>

ሲያልቅ አያምር፤ “የሥርዓቱን አሟሟት ያሳምርልን!” (ያሬድ ኃይለማርያም)

የዛሬ ሦስት አመት ታህሳስ 10 ቀን 2007 ዓ›ም “ግፍና አፈና ዐመጽን ይወልዳሉ፤ የዐመጸኛ አፍ ጥልቅ ጉድጓድ ነው (መ.ምሳሌ ም.22፣ ቁ.14)”  በሚል አርዕስት ለንባብ ባበቃሁትና በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ በገመገምኩበት ጽሁፍ ይህን ከትቤ ነበር፤ “አንድሕዝብ በላዩ ላይ ገዢዎች እየተፈራረቁበት ረዘም ላለ ጊዜ በአገዛዝሥርዓት ሥር ስር ሊቆይ ይችል:: ይሁንና እድሜ ልክ የገዛ አፋኛሥርዓት ግን የለም:: ሥርዓቱም እንደ ድርጅት፣ ሹማምንቱ እንደሰው የጉብዝና እድሜያቸው የተወሰነ ነው:የአፈናን ስልትበመለዋወጥና ሸምቀቆውን በማጥበቅም እድሜን ማራዘም የሚቻል ቢመስልም በተቃራኒዉ ውድቀትንም ያፋጥናል:: ግፉ እየበረታናየመብት ጥሰቱም መረን እየለቀቀ በሄደ ቁጥር የሕዝብ ትእግስት ይሟጠጣል:: ሕዝብ መቆጣት ከጀመረና ቁጣው ወደ አደባባይአመጽ በተቀየረ ጊዜ የግፍ አገዛ ወደ መቃብር፣ ግፈኞቹም ወደ ዘብጥያ እንደሚወርዱ እርቀን ሳንሄድ ባለፉት አምስትና አሥርትአመታት ውስጥ በአለም የታዩ ሕዝባዊ ነውጦችንና ያስከተሉትን መዘዝ ማጤን በቂ ነው::”  የዚህ ጽሁፍ አላማም የነበረው የኢትዮጵያ ሕዝብ ደግ ቀን ይመጣል እያለ አምቆ የያዘው ብሶትና ክፌት ሊፈነዳ ጥቂት ስለቀረው ሥርዓቱ በጊዜ እራሱን ያርቅ፤ ካልሆነ ግን የማይቀረው አመጽ ይነሳል። የሥርዓቱም ፍጻሜ እንዳያምር ይሆናል። የሚል ማሳሰቢያ ጭምር ነበር። አመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ነገሮች እያፈጠጡ መጡ። ይህን ጽሁፍ ምሉውን ለማንበብ ከዚህ ገጽ ሥር ያለውን ማስፈንጠሪያ ይጫኑ።[1]

ኢትዮጵያ ላለፉት ሁለት አመታት በማያባራ የሕዝብ ተቃውሞ ስትናጥ ቆይታለች። ከአንድ አመት በፊትም መጋቢት 14 ቀን 2016 ዓ.ም ግፍ በገፍ የሞላባት አገር በሚል በጻፍኩት አጭር ጽሑፍ ይህን ሃሳብ አቅርቤ ነበር፤ “ከአፋኝና ታፋኝ የፖለቲካ አዙሪትለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ልንላቀቅና ጭቆናን ታሪክ አድርገን ወደ ዲሞክራሲያዊ ጎዳና ልንሸጋገር የምንችለው ግፉአ ብቻሳይሆኑ ግፍ ፈጻሚዎቹም አብረው ነጻ ሲወጡ ብቻ ነው፡፡ ስለዚህም አገርን የማዳን ትግሉ አገዛዝ ሥርዓቱ የመጨቆኛ መሳሪያበመሆን እያገለገ ያሉ አጋር ድርጅቶችን እና ግለሰቦችን ከወያኔ ጉያ ማውጣትና የሕዝብ ወገንተኛ እንዲሆኑ ማድረግን ዋና ግቡማድረግ አለበት፡፡ ለዚህም በመሳሪያ አቅም፣ በፖለቲካ አደረጃጀት፣ በገንዘብም አቅም ይሁን ሰፊውን የአገሪቱን ክፍል በማስተዳደርዕረገድ የማይናቅ ድርሻ ያላቸውን ኦህዴድ፣ ብአዴን እና ሌሎች አጋር ድርጅቶችን የትግሉ አካል እንዲሆኑ ሁኔታዎችን ከወዲሁማመቻቸት ትግሉን ከማፋጠን ባለፈም ሊደርስ የሚችለውን የጥፋትና እልቂት ደጋም የመቀነስ ኃይል ይኖረዋል፡[2]

የአገዛዝ ሥርዓቱ በጠመንጃ ብቻ ሊቆጣጠረው ያልቻለውን የሕዝብ ቁጣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በመደንገግና የፈላጭ ቆራጭነት ስልጣን የተሰጠው ኮማንድ ፖስት በማዋቀር ቁጣውን ለማፈን ያደረገውም ጥረት ከሽፏል። ለዚህም ሰሞኑን በኦሮሚያ ክልል በተጠናከረ መልኩ የቀጠለው ሕዝባዊ ተቃውሞ ጥሩ ማሳያ ነው። ይህ የተቀጣጠለው ተቃውሞ እያደርም ሥርዓቱን ይቦረቡረው ጀምሯል። ትላንት ፊታቸውን ከልለው የተቃውሞ ምልክት በእጆቻቸው እያሳዩ ለሕዝባቸው ድጋፍ ይሰጡ የነበሩ የኦሮሚያ ክልል ፖሊሶች ዛሬ በይፋ ከሰልፈኛው ጋር ተቀላቅለው ድጋፋቸውን ሲሰጡ በግላጭ እያየን ነው። ከሥርዓቱ ምስረታ አንስተው በከፍተኛ አመራርነት ላይ ያገለገሉ ባለስልጣናትም፤ አባዱላ ገመዳ እና በረከት ስምዖንን ጨምሮ የጊዜውን መጨላለም አይተው ሳይዳፈን በፊት ገለል ማለታቸው ሌላው ሥርዓቱ ክፉኛ መታወኩን ማሳያ ምልክት ነው። ሌሎች በግልጽ ጎልተው የሚታዩ በርካታ ምልክቶችንም መጠቃቀስ ይቻላል።

በጡንቻ የተገኘ የፖለቲካ ሥልጣን ልክ እንደ ሰው እድሜ ነው። ልክ እንደ ሰው እጅግ አስጨናቂ በሆነና እንደምጥ ህመም መገለጫ በሌለው ስቃይ ይወለዳል። እንቦቃቅላ፣ ጨቅላ፣ ታዳጊ ልጅ፣ ወጣት፣ ጎልማሳ፣ ሽማግሌ እያለ እድሜ ከሰጠውም እስከ መጃጀት ደርሶ ወደ ማይቀረው ሞት ያቀናል። ልዩነቱ የሰው ልጅ ይህን የእድሜ እርከን ሙሉውን የሚዘልቀው ከ70 ዓመታት በላይ መኖር ሲችል ነው። ከዚያ በታች ሲሆን ሂደቱ እንደተቋረጠ ነው የሚቆጠረው። ከ60ዎቹ በታች ሲሆን ህልፈቱ የዛ ሰው ህይወት በጊዜ እንደተቀጨ ነው የሚቆጠረው። አንድ የአገዛዝ ሥርዓት በሥልጣን ስንት ዓመት ሲቆይ ነው ጎለመሰ፣ አረጀ ወይም ጃጀ የሚባለው?

ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በሰፈነባቸው አገሮች ያለውን አሰራር መነሻ ያደረግን እንደሆን በሥልጣን ላይ የሚቆየው ኃይል ህድሜው የሚወሰነው በሕግና በየወቅቱ በሚካሂዱ ምርጫዎች ላይ በሚገኝ የሕዝብ ድምጽ ነው። በእነዚህ አገሮች ሕግ አንድ ግለሰብ ወይም የፖለቲካ ፓርቲ ለምን ያህል ጊዜ በሥልጣን መቆየት እንደሚችል በግልጽ ስለሚደነገግ የሕዝብን ቅቡልነት ቢያገኝም እንኳን ሥልጣን ይዞ የሚቆይበት ጊዜ ከ8 እስክ 12 ዓመታት ባለው ጊዜ ውስጥ የተወሰነ ነው። የሕግ ልጓም ያልተበጀለት፣ ሕዝብም የስልጣን ባለቤት ባልሆነበት፣ የሥልጣን ምንጩም ሆነ ዋስትናው ጠመንጃ በሆነበት እንደ ኢትዮጵያ ባለ አገር የአገዛዝ ሥርዓቱ እድሜ የእንድ የሽማግሌን ሰው እድሜ ግማሽ ወይም እሩቡን ያህል ይዘልቃል። ለዚህም ያለፉትን ሦስት ሥርዓቶች፤ እንዲሁም በሌሎች የአፍሪካና በመካከለኛው ምስራቅ የሚገኙ የአረብ አገራት አንባገነኖችን የሥልጣን እድሜ ማሰብ በቂ ነው።

Filed in: Amharic