>
5:14 pm - Wednesday April 20, 4766

ዋርካው አቅም ሲያጣ!! (ዘውድአለም ታደሰ)

ስማኝማ ዘመዴ … በነዚህ 26 አመታት ውስጥ ከኦሆዴድ ሊቀመንበርነት እስከ ሐገሪቱ ፕሬዘዳንትነት የደረሰ ሰው፥ በከፍተኛ የስልጣን ዙፋኖች ላይ የተቀመጠ ሰው፥ በሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር ሳይቀር ከፍተኛ ከበሬታ የነበረው ሰው። በትምህርቱ በከፍተኛ ውጤት ዶክትሬት ድግሪውን የያዘ ሰው። ላመነበት እውነት ስልጣንን አሽቀንጥሮ ጥሎ ፣ የቤተመንግስትን ምቾት ረግጦ ፣ ለሚሊየኖች የሚያጓጓውን ታላቅ ስልጣን ወርውሮ ፣ እንደጲላጦስ እጁን ከደም አንፅቶ፣ ወደህዝቡ ተቀላቅሎ እንደተራ ዜጋ ሲኖር አይተህ ታውቃለህ? ታውቃለህ ወይ?

እንግዲያውስ ልንገርህ ይሄ የዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ ታሪክ ነው!!!

አንድ ግዜ ለፓርላማ የሚወዳደሩበትን የተቃዋሚ ፓርቲ ታፔላ በእግራቸው እየዞሩ በየታክሲው ላይ ሲለጥፉ የሚያሳይ ፎቶ በፌስቡክ አይቼ ደነገጥኩ!!
ከዚያ በኋላ በሳቸው ዙሪያ አንዳንድ ነገሮችን ሳጣራ ከፍተኛ ድንጋጤ ወደቀብኝ። አንድ ለሳቸው ቅርበት የነበራት ጓደኛዬ ዶክተሩ ከመንግስት የሚያገኙት ምንም አይነት ድጋፍ እንደሌለ፣ ሊቀመንበር ሆነው መርተውት የነበረው ድርጅታቸው ኦህዴድ ሳይቀር እንደረሳቸው፣ በህመም እንደሚሰቃዩና መድሃኒት መግዣንኳ እንደሚቸግራቸው ብቻ ልብ የሚያደማ ነገር ነገረችኝ።

ብዙ ግዜ መፃፍ ፈልጌ ነበር። ግን ምን ብዬ ይሄን ለመስማት እንኳ የሚዘገንን ሃዘን እንደምፅፍ ግራ ገባኝ። የሳቸውንም ፈቃድ ሳላገኝ የግል ነገራቸውን መፃፉም ከበደኝ። ዛሬ ግን Nahusenay Belay  ስለሳቸው ሲፅፍ የሆነ ነገር ማለት እንዳለብኝ ወሰንኩ።

አምና ነው፤ የቐድሞ የሀገራችን ፕሬዚዳንት የነበሩት ክቡር ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ ለማስተምረው አንድ ኮርስ ስለ ኢትዮጵያ ህገመንግስት አወጣጥ የነበረዉን ሂደት ለተማሪዎቼ በተጋባዥነት ሌክቸር እንዲያደርጉልኝ ስጠይቃቸው “ምንም ችግር የለም፣ ሰዎቹ ግን እንዳይተናኮሉህ” አሉኝ። ችግር የለም ሃላፊነቱ ራሴ እወስዳለሁ ብየ ቀጠሮ ይዘን ተለያየን።

በተነጋገርነው ቀንም ወደ መኖርያ ሰፈራቸው ሄጄ በኮንትራት ታክሲ አብረን መጣን፣ የሚገርም ትምህርት አስተማሩን፣ እኔም ተማሪዎቼም በጣም አመሰገንናቸው። ከባለቤቱ እንደመስማት የሚያስተምር እና የሚያረካ ዘይቤ የለም። ዘንድሮም ይህ አካሄድ ሰፋ አድርጌ እቀጥልበታሉ።

ዶክተር ነጋሶ የእግር መኪና እንኳን የላቸዉም፣ ጥበቃና ሰራተኛም ተነፍገዋል፣አስቤዛም በሚስታቸው በኩል ነው። እሳቸዉን በኮንትራት ታክሲ ሳሳፍር ዉስጤ ተረብሾ ነበር። ደግሞ ልባቸው ያማቸዋል። ብቻ ሁሉም ነገር ያሳዝናል፣ ይህን ያክል ለምን ተጨከነባቸው።

ኢትዮጵያን የምታክል ሀገር በከፍተኛ ሃላፊነት ያገለገሉት ዶክተር ነጋሶ የሚገባቸው ክብር እና የኑሮ ደረጃ ተነፍገው በሚስታቸው ቸርነት እየኖሩ እንደሆኑ ሲያወጉኝ በጣም አዘንኩኝ። 

ገጣሚ በረከት በላይነህ ሁሌ በፅሁፎቼ የምጠቅሳት ጥልቅ ሃሳብ የያዘች የግጥም ስራ አለችው። ቆንጥሬ ላካፍላችሁ

ሰጪ ካለቀሰ ተበዳሪ ስቆ
ጌታ ከለመነ አማኙ ‘ግር ወድቆ
ልዑል ከዘመረ ንጉሱ ተዋርዶ
ገፁ ተመሳቅሎ ሽፋኑ ካማረ
ወለሉ ተንቆ ምንጣፍ ከከበረ
ባ’ገርኛ ስሌት ማነው ያልከሰረ?
.
እላለው……..እላለው
.
ከየጎዳናው ገፅ ጥያቄ አነሳለው
ጥያቄ እጥላለው
እርጅና ለማምሻው ጎዳናን ካመነ
አያት ከልጅ ልጁ ሳንቲም ከለመነ
ባገርኛ ስሌት ማነው ያልመከነ?
.
በ’ግዚኦታ ዘመን በምዕላ ዘመን
እመንገድ ዳር ወድቆ ትራፊ መለመን
በጥሞና ዘመን የሚያስቡት ማጣት
በማውረሻ እድሜ የሚሰጡት ማጣት
በማልበሻ ዘመን በ’ርዛት መቀጣት
በለጋሽነት ወቅት በማጉረሻ ዘመን
በጥማት መገረፍ በርሀብ መመንመን
ከሆነ እጣችን
ይጠየቅ ትርጉሙ የልጅነታችን
ይፈተሽ መንገዱ የልጅ ልጆቻችን!

ግድ የለም እንመን……..እንመን

የስኬት ክብደቱ
የምቾት አይነቱ
የነገ ውበቱ ባሻው ቋት ቢለካ
በምንም ቢሰፈር ባሻው ቃል ቢነገር
ጀግና ልጅ አትወልድም
አያቶቿን ገድላ የምትሸልል ሀገር!
.
ከፎቆቹ ጥላ….
ከያስፓልቱ ገላ ሲታተም ድምቀቴ
በመስታወት አጀብ ሲጠገን ጉልበቴ
ይኸው አነበብኩት
አያቶቼ ፊት ላይ ተፅፏል ሽንፈቴ
በመኪና ብዛት
በመስታወት አይነት ሲለካ ፍጥነቴ
በግንብ አጥር መአት
በፎቆች ጋጋታ ሲሰላ ስኬቴ
ይኸው ይታየኛል
አያቴ ገፅ ላይ ተስሏል ውድቀቴ!!

ወዳጄ ….. ምን ልፃፍልህ? ምን ልበልህ? በምን ቃል ልግለፅልህ? እኚህ ምሁር፣ እኚህ ያገር ክብር፣ እኚህ ታላቅ ሰው፣ እኚህ የእውነት ባርያ ፣ እኚህ የኢትዮጵያ ልጅ፣ እኚህ ታሪክ የማይረሳቸው የሃቅ አርበኛ፣ እኚህ ኩሩ ሰው፣ ዛሬ ላመኑበት ነገር መስዋእት እየከፈሉ ነው። የሚኖሩት እንኳ በጀርመናዊቷ ባለቤታቸው ድጋፍ ነው። ይታመማሉ። መድሃኒቱን የምትገዛላቸውም ባለቤታቸው ነች። ቤት የላቸውም። ስራ መስራት አይችሉም። ነገር ግን ዛሬም ከነእውነታቸው መሞት መርጠዋል። ለልመና ረግጠውት ወደሄዱት ህይወት አልተመለሱም።

ፕሬዘዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ ጡረታ ሲወጡ ከጥቅማጥቅማቸው ውጭ በወር 450 ሺ ብር የሚከፈልበት ቪላ ነው የተቸራቸው። እኚህን ሰው ግን ካለቻቸው ትንሽ ቤት እንኳ እንዲፈናቀሉ ነው ከላይ ትዛዝ የወረደው። እሳቸው በግዜው እንዲህ ብለው ነበር .. «መንግስት ቤቴን የሚወስድብኝ ከሆነ፣ ባለቤቴን ውጪ ልኬ እኔ ድንኳን ወጥሬ ጎዳናው ላይ አድራለሁ እንጂ የትም አልሄድም»

በቃ ሰውዬው እንዲህ ናቸው። ላመኑበት ነገር እስከመጨረሻ ህቅታቸው ነው ሚታገሉት። አሁን እንኳ ፓርቲያቸው ኦህዴድ ሳይቀር በጣላቸው፣ መንግስት በተበቀላቸው ፣ የኢትዮጵያ ህዝብም አይቶ እንዳላየ ባለፋቸው በዚች ሰአት እንኳ ከህመማቸው ጋር እየታገሉ፣ የህይወትን መራራ ቀንበር ተሸክመው ፈገግ ይላሉ … ፈገግ!! ፅኑው የሐገር ዋርካ ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ!

(እኚህን ታላቅ ሰው መርዳት የሚፈልግ ካለ አብሬህ ነኝ ይበለኝ!)

ኢትዮጵያን እግዚአብሔር ይቅር ይበላት!

Filed in: Amharic