>

ኦሮማይ 1፣2፣3 (ስዩም ተሾመ)

​ኦሮማይ-1፡ በይስሙላ ምርጫ ወደ ለውጥ ማዕበል!

የአስቸኳይ ግዜ አዋጁ የተነሳ ሰሞን ባወጣሁት “ኢትዮጲያ የማን ናት”  የሚል ፅሁፍ፤ “የኢህአዴግ መንግስት በ2002ቱ ምርጫ 99.6%፣ በ2007ቱ ደግሞ 100% ‘አሸነፍኩ’ ብሎ ተሳልቋል። ይህ “የይስሙላ ምርጫ” ግን በዴሞክራሲ መቃብር ላይ የበቀለ አረም ነው” ብዬ ነበር። ይህ ዛሬ ላይ በድንገት የተገለጠልኝ እውነት አይደለም። ልክ የ2007ቱ ምርጫ ውጤት ይፋ እንደተደረገ “100% የምርጫ ቅሌት እንጂ ውጤት አይባልም” በማለት የሚከተለውን ፅፌ ነበር፡-

“100% የሚባለውን አሰቃቂ ክስተት “የምርጫ ውጤት” በሚል ሰርግና ምላሽ እየተደረገ ያለበት ሁኔታ ነው ያለው። በዞንና ወረዳ ደረጃ ያሉትስ አይፈረድባቸውም። በፌዴራልና ክልል ደረጃም ተመሳሳይ አቋም የሚያራምዱ ባለስልጣናት ካሉ ግን በጣም አስገራሚ ነው የሚሆነው ። ይሄ 100% ተብዬ ነገር’ኮ ባለፉት 20 አመታት ውስጥ ሀገሪቱ በዲሞክራሲ ረገድ ያሳየችውን ለውጥና መሻሻል ወደ ኋላ የቀለበሰ፣ ህዝቡ ሰላማዊ ፖለቲካ፣ በሕግ የበላይነት እና በሌሎች ዴሞክራሲያዊ እሴቶች ላይ ያለውን እምነት ሽርሽሮ በመናድ ዴሞክራሲን በጭቅላቱ ዘቅዝቆ ያቆመ፣ ልክ እንደ ደርጉ ቀይ-ሽብር ህዝብን በፍርሃት ቆፈን የሚቀፈድድ እጅግ አስቀያሚ ድርጊት ነው።” 

በተለይ ባለፉት አስር አመታት የኢህአዴግ መንግስት፤ በፀረ-ሽብር ሕጉ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶችን፣ በሚዲያና የመረጃ ነፃነት ሕጉ ነፃና ገለልተኛ ሚዲያዎችን፣ እንዲሁም በበጎ አድራጎት ድርጅቶች ማቋቋሚያ አዋጅ የሲቪል ማህበራትን አጥፍቷቸዋል። የኢህአዴግ መንግስት እነዚህን የዴሞክራሲ ተቋማት ከማጥፋቱ በተጨማሪ፣ የተለየ ሃሳብና አመለካከት ያላቸውን የራሱን አመራሮች “በሃይማኖት አክራሪነት፣ ብሔርተኝነት ወይም ትምክህተኝነት” እየፈረጀ የተወሰኑትን ለእስርና ስደት ሲዳርጋቸው፣ የተቀሩት ደግሞ ሃሳባቸውን ከመግለፅ እንዲቆጠቡ አድርጓቸዋል።

በአጠቃላይ፣ በአንድ ሀገር ውስጥ ጠንካራ ተቃዋሚ የፓለቲካ ድርጅቶች፣ ነፃና ገለልተኛ ሚዲያ እና የሲቭል ማህበራት ከሌሉ፣ እንዲሁም ገዢው ፓርቲ የተለየ ሃሳብና አመለካከት የማስተናገድ ባህል ከሌለው ሕገ-መንግስታዊ ዴሞክራሲ (Constitutional Democracy) አብቅቶለታል። በተቃራኒው፣ ከ2008 ዓ፣ም ጀምሮ ባለው ግዜ ውስጥ ብቻ በሕዝቡ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ላይ የታየው ለውጥ የሩብ ምዕተ አመታት ያህል ሰፊ ነው። ሕዝቡ የሚያነሳቸው ጥያቄዎችና እያሳየ ያለው የለውጥ ፍላጎት ከእለት-ወደ-እለት እየተቀያየረና እየጨመረ መጥቷል። በዚህ ፈጣን የለውጥ ሂደት ውስጥ ባለበት የቆመው የኢህአዴግ መንግስት ብቻ ነው።

በ2008 ዓ.ም 3ኛው ማዕበል በሚለው ባወጣሁት ፅሁፍ ባለፉት ሃያ አምስት አመታት በሀገሪቱ ውስጥ የታየው ለውጥ በሀገሪቱ ታላቅ የፖለቲካ ማዕበል እንደሚያስነሳ ገልጬያለሁ። ሆኖም ግን፣ የኢህአዴግ መንግስት አስፈላጊውን ለውጥና መሻሻል ለማምጣት አንዲት እርምጃ መራመድ ተስኖታል። ለኢህአዴግ መንግስት ዛሬም፥ የዛሬ ሁለት አመት ሆነ የዛሬ አስር አመት “ፈተናዎቹ”፤ የመልካም አስተዳደር እና ኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከት፡- ትምክህተኝነት፥ ጠባብ ብሔርተኝነት እና አክራሪነት” ናቸው።

የህዝቡ ጥያቄና እንቅስቃሴ ተፈጥሯዊ የለውጥ ሂደትን ተከትሎ የመጣ እንደመሆኑ አይቀሬና አስገዳጅ ነው። በመጀመሪያ ደረጃ፣ የህዝቡ ኑሮና አኗኗር እየተለወጠ፣ በተለይ ደግሞ የመረጃ አቅርቦትና አጠቃቀም እየተሻሻለ በሄደ ቁጥር፣ አብዛኛው የሕብረተሰብ ክፍል መብትና ግዴታውን ይበልጥ ያውቃል፥ ይጠይቃል። በልማትና ዴሞክራሲ ረገድ ህዝቡ የሚያነሳቸው ጥያቄዎች ይበልጥ እየሰፉና እየተወሳሰቡ መሄዳቸው እርግጥ ነው።

ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ እየታየ ያለው ተቃውሞ ህዝቡ በሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ መንገድ መብቱን ለማስከበር የሚችልበት አማራጭ መንገድ በማጣቱና ብሶትና ምሬቱን የሚተነፍስበት ትንሽ ቀዳዳ ባለመኖሩ የተከሰተ ነው። በአንድ በኩል ህዝቡ በፍትህና የመልካም አስተዳደር እጦት ምክንያት እየተሰቃየ ነው። በሌላ በኩል፣ ለአስር አመታት የተጠራቀመ ብሶቱንና ምሬቱን የሚያስተነፍስበት ቀዳዳ ሲያጣ፣ አመፅና ተቃውሞ ብቸኛ አማራጭ ይሆናሉ። በተለይ ደግሞ፣ ቀልጣፋ አገልግሎትና ፍትህ ያልሰፈነበት ምክንያት ሌላ ሳይሆን መንግስት የአስተዳደርና ፍትህ ሥርዓቱን ማሻሻል ስለተሳነው እንደሆነ በበቂ መረጃ ላይ የተመሰረተ ግንዛቤ ሲኖረው ህዝብ ይቆጣል፣ ህዝባዊ አመፅ ይቀሰቀሳል።

በጅምላ የታሰሩ ወጣቶች እርስ በእርሳቸው ፀጉራቸውን እንዲላጩ ይደረጋል!

ከዚያ በመቀጠል “ኢህአዴግ፡ ከለውጥና ሞት አንዱን ምረጥ” በሚል ርዕስ ባወጣሁት ፅሁፍ የኢህአዴግ መንግስት ሁለት አማራጮች እንዳሉት ገልጩ ነበር። የመጀመሪያ አማራጭ የሕዝቡን ጥያቄና የለውጥ ፍላጎት ጋር አብሮ በመጓዝ በሀገሪቱ ልማት፣ ሰላምና ዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ሂደት ወደ ወሳኝ ምዕራፍ ማሸጋገር። ሁለተኛው አማራጭ ደግሞ በሕዝቡ ዘንድ እየተነሳ ያለውን ጥያቄና የለውጥ ፍላጎት በማፈን የተሻለ ሕይወት የመኖር ተስፋውን ማጨለም ነው። በዚህ መንገድ የብዙ ንፁሃን ዜጎችን ሕይወት መስዕዋት የሚጠይቅ ይሁን እንጂ እንደ ማንኛውም አምባገነናዊ ሥርዓት መጨረሻው ውድቀት ይሆናል።

ከላይ በተጠቀሰው ፅሁፍ  የኢህአዴግ መንግስት አካሄድ የፈጠረብኝን ስጋት፤ “አሁን ላይ ይበልጥ እያሳሰበኝ ያለው ነገር፣ ኢህአዴግ ከሕዝቡ ጥያቄና ፍላጎት ጋር አብሮ መሄድ አለመቻሉ ሳይሆን በዚህ ምክንያት የሀገሪቱ ዜጎች ሰላምና ደህንነት አደጋ ላይ እየወደቀ መምጣቱ ነው!” በማለት ገልጩ ነበር። ከዚሁ ጋር አያይዤ፣ ከ2008 ዓ.ም ሁለተኛ አጋማሽ ጀምሮ የኢህአዴግ መንግስት የሚወስደው እርምጃ ከለውጥ እና ሞት አንዱን እንደመምረጥ መሆኑን ጠቅሼ ነበር። ሆኖም ግን፣ በቀጣዩ የ2009 አመት የተካሄደውን “ጥልቅ ተሃድሶ” ከተመለከትኩ በኋላ “ኢህአዴግ እና ፀጉራም ውሻ አንድ ናቸው” የሚል ፅሁፍ አወጣሁ። ይህ የኢህአዴግ መንግስት ከለውጥ ይልቅ ሞትን እንደመረጠና እንደ ፀጉራም ውሻ ማንም ሳይውቅለት ውስጥ-ለውስጥ እየሞተ እንደሆነ ይጠቁማል።

ኦሮማይ-2፡ ከለውጥ ማዕበል ወደ ብጥብጥ! 

 በሕዝቡ እየተነሱ ያሉ ጥያቄዎች ተገቢ ምላሽ እስካልተሰጣቸው ድረስ ግጭትና አለመረጋጋቱ እየጨመረ ይሄዳል። ይህን የለውጥ ጥያቄ ለማስቆም መሞከር ከትውልድ ጋር ግጭት ውስጥ እንደ መግባት ነው። መንግስት ሕዝቡ እያነሳቸው ላሉት የዴሞክራሲ ጥያቄዎች ተገቢ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ በኃይል ለማፈን የሚደረገው ጥረት ሀገሪቱን ወደ ለየለት ግጭትና አለመረጋጋት ያስገባታል።

የኢህአዴግ ባለስልጣናት ሥራና አሰራራቸውን ከማሻሻል ይልቅ ፖሊሶች፣ ወታደሮችና የደህንነት ሰራተኞች በመላክ ሕዝቡን ለሞት፣ ጉዳትና ለእስራት የሚዳርጉት ከሆነ ባለስልጣናቱ በሕዝቡ ዘንድ ያላቸውን ቅቡልነት፣ እንደ መንግስትም ያላቸውን ተቀባይነት ከግዜ ወደ ግዜ እያጡ ይሄዳሉ። በዚህም አንደኛ፡- መንግስት በሕዝቡ ዘንድ ያለውን የማስተዳደር ስልጣን ይገፈፋል፤ ሁለተኛ፡- ሕዝቡ ራሱን-በራሱ ማስተዳደር መብቱን ተጠቅሞ የጋራ ሰላምና ደህንነቱን በራሱ ለማስከበር ጥረት ያደርጋል። ይህ ደግሞ ገና በ2008 ዓ.ም መጀመሪያ ላይ በግልፅ ተጀምሯል።

ነጭ ሽብር ተጀምሯል፣ ቀይ ሽብር ይከተላል” በሚል ርዕስ ባወጣሁት ፅሁፍ የኢትዮጲያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ሪፖርትን ዋቢ በማድረግ በ2008 ዓ.ም ብቻ በኦሮሚያ ክልል 173 ሰዎች ሲገደሉ ከእነዚህ ውስጥ 14 የፀጥታ ኃሎች ሲሆኑ ሌላ 14 ደግሞ የክልሉ መንግስት ኃላፊዎች ናቸው። በተመሳሳይ በዚያኑ አመት በጎንደር ከተማ በፌደራል ፖሊስ አባላት ላይ የሞትና የአካል ጉዳት መድረሱ ይታወሳል። እነዚህና ሌሎች ተያያዥ ክስተቶች በኦሮሚያና አማራ ክልላዊ መስተዳደሮች ላይ ከፍተኛ ለውጥ አምጥተዋል።

የአማራ ክልል መስተዳደርና የብአዴን አመራሮች ከሕዝቡ ለሚነሳው ጥያቄ የድጋፍ አዝማሚያ ማሳየታቸው ይታወሳል። በተቃራኒው የቀድሞ የኦህዴድ የበላይ አመራር በክልሉ ሲካሄድ የነበረውን የሕዝብ አመፅና ተቃውሞ በኃይል ለማዳፈን ያላሳለሰ ጥረት አድርጓል። ይህ ግን በአቶ ለማ መገርሳ የሚመራውን አዲሱን የኦህዴድ አመራር ወደ ስልጣን እንዲመጣ አድርጎታል። በሌላ አነጋገር፣ የአቶ ለማ መገርሳ አመራር በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ በኦሮሞ ሕዝብ ጫና እና ግፊት ወደ ስልጣን እንደመጣ መገንዘብ ይቻላል። በአቶ ገዱ አንዳርጋቸው የሚመራው የአማራ ክልል መስተዳደር በስልጣን ላይ መቆየት የቻለው በወቅቱ የክልሉ ሕዝብ ላነሳቸው የነፃነት፥ እኩልነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጥያቄዎች የመደገፍ ዝንባሌ ስለነበረው ነው።

ሆኖም ግን፣ የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ራሱን ለለውጥ ከማዘጋጀትና የተሃድሶ አቅጣጫ ከማስቀመጥ ይልቅ ለህዝቡ ጥያቄ የድጋፍ አዝማሚያ ያሳዩትን የብአዴን እና የኦህዴድ አመራሮችን ተጠያቂ ማድረግ መርጧል። በ2008 ዓ.ም መጨረሻ ላይ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ባደረገው ስብሰባ ህዝቡን በማስመረር ላይ ያለው ችግር ዋነኛ መንስዔ የመልካም አስተዳደር እጦት እንደሆነ በመጥቀስ በቀጣይነት “ከራሱ ጀምሮ” የሚታዩ የጥገኝነት አስተሳሰቦች እና የጥገኝነት ተግባራትን ለመታገል መወሰኑን ገልፆ ነበር።  በወቅቱ ኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ የሚከተለውን መግለጫ አውጥቷል፡-

“… ስልጣን ያለአግባብ ለመጠቀም ለሚሹ ግለሰቦች በመሳሪያነት ማገልገል ሲጀምር የተጀመረው ልማት ይደነቃቀፋል፡፡ መልካም አስተዳደርም ይጠፋል። …በአሁኑ ጊዜ ህዝብን በማስመረር ላይ ያለው ችግር ዋነኛ መንስዔ ይህ ነው፡፡ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው በዚህ ረገድ ከራሱ ጀምሮ የሚታዩ የጥገኝነት አስተሳሰቦችና መገለጫ የሆኑትን ጠባብነትና ትምክህተኝነትት እንዲሁም የጥገኝነት ተግባራትን በጥብቅ በመታገል ይህ አዝማሚያ እንዲገታ ለማድረግ የሚያስችሉ ዝርዝር ዕቅዶችም አዘጋጅቷል፡፡”

በመግለጫ መሰረት የጥገኝነት አስተሳሰብ፣ በዋናነት ጠባብነትና ትምክህተኝነት ይታይባቸዋል የሚባሉ የኢህአዴግ አመራሮች ለሕዝብ ጥያቄና አቤቱታ አዎንታዊ ምላሽ ወይም ለዘብተኛ አቋም ያላቸው ናቸው። ላለፉት አስር አመታት ኢህአዴግ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮችንና ጋዜጠኞችን ለእስርና ለስደት በመዳረግ በሀገሪቱ አማራጭ የፖለቲካ ኃይሎች አንዳይኖሩ አድርጓል። በተለይ በጀማሪና መካከለኛ ደረጃ ላይ ያሉት አመራሮች የኢህአዴግ መንግስት አፋኝና ጨቋኝ መሆኑን ተከትሎ አባል ፓርቲውን ከውስጥ ለመቀየር ጥረት ያደረጉ ሰዎች ናቸው። በአማራና ኦሮሚያ ክልሎች እየታየ ያለው ግጭትና አለመረጋጋት የሕዝብ ጥያቄ በሰላማዊና በሰለጠነ መንገድ ስላልተመለሰ እንጂ በተወሰኑ የኢህአዴግ አመራሮች የተፈጠረ ችግር አይደለም።

በ2009 ዓ.ም መጀመሪያ ላይ በታወጀው የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ አማካኝነት ሀገሪቷ ሙሉ በሙሉ በወታደራዊ ቁጥጥር ስር የቆየች ቢሆንም የሁለቱን ክልሎች አመራር እንደ ቀድሞ ለፌደራል መንግስቱ ተገዢ እንዲሆኑ ማድረግ አልተቻለም። ከዚያ ይልቅ፣ ብአዴን እና ኦህዴድ አመራሮች የሕዝቡን ጥያቄ ተቀብለው ማስተጋባት በጀመሩበት ወቅት ለሕገ-መንግስቱና ለፌደራሊዝም ስርዓቱ ጥብቅና የቆሙት በዋናነት የህወሓት ከፍተኛ አመራሮች እና የሶማሌ ክልል መስተዳደር ናቸው።

ህወሓት/ኢህአዴግ በሀገሪቱ የፖለቲካ ላይ ያለውን የበላይነት ለማረጋገጥ ብቸኛ አማራጭ እንደመሆኑ ለሕገ መንግስቱና መንግስታዊ ስርዓቱ ጥብቅና ከመቆም ውጪ ሌላ ምርጫና አማራጭ የለውም። የሶማሌ ክልል መስተዳደር ግን ከተላላኪነት የዘለለ ሚና የለውም። በተለይ የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳደር የሆኑት አቶ አብዲ መሃመድ ኦማር (አብዲ ኢሌ) ገና ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ የኦሮሞና አማራ ሕዝብ የመብት ጥያቄን በማጣጣልና የመከላከያና ፌደራል ፖሊስ ሁኔታውን ለመቆጣጠር በሚያደርጉት ጥረት ቀጥተኛ ተሳትፎ ለማድረግ ፍላጎታቸውን በይፋ መግለፃቸው ይታወሳል። በተመሳሳይ ወቅት የሶማሌ ክልል ልዩ ፖሊስ በምስራቅና ደቡብ ምስራቅ ኦሮሚያ አከባቢዎች ላይ ጥቃት መፈፀም ጀምሯል።

የህወሓት/ኢህአዴግ አባላትና አመራሮች

የሶማሌ ልዩ ፖሊስ በምስራቅና ደቡብ ምስራቅ ኦሮሚያ በሚገኙ አከባቢዎች ላይ ተከታታይ ጥቃት በመፈፀም በመቶዎች የሚቆጠሩ የክልሉ ነዋሪዎችን ከሞት፣ ከ200ሺህ በላይ ደግሞ ማፈናቀሉ ይታወሳል። ይህ ሲሆን የፌደራሉ መንግስት፥ የሀገር መከላከያ፥ የደህንነትና ፖሊስ ኃይሎች በሶማሌ ክልል ልዩ ፖሊስ የሚፈፀመውን ኢሰብዓዊ ድርጊት ለማስቆም በተጨባጭ ይሄ ነው የሚባል ጥረት አላደረግም። ለዚህ ደግሞ ተጠያቂ የሀገሪቱ የፀጥታ ኃይል መዋቅር በበላይነት የተቆጣጠረውና አዲሱን የኦህዴድ አመራር ለፌደራል መንግስቱ ተገዢ እንዲሆን ከፍተኝ ጥረት እያደረገ ያለው ህወሓት/ኢህአዴግ ነው።

የብአዴን አመራር በራሱ ከፌደራሉ መንግስት ቁጥጥር ለመውጣት የበኩሉን ጥረት እያደረገ ሲሆን የደኢህዴን አመራር ደግሞ በፌደራል መንግስቱ መዋቅርና እንቅስቃሴ ላይ ያለው የመወሰን አቅም እጅግ በጣም ውስን ነው። በዚህ መሰረት፣ የፌደራሉ መንግሰት ህወሓት ብቻውን የሚንከላወስበት ኦና ቤት ሆኗል። በአጠቃላይ የመከላከያና ደህንነት ኃይሉን በበላይነት የተቆጣጠረው የህወሓት/ኢህአዴግ ከፍተኛ አመራር ግራ ተጋብቶ ሀገሪቷን ወደ እርስ በእርስ ግጭትና እልቂት ውስጥ ሊያስገባት ከቋፍ ላይ ደርሷል።

ኦሮማይ-3፡ ያለ ለውጥ ብጥብጥ ውድቀትን ማረጋገጥ!

 

 

ከሕዝቡ ሲነሱ ለነበሩት የዴሞክራሲና መልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት ባለፉት ሁለት አመታት የኢህአዴግ መንግስት መውሰድ የነበረበት የለውጥ እርምጃዎች ምንድን ናቸው? በመጀመሪያ ደረጃ ራሱ ኢህአዴግ መታደስ አለበት። በተለይ የአማራና ኦሮሞ ሕዝብ ጥያቄን የሚያነሱ ግለሰቦችን በአሸባሪነት፣ እንዲሁም ተመሳሳይ አዝማሚያ ያላቸውን የራሱን አመራሮች በጠባብነትና ትምክህተኝነት መፈረጅ ማቆም አለበት።

በመቀጠል በዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ረገድ ስር ነቀል የለውጥ እርምጃዎች መውሰድ ይጠበቅበታል። በዚህ ረገድ ከኢህአዴግ የሚጠበቀው፤ አንደኛ፡- የዜጎችን ዴሞክራሲያዊ መብትና ነፃነት ማክበር ሁለተኛው ደግሞ የመልካም አስተዳደር እጦትን በዘላቂነት መቅረፍ ነው፡፡ በዚህ መሰረት የኢህአዴግ መንግስት ከሕዝቡ እየተነሱ ያሉትን የዴሞክራሲ ጥያቄዎች በአግባቡ ለመመለስ አስተዳደራዊ ተሃድሶ (Administrative reform) እና ፖለቲካዊ ተሃድሶ (Political reform) ማድረግ ይጠበቅበታል።

ከተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች እየተነሱ ያሉት የእኩልነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጥያቄዎች ከመልካም አስተዳደር እጦት ጋር በቀጥታ የተያያዙ ናቸው፡፡ የመልካም አስተዳደር ችግርን ለመፍታት ግልፅነትና ተጠያቂነት የሰፈነበት የአስተዳደርና አገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓት መዘርጋት ያስፈልጋል፡፡ በዚህ መልኩ የአስተዳደርና አገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓቱን ጥራት ለማሻሻል በቅድሚያ ብቃት ያለው አመራር ሊኖር ይገባል፡፡ ከሙያዊ ብቃት ይልቅ በፖለቲካ ታማኝነት ላይ የተመሰረተ አመራር ግልፅነትና ተጠያቂነት የሰፈነበትና ጥራት ያለው አስተዳደርና የአገልግሎት አሰጣጥ ለመዘርጋት ዋና ማነቆ ነው፡፡ በዚህ ረገድ ሥር-ነቀል የሆነ ለውጥ ማድረግ ካልተቻለ ሕዝቡን ክፉኛ እያማረረ ያለውን የመልካም አስተዳደር እጦት ችግርን በዘላቂነት መቅረፍ አይቻልም፡፡
የፖለቲካ ተሃድሶ መሰረታዊ ዓላማው የብዙሃኑ የሕብረተሰብ ክፍል እኩልነት፣ ነፃነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት የተረጋገጠበት ፖለቲካዊ ሥርዓት – ዴሞክራሲ – መገንባት ነው፡፡ ይህ በሕገ-መንግስቱ ዋስትና የተሰጣቸውን የዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ያለ ምንም መሸራረፍ ማክበርና ማስከበር ይጠይቃል፡፡ ይህ ደግሞ በተራው በተለያየ ግዜ የወጡና የዜጎችን መብትና ነፃነት የሚገድቡ ፖሊሲዎችን፣ አዋጆችን፣ ደንቦችንና መመሪያዎችን፣ እንዲሁም ከሕገ-መንግስታዊ መርሆች ውጪ የሆኑ ሥራና አሰራሮችን ሙሉ ለሙሉ መቀየር ያስፈልጋል፡፡

የኢህአዴግ መንግስት ከፍተኛ አመራሮች ስብሰባ

በዚህ መሰረት፣ የኢህአዴግ መንግስት ሊያከናውናቸው ከሚገቡ የለውጥ ተግባራት ውስጥ ዋና ዋናዎቹ የሚከተሉት ናቸው፡-

  • የታሰሩ ፖለቲከኞችን፣ ጋዜጠኞችን፣ የመብት ተሟጋቾችን እና ሌሎች የፖለቲካ እስረኞችን ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ መፍታት፣
  • የዜጎች ዴሞክራሲያዊ መብቶችን የሚገድበውን የፀረ-ሽብር አዋጁን መሻርና ከሕገ-መንግስቱ ጋር በተጣጣመ መልኩ እንደገና ማርቀቅ፣
  • የመንግስትና የግል ሚዲያ ተቋማትን ሥራና አሰራር ከፖለቲካ ወገንተኝነት ነፃ ማድረግ፣ ለዘርፉ እድገት ማነቆ የሆነውን የመረጃ ነፃነትና ሚዲያ አዋጅ ከሕገ-መንግስቱ ጋር በተጣጣመ እንደገና ማርቀቅ፣
  • የሙያና ሲቪል ማህበራት በሀገሪቱ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ምቹ ሁኔታ መፍጠር፣ ለተቋማቱ አንቅስቃሴ ማነቆ የሆነውን የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ማቋቋሚያ አዋጅ እንደገና ማርቀቅ፣
  • የተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶችን እና ሌሎች የፖለቲካ ኃይሎችን “ፀረ-ስላም…ፀረ-ሕዝብ…ፀረ-ልማት” ብሎ በመፈረጅ የጠላትነት መንፈስ እንዲያቆጠቁጥ ከማድረግ ይልቅ መልካም ግንኙነት ማዳበርና ለብሔራዊ መግባባት መስራት ይጠበቅበታል፡፡

ባለፉት ሁለት አመታት ውስጥ የኢህአዴግ መንግስት ከላይ ከተጠቀሱት ዋና ዋና ተግባራት አንዱን እንኳን ተግባራዊ አድርጓል? አላደረገም! ከዚያ ይልቅ፣ በሶማሌ ክልላዊ መስተዳደር አመራርና ልዩ ፖሊስ አማካኝነት ከላይ የተጠቀሱት የለውጥ ጥያቄዎች ዳግም እንዳይነሱ ለማድረግ፣ በዚህም የለውጥና መሻሻል ንቅናቄውን በእጅ አዙር ለማዳፈን ጥረት እያደረገ ነው።

በሁለቱ ክልሎች መካከል ግጭት በመፍጠር ወይም እንደ መንግስት የሚበቅበትን ድርሻና ኃላፊነት ከመወጣት ይልቅ ዳር-ቆሞ በመመልከት ላይ ይገኛል። በመሆኑም እንደ መንግስት ድርሻና ኃላፊነቱን በተግባር መወጣት ተስኖታል። ስለዚህ በግልፅ የፌደራሉ መንግስት መዋቅሩን ተከትሎ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ማድረግ ተስኖታል። በአጠቃላይ የፌደራሉ መንግስት በተግባር ወድቋል፥ አልቆለታል፥ አብቅቶለታል፥…. ኦሮማይ!!

Filed in: Amharic