>

ህወሃት ቆሞ ቀር ድርጅት ነው! (ስዩም ተሾመ)

ቅድም… <<በመቐለ ከተማ ሲካሄድ የነበረው #የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ “ተጠናቀቀ ወይስ ተቋረጠ?”>> የሚል ጥያቄ በውስጤ ተጫረ፡፡ ከዛ <<“በመሰረታዊ #የሀገሪቱ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማሕበራዊ ጉዳዮች ላይ ይመክራል” የተባለለት ስብሰባ እንዲሁ በከንቱ አለፈ በቃ?>> ዜና ስጎረጉር #ፋናዬ “የህወሃት ማዕከላዊ ኮሚቴ ላለፉት ሰባት ቀናት ያካሄደውን ስብሰባ አጠናቀቀ” በሚል ያቀረበችውን ዘገባ አገኘሁ፡፡ የህወሃት ማዕከላዊ ኮሚቴ ካወጣው መግለጫ ውስጥ የሚከተለው ይገኝበታል፦
<<በኦሮሚያ እና የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ድንበር አዋሳኝ አካባቢዎች የተፈጠረውን #ግጭት [ህወሃት] ማዕከላዊ ኮሚቴው ችግሩን ከሌሎች እህት ድርጅቶች ጋር በመሆን፥ #በአብዮታዊ_ዴሞክራሲ መንገድ ለመፍታት በሚደረገው ጥረት የበኩሉን እንደሚወጣ ጠቁሟል። …ህገ መንግስታዊ የፌደራል ስርዓቱን ለማፍረስ መልኩን እየቀያየረ እየተከሰተ ያለውን #የትምክህት እና #ጥበት አደጋ ለመመከትም፥ ህወሃት ከእህት ድርጅቶቹ ጋር ተባብሮ ይሰራልም ብሏል ኮሚቴው።>> ከስብሰባው በፊት “ተገዢዎች ሁሌም የገዢዎቻቸውን ፍላጎት እንዲያሟሉ ይጠበቅባቸዋል፣ ገዢዎች ደግሞ ሁሌም እንዴት እንደሚገዙ ያስባሉ” ብዬ ነበር፡፡ በእርግጥ እንደ ህወሃት የለየለት ትምክህተኝነት እና በጠባብ ብሔርተኝነት የናወዘ የፖለቲካ ቡድን በዓለም ታሪክ ራሱ ተፈልጎ የሚገኝ አይመስለኝም፡፡ ይህ ግን ለህወሃት በፍፁም አይታየውም፡፡ ዛሬም ሆነ ነገ የህወሃት የሚያስበው የብአዴንን ትምክህት፣ የኦህዴድን ጥበት እንጂ ራሱ የተዘፈቀበትን ትምክህተኝነትና ጠባብነት አይደለም፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች የወደፊት እርምጃ ወይም ከስብሰባ በኋላ ስለሚሰጡት መግለጫ ብዙ አይነት ግምቶችና መላምቶች ይሰጣሉ፡፡ ምክንያቱም የድርጅቱን አቋምና ውሳኔ በእርግጠኝነት ማወቅና መገመት ያዳግታል፡፡ እንዲህ ባለ ግዜ የአቋም ለውጥ ይኖራል፣ ያልተጠበቀ ውሳኔ ይሰጣል፡፡ የህወሃት ግን ከሁሉም የተለየ ነው፡፡ ምክንያቱም የህወሃትን አቋምና ውሳኔ በእርግጠኝነት ማወቅና መገመት ትችላለህ፡፡ ከአንተ የሚጠበቀው፣ “ህወሃት የህዝቡን ጥያቄ ማየትና መስማት የተሳነው #ቆሞ_ቀር ድርጅት መሆኑንና ለለውጥና መሻሻል ቅንጣት ያህል ተስፋ እንደሌለው ማወቅ ብቻ ነው፡፡ መቼም፥ የትም ደርሰህ ና፣ ህወሃት ግን <<በአብዮታዊ ዴሞክራሲ መንገድ ለመፍታት…፣ ህገ መንግስታዊ የፌደራል ስርዓቱን ለማፍረስ፣ … የትምክህት እና ጥበት አደጋ ለመመከት…>> ከሚል መግለጫ ጋር ቆሞ ይጠብቅሃል፡፡ የህወሃትን የወደፊት ስራና ተግባር ማወቅና መገመት የሚሳንህ “ሀገሪቱ መንታ መንገድ ላይ በቆመችበት ወቅት መቼም ህወሃት እንደ ድርጅት ለአመታት ተገትሮ በነበረበት ቦታ አይቆምም፣ ትንሽማ ነቅነቅ ይላል” ብለህ ካሰብክ ብቻ ነው፡፡ ምክነያቱም ህወሃት ቆሞ_ቀር ነው!!

Filed in: Amharic