>
5:13 pm - Friday April 19, 9072

"የተቃዋሚው መሪ ኢትዮጵያ ቢሆን ምን ይደረጉ ነበር? (ቅዱስ መላኩ)

በእንዲህ ያለ ወቅትስ የት ይገኙ ነበር?” 

ኬንያዊያን ዛሬ የነጻነት ቀናቸውን እያከበሩ ነው። ስራ የለም፤ብሄራዊ በዓል ነው። የሃገሪቱ መዲና ታላላቅ ጎዳናዎችም ጭር ብለዋል። ከነዚህ ዋና ዋና ጎዳናዎች መሃል በማዕከላዊ ናይሮቢ የሚገኘውና ከሌሎቹ የተሻለ የንግድ እንቅስቃሴ የሚበዛበት ወደ ጆሞ ኬንያታ አውሮፕላን ማረፊያ የሚወስደውን እና የሞምባሳን ዋና ጎዳና የሚያገናኘው ትልቁ የንጉስ ኃይለሥላሴ ጎዳናም ያለወትሮው ጭር ብሏል። በኬንያ ከ5 ቀናት በኋላ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ የሚደረግ ሲሆን ዋናው የተቃዋሚ መሪ ራይላ ኦዲንጋ ምርጫውን አልወዳደርም ማለታቸውን ተከትሎ የሃገሪቱ ምርጫ ቦርድ ሰብሳሲ አገር ጥለው ወደ አሜሪካ መኮብለላቸው ቀጣዮቹ ቀናቶች ለኬንያ በጎ ዜና ይዘው እንደማይመጡ በእግጠኛነት መናገር ይቻላል። የኬንያ ፖሊስ ሰሞኑን ተቃዋሚዎች ላይ ጥቃት በመሰንዘሩ እና ገዳይ ጥይት በቀጥታ ሰልፈኞች ላይ ከተኮሰ በኋላ ኬንያዊያን በየቀኑ አደባባይ በመውጣት መንግስት እየተቃወሙ ነው። ትናንትና ፖሊስ በኬንያዊያን ሰላማዊ የተቃውሞ እንቅስቃሴ እና ሰልፍ ጣልቃ መግባቱን የሚያወግዝ ሰልፍ በማዕከላዊ ናይሮቢ ተደርጓል። በሃገሪቱ በሚገኙ በርካታ የቴሌቪዥን ማሰራጫዎች እየቀረቡ ሰልፈኞቹ ፖሊስ እና ወታደሮች በሃገራቸው ዕጣ ፈንታ ላይ ከሕዝቡ ጎን መቆም እንዳለባቸው ሲያሳስቡ ውለዋል። የኬንያ ወታደሮች ከሰልፉ ፊት ለፊት ጠመንጃ ይዘው ቆመው ይታያሉ። ኬንያዊያን ለወታደሮች መልክት ሲያስተላልፉም ወታደሮቹ በአካል እዚያው ቆመው እየተመለከቱ እና እየሰሙ ነበር። አንድም ወታደር ካሜራ የያዘ ሰው እና ሕዝቡን እየዞሩ ቃለ መጠይቅ የሚያደርጉ ጋዜጠኞች ላይ ጥቃት ሲሰነዝሩ አለማየቴ አስቀንቶኛል።በአንጻሩም የፖሊስ እና የወታደሩን የተገራ ስልጡን ባህሪ አይቻለሁ። በኬንያ ከ40 በላይ ጎሳ የሚኖር ሲሆን በሰልፉ ላይ የተሳተፉት ሰዎች አደባባይ የወጡት የትኛውንም ጎሳ ወክለው ሳይሆን “የፈጣሪ ምድር” ለሚሏት ሃገራቸው ኬንያ የወደፊት መልካም ዕጣ ፈንታ ላይ መወሰን የሚያስችል የምርጫ መዋቅር እንዲኖር ለመጠየቅ እና ፖሊስ እና ወታደሩም በሕዝብና በመንግስት መሃል በሚኖር ግንኙነት ውስጥ ሕገመንግስቱን ብቻ በተከተለ መልኩ ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ ለመጠየቅ ነው።

ዛሬ የሃገሪቱ ፕሬዝዳንት ከመዲናዋ ናይሮቢ 354ኪሜ በምትርቀው የኪሱሙ ከተማ በሚያደርጉት ሕዝባዊ ንግግር በትይዩ ራሳቸውን ከምርጫ ያገለሉት ራይላ ኦዲንጋም “እኔም በኪሱሙ ደጋፊዎችን እሰበስባለሁ” ማለታቸው ብቻ ሳይሆን ሕዝቡን ሰብስበው ምን ሊሉ እንደሚችሉ በጉጉት እና በፍርሃት እየተጠበቀ ነው። የሆኖ ሆኖ ግን እኔን ይህኛውም ጉዳይ ቢሆን አስቀንቶኛል። ኢትዮጵያ ቢሆን “የተቃዋሚው መሪ ምን ይደረጉ ነበር?በእንዲህ ያለ ወቅት የትስ ይገኙ ነበር?” የሚለውን ሳስበው•••ኬንያ ብዙ ነገሯ ያስቀናል። በቴሌኮም ጉዳይ ደግሞ ለደምበኞቼ ከምስራቅ አፍሪካ ሁሉ ዝቅተኛ ክፍያ አስከፍላለሁ የሚለውን የኢትዮጵያ ቴሌኮም ከኬንያ የቴሌኮም ካምፓኒዎች ጋር በተግባር በደቂቃ ምን ያህል እንደሚያስከፍል እያነጻጸርኩ ለመዳሰስ እሞክራለሁ። ከዚያ ጠቅላይ ሚንስትሩ “ቴሌ ማለት የምትታለብ ላም ማለት ነው።” ካሉት አባባላቸው በስተጀርባ የሚታለቡት ላሞች እንደማን እንደሆኑ በየራሳችን በቂ መልስ እናገኝበታለን።መልካም የነጻነት ቀን•••እንዲመጣልን እመኛለሁ።

Filed in: Amharic