>

«የብሔርተኝነት» እሳቤው ወያኔ አምሶ ከቆላው የሚተርፈውን ማሳረር ነው (አቻምየለህ ታምሩ)

ካለፉት ጥቂት ሳምንታት ጀምሮ እስካሁንም ድረስ እንደቀጠለ ያለው የምስራቅ ኢትዮጵያ «ችግር» ወያኔ የፈጠረው እንጂ በቋንቋ ላይ የተመሰረተው «የብሔር ፌድራሊዝም» የወለደው እንዳልሆነ ለማሳየት በጎሳ ብሔርተኞች ዘንድ ያልተፈነቀለ ድንጋይና ያልተማሰ ጉድጓድ የለም። ሶማሌና ኦሮሞ ባህልና ቋንቋ እንደሚጋራ፤ የረጅም ዘመን ጉርብትና እንዳላቸው፤ እንደተጋቡና እንደተዋለዱ፤ ወዘተ እየተጠቀሰ የተፈጠረው ግጭት የወያኔና ያብዲ ኢሌ ስሪት እንጂ «የብሔር ፌድራሊዝሙ» የወለደው የጎሳ ግጭት እንዳልሆነ ብሔርተኛ ተንታኞች ሲነግሩን ሰንብተዋል።

የሶማሌና የኦሮሞን ግንኙነት በመዘርዘር በሁለቱ መካከል የጎሳ ግጭት እንዳልተፈጠረ፤ ሶማሌና ኦሮሞ ወንድማማቾች እንደሆኑ ሲነግሩን የሰነበቱት ብሔርተኛ ፖለቲከኞቻችን፤ ኦሮሞ ከአማራ ጋር ስላለው ግንኙነት ሲነሳ ግን አንድም አፍ የላቸውም፤ ካላቸውም እጅጉን አሉታዊ ነው።

እንደ እውነቱ ከሆነ ኦሮሞ ከአማራ ጋር የሚጋራውን ያህል ቋንቋ ከሶማሌም ሆነ ከሌላ ከማንም ጋር አይጋራም። በአስር ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ኦሮሞዎች አማርኛን በተደራቢ ቋንቋነት ይናገራሉ። በአስር ሚሊዮን የሚቆጠሩ ኦሮሞዎች ሶማሊኛን አይናገሩም። ኦሮምኛ ከሚናገሩ ሶማሌዎች የሚበልጥ ቁጥር ያላቸው አማሮች ደግሞ ኦሮምኛን በተደራቢነት ይናገራሉ። ኦሮሞ ከአማራ ጋር የተጋባውን ያህል ከሶማሌ ጋር አልተጋባም። በአስር ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት ከአማራና ከኦሮሞ የተወለዱ ልጆች ናቸው። በአስር ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ከኦሮሞና ከሶማሌ የተወለዱ ልጆች የሉም። ብሔርተኞቹ ግን ስለዚህ አገር አድን እውነት አያወሩም። እንዴውም የሚያወሩት አማራና ኦሮሞ የጋራ ታሪክና ባህል እንደሌላቸው ነው።

ባጭሩ የጎሳ ግጭቱ የርዕዮተ ዓለም ጉዳይ ሳይሆን የመጋባት፣ የመዋለድ፣ የመዛመድና የጋራ ቋንቋ የመናገር ጉዳይ ቢሆን ኖሮ የኦሮምያና የሶማሌ ክልሎች «የድንበር ግጭት» በሚል የተሸፈነውን ነገር «የብሔር ፌድራሊዝሙ» ውጤት እንዳልሆነ ለማሳየት ከሁሉ አስቀድሞ ላይ ታች ሲሉ ከሰነበቱት ብሔርተኞች መካከል ቀዳሚ የሆነው ጸጋዬ አራርሳ የተወለዳቸውን የእናቱን ወገኖች እያሰየጠነ ያልተዋለዳቸውን ፍለጋ አይኳትንም ነበር። ሁቱና ቱትሲም አንድ ቋንቋ እየተናገሩ አይጫረሱም ነበር። የዐፄ ዮሐንስ ልጆች ወያኔና ሻዕብያም አይዳሙም ነበር።

በአጭር ጊዜ ውስጥ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ግፉዓን በቋንቋቸው አማካኝነት አገር ሰላም ብለው ይኖሩበት ከነበረው የአገራቸው ክፍል ከተፈናቀሉ ይህ ተራ የሳርና የግጦሽ ግጭት ሊሆን አይችልም። ብሔርተኛ ተንታኞች በብሔር ላይ የተመሰረተውን ፌድራሊዝም ማርና ወተት አድርገው በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ኦሮሞዎች ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉበትን ክስተት ግን የወያኔ ሴራ አድርገው ያቀርቡታል። አስቂኙ ነገር በዚህ አባባላቸው በራሱ መፈናቀሉን ያመጣው የብሔር ፌድራሊዝሙ እንደሆነ እያስረገጡልን እንደሆነ አለመገንዘባቸው ነው።

ወያኔን የፈጠረው ዛሬ «ገዢ» የሆነው «የብሔርተኝነት» እሳቤ ነው። ይህ «በብሔርተኝነት» ላይ የተመሰረተ አስተሳሰብ ዛሬ በስራ ላይ የዋለውን በቋንቋ ላይ የተመሰረተ ፌድራሊዝም ወለደ። እያየነው እንዳለው ዛሬ ያለውን የቋንቋ ፌድራሊዝም ተጠቅሞ ወያኔ በፈለገው ጊዜ ግጭት እያስነሳ ሕዝብ እንዲጫረስ እያደረገ ነው። የቋንቋ ፌድራሊዝሙ ችግር መሆኑን ለመገንዘብ የግድ እያንዳንዱ የሶማሌ ተወላጅ ተነስቶ ኦሮሞን ማባረር የለበትም። ማንም ያንቀሳቀው ማን አንድ አካል አስተሳሰቡን ተጠቅሞ ግጭቱ ማስነሳት ከቻለ ችግሩ ያለው ከሰዎቹ [ከወያኔዎች] ሳይሆን እነሱን [ወያኔዎችን] ከወለደው አስተሳሰብ ነው ማለት ነው። መገንዘብ ለቻለ ዛሬ አገራችን ላይ የተፈጠረው ችግር ይህ የወያኔና የግራ ኃይሎች አስተሳሰብ የወለደው ነው።

እንግዲህ! ማርና ወተት ተደርጎ እየተሽሞነሞነ ሲቀርብ የምንሰማው የወያኔ እሳቤ በቀናት ልዩነት መቶ ሺዎችን ቤት አልባ አድርጎ ሜዳ ላይ እንዲወድቁ ያስቻለውን አስተሳሰብ ነው። በዋናው አፈናቃይ ወያኔና የወያኔ እያፈናቀለበት ያለውን ፌድራሊዝም ፍቱንነት ካልተነተንን ሞተን እንገኛለን በሚሉን ብሔርተኛ ተንታኞች መካከል አንዳች ልዩነት የለም። የነገ ተስፈኞች የቆሙለት አላማ ዛሬ የምንሳደብደብት የወያኔ አስተሳሰብ ነው። ዛሬ ላይ ሆነው የወያኔን አስተሳሰብ በአንቀልባ አዝለው የተስፋይቱን ምድር አንቧቀው የሚያዩት ወያኔ አምሶ ከቆላው የሚተርፈውን እስከቻሉት ያህል ለማሳረር ነው።

Filed in: Amharic