች ካሳ የማግኘት መብት፤ (ውብሸት ሙላት)

የመንግሥት የፍትሐ ብሔር ተጠያቂነት፤
ከኢትዮጵያ ሶማሌ የተፈናቀሉት ኦሮሞዎች እንደ አብነት፤
በየትም አገር ቢሆን ዜጎች በተለያዩ ሕግጋት ጥበቃ የተደረገላቸው ወይንም ከሕግ የሚመነጩ ስፍር መብቶች እንደሚኖራቸው የታወቀ ነው፡፡ መብቶቻቸውንም ለማስከበር ሲባል ተቋማት የመኖራቸውም ጉዳይ የሚያጠያይቅ አይደለም፡፡የመብት ጥሰት ባጋጠመ ጊዜ ማን ምን መደረግ እንዳለበትም ተግባርና ኃላፊነትን የሚዘረዝር ሕግ መኖሩ አይቀሬ ነው፡፡ የመብቶቹ ዓይነቶች መበራከት መብቶቹን የሚጥሱት እና ጥበቃ ማድረግ ያለባቸው አካላትም እንዲሁ ሊበረክቱ ይችላሉ፡፡

የዚህ ጽሑፍ ትኩረት ግን የመብቶቹ ዓይነቶች በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 32 ላይ ዕውቅናም ጥበቃም የተሰጠው የዜጎች በየትኛውም የአገሪቱ ክፍል ውስጥ የመንቀሳቀስና የመኖሪያ ስፍራን የመመምረጥ መብት እንዲሁም በአንቀጽ 41 ላይ ጥበቃ የተደረገለትን የዜጎችን በየትኛውም አገሪቱ ክፍል ውስጥ ለመተዳደሪያቸው በመረጡት የሥራ መስክ መሰማራትን መብቶች በመጣሳቸው ጥበቃ የማድረግ ግዴታ ያለበት የመንግሥት አካል ሕጋዊ ግዴታውን ባለመወጣ ሊኖር የሚችለውን የፍትሐ ብሔር ተጠያቂነት መዳሰስ ነው፡፡

በሕገ መንግሥቱም መሠረት ይሁን በዓለም ዓቀፍ የሰብኣዊ መብት ሰነዶች እንደሚያሳዩት የዜጎችን መብት በተመለከተ መንግሥት ቢያንስ በሦስት ምድቦች ሥር የሚካተቱ ግዴታዎች አሉበት፡፡ እነዚህም የማክበር፣ የማስከበር እንዲሁም የማሟላትም ግዴታዎችም ናቸው፡፡

የመጀመሪያው ግዴታ የሚመለከተው መንግሥት ራሱ የዜጎችንም ይሁን የሌሎች ሰዎችን መብት ከመጣስ መታቀብን ነው፡፡ በተለያዩ እርከን ላይ ከሚገኙ ከተቋማቶቹ አንዱ ወይንም ባለሥልጣናት ወይንም ሠራተኞች የሌላን ሰው መብት በመጣሳቸው ምክንያት ጉዳት ከደረሰ እንደሁኔታው የፖለቲካ፣ የወንጀል፣ የፍትሐ ብሔር ወይንም አስተዳደራዊ ርምጅ መውሰድ ይጠበቅበታል፡፡

የማስከበር ግዴታውን ደግሞ ከመንግሥት አካላት ውጭ ያሉ ነገር ግን ሰብኣዊ/ሕጋዊ መብቶችን የሚቃረን ድርጊት እንዳይፈጽሙ መከላከል ከፈጸሙም ርምጃ መውሰድን ይመለከታል፡፡ ሦስተኛው፣ የተለያዩ መብቶችም እውን ይሆኑ ዘንድ መሟላት ያለባቸውን ነገሮች ሲኖሩ ቢያንስ ሕግ በሚጠይቀው መጠን ነገር ግን አቅም እንደፈቀደ ማሟላት ግዴታን የሚመለከት ነው፡፡

ከላይ በተጠቀሱትን ግዴታዎች ማእቀፍ ሥር የሚወድቁ፣ የተለያዩ ነጠላ መብቶችን መንግሥት ማክበር፣ ማስከበር ወይም ማሟላት ባለመቻሉ ምክንያት ዜጎች ላይ ጉዳት በሚደርስት ወቅት ተጎጂዎቹ የሚኖራቸውን የፍትሐ ብሔር መብት እንመለከታለን፡፡

በአገሪቱ ውስጥ በተለያዩ ክልሎች የሚኖሩ ዜጎች በየጊዜው ሲፈናቀሉ እንደነበር የሚታወቅ ነው፡፡ ከደቡብ ብሔሮች፣ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች፣ ከጋምቤላ፣ ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ከአማራ እና ከኦሮሚያ ክልሎች የተፈናቀሉትን መጥቀስ ይቻላል፡፡ በአንድ ጊዜ ከአንድ ክልል ውስጥ በማስወጣት ከቁጥር አንጻር ተወዳዳሪ የሌለው ግን በቅርቡ ከኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል የተፈናቀሉትን ኦሮሞዎችን የሚያክል የለም፡፡ ለዘመናት ጥረው ግረው ያካበቱት ሃብት በተወሰኑ ቀናት ብቻ ምስቅልቅሉ ወጥቷል፡፡ በአግባቡ እንኳን ሰብስበውና አሽገው ይዘው መንቀሳቀስ በሚችሉበት ሁኔታ አልነበሩም፡፡ ይህ ዓይነቱ ድርጊት አሁን ብቻ ሳይሆን ከየክልሉ በተለያዩ ጊዜያት የተፈናቀሉትንም ጭምር የሚመለከት ነው፡፡

መፈናቀሉ በተፈጸመበት ወቅት በተለይም ደግሞ ተንቀሳቃሽ ንብረቶቻው ላይ ጉዳት ደርሷል፡፡ ከመኖሪያ ቤታቸው በግዳጅም ይሁን በፍርሃት ለቅቀው እንዲወጡ ተደርገዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ከንብረታቸው በተጨማሪ አካለዊ ስቃይ እና እንግልት ደርሶባቸዋል፡፡ እነዚህ ዜጎች በዋናነት በአገሪቱ ውስጥ በየትኛውም ቦታ እና በመረጡት የሙያ ዘርፍ ተሠማርተው የመኖር ብሎም ሃብትና ንብረት የማፍራት መብተቻው በመፈናቀላቸው ምክንያት ተጥሷል፤ጉዳትም ደርሶባቸዋል ማለት ነው፡፡

እንዲህ ዓይነት የመብት ጥሰቶች ሲኖሩ ከሚወሰዱት ፖለቲካዊ፣አስተዳደራዊ እና ሕጋዊ መፍትሔዎች ውስጥ የመጨረሻውን እንመለከታለን፡፡ በእርግጥ በዚህ መጠን ለተፈናቀለ ሕዝብ ፍርድ ቤት ክስ አቅርቦ ካሳ የማግኘቱ ጉዳይ በቀላሉ እውን የሚሆን እንደማይሆን ይታወቃል፡፡ ነገር ግን፣ ይህን ማድረግ ካልተለማመድን ዜጎች በአገሪቱ ሕግና የፍትሕ ሥርዓት ላይ አመኔታ መጣላቸው ይቀራል፡፡

በመሆኑም፣ ዜጎች ለደረሰባቸው ጉዳት በጊዜያዊነት ከሚሠጣቸው እርዳታ በተጨማሪ ጉዳት ያደረሰባቸው አካል ላይ የፍትሐ ብሔር ክስ በማቅረብ ካሳ የማግኘት መብታቸው ሊጠበቅ ይገባል፡፡ ይህን ለማድረግ የሚያስችል የሕግ ማእቀፍ መኖሩን እንመልከት፡፡

ከዚሕ አንጻር በዚህ ጽሑፍ ዜጎች የዜጎችን መብት እንደሚጥሱ ሁሉ መንግሥትም የዜጎችን በሚጥስበት ጊዜ የፍትሐ ብሔር ተጠያቂነት እንዳለበት ለማሳየት ነው፡፡ ከላይ የተገለጹትን የመብት ጥሰቶች መሠረት በማድረግ ሊኖር የሚችለውን ጥያቄ (የካሳና ሌላም) እንደምን አድርጎ ማቅረብ እንደሚቻል ቀጥሎ ይቀርባል፡፡

ለፍትሐ ብሔር አላፊነት ምንጮቹ፤

ሰዎች በኑሯቸው የሚያደርጓቸው ድርጊቶች የሌላን ሰው መብት የሚጥሱ ሆነው በተገኙበት ጊዜ የወንጀል ወይንም የፍትሐ ብሔር፣ እንደነገሩ ሁኔታ ሁለቱንም አላፊነቶች በጥምር ሊያስከትልባቸው ይችላል፡፡ የፍትሐ ብሔር አላፊነት (liability) መነሻው ከውል ወይም ከውል ውጭ ከሆነ ድርጊት ሊመጣ ይችላል፡፡ መነሻው ውል የሆነ እንደሆነ የአላፊነቱ ሁኔታ እና መጠን በውሉ ይታወቃል፤ እንደ ውሉ ይፈታል፡፡ ውል ያላደረጉ ሰዎች አንዱ ሌላው ላይ አላፊነት የሚስከትል አድራጎት ካደረጉ ግን መፍትሔው ሊገኝ የሚችለው ከሕግ ብቻ ነው፡፡

የአላፊነቱ መነሻ ከውል ውጭ በሚሆንበት ጊዜ በሦስት ምድብ ከሚካተቱ መነሻዎች እንዳሉት የኢትዮጵያ የፍትሐ ብሔር ሕግ ላይ መገንዘብ ይቻላል፡፡ ከዚህ ጽሑፍ ጭብጥ ጋር በቀጥታ የሚገኛኙት ግን ሁለቱን ብቻ ስለሆኑ እነሱን እንመለከታለን፡፡

የመጀመሪያው አንድ ሰው በራሱ ጥፋት ምክንያት ሌላን በመጉዳቱ ምክንያት የሚመጣ አላፊነት ነው፡፡ በዚህን ጊዜ የተፈጸመው ድርጊት ጥፋት መሆን አለበት፡፡ በተጨማሪም፣ ይህ ጥፋት የሆነው አድራጎት ሌላ ሰው ላይ ካሳ ሊያስከፍል የሚችል ጉዳት ያስከተለ መሆን አለበት፡፡ ጥፋት ብቻ መፈጸሙ ሳይሆን ጥፋቱን ተከትሎ የመጣ ጉዳት መኖር አለበት፡፡ እንዲህ ያደረገው ሰው በጥፋቱ ምክንያት ያደረሰውን ጉዳት ማሰተካከል ወይንም ማቃናት ወይንም ካሳ መክፈል ይጠበቅበታል፡፡

ጉዳት ያደረሰው አካል ደግሞ የግድ በተፈጥሮ ሰው የሆነ ብቻ ሳይሆን ተቋማት፣ መንግሥታት፣ ድርጅቶች ወዘተ ሊሆንም ይችላል፡፡ ዋናው ነገር ሌላ ሰው ላይ ጉዳት ያመጣ ጥፋት መፈጸሙ ላይ ነው፡፡ ጥፋት የሚባለው ደግሞ የግድ ወንጀል መሆን የለበትም፡፡በሕግ የተገለጸን አሠራር መጣስ፣ መልካም ጠባይን የጣሰ ወይንም አሠራርን የሚቃረን እስከሆነ እና አፈጻጸሙ ሆን ብሎ ወይንም በቸልተኝነት መሆኑ ብቻ ይበቃል፡፡

ሙያተኛ የሆነ ሰው ሙያው ከሚያዘው ውጭ በመሥራቱ ጥፋትና ጉዳት ከመጣ አላፊ መሆንም አይቀርም፤ይከተላል፡፡ሙያተኛ ሲባል እንግዲህ ሐኪም፣ ጠበቃ፣ፖሊስ፣ ወታደር ባለሙያ ወዘተ ሊሆን ይችላል፡፡ጥፋተኛ ለማለትም ይሁን ላለማለት መመዘኛው የየሞያዎቹ ደንቦች ናቸው፡፡ በሞያዎቹ ደንቦች ሲመዘን ጥፋት ከሌለበት አላፊነት አይኖርበትም ማለት ነው፡፡

በሕግ ላይ በግልጽ የተቀመጠን አሠራርን የጣሰ ካለ አላፊነቱ ያው የጣሰው ሰው ላይ ይሆናል፡፡ እዚህ ላይ ሕግ የሚባለው በግልጽ ተለይቶ ስላልተቀመጠ ሕገ መንግሥት፣ ኢትዮጵያ ተቀብላ ያጸደቀቻቸው የሰብኣዊ መብት ስምምነቶች፣ አዋጆች፣ ደንቦች እንዲሁም መመሪያዎች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡በመሆኑም፣ የማንም ሰው አድራጎት ሕግን የጣሰ እና በመጣሱም ምክንያት ጉዳት እስከደረሰ ድረስ ኣለፊነትን ሊያስከትል ይችላል ማለት ነው፡፡

ከእነዚህ አኳያ፣ በየክልሉ የሚገኙ የፖሊስና የጸጥታ ሠራተኞች በኗሪዎች ላይ ጥቃት እንዳይደርስባቸው የመጠበቅ ግዴታ ወይም ተግባር አለባቸው፡፡ የሕዝብን ሰላም እና ደኅንነት የመጠበቅ የሕግ ግዴታ አለባቸው፡፡ የየክልሉ መንግሥትታትም ይሄንን ሁኔታ የመከታተልና የመቆጣጠር ኃላፊነት አለባቸው፡፡

ይህ ኃላፊነታቸው የሚመነጨው ደግሞ ከሕገ መንግሥቱ ነው፡፡ እነዚህ ተቋማት የተጣለባቸውን ግዴታ ባለመወጣታቸው ምክንያት ዜጎች በገፍ እየተፈናቀሉ ነው፡፡ በመፈናቀላቸው ምክንያት በአካልና በንብረት ላይ ጉዳት ደርሷል፡፡ እንዲህ ዓይነት ጉዳት ሲደርስ ተጎጅዎቹ እነዚህ ተቋም ላይ ክስ ከማቅረብ የሚከለክላቸው ሕግ የለም፡፡

የሕዝብን ደህንነት የመጠበቅ ወይም የማስጠበቅ ግዴታውን ባለመወጣቱ ሕግ ስለጣሰ (ሕጋዊ ግዴታውን ስላልተወጣ) በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል እንደተፈጸመው የክልሉ ፖሊስም ይሁን ሚሊሻዎች በሕግ የተጣለባቸውን ኃላፊነት ካለመወጣትም አልፈው የሌሎች ብሔር ተወላጆች ላይ ጉዳት ሲያደረሱ ዞሮ ዞሮ ሕግ ስለተጣሰ በፍትሐ ብሔር ሕጉ አንቀጽ 2035 መሠረት አላፊ መሆንን ያስከትላል፡፡ በመሆኑም፣ ይህንን ያለከበረው የክልሉ ፖለስ ኮሚሽን ወይም አስተዳደር እና ፀጥታ ቢሮ በቀጥታ አላፊነት ይኖርበታል ማለት ይቻላል፡፡

በመንግሥት መሥሪያ ቤት ሆነ ባለሥልጣኑ አንድን አድራት በሥልጣን አላግባብ በመጠቀሙ ሌላ ሰው ላይ ጉዳት ካደረሰም አላፊነቱ ያደረሰው ሰው ራሱ ስለሆነ ጉዳቱን ማስተካከል ወይንም ካሳ መክፈል አለበት፡፡ በሥልጣን ያለአግባብ ባይገለገልበትም እንኳን ሕጉ ከሚያዘው ውጭ ከተፈጸመ እንዲሁ ተጠያቂነቱ የመንግሥት አይሆንም፡፡

ነገሩን በምሳሌ ለማስረገጥ፣ ፖሊስ በሕግ የተቀመጠውን አሠራር በመተላለፍ የእጅ እልፊትና ድብደባ አድርሶ ከሆነም ተጠያቂነቱ የፖሊሱ ነው፡፡ መንግሥትም እንዲህ ዓይነቱን የተጠያቂነት አሠራር የማመቻቸት ግዴታ አለበት፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ጉዳት ያደረሱ ፖሊሶችም ይሁኑ ሚሊሻዎች በግላቸው ከሆነ ተጠያቂነቱ በግል ብቻ ይሆናል፡፡

ዓለም አቀፉ የሲቪል እና የፖሊቲካ መብቶች ስምምነት ላይ እንደተገለጸው እና ኢትጵያም እንዳጸደቀችው ሰብኣዊ መብት ጥሰት በሚኖርበት ጊዜ የማስተካከል ግዴታን አለባት፡፡ለደረሰውም ጉዳት ካሳ መክፈልም ቢሆን ተጨማሪ ግዴታ ነው፡፡ ስለሆነም፣ አላግባብ ለታሰሩ ሰዎቸ፣ የመዘዋወር ነጻነታቸው ከሕግ ውጭ ለተገታባቸው ካሳ የመከፈል መብታቸው የተጠበቀ ነው፡፡ ከላይ የተጠቀሰው የሰብኣዊ መብት ሰነድ መብትንም በግልጽ ያስቀምጣል፡፡

ሌላውው የአላፊነት መነሻው ደግሞ ድርጊቱን ለፈጸመው ሰው፤ ሌላ ሰው አላፊነትን የሚወሰድበት ሁኔታ እንደሆነ ከላይ ገልጸናል፡፡ አካለ መጠን ላልደረሰው ልጅ ድርጊት ሞግዚቱ፣ ለሠራተኛው ደግሞ አሠሪው አላፊነት የሚወስዱበት አካሔድ ማለት ነው፡፡ የድርጊቱ ፈጻሚ 18 ዓመት ያልሞላው ወይንም ደግሞ ሥራውን በቀናነት ደፋ ቀና እያለ የሚሠራ አንድ ለፍቶ አዳሪ የሠራው ሥራ አማካይነት ሌላ ሰው ላይ ጉዳት ካስከተለ አላፊነቱ የልጁ ወይንም የሠራተኛው ሳይሆን የሞግዚቱ ወይንም የአሠሪው ነው፡፡ አሠሪ በሚባልበት ጊዜ የግል ድርጅት፣ መንግሥታዊ የሆነ ወይንም ያልሆነ ሊሆን ይችላል፡፡

አንድ የመንግሥት ሹመኛ ወይንም ሠራተኛ የሥራው አካል ባልሆነ፣ ወይንም የሥራውም አካል ቢሆን እንኳን ከቅን ልቦና ውጭ ያደረገው ከሆነ፣ ወይንም ሥልጣኑን በኣግባቡ ባለመጠቀሙ የመጣ አላፊነት ካለሆነ በስተቀር መንግሥት ኣላፊ እንደሆነ በፍትሐ ብሔር ሕጉ ላይ ተደንግጓል፡፡ በመሆኑም የግል ጥፋት የግል አላፊነትን ያስከትላል እንጂ የመንግሥት አይሆንም፡፡

ይሁን እንጂ ከቅን ልቦና ውጪ ስለመሆኑ ማስረጃ እስካልቀረበ ድረስ የሕጉ ግምት የተሠራው በቀና ልቦና እንደሆነ ነው፡፡ እንዲህ ከሆነ ደግሞ መንግሥትም ስለጉዳቱ ያልፍበታል፡፡ መንግሥት ማለት የፌደራል፣ የክልል እንዲሁም ከዚያ በተቻ ያሉ መዋቅሮች እና መሥሪያ ቤቶችምን ይጨምራል፡፡

ጉዳት አድራሹ ድርጊቱን ለመፈጸሙ ምክንያት የሆነው የበላይ ትእዛዝ ቢሆንም ከመጠየቅ አያድነውም፡፡ አላፊነት ላይኖርበት የሚችለው ፈጻሚው ወታደር ወይንም ተመሳሳይ ሙያ ያለው ሆነ ከአለቃው ጋር ስለጉዳዩ ለመወያየት የማይችልበት ሁኔታ ውስጥ ሲሆን ብቻ ነው፡፡ በዚህን ጊዜ የበላዩ ኣላፊ ይሆናል ማለት ነው፡፡

በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል የተፈጸመውን በገፍ የማፈናቀል ድርጊት በተመለከተ ፖሊሶችንና ሚሊሻዎችን ለተፈናቃዮች ከለላ እንዳይሰጡ ቢታዘዙ እንኳን ከተጠያቂነት ነጻ የሚያደርግ አይሆንም፡፡ ምክንያቱም፣ድርጊቱ በራሱ ወንጀል እንደሆነ መረዳት ስለሚቻል እና ትእዛዝ በሚሰጥበት ጊዜ ከአለቃ ጋር ውይይትን የሚከለክል ሁኔታ ነበር ማለት የሚቻል ባለመሆኑ ነው፡፡

ከላይ ከቀረቡት ማብራሪያዎች በመነሳት ዜጎችን በማፈናቀሉ ረገድ ተሳታፊ የነበሩ የመንግሥት ሠራተኞች (ፖሊስም ይሁን ሌላ) ተሳታፊ ከነበሩ፤ተሳታፊ ባይሆኑም የመፈናቀል ድርጊቱን የመከላከል ተግባር እያለባቸው ኃላፊነታቸው ካልተወጡ መፈናቀሉ ጋር ተያይዞ ለሚመጣው የፍትሐ ብሔር ጉዳት ዞሮ ዞሮ የክልሉ መንግሥት ካሳ የመክፈል ግዴታ ይኖርበታል ማለት ይቻላል፡፡ እዚህ ላይ የክልሉ መንግሥትን የማያስጠይቀው ወይም ከኃላፊነት ነጻ የሚያደርገው፤ ዜጎች ከመኖሪያ ቦታቸው ባይፈናቀሉ የሚደርስባቸው ጉዳት እንዳልነበር እና ጥበቃ እንዳደረገ ማስረዳት ሲችል ነው፡፡

በፍትሐ ብሔር ሕጉ አንቀጽ 2136 መሠረት ግን ምንም እንኳን የመጨረሻ አላፊ የሚሆነው ሠራተኛው ቢሆንም መንግሥትን ከተጠያቂነት አያድነውም፡፡ በአንድነት እና በነጣላ ሊያስጠይቅ ይችላል፡፡ ኋላ ላይ ግን በመዳረግ (መልሶ ሠራተኛውን የመጠየቅ) ክስ የማቅረብ መብት እንደተጠበቀ ሆኖ፡፡ ጉዳቱን ያደረሰው የመንግሥት ሠራተኛ ለይቶ ማመልከት ካልተቻለም ግን ፍርድ ቤቶች እንዳለ ስብስቡ ላይ ሊወስኑ እንደሚችሉ ተቀምጧል፡፡

በመሆኑም፣ በርካታ ሆነው በአንድነት ባሉበት ሁኔታ ማን የተባለ ፖሊስ ወይንም ወታደር ወይንም የጸጥታ ሠራተኛ ጉዳት እንዳደረሰ አለመታወቁ ጉዳት የደረሰበትን ሰው ካሳ ከማግኘት ኣያግደውም፡፡ መሥሪያ ቤቱን ወይንም ስብስቡንም ከኣላፊነት ነጻ አያደርገውም፡፡

ከላይ በተገለጹት አከኋኖች ጉዳት የደረሰበት ሰው ካሳ የማግኘት መብት አለው፡፡ ጉዳቱ የደረሰበት ሰው በከፊል የራሱ ጥፋት ቢኖርበትም እንኳን እንዲሁ በከፊል ካሳ ሊያገኝ ይችላል እንጂ ሙሉ በሙሉ አይነፈግም፡፡ ሰብኣዊ መብቶችን እና ሕገ መንግሥታዊ መብቶች በሚጣሱበት ጊዜ ስለሚሆነው ዘርዘር አድርገን እንመልከተው፡፡

የአገራት ተሞክሮ፤
ጠቅለል ባለ መንገድ በሕገ መንግሥት ወይንም ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ሰነዶች ላይ የተቀመጡ መብቶች በመጣሱበት ምክንያት ጉዳት ሲደርስ ካሳ የሚከፈልበትን አኳኋን በተመለከተ አንዳንድ አገራት የተለየ አካሄድን ተከትለዋል፡፡ ከላይ በተገለጹት የመንግሥት ድርጊቶች አማካይነት ለተፈጸሙ ተግባራት መንግሥትን ወይንም ሠራተኞቹን አላፊ እንዳይሆኑ መከታ የሚሆናቸው ሕግ እስካሁን አልወጣም፡፡ ወደፊት በሌላ አገላለጽ ዜጎችም በመፈናቀላቸው ምክንያት ለሚደርስባቸው ጉዳት ካሳ የመጠየቅ መብት አላቸው ማለት ነው፡፡

ሕገ መንግሥታዊ ወይንም ሰብኣዊ መብቶች ሲጣሱ መፍትሔ ሊሆን የሚችል በሌላ ዝርዝር ሕግ የተብራራ ነገር ካለ የኣለፊነቱን ሁኔታ የሚወሰነው በዚህ ሕግ ይሆናል፡፡ ሌላ ሕግ ከሌለ ግን፣ ራሱን ሕገ መንግሥቱን መሠረት አድርጎ ካሳ መጠየቅ በበርካታ አገራት ከተዘወተረ ቀይቷል፡፡

አሜሪካ እና ካናዳ ፍርድ ቤቶቻቸው በሰጡት ትርጉም መነሻነት ሕገ መንግሥታዊ መብት በመጣሱ ለደረሰ ጉዳት ካሳ ይጠየቃል፡፡ በእርግጥ ካናዳ የሰብኣዊ መብት ኮድ የብቻው ለይታ በማውጣት እና የተለየ የሰብአዊ መብት ፍርድ ቤት በማቋቋሟ እንዲሁም የጣሰው በገንዝብ ካሳ የመክፈል አሠራር መዘርጋቷን ልብ ይሏል፡፡

አንዳንድ አገራት (ለምሳሌ ጀርመን፣ፖርቹጋል፣ ስሎቬኒያ፣ፖላንድ) የሰብኣዊ ወይንም ሕገ መንግሥታዊ መብቶች በመጣሳቸው ምክንያት ዜጎች ላይ ጉዳት ከደረሰ ለጉዳቱ የመካስ መብትን ሕገ መንግሥታዊ መብት አድርገውታል፡፡ በተለይ ሰብኣዊ መብት በብዛት የሚጥሰው መንግሥት በመሆኑ በመፍትሔነት በግልጽ አስቀምጠዋል፡፡

ኢስቶኒያ ለደረሰው ጉዳት የገንዘብ ካሳ ሊከፈልባቸው የሚችሉትን በሙሉ እና በገንዘብ ከማይተመኑት ደግሞ የተወሰኑትን ቀጥታ ፍርድ ቤት ማቅረብ እንደሚቻል ሕገ መንግሥቷ ይገልጻል፡፡ ብራዚል ደግሞ የማይጣሱ እና የማይገሰሱ የሰብኣዊ መብቶችን መንግሥት ከጣሰ ጉዳት የደረሰበት ሰው ካሳ የማግኘት መብት እንዳለው ሕገ መንግሥታዊ አድርገውታል፡፡

ቁምነገሩ፣ የሰብኣዊ መብቶቹ ዓይነት በራሳቸው ለካሳ አከፋፈልና ግምት የሚመቹ እና ቀላል የሆኑ እንዳሉት ሁሉ አስቸጋሪ እና ውስብስብም መኖራቸው ነው፡፡ የሲቪል እና የፖለቲካ መብቶችን ከማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና የባህል መብቶች አንጻር የመብቶቹን ጥሰት በገንዘብ በመተመን መካስ ይቻላል፡፡ አቅም እንደፈቀደ እና እያደር እውን የሚሆኑ መብቶችን ግን በአንዴ መካስ አይቻልም፡፡

ይሁን እንጂ፣ ለዘመናት በአንድ ቡድን ላይ የተፈጸመን ኢፍትሐዊ ተግባር በገንዘብ መካስ የተለመደ ነው፡፡ ገንዘቡ ለቡድኑ አባላት ለእያንዳንዳቸው ወይንም በጥቅሉ ለቡድኑ ሊሠጥ ይችላል፡፡በተለይ በመገለላቸው ምክንያት በብዙ መልኩ ከሌሎች ወደ ኋላ የቀሩ፣ እንዲሁም ሃብታቸውን የተበዘበዙ ነባር ሕዝቦችን ይመለከታል፡፡

አገራት ስለ ሰብኣዊ መብቶች የካሳ ሁኔታ በሕገ መንግሥታቸው ባያስቀምጡም እንኳን ጉዳዩ የሕግ የበላይነት ጋር አብሮ ተሰናስሎ የሚኖር ስለሆነ፤ የጣሰውን ከኃላፊነት ነጻ በማድረግ የሕግ የበላይነት ማስከበር ስለማይኖር፣ የሰብኣዊነት ክብር እና እኩልነት የሚመለከት በመሆኑ የካሳ ጉዳይ መለመድ ያለበት ነው፡፡

የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥትም ይሁን የክልሎቹ አንቀጽ 13 ላይ እንደገለጹት ሕግ አውጭው፣ አስፈጻሚው እንዲሁም ተርጓሚው የሰብኣዊ መብቶችን ከመጣስ በመቆጠብ ማክበር እንዳለባቸው ተቀምጧል፡፡ እነዚህ ተቋማት በሕግ ከተባለው በተቃራኒው በመጓዝ ሰብኣዊ መብቶችን ካላከበሩ፣ ብሎም ባለማክበራቸው የማይጠየቁ እና ላደረሱትም ጉዳት ኣላፊነት ከሌለባቸው በሕገ መንግሥቱ ላይ የተቀመጡት መብቶች በአንድ ሌላ ተራ መጽሐፍ ላይ ከተዘረዘሩ መብቶች ልዩነት አይኖራቸውም፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣እነዚህን መብቶች ለማስከበር ፍርድ ቤት አቤቱታ ለማቅረብ የሚመቸው በቡድን ቢሆን የፍትሐ ብሔር ሥነ ሥርዓት ሕጉ አንቀጽ 38 ላይ በቡድን ክስ ለመመሥር የተቀመጡት ቅድመ ሁኔታዎችን ማሟላት አስቸጋሪ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ለሕዝብ ጥቅም ሲባል እንደሚቀርቡ ክሶች (public interest litigation) ሌላ ማንኛውም ያገባኛል የሚል ሰው፣የሕግ ባለሙያ ወይንም ድርጅት ክሱን እንዳያስቀጥል የሚፈቅድ የሥነ ሥርዓት ሕግ የለም፡፡ ስለሆነም፣አሁን ባለው የሕግ ማዕቀፍ በተናጠል ብቻ ነው አቤቱታ ለማቅረብ የሚቻለው፡፡

ማጠቃለያ

ከላይ በአጭሩ ለመቃኘት የተሞከረው ዜጎች የሰብኣዊ ወይንም ሌሎች መብቶቻቸውን መንግሥት በተቋማቱ ወይንም በሠራተኞቹ አማካይነት በሚጥስበት ጊዜ ሊኖር የሚችለውን የፍትሐ ብሔር መፍትሔ ነው፡፡ ይኽንን አሠራር መከተል ሕግን ማክበር ነው እንጂ ብዙም ፖሊሲ እና ሌላ ነገር አያስፈልገውም፡፡

ሕግን ማክበር በራሱ ያለው ፋይዳ ከፍ ያለ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ መልካም አስተዳደርን ለማስፈን፣የዜጎችን መብት ለማስጠበቅ፣ ጉዳት አድራሽዎችን ለመቅጣት ወይንም ላለማበረታታት እንዲሁም ዜጎች በሕግ ላይ የሚኖራቸውን አመኔታን ለመጨመር ይረዳል፡፡

በነጻነት መንቀሳቀስ ከሰው ልጅ የልዕልና ጉዞ ጋር በጣም የተያያዘ ነው፡፡ ሰብኣዊ ልማት ይኖር ዘንድ ለመንቀሳቀስ ነጻነት ጥበቃ ማድግ ያስፈልጋል፡፡ ይህ ነጻነት የመኖሪያ ቦታን ከመምረጥ ጋር የተቆራኘ ነው፡፡ ለኑሮ የሚያስፈልጉ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች በመምረጥ መሥራትንም ይይዛል፡፡ እነዚህን መብቶች የማክበር እና የማስከበር ግዴታዎች ደግሞ መንግሥት ላይ ይወድቃል፡፡ ግዴታዉን የሚጥለው ደግሞ የፌደራሉ እና የክልሎቹ ሕግጋተ መንግሥታት እንዲሁም ኢትዮጵያ ተቀብላ ያጸደቀቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች ናቸው፡፡

ለአተገባበር እንዲያመች እና ሥራ ላይ በአግባቡ ለመፈጸም ይመች ዘንድ እነዚህ ሕጎች በተራቸው የወንጀልና የፍትሐ ብሔር መፍትሔዎችን ይዘው መጥተዋል፡፡ ሕጎቹን ተግባራዊ በማድረግ ከየክልሉ በየጊዜው ማፈናቀልን ለማስቆም ጥረጥ ማድረግ መንግሥታዊ ግዴታ ነው፡፡ ሥልጣናቸውን መከታ በማድረግ በማፈናቀል ድርጊት ውስጥ የሚሳተፉትንም ተጠያቂ ማድረግ በሕግ መሠረት አገርን ከሚመራ መንግሥት የሚጠበቅ ነው፡፡

ከሕገ መንግሥቱ ጀምሮ ባሉ ሕግጋት ውስጥ ዕውቅናም ጥበቃም የተሰጣቸውን ሰብኣዊ መብቶች በሚጣሱበት ጊዜ ተጎጂዎች እንደ ሕጉ ካሳ እና ተያያዥ ክፍያዎችን ማግኘት ካልቻሉ በሕጉም በሥርዓቱም በተቋማቱም ላይ የሚኖራቸው እምነት ከዜሮ በታች መውረዱ አይቀርም፡፡

Filed in: Amharic