>

የድሮ ሥርዓት ናፈቀኝ! (ዘመድኩን በቀለ)

¶ ከነገ ጀምሮ 100 ብር ያለው ሰው መንግሥት 17 ብር ይቀማውና 83 ብር ይኖረዋል ማለት ነው ። [ሠአገ]

¶ ብርም ከዋሌት ወደ ፌስታል ልትሸጋገር ነው ። ቀጥሎ ደግሞ ወደ ጆንያ ። ከዚያ ዘመንስ አያድርሰን ።
እግዚኦ !

ከነገ ጠዋት ከጥቅምት 1/2010 ዓም ጀምሮ የሀገሬ ገንዘብ የኢትዮጵያ ብር የመግዛት አቅሙ ወርዶ አንድ የኢትዮጵያ ብር በ27 ዶላር ስለሚመነዘር ብቻ አይደለም የድሮ ሥርዓት የናፈቀኝ።

በቃ ዝም ብሎ ናፈቀኝ ።

የድሮው 14ቱ ክፍላተ ሀገራት ፤ ሁለቱ ወደቦች ፣ አንዷ ባንዲራ ናፈቁኝ ። ናፈቁኝ የእነያ ዶሮ 50 ሳንቲም በግ 2 ብር በሬ 20 ብር ይሸጡ የነበሩ የጨቋኞቹ ነገሥታት ሥርዓትና ፣ ኩንታል ጤፍ 50 ብር ቀይ ወጥ 3 ብር በግ 40 ብር ፣ ዳቦ 10 ሳንቲም ፣ ታክሲ 25 ሳንቲም ፣ አውቶቡስ 15 ሳንቲም ፣ የቤት ኪራይ 50 ሳንቲም ያከራይ የነበረው ጨካኙና አረመኔው የደርጉ ሥርዓት የመንግሥቱ ኃይለማርያም ድምጽ ናፈቀኝ ።

 በቃ ዝም ብሎ ናፈቀኝ

ስኳር ቅመሱና ስትወዱት ግዙኝ የሚለው የጃንሆይ ዘመን ፣ ኪሎውን 1 ብር ግዙ ብሎ የሚለምነው  የደርግ ዘመን ናፈቀኝ ። ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ ቅደሚ የሚለው ብሔራዊ መዝሙር ናፈቀኝ ። ውኃ ከቦኖ ፣ መብራት ከቤቱ ያስገባ ማይጠፋበት ያ የቀድሞው ሥርዓት ናፈቀኝ።

እንዲህ ስል ግን የአሁኑን እንደ ፍቅረኞች ቀን በሻማ ብርሃን እንድንኖር ፈርዶብን ፤ ፈርዶብን እንኳ አይደለም ለኛ አስቦልን ከወጪ ደግ ሥርዓት ግን ጠልቼ አይደለም ። ምንም እንኳ ከ14 ክፍለ ሀገር ወደ 9 ሀገርነት ብንቀየርም ፣ ሱማሌ ክልል ለመግባት ቪዛ ለመጠየቅ ጫፍ ላይ ብንደርስም ። ወደብ ሽጠን በትርፉ ብንከራይም ፣ መብራት ከእኛ ተርፎ ለጅቡቲና ለሱዳኖች ብንሸጥም ፣ ውኃ በ15 ቀን አንዴ ጭቃ ለብሳ ፣ ጭቃ ጎርሳ ብትመጣልንም ፣ 1 ዶላር በ27 ብር ብንመነዝርም ። ይኽን ሥርዓት እየኖርኩበት የእነዚያ የቀደሙቱ እንደጉድ ናፈቁኝ ።

ይቅርታ ! በነገራችን ላይ ግን በሀገሬ አሁን የጤፍ ዋጋ ስንት ገባ ? ፣ ትራንስፖርትስ ጨመረ እንዴ ? ፣ ዶሮ ፣ በግ ፣ በሬና ፍየልስ ተወደዱ ረከሱ ? ሥጋ ኪሎው አልጨመረም ? አረ ብርቱካን በሀገሩ አለች ? ሎሚስ በብር ስንት ገባች ፣ ሽንኩርት ፣ ድንች ፣ ካሮት ፣ ቲማቲምስ አሁንም ኪሎአቸው 3 ብር ነው 4 ብር ፣ የታክሲ ዋጋ ስንት ገባ ? የአውቶቡሱስ ጨመረ ይሆን ?

ጭራሽ ደግሞ ይባስ ብሎ ክቡር ሠዓሊ አምሳሉ ገብረኪዳን በፌስ ቡክ ገጹ የለጠፈው ጦማር የበለጠ ጆሮዬን ጭው አድርጎ የቀድሞ ሥርዓት ናፋቂነቴን ጨመረው ። ሠዓሊ እንዲህ በማለት ነው ጦማሩን በጥያቄ የሚጀምረው ።

በብር ምንዛሬ ለውጥ ምክንያት እያንዳንዳችን በአገዛዙ እንደተዘረፍን እናውቅ ይሆን? በማለት በጥያቄ ይጀምርና ወደ ዝርዝር ሃሳቡ ሰተት ብሎ የዝርፊያውን አይነት ይተነትንልናል ።

ከነገ ጥቅምት 1 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ የብር ምንዛሬ ለ1 የአሜሪካ ዶለር 22.97 (23 ብር) ከነበረው 27 ብር እንዲሆን ብሔራዊ ባንክ (ቤተንዋይ)ገልጿል፡፡ ይሄ ማለት ምን ማለት እንደሆነ ልብ ብላቹህታል ወገኖቸ? በማለት መልሶ ይጠይቀናል ። ሰዓሊ ደግሞ ብናውቅ ምን አስደበቀን ቀጥል ወዳጄ ?

ይሄ ማለት ከነገ ጀምሮ [ ከጥቅምት 1/2010 ዓም ጀምሮ ማለቱ ነው]

¶ 1 መቶ ብር ያለው ሰው ከመቶው ብሩ ላይ 17 ብሩን አገዛዙ ወስዶበት 83 ብር ተደርጎበታል ማለት ነው ፡፡

¶ 1 ሽህ ብር ያለው መቶ ሰባ ብር ተወስዶበት 830 ብር ተደርጎበታል ማለት ነው፡፡

¶ 10 ሽህ ብር ያለው 1,700 ብር ተወስዶበት 8,300 ተደርጎበታል ማለት ነው፡፡

¶ 100 ሽህ ብር ያለው 17 ሽህ ብር ተወስዶበት 83 ሽህ ብር ተደርጎበታል ማለት ነው፡፡

¶ 1 ሚሊዮን (አእላፋት) ብር ያለው መቶ ሰባ ሽህ ብሩ ተወስዶበት 8 መቶ ሽህ 3 መቶ ብር ተደርጎበታል ማለት ነው፡፡ እንዲህ እያላቹህ እንግዲህ ባላቹህ ገንዘብ መጠን ምን ምን ያህል ገንዘብ እንደተዘረፋቹህ ማስላት ነው ይለናል ሰዓሊ አምሳሉ ገብረኪዳን ።

በሌላ አማርኛ የብር የመግዛት አቅም በ17 በመቶ ይቀንሳል ማለት ነው፡፡ ይሄም ማለት ቀደም ሲል በመቶ ብር ስንገዛው የነበረው ዕቃ አሁን 117 ብር እንገዛለን ማለት ነው፡፡ በዚህ የምንዛሬ ለውጥ ምክንያት ገበያው ላይ የሚከሰተው የዋጋ ግሽበት ግን በ100 ብር ዕቃ በ17 ብር ጭማሪ ሒሳብ ይወሰናል ብየ አልጠብቅም ፡፡ እንደምታውቁት ትንሽ ምክንያት ብቻ የሚፈልገው ገበያችን ይሄንን የምንዛሬ ለውጥ ምክንያት አድርጎ ገበያው እሳት እንደሚሆን ከፍተኛ ሥጋት አለኝ ፡፡

ምናልባትም መቶ ብር እንገዛው የነበረውን ዕቃ 150 እና ከዛ በላይ ሊሆን እንደሚችል እሠጋለው፡፡ በ150 ብንይዘው እንኳ ነጋዴው ተጨማሪ 33 ብር በመቶ ብር ይወስድብናል ማለት ነው፡፡ [ ቀጣይዋን መስመር በጥንቃቄ አንብቡልኝማ ] ይሄም ማለት #መቶ_ብር_ያለው_ሰው_ከነገ_ጀምሮ_ሐምሳ_ብር_ይሆንበታልማለት ነው፡፡ ስሌቱን ከላይ ባስቀመጥኩላቹህ ስሌት መሠረት አስሉት ፡፡

በአጭር ቋንቋ #የአምስት_ሽህ_ብር_ደሞዝተኛ ከነገ ጀምሮ ኑሮን የሚኖረው የ2,500 ብር ደሞዝተኛን ሰው ኑሮ ነው ፡፡ አንድ የአምስት ሽህ ብር ደሞዝተኛ እስከ አሁን የነበረውን የማያዘባንን ኑሮ ከዚህም ሳይከፋ ከነገ በኋላ መኖር ካለበት ከነገ ጀምሮ ደሞዙ 7,500 መሆን አለበት ማለት ነው፡፡ ይሄ የሚሆንበት ዕድል ደግሞ የለም፡፡

እናም የኢትዮጵያ ሕዝብ ሆይ! በአዲሱ የተመሰቃቀለና የችጋር ኑሮ ለመጠበስና ለመሰቃየት ዝግጁ ነህ ወይስ በቃኝ ብለህ የችጋርህን፣ የግጭትህን፣ የመለያየትህን፣ የውድቀትህን፣ የአሣርህን፣ የመከራህን የሁሉንም ክፉ ነገሮችህን ምንጭ ወያኔን ትገላገላለህ ??? ብሎ በመፈክር ትንተናውን ይዘጋዋል ።
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!! ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!
ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው amsalugkidan@gmail.com

ስለዚህ ከነገ ጀምሮ መንግሥታችን በህጋዊ መንገድ የዜጎቹን ገንዘብ በጠራራ ፀሐይ ይዘርፋል ማለት ነው ? በዚያውም ይኽንን ጭማሪ ተከትሎ የዋጋ ንረት ይፈጠራል ማለት ነው ። ምክንያቱም
ከውጭ ወደ ሀገር ውስጥ የሚመጡ የገቢ እቃዎች ላይ በሙሉ ጭማሪ ያመጣል ፣ የምግብ ፣ የስኳር ፣ የአልባሳት ፣ የጫማ ፣ ብቻ ማንኛውም ከውጭ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ ምርቶች በሙሉ እና ቀደም ብለው ከዋጋ ጭማሪው በፊት የገቡ ምርቶች ጭምር ዋጋቸው ይንራል ማለት ነው ።

ከዚያ ደጉ መንግሥት ፣ ፀሐዩ መንግሥታችን ሆዬ በቀጥታ ወደ ሆቴል በመሄድ ዋጋ በመወሰን ሜኖው ላይ ወደ መጻፍ ይገባና ፣ ዱለት 15 ብር ፣ ሽሮ 15 ብር ፣ በየአይነት 20 ብር ፣ ተጋቢኖ 18 ብር ፣ ስንግ ቃሪያ ከ50 ሳንቲም እንዳይዘል በየሆቴሉ ሲሽከረከር ፣ በየሥጋ ቤቱ በራፍ ሚዛን ስር ቆሞ ሲጨቃጨቅ ይውላል ። ነዳጅ ከጨመረ ደግሞ ሁሉም ነገር እሳት ይሆናል ማለት ነው።

ለምሳሌ ዛሬ 2 መቶ ሺህ ብር ልትገዛው የነበረው ቪታራ ነገ 230 ሺነህ ብር ሆኖ ይጠብቅሃል ማለት ነው ። ለስላሳ ስንት ገባ ፣ ሻይ ቡና ማክያቶስ እንደድሮው 3 ብር ነው? ኬክና ዳቦስ ጨመሩ ይሆን ? ድራፍትና ቢራ ግን የሚረክሱ ይመስለኛል ። ምክንያቱም በቂ አምራች ፋብሪካና ምርት ከበቂ ጨጓራው የተላጠ ጠጪ ጭምር አቅርቦትና ፍላጎትን ባሟላ መልኩ ስላለ እሱ ነገር የሚወደድ አይመስለኝም ። አይመስለኝም ነው ያልኩት ከተሳሳትኩ እታረማለሁ ።

ለማንኛውም ጸሎት ምሕላ ቢያዝ ልል አሰብኩና ለካ ሳስበው ቤተክርስቲያናችን ባንክቤት ልትከፍት ነው ። ካህናቱም ከመቅደሱ አገልግሎት ወደ ባንክ ገንዘብ ቆጣሪነት ሊሸጋገሩ ነው ። እነ አቡነ ማርቆስና አቡነ ቶማስ ከቅዱስነታቸው ጋር ሆነው ስለሚፈርስ ማኅበር ምክር ላይ ናቸው ። እናም የሚያጸልይ ስለሌለ የጸሎቱን ነገር እነሱን መጠበቁን ትገን እንዲሁ እግዚኦ ማለቱ ይሻላል ባይ ነኝ ። አደራ ቅር እንዳይላቸው ግን ሙዳየምጽዋት መስጠታችሁን እንዳታቋርጡ ። አደራ አደራ ።

እናም እነዚያ ጨካኝ የድሮ ሥርዓቶች ናፈቁኝ ። የኖርኩበት የደርግና ያልኖርኩበት የአጼ ኃይለሥላሴ ሥርዓቶች ናፈቁኝ። ደግሞ ናፋቂ ፣ አቆርቋዥ ፣ ፊውዳል ፣ ነፍጠኛ ፣ ቆለኛ ፣ ደገኛ ፣ ፀረ ህዝብ ፣ ፈሽስት ፣ ጨቋኝ ፣ አረመኔ ምናምን በሉኝ አሏችሁ ። የፈለጋችሁትን በሉኝ እኔ ግን የቀድሞው ሥርዓት ናፈቆኛል

Filed in: Amharic