>

ሄሎ ኢህአዴግ!! (አፈንዲ ሙተቂ)

ፖለቲካ ቁማር ነው ይባላል። ታዲያ እንዲያ ከሆነ ይሄ መንግስት ቁማሩን በትክክል የተበላው መቼ ነው እንበል? ብዙ ጊዜ ነው። የሩቁን ትተን የቅርብ ጊዜውን ብቻ ብናወሳ እንኳ ሁለት ጊዜ “አፋሽ” በሌለው ሁኔታ በወፍራሙ ተበልቷል

1ኛ. በ2008 ሀገር ምድሩን ያናወጠ ህዝባዊ ተቃውሞ በተነሳ በሶስተኛ ወሩ “ጥፋቱ የኔ ነው፣ ወደ ሌሎች ጣቴን አልቀስርም” ብሎ ለፈፈ። እኛም ይሁን አልነው። ታዲያ ኢህአዴግዬ ህዝቡ ሲረጋጋለት ብዙዎች የጠቆሙትን የማሻሻያ እርምጃ መውሰዱን ትቶ በህዝቡ ላይ ሸምቀቆውን ወደ ማጥበቅ ነው የተራመደው። ታዲያ ህዝቡም አመጹን ገፋበትና ሀገር ቀውጢ ሆነች። ከደርግ ውድቀት ወዲህ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታወጀብን። ኢህአዴግም ቁማሩን በወፍራሙ ተበላ።

2ኛ. ሁለተኛው አጋጣሚ ደግሞ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስር የቆየንበት ወቅት ነው። የኢህአዴግ መንግሥት “በአዋጁ ተጠቅሜ በጥልቀት የመታደስ እንቅስቃሴ እያካሄድኩ ነው” እያለ ሲናገር ነበር። ህዝቡ “እስቲ ተስፋ እናድርግ” በማለት በተስፋ ሲጠብቅ ሰነበተ። ሐምሌ ሲብት ያየነው ግን ተስፋ አስቆርጦ መኖርን የሚያስጠላ ነገር ሆኖ ተገኘ። በዜጎች ላይ የተጣለው ግብር በየትኛውም ዓለም ባልተለመደ መልኩ እስከ ሶስት መቶ እጥፍ ተደራርቦ መጣ። የአመፅ ገምቦ የሆነችው አምቦ “እምቢ” ብላ በአመፅ ተነሳች። ብዙ የኦሮሚያና የአማራ ክልል ከተሞች የርሷን ፈለግ ተከትለው ተነቃነቁ።

ታዲያ ኢህአዴግዬ እንደገና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጁ አቅሉን እንደሚያስተውና በዓለም ፊት እንደሚያሳጣው ገብቶት በተቆለለው ግብር ላይ ከፍተኛ ማሻሻያ ለማድረግ ፈቅጃለሁ አለ። ህዝብ በድጋሚ አሸነፈ። ኢህአዴግም በድጋሚ ቁማሩን ተበላ።
——-
አሁን ኢህአዴግ ለቁማሩ የሚመድበው የተወሰነ ገንዘብ ቀርቶታል። የጨዋታው ዓይነት ደግሞ ሰዓታትን የሚፈጀው ቼዝ፣ ወይንም “ኧርዝ” የሚባለው የካርታ ጨዋታ ዓይነት አይደለም። አንዳንድ ዋልጌዎች ጊዜ ለመግደል የሚጫወቷቸው “ኮንከር” እና “ሴካ” የተባሉ የካርታ ጨዋታዎችም አይደሉም። የአሁኑ ጨዋታ ተሳታፊዎቹን በሙሉ እዳ በእዳ አድርጎ ጨርቃቸውን የሚያስጥለው “ክሬዚ” የተባለ የካርታ ጨዋታ ነው። ስለዚህ ኢህአዴግ በእጁ የተረፈውን መመደቢያ ተበልቶ ከተጋጣሚዎች የተረፈውን ቅንጥብጣቢ ወደሚቀላውጡትና “አፋሽ” ወደሚባሉት የጨዋታ አዳማቂዎች ተርታ እንዳይንሸራተት ከፈለገ ጨዋታውን በጥንቃቄ እንዲጫወት ይፈለጋል።

ወዳጄ Dereje Gerefa አንድ ምልከታ ጠቁሞን ነበር። ኢህአዴግ በአስቸኳይ መስተካከል አለበት የምንለው ለራሱ ብቻ ስንል አይደለም። ዘወትር በሚንጠራወዝበት የጀብኝነት ጉዞው ራሱንም አጥፍቶ ሀገሪቱንም ከማትወጣበት የመከራ አዘቅት ሊከታት ስለሚችል ነው ቆም ብሎ ያስብ የምንለው።

አዎን! ጨዋታው የጅላጅሎቹ “ኮንከር” ሳይሆን በሽንፈትና በእዳ አሳብዶ ጨርቅ የሚያስጥለው “ክሬዚ” ነው። ኢህአዴጎች እባካችሁ ለራሳችሁ አብዳችሁ እኛንም ጨርቃችን አታስጥሉን። አሁንም ከመበላታችሁ በፊት አስቡበት።

Filed in: Amharic