>

የሴናተር ኢንሆፍ ህወሓትን የመታደግ ዘመቻ ቀጥሏል! (ኦባንግ ሜቶ)

ጉብኝቱ “ከHR 128 … ውጪ ሊሆን አይችልም” ኦባንግ
የአሜሪካ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት አባል ሴናተር ጀምስ ኢንሆፍ ህወሓት/ኢህአዴግን ለመታደግ በአዲስ አበባ ላይ ከኢህአዴግ ሹሞች ጋር መከሩ። አቶ ኦባንግ ሜቶ ጉብኝቱ “ከHR 128 የተያያዘ ነው፤ ከዚህ ውጪ ሊሆን አይችልም” ይላሉ።
በያዝነው የአውሮጳውያን ዓመት (2017) መጀመሪያ አካባቢ ወደ ኢትዮጵያ ሄደው የነበሩት ሴናተር ጀምስ ኢንሆፍ ከከፍተኛ የሕወሓት/ኢህአዴግ ሹሞች ጋር መነጋገራቸው ህወሓት የሚቆጣጠረው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዘግቧል። የዜና አገልግሎቱ ውይይቱ መቼ እንደተደረገ ባይዘግብም ዜናውን ግን ጥቅምት 2/2010 በማለት ነው ያተተው።
በውይይቱ ላይ ሴናተሩ ሌሎች የአሜሪካ እንደራሴዎችንና የሕግ መወሰኛ ምክርቤት አባላትን በመምራት እንደተገኙ ዜናው አስታውቋል። የውይይቱ ትኩረትም “በሠላምና ጸጥታ ማስከበር ጉዳዮች ላይ” እንዲሁም “የኢትዮጵያና የአሜሪካን ግንኙነት ይበልጥ ለማሳደግ” እንደተካሄደ ተወስቷል።
ከዚህ በፊት ባልተለመደ መልኩ በውይይቱ ላይ ከወርቅነህ ገበየሁ በተጨማሪ የኃይለማሪያም ምክትል ደመቀ መኮንንና የክልል ኃላፊዎች ሌሎች ሹሞችን ጨምሮ ተገኝተዋል። የክልል ሹሞች በውይይቱ ላይ የመሳተፋቸው ጉዳይ የስብሰባውን አጀንዳ ክብደት የሚያሳይ ቢሆንም ከጥቂት ቀናት በፊት “የአፈጉባዔ ሥልጣኔን ለቅቄአለሁ” ያለው አባዱላ ገመዳ በቀዳሚነት መታየቱ “የለቀቀው ከየት ነው?” አሰኝቷል።
 የክልል ኃላፊዎች በውይይቱ ላይ መገኘታቸው የሕጉ መጽደቅ ሁሉንም የአገሪቱን ሕዝብ የሚነካ ጉዳይ ብሎ ለማሳሰብ በህወሓት በኩል የታቀደ “የከሸፈ ስልት” ነው ይላሉ፡፡
ጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ “HR 128/SR 168 ጸሐይ እየጠለቀችበት ነው!” በሚል ርዕስ ከጥቂት ቀናት በፊት ሲዘግብ አሁን በሥልጣን ላይ ያለው የትራምፕ አስተዳደር “አልሻባብን ለአስር ዓመት ያህል ስንዋጋ ቆይተን ለምንድነው እስካሁን ያላሸነፍነው?” የሚለውን ጥያቄ ማንሳቱን ዘግቦ ነበር። ይህም አስተዳደሩ ከኦባማ በተለየ መልኩ “አሸባሪነትን መዋጋት” ለሚባለው አጀንዳ ህወሓት/ኢህዴግን እንደ “ስትራቴጂካዊ አጋር” አድርጎ እንደማያየው አመላካች መሆኑን አብሮ በዘገባው ላይ መተንተኑ ይታወሳል።
“የትራምፕ አስተዳደር በአፍሪካ ላይ የተለየ አቋም የመያዙን ሁኔታ ተከትሎ በተለይ ከሕዝብ እንደራሴዎች ምክርቤት የኢትዮጵያን የሰብዓዊ መብቶች አስመልክቶ የተቀናበረው HR 128 የህወሓት ሹሞችንና ቤተሰቦቻቸውን ያስጨነቀ መሆኑን ጎልጉል ዘግቦ ነበር። በዚህ ሁሉ መካከል የህወሓት ታዳጊ ሆነው ብቅ ያሉት የኦክላሆማው ሴናተር ጂም ኢንሆፍ ናቸው”።
ይህንን የታዳጊነት ተግባር ለመፈጸም ሴናተር ኢንሆፍ በሰባት ወር ልዩነት በድጋሚ ወደ ኢትዮጵያ አምርተዋል። “HR 128”ን ለማክሸፍ የሚጥሩት ኢንሆፍ ብቻ ሳይሆኑ ሌሎችም እንዳሉበት በዚሁ የጎልጉል ዘገባ ላይ ተመልክቶ ነበር።
“ህወሓት ለወትዋቾች (ሎቢይስቶች) በጀት መድቦ መንቀሳቀስ ከጀመረ አስር ወራት ሆኖታል። በዋሽንግቶን ዲሲ የኢህአዴግ ጽ/ቤት ተጠሪ የሆነው ግርማ ብሩ SGR Government Relations ከተባለ የወትዋቾች ድርጅት ጋር በተፈራረመው ሰነድ ላይ በግልጽ እንደተመለከተው ለዚህ የውትወታ ሥራ ድርጅቱ በወር 150ሺህ ዶላር፤ በጥቅሉ 1.8 ሚሊዮን ዶላር ይከፈለዋል። በርካታ የተቃዋሚ ድርጅቶችና ቡድኖች (በተለይ በዳያስፖራ ያሉቱ) ተገቢውን ትኩረት ሳይሰጡት ቀሩ እንጂ ሁኔታዎች እንዳላማሩለት የተረዳው ህወሓት የቤት ሥራውን መሥራት የጀመረው አስቀድሞ ነበር”።
የኢንሆፍን ጉብኝት “በሠላምና ጸጥታ ማስከበር ጉዳዮች ላይ” ነበር ቢባልም “HR 128”ን በቅርብ ከሚከታተሉት በቀዳሚነት የሚጠቀሱት አቶ ኦባንግ ሜቶ “ሴናተር ኢንሆፍ ወደ አዲስ አበባ የሄዱት ስለ ረቂቅ ሕጉ ለመነጋገር” ነው በማለት ከጎልጉል ጋር ባደረጉት አጭር የመልዕክት ልውውጥ አስታውቀዋል።
አቶ ኦባንግ እንደሚሉት ከሆነ ይህ ሕግ በህወሓት ላይ ከፍተኛ ጫና የሚያሳድር ብቻ ሳይሆን ለኅልውናውም የሚያሰጋው ጠንካራ ረቂቅ ሕግ በመሆኑ ህወሓት/ኢህአዴግ ውስጥ መሸበር ስለመፍጠሩ መረጃ እንዳላቸው ጠቁመዋል። በተለይም በከፍተኛ የአገዛዙ ባለሥልጣናት ላይ ትልቅ ጫና የሚያስከትል በመሆኑ ሕጉ እንዳይጸድቅ መታገላቸው የሚደንቅ አይደለም በማለት “ጥቁሩ ሰው” ኦባንግ ይናገራሉ።
ረቂቅ ሕጉ እንዳጸድቅ ህወሓት በወትዋቾች በኩል ከፍተኛ ሥራ እየሠራ እንደሆነ የጠቆሙት የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ ዋና ዳይሬክተር ኦባንግ ከዚህም ሌላ ህወሓት ረቂቅ ሕጉ ከጸደቀ ጋር በአሸባሪነት ጉዳይ ከአሜሪካ ጋር አልተባበርም ማለቱ የጭንቀታቸውን ልክ የሚያሳይ ነው ይላሉ። “ከዚህ ሁሉ አንጻር ስናየው” ይላሉ ኦባንግ ሜቶ “ህወሓት ጨንቆታል፤ በተፈጥሮው ደግሞ አጥፍቶ ጠፊ ነው፤ ትውልድ አምጾበታል፤ ስለዚህ እንደ ኢንሆፍ ዓይነት ታዳጊ ያስፈልገዋል፤ የሴናተሩም ጉብኝት ይህንኑ የማክሸፍ ሥራ ለመተግበር ነው” በማለት የማስጠንቀቂያ አስተያየት ይሰጣሉ።
“ይህ ረቂቅ ሕግ በምንም ዓይነት ሁኔታ እንዲከሽፍ መፍቀድ የለብንም፤ ህወሓት በሁላችንም ላይ ጉዳት አድርሷል፤ ስለዚህ እንደ ተጎጂ ልዩነታችንን ወደጎን አድርገን በአንድነት ልንዋጋው ይገባናል፤ በተለይ በአሜሪካ ያለን ኢትዮጵያውያን የምንችለውን ሁሉ ተጽዕኖ ማድረግ አለብን፤ እንደራሴዎቻችንና ሴናተሮቻችንን በማግኘት የዚህን ሕግ መጽደቅ አስፈላጊነት በደንብ ማሳወቅ አለብን፤ ህወሓት ላመነበት ዓላማ በሚሊዮን የሚቆጠር ብር እየከፈለ እንዴት እኛ ዝም እንላለን?” በማለት ምክር አዘል አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
ሌሎች የረቂቅ ሕጉ ጉዳይ የሚያሳስባቸው ወገኖች “ሁላችንም አንድ የጋራ ጠላት እንዳለን በማመን የተባበረ ክንዳችንን በህወሓት ላይ በማሳረፍ ይህ በህወሓት አንገት ላይ ማነቆ ለማድረግ የተመቻቸ አጋጣሚ ልንጠቀምበት ይገባናል፤ ካልሆነ ግን ይህ ከአስራ አራት ዓመት በኋላ የተፈጠረ ዕድል ይከሽፋል፤ ብዙ ተስፋ የተጣለበት HR128 ፀሐይ ይጠልቅበታል፤ ህወሃትም አፈር ልሶ ይነሳል” በማለት ሥጋታቸውን ይናገራሉ።
ጎልጉል
Filed in: Amharic