>
5:13 pm - Tuesday April 19, 8568

የችግሩ ፈጣሪዎች የመፍትሔው አካሎች ሊሆኑ ይችሉ ይሆን? (ከአብርሃ ገብረእግዚአብሔር)

 ዛሬ አገራችን ከምንጊዜው በላይ የከፋ የመነጣጠል አደጋ ተደቅኖባታል። ይህን አደጋ ስንቶቻችን ተረድተነው እንደሆን በእርግጠኝነት እንዲህ ነው ለማለት ያስቸግራል። ችግሩ ግን የተራራ ያህል ገዝፎ እየታየነው። አገራችን የገጠማትን ይህ የመበታተን አደጋ የጋረጠው ችግር መሠረቱን የጣለው፣ እንደ ኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር በ1950 አጋማሽና በ1960ዎቹ መግቢያ ላይ የቀድሞው የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች የነበሩና በነዚሁ ዘመኖች ለከፍተኛ ትምህርት ወደ ውጭ ተልከው የነበሩ ተማሪዎች ያቀነቀኑት የለውጥ ድምፅ ያስከተለው ቀውስ እንደሆነ ግልጽ ነው።

\እነዚህ «ተማርን» ያሉ ወጣቶች፣ የአገራችውን ታሪክ፣ የፖለቲካ ባህል፣ የሕዝቡን ሥነ-ልቦና፣ የአገሪቱን የመሬት ሥሪት ተያያዥ ታሪኮች፣ የሕዝቡን የአብሮተትና የአንድነት አፈጣጠር ሂደት በቅጡ ያላውቁ፣ ሊያውቁም ያልፈለጉ ፣ የአገር ዕድገት መሠረቱ ተከታታይነት መሆኑን ያልተገነዘቡ፣ እንኳን ያን ጊዜ ዛሬም ለመገንዘብ ያልፈለጉ፣ በተቃራኒው ኢትዮጵያ ልትፈርስ የምትችልበትን መንገድ በሰከነ መንገድ ሲያጠኑ የነበሩ የውጭ ኃይሎች እንደ ሮማን ፕሮቻስካ እና ዮሐን ክራፍ የተሰኙ ፀረ-ኢትዮጵያ የሆኑ ግለሰቦችና ሰላዮች የተጻፉትን መጽሐፍት በቅጡ ሳይረዱ፣ የእነርሱን ሀሳብ ባቀነቀኑ አገር በቀል ፀረ-ዐማራና ፀረ-ኢትዮጵያ በሆኑ ቡድኖችና ግለሰቦች ተራግቦ ዛሬ አገሪቱና ሕዝቡ ለሚገኙበት አስፈሪ የመበታተንና የዕልቂት ደረጃ እንዳደረሱት ግልጽ ነው። አገራችን ለዚህ ፈታኝ ችግር ውስጥ እንድተዘፈቅ የአንበሣውን ድርሻ የተጫወጡት ደግሞ፣ በድርጅት፣ ጀብሃ፣ ሻዕቢያ፣ ሕወሓት፣ ኦነግ መኢሶን፣ ወዛደር-ሊግ፣ ኢጭአት እና አብዮታዊ ሰደድ ወዘተ እነደሆኑ በግልጽ ይታወቃል። በግለሰብ ደረጃ የነዚህ ድርጅቶች መሪዎች የነበሩና ያሉ መሆናቸው ማንም ይስተዋል የሚባል አይደለም።

ዛሬ በአገራችንና በሕዝባችን ላይ ለተጋረጠው ከፍተኛ የመበታተን አደጋ በወሳኝነት ሚና ተግቶ እየሠራ ያለው ወያኔ (ሕወሓት) መሆኑን ማናችንም የምንገነዘበው ጉዳይ ነው። የዚህ ድርጅት መሥራችና አመራር ሆኖ ለረጅም ዘመናት የመራው አረጋዊ በርሀ እንደሆነ ይታወቃል። ይህ ሰው «ዐማራው የትግሬ አውራ ጠላት ነው፤ ዐማራ ካልጠፋ የትግራይ ሕዝብ ማኅበራዊ ሰላም አያገኝም»፤ የታላቋን ትግራይ ረፐብሊክ የመመሥረት ዓላማን ያራመደ እና ከጎንደር የተወሰዱትን አምስት ወረዳዎችና ከወሎ የተወሰደውን አንድ አውራጃ በካርታ አካሎ ለተፈጻሚነቱ ብዙ የሠራ መሆኑ ይታወቃል። ይህን ዓላማ ዛሬም በራሱ ፍጡራን በመለስና ስየ ተገፍትሮ ከድርጅቱ ከተባረረም በኋላም፣ ወልቃይት፣ ጠገዴ፣ ጠለምት፣ ራያና ቆቦ የታላቋ ትግራይ አካላት ሆነው መቀጠል አለባቸው ብሎ ከልቡ የሚምን ነው። ወያኔ በዐማራ ላይ የወሰደው የዘር ማጥፋትና የዘር ማጽዳት ተግባር ተገቢ ነው ብሎ የሚያምን ነው። ወያኔ ለመሬት ቅርምትና ዐማራውን ለማፈናቀል እንዲያመቸው የተከተለውን የስም ፌደራሊዝም መቀጠል እንዳለበት የሚይምን ነው።

ለጽሑፌ መንደርደሪያነት ከዚህ በላይ ያሰፈርኩትን እንድል የገፋፋኝ እኤአ 9/21/2017 አረጋዊ በርሀ «ትውልድ ፈታኝ ቀውጥ» በሚል ርዕስ በኢትዮ-ሜዲያ ድረ-ገጽ ላይ የተሰራጨው ጽሑፍ ነው። የጽሑፉ አንኳር ጭብጥ ኢትዮጵያ የመበታተን አደጋ የተጋረጠባት ስለሆነ፣ ትውልዱ አገር አድን የሆነ የአንድነት ግንባር በአስቸኳይ እንመሥርት የሚል ነው። አረጋዊ በዚህ ጽሑፉ ያነሳው ሐሳብ ይውደቅ የሚባል አይደለም። የአገሪቱ ችግር ከድጡ ወደ ማጡ የተሸጋገረ ከሆነ ዓመታት ተቆጥረዋል። አገሪቱን ከብተና ለማትረፍም ትውልዱ ያሉትን ልዩነቶች ለጊዜው ወደ ጎን ብሎ፣ የጋራ የሆነችው አገራችን ከመበታተኗ በፊት አንድ ነገር በጋራ እናድርግ ማለቱ ተገቢ ነው። ጥያቄ የሚነሳው ይህን ጥያቄ የሚያቀርቡ ሰዎች ካለፈው ስሕተታቸው ተምረዋል ወይ? ችግሩን የፈጠሩት ግለሰቦችና ድርጅቶች የመፍትሔው አካል መሆን ይችላሉ ወይ? የሚሉት ጥያቄዎች ተገቢና ሁነኛ አሳማኝ መልሶች ማግኘታቸው ላይ ነው። ችግሩን የፈጠሩ ሰዎች የመፍትሔው አካል የሚሆኑበትንና የማይሆኑበትን ድንበር ማስመር ያስቸግራል። በጥቅሉ ችግሮችን የፈጠሩ የመፍትሔ አካላት ሊሆኑ እንደማይችሉ ይታመናል። ሆኖም፣ ማኅበራዊ ሣይንስ ነውና፣ የችግር ፈጣሪዎች የፈጠሩትን ችግር ካመኑ፣ ለዚህም የሕዝቡን አመኔታ ካገኙ፣ ችግሩን እንዴት እንደፈጠሩት በሚገባ ስለሚያውቁ፣ የመፍትሔው አቋራጭ መልስ ሊኖራቸው እንደሚች ይገመታል።
ምክንያቱም፣ የችግሮችን ምንጭ ማወቅ፣ የመፍትሔው ግማሽ አካል ሊሆን እንደሚችል ስለሚታመን። ከዚህ አጠቃላይ ሁኔታ ተነስተን አረጋዊ በርሀ ባለፈው ከተጓዘበትና ከልቡ ከሚያምንበት ያ ትውልድ ከተጓዘበትና አገሪቱንና ትውልዱን ወደ ጥልቅ አዘቅት ከከተተበት የጥፋት ጉዞ የተማረና ስሕተቱን ያመነ ሆኖ አልቀረበም። ባለመቅረቡም የመፍትሔው አካል ሊሆን ይችላል ለማለት የሚያስደፍሩ ማሳያዎች ማቅረብ የሚቻል አይሆንም። ለዚህ አባባሌ ዋቢየ የሚከተለው አባባሉ ነው። «–እስካሁን ድረስም በኢትዮጵያችን የሀገር ሉዓለዊነትና የሕዝቧ መብት የሚያስከብር ሥራዓተ- መንግሥት ተመሥርቶ አያውቅም፤» ይላል። ይህ የአረጋዊ አባባል የታሪክ ዕውቀት ድሕነቱን ከመግለጥ ባሻገር፣ ለተነሳለት ሕዝብን አስተባብሮ የአንድነት ግንባር ለመመሥረት ላሰበው ሀሳብ ቅንጣት ያህል ፍሬ ሊያስገኘው የሚችል አይሆንም። ምክንያቱ መነሻ ሀሳቡ ውሸት ስለሆነ መድረሻውም ውሸት ስለሚሆን ነው።
ማንም እንደሚያውቀው፣ ኢትዮጵያ ጥንታዊና ታሪካዊ ከሚባሉት የሮም፣ የግሪክ፣ የባዛንታይን፣ የባቢሎን፣ የቻይናና የግብፅ መንግሥታት ጋር የሚስተካከል የመንግሥትነት ታሪክ ያላት፣ የዓለም ማኅበረሰብ በደረሰበት የዕድገት ደረጃ አንፃር አቻ የሆነ አገራዊ ሉዓላዊነትና የሕዝብ መብት የሚያስከብር ሥርዓተ-መንግሥት መሥርታ በመንግሥትነት ፀንታ የኖረች ለመሆኗ፣ የአክሱም፣ የሮሐ (ላሊበላ) የጎንደር ሀውልቶች፣ የነገሥታት ዜና መዋዕሎች፣ ውቅር አብያተክርስቲኖች፣ ፍትሐ-ነገሥት በተሰኘ የመንግሥት፣ የሃይማኖትና የሕዝብ ግንኙነት በምን መልክ መከናወን እንዳለበት በሚደነግግ ሕገመንግሥታዊ ሥርዓት ዘርግታ፣ሕዝብ የመራችና ያስተዳደረች፣ ለመንግሥትና ሕዝብ ግንኙነት የምትጠቀምበት ቋንቋ የራሷ ፊደል ያላት መሆን፣ በዘመነ ቅኝ ግዛት ነፃነቷንና አንድነቷን ጠብቃ፣ የጥቁር ዓለም ሕዝብ የነፃነት ቀንዲል መሆኗ፣ ከአንደኛው የዓለም ጦርነት ፍፃሜ በኋላ የተመሠረተው የመንግሥታቱ ማኅበር ብቸኛ አፍሪካዊት አገር ሆና የማኅበሩ አባል መሆኗ፣ ቀጥሎም ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የተመሠረተው የተባበሩት መንግሥታት ማኅበር ሲመሠረት ብቸኛዋ ነፃ አፍሪካዊት አገር ሆና የድርጅቱ አባል መሆኗ፣ ከቅኝ አገዛዝ ነፃ የወጡ የአፍሪካ ሕዝቦች የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን ሲመሠርቱ የድርጅቱ ጽሕፈት ቤት አዲስ አበባ እንዲሆን የተደረገው ኢትዮጵያ ረጅም ዘመን ያስቆጠረ ግዛታዊ አንድነት፣ሉዓላዊነትና የፀና ሥርዓተ-መንግሥት ባለቤት በመሆኗ ነው። ይህን ዓለም በአድናቆት የተቀበለውን ግዙፍ ሀቅ ያልተቀበለ ቡድንና ግለሰብ አሁን አገሪቱ ለገጠማት ችግሮች ሁሉ የአንበሳውን ድርሻ ያበረከቱና እያበረከቱ ያሉ ግለሰቦችና ድርጅቶች የአገሪቱ ችግሮች የመፍትሔ አካላት ይሆናሉ፣ ማለት «ያልወለድኩት ልጅ፣ አባባ ቢለኝ አፌን ዳባ ፋባ አለኝ» ከሚሉት የተለየ አይሆንም። አረጋዊ በርሀ «ያደቆነ ሰይጣን፣ ሳያቀስስ አይለቅም» የሚሉት የአባቶቻችን አባባል ዕውነተኛ መገለጫ መሆኑን በዚህ የአንድነት ግንባር ጥሪው በግልጽ አሳይቷል። እንዲህም ሲል ይነበባል። «የአፄዎቹም ይሁን የደርጎቹ እንዲሁም የኢሕአዴጎቹ መንግሥታዊ ሥራዓቶች በቅርጽ ይለያዩ እንደሆነ እንጂ፣ በይዘት አይራራቁም።» ይለናል።
በመጀመሪያ ኢሕአዴግ የሚባለው ድርጅት አይደለም። ይህ አለመሆኑን ስብሃት ነጋ ደጋግሞ ነግሮናል። እንደድርጅት አባላት አይመለምልም። ድርጅታዊ መዋቅርም የለውም። ኢሕአዴግ፣ ለትግሬ-ወያኔ ዓላማ ማስፈጸሚያ፣ ራሱ ፕሮግራም ጽፎ፣ መተዳደሪያ ደንብ አዘጋጅቶ፣ መልምሎና አደራጅቶ ያሰለፋቸው የዐማራው ፣ የኦሮሞውና የደቡቡ አማርኛ፣ ኦሮሞኛ እና የደቡብ ነገዶች ቋንቋ አስተርጓሚዎች መሆናቸውን ሕዝባችን ጠንቅቆ ያውቃል። ይህን አረጋዊ አያውቅም ለማለት ያስቸግራል። አረጋዊ ማወዳደር ካለበት ውድድሩ መሆን ያለበት ዕውነተኛው የሥልጣን ባለቤት ከሆነው የትግሬ-ወያኔ(ሕወሓት) ጋር መሆን ነበረበት። ይህ እንዲሆን ግን አረጋዊ አልፈለገም። ይህም በራሱ ሸፍጥ ነው። በሸፍጥ ደግሞ የኢትዮጵያ ችግር አይፈታም። ሌላው የዐፄዎቹና የደርጎቹ መንግሥታዊ ሥርዓቶች ከወያኔው ጋር በቅርጽ ይለያዩ እንደሆነ እንጂ፣ በይዘት አይራራቁም ሲል ያሰፈረው ሀሳብ ግራ የሚያጋባ መሆኑ ነው። ሀሳቡ ግራ የሚያጋባው የሦስቱንም መንግሥታዊ ሥርዓቶች የሚመሳሰሉበትንና የሚለያዩበትን ጠንቅቆ ካለማወቅ፣ ወይም ሆን ብሎ የራስን ድብቅ ዓላማ ለማራመድ ከመፈለግ በሚመነጩ ምክንያቶች የተሰነዘረ እና ከየትኛው አቅጣጫ እንደመጣ መለየት አለመቻሉ ነው።
አረጋዊ ከትኛውም አቅጣጫ ይነሳ፣ የሦስቱን መንግሥታት፣ መንግሥታዊ ሥርዓቶች በቅርጽም ሆነ በይዘት መመሳሰላቸውንም ሆነ መቃረናቸውን ለማወቅ፣ የመንግሥታቱን አደረጃጀት፣ የሥልጣን ምንጩ ምን እንደሆነ፣ የሚመሩበት ርዕዮተ-ዓለም ምን እንደሆነ፣ በአገሪቱ አንድነትና ታሪክ ያላቸው አቋም፤ አገዛዛቸው በምልዐተሕዝቡ ያላቸው ተቀባይነት፣ የአገዛዛቸው ሕጋዊነት (ለሕግ የሰጡት ቦታ) የመሳሰሉትን መስፈርቶች በማስቀመጥ የምናገኘው ውጤት የመንግሥታቱን በቅርጽም ሆነ በይዘት መራራቅም ሆነ መቀራራብ ለምንደርስበት ድምዳሜ ተገቢ የሆነ መስፈሪያ እንደሚሆን ይታመናል። ከዚህ አንፃር የቀዳማዊ ኃይለሥላሴን መንግሥት እንደማሳያ ወስደን ከደርግና ከትግሬ-ወያኔ አገዛዞች ጋር ብናነፃጽር የምናገኘው ሥዕል አረጋዊ ከነገረን በብዙ መልኩ በስፋት እንደሚለይ ግልጽ ነው። የንጉሡ መንግሥት፣ ሕገመንግሥታዊ ንጉሣዊ አገዛዝ የሆነ፤ የመስተዳድሩ አደረጃጀት አሀዳዊ የሆነ፣ የሥልጣን ምንጩ ዋና ቋጠሮው ንጉሠ-ነገሥቱ የሆኑበት፣ ሕግ የማውጣት ሥልጣን ያለው በሕዝብ በቀጥታ የሚመረጡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት(ፓርላማ) እና በንጉሡ የሚመረጡ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ያሉት ባለሁለት ክፍሎች ሕግ አውጪ አካል የነበረበት፣ ሕግ አስተራጓሚው አካል (ፍርድ ቤቶች፣ አቃቢ ሕጎች፣ ፖሊስና ወህኒ ቤቶች) ራሳቸውን ችለው የተደራጁበት፣ አስፈጻሚ አካሉ በንጉሡ የበላይነት የሚመራ ጠቅላ ሚኒስትራና የካቢኔ ሚኒስትሮች ያሉት፣ በኢትዮጵያ ረጅም ታሪክ ባለቤትነት በጽኑ የሚያምን፣የንጉሡ ሥልጣን ለረጅም ዘመን ከአገሪቱና ከመንግሥትነቱ ታሪክ ጋር በጥብቅ የተቆራኘ በመሆኑ፣ የአንድነትና የሥልጣን ምንጭ ሆኖ የሚቆጠርና ሕጋዊነቱ ጥያቄ ውስጥ የማይገባ፣ለዕድገትና ልማት ሲባል በርዕዮተ-ዓለም ደረጃ ያንዱ ወገን ያልሆነ፣ በገለልተኝነት መርሕ የሚመራ ወደ ነፃ ገበያ ኢኮኖሚ ያዘነበል እንደነበር ይታወቃል። የደርጎቹ መንግሥት አደረጀጀቱ አሀዳዊ የመንግሥት አደረጃጀትን የተከተለ ነበር። ደርግ በአገሪቱ አንድነትና ረጅም ታሪክ ውስጥ የጠጠረ አቋም የነበረው እንደሆነ ወዳጅም ጠላት ያረጋገጠው ነው። ሆኖም ደርግ በሕግ የበላይ የሚመራ አልነበረም። ይመራ የነበረው በተለያዩ አዋጆች ስለነበር ሕግና ሕጋዊነት ቦታ አልነበራቸውም። የአገዛዙ ሕጋዊነትም በሕዝባዊ እንቢተኝነት በታገዘ አመጽ ለሥልጣን የበቃ በመሆኑ፣ በተለያየ ደረጃ በተደራጁ ፖለቲካ ድርጅቶች ዕውቅና የተሰጠው አልነበረም። የሚከተለው ርዕዮተ-ዓለም የግራ ዘመም የሆነው የማርክሲስት-ሌኒኒስት ርዕዮተ-ዓለም እንደነበር ይታወቃል። ይህም ከንጉሡ አገዛዝ ጋር የቅርጽም የይዘትም ልዩነት ያላቸው መሆኑ ጥርጣሬ ውስጥ የሚከት አይደለም። የአብዮቱ ዋና መፈክር ሥር ነቀል ለውጥ ማምጣት ስለነበር የቅርጽና የይዘት መመሳሰልን የሚያስከትል አልነበረም።
በአንፃሩ የትግሬ -ወያኔው አገዛዝ ከሁለቱም መንግሥቶች፣ መንግሥታዊ ሥርዓት በፍጹም ተፃራሪ ሆኖ የቆመ ነው። የመንግሥት አደረጃጀቱ ለመሬት ቅርምትና ዐማራን ነጥሎ የዘር ማጥፋትና የዘር ማጽዳት ተግባር ለመፈጸም በሚያስችለው መልኩ ነገድን መሠረት ያደረገ ስም ብቻ የሆነ ፌደራሊዝም ነው። የኢትዮጵያን የረጅም ዘመን ታሪክ በመካድ በመቶ ዓመት የደገበ ነው። የኢትዮጵያ ሕዝብ አንድነት ኖሮት እንደማያውቅና በዐማራ ተገዶ የተያዘ ነው፣ ስለሆነም ማነኛው ነገድ ከፋኝ፣ አብሬ መኖር አልችልም ብሎ ባሰበና በተመኘ ቁጥር መገንጠል እንዲችል ዕውቅና የሰጠ ሕገመንግሥት ያዘጋጀ ነው።
የትግሬ ወያኔ ሕዝባዊ ተቀባይነት የሌለው የሽፍታ ቡድን ነው። በሕግ የበላይነት የማያምን፣ በአንፃሩ የሕግና ሕጋዊነት ጠላት ሆኖ የቆመ የወንበዴዎች ስብስብ በመሆኑ፣ ሕዝባችን በመንግሥትነት ተተቀበለው አይደለም። የሚመራበት ርዕዮት የጀርመኑ ሒትለር እና የደቡብ አፍሪካዊ አፓርታይድ አገዛዞች መመሪያ የሆነው ዘረኝነት ነው። ይህም በመሆኑ ከሁለቱ መንግሥታት ጋር የቅርጽም ሆነ የይዘት ተመሳሳይነት የለውም። የትግሬ -ወያኔ በቅርጽም ሆነ በይዘት የሚመሳሳለው የፋሽስቱ ሞሶሎኒ አገዛዝ ነው። እና አረጋዊ «ሊበሏት ያሰቧትን አሞራ፣ ጅግራናት ይሏታል» እንዲሉ፣ ካልሆነ በቀር ያቀረበልን ንጽጽር አራምባና ቆቦ በመሆኑ ላቀረበው ትልቅ አጀንዳ ማስፈጸሚያ ሊያገለግል የሚችል አይደለም።
ይህ ኢትዮጵያን የመታደግ አጀንዳ ትልቅ አስተሳሰብ፣ ሠፊ ራዕይ ያላቸውን ሰዎች ተነሳሽነት የሚጠይቅ እንጂ፣ ኢትዮጵያን ከዚህ ባደረሱ እንደ አረጋዊ ባሉና ስህተታቸውንም በግልጽ ባላመኑና ባለፈው የያዙትን አጀንዳ ወደፊት በሚገፉ ሰዎች እንዲቀነቀን ልንፈቅድ አይገባም።
አረጋዊ ፀረ-ዐማራ ሆኖ የተወለደውን ያሕል፣ ዛሬም ከ60 በላይ በሆነ ዕድሜው ላይ ሆኖ፣ ባለፈው የሠራቸውን ስሕተቶች ለማረምና ለማስተካከል ፍላጎት ያለው ሆኖ ያላሰው በዚህ ጽሑፉ እንዲህ ሲል ያሰፈረው ያሳብቅበታል። «–ቀደም ሲል በአኙዋክና በኑዌር ጋምቤላዎች ላይ፣ አሁን ደግሞ በኦሮሞና በሶማሌ ዜጎቻችን መካከል የተካሄደውና እየተካሄደ ያለው እልቂት ከብዙ በጥቂቱ እንደአብነት መጥቀስ ይቻላል።» ሲል በራሱ አመራር ሰጭነት ከወልቃይት፣ ጠገዴ፣ ጠለምት፣ ራያና አዘቦ፣ ራናቆቦ ያለቁትን ዐማሮች ማስታወስ አልፈለገም።
በእርሱ እግር የተተኩት መለስ ዜናዊ፣ ዐባይ ፀሐየ፣ ሣሞራ የኑስ፣ አርበከበ ዕቁባይ፣ ስብሓብ ነጋ፣ገብሩ አሥራት፣ ዐባይ ወልዱ ወዘተ አመራር በደቡብ ጎንደር፣በጊንቢና በቄለም፣ ምሥራቅ ወለጋ፣በጃዊ የተፈናቃዮች ጣቢያ፣ በሐረርጌ ጋራ ሙለታ፣ወተር፣ በደኖ፣ ድሬዳዋ፣ ሀብሩ፣ አሰቦት ገዳም፣አርባጉጉ፣ ምዕራብ አርሲ፣ በጅማ ዞን፣ በአጋሮ፣ በሸቤ፣ በቤንች ማጂዞን፣ ጉራፈርዳ፣ በምራብ ሸዋ፣በቤንሻንጉል ጉምዝ፣ በመተከል፣በዐባይ ነጌሶ ቀበሌ ወዘት በግፍ የተፈጁትና ሀብት ንብረታቸውን ተነጥቀው የተባረሩት ዐማሮች በአረጋዊ ዕይታ የግፍ ማሳያ ሆነው ለመቆጠር ሚዛን የማይደፉ ናቸው። አረጋዊ የዐማራውን ፍጅትና መፈናቀል እንደማሳያ ለመጥቀስ ያልፈለገበት ዋናው ምክንያት ፀረ-ዐማራ ባሕሪው አሁንም ከአዕምሮው ያልወጣ በመሆኑ ነው። ይህንም ሆን ብሎ ያደረገው መሆኑ ማሳያው ባቀረበው ሠንጠረዥ ዐማራ የለም። ከሁሉም በላይ ዐማራውን እና ለዐማራው ድምፅ ሆነው የሚጮሁትን ግለሰቦችና ድርጅቶች በማንአህሎኝነት ይከሳቸዋል።
ወደድንም ጠላንም ከእንግዲህ ለዐማራው እንዳለፉት ሁሉ የተለያዩ ስሞች እየለጠፉ እርሱን ለማጥቃትና ከኢትዮጵያ ፖለቲካ ዕምብርት የመግፋት ሙከራዎች ለመላላጥ ካልሆነ ለአገሪቱ ችግር መፍትሔ ይሆናል አይባልምና ለአንድነት ቆመናል የሚሉ ወገኖች የዐማራውን ጉዳይ ጉዳያችን ብለው ካልያዙ እንቅስቃሴአቸው ጋት ያህል ወደፊት ሊራመድ የማይችል መሆኑን ሊያውቁት ይገባል።

 

Filed in: Amharic