>

ኢትዮጲያ: በግራ መጋባት ወደ እርስ-በእርስ ግጭት! (ስዩም ተሾመ)

አሁን ባለው የኢትዮጲያ ፖለቲካዊ ሁኔታ ላይ ከፍተኛ ግራ-መጋባት ይታየኛል። ግራ መጋባቱ በዋናነት “ሀገሪቱ ወደየት እያመራች ነው?” በሚለው ጥያቄ ላይ የተመሰረተ ነው። ይህ ግራ መጋባት ታዲያ በአንዱ ወይም በሌላኛው ወገን ላይ ሳይሆን በሁሉም ወገኖች ላይ የሚስተዋል ነው። የገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ ከፍተኛ አመራሮች እና ደጋፊዎች፣ በብሔርተኝነት እና በአንድነት ጎራ በተሰለፉት ተቃዋሚ የፖለቲካ መሪዎችና ደጋፊዎች ላይ በግልፅ ይስተዋላል። በዚህ ፅሁፍ ከሦስቱም ጎራዎች አንዳንድ ምሳሌዎች በመጥቀስ ግራ መጋባቱን ለማሳየት እንሞክራለን። ከዚያ በቀጠል ደግሞ “ሀገራችን ወደየት እያመራች ነው?” የሚለውን ጥያቄ ከሌሎች ሀገራት ታሪክና ፖለቲካዊ ክስተት ጋር በማያያዝ ምላሽ ለመስጠት እንሞክራለን።

የመጀመሪያው ግራ መጋባት የህወሓት/ኢህአዴግ መስራች እና ከፍተኛ አመራር የሆኑት አቶ አባይ ፀሐዬ በኢትዮጲያ ፌደራሊዝም ስርዓትን አስመልክቶ የሰጡት አስተያየት ነው። እንደ እሳቸው አገላለፅ፣ በዩጎዝላቪያ (Yugoslavia) የነበረው የፌደራሊዝም ስርዓት የወደቀው በአንድ ብሔር (the Serbs) የበላይነት ላይ የተመሰረተና ሌሎችን ብሔሮች ያገለለ በመሆኑ ነው። ከዚህ በተጨማሪ፣ የሶቭዬት ፌዴሬሽን (Soviet federation) የተበታተነው ደግሞ በስርዓቱ ጨቋኝነት እና በዴሞክራሲ እጦት እንደሆነ ገልፀዋል።

“አዎ…የህወሓት/ትግራይ የበላይነት አለ’ በሚል ርዕስ ባወጣሁት ፅሁፍ በዝርዝር ለማብራራት እንደሞከርኩት አሁን ባለው ፖለቲካዊ ስርዓት ላይ የህወሓት/ትግራይ የበላይነት በግልፅ የሚታይ ሃቅ ነው። በሌላ በኩል፣ የኢህአዴግ መንግስት በተለያዩ የሀገሪቱ አከባቢዎች ከሕዝብ ለሚነሱ የነፃነት፥ እኩልነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጥያቄዎች ተገቢውን ምላሽ ከመስጠት ይልቅ በኃይል ለማፈን ጥረት እያደረገ ነው። በዚህ ምክንያት፣ የኢህአዴግ መንግስት ከቀን ወደ ቀን ይበልጥ ጨቋኝና አምባገነን እየሆነ መጥቷል። ነገር ግን፣ የመንግስታዊ ስርዓቱ መስራችና ከፍተኛ አመራር የሆኑት አቶ አባይ ፀሐዬ “ዩጎዝላቪያና ሶቬት ሕብረት የፈረሱት አሁን የኢህአዴግ መንግስት እየፈፀመ ያለውን ስህተት በመፈፀማቸው ነው” ማለታቸው በኢህአዴግ ውስጥ ያለውን ግራ መጋባት ያሳያል።

ከላይ በተጠቀሰው የአቶ አባይ ፀሐዬ አስተያየት ግራ የተጋባው አንድ የኦሮሞ ብሔርተኛ ወዳጄ “ይሄ ነገር ‘ኣላዋቂነት’ ወይስ ‘ንቀት’ ነው?” በማለት ጠየቀኝ። በእርግጥ እንደ አባይ ፀሐዬ ያሉ አንጋፋ ፖለቲከኞች “አላዋቂ ናቸው” እንዳይባል ሀገሪቱ የምትመራበትን ፖለቲካዊ ስርዓት መዘርጋት የቻሉ ናቸው። አይ…ነገረ ስራቸው ሁሉ “ንቀት ነው” እንዳይባል ደግሞ በንቀት ራሳቸውን ለውድቀት አይዳርጉም። ምክንያቱም፣ የዩጎዝላቪያና ሶቬት ህብረት የወደቁበትን መሰረታዊ ምክንያት እያወሱ ተመሳሳይ ስህተት ይፈፅማሉ ብሎ ማሰብ ይከብዳል።

ሦስተኛውን ግራ መጋባት የታዘብኩት ደግሞ የአንድነት አቀንቃኝ በሆነው ወዳጄ ላይ ነው። ከዚህ ጓደኛዬ ጋር ከረጅም አመታት በኋላ ታክሲ ውስጥ ተገናኘንና እንዲህ ሲል ጠየቀኝ፡- “የኢህአዴግ መንግስት አሁን ካለንበት የፖለቲካ ቀውስ ላይ ያደረሰን አውቆና አቅዶ ነው ወይስ ሳያውቅ በስህተት ነው?” በእርግጥ አውቆና አቅዶ ሀገሪቱን አሁን ካለችበት ደረጃ ላይ ማድረስ በጣም ከፍተኛ የሆነ የፖለቲካ ዕዉቀት ይጠይቃል። ነገር ግን፣ ሀገርና ሕዝብን ለፖለቲካ ቀውስና ውድቀት የሚዳርግ አሻጥር ክፋት እንጂ ዕውቀት ሊባል አይችልም። በሌላ በኩል ደግሞ “ሳያውቁ በስህተት የፈፀሙት ነው” እንዳይባል ደግሞ ስህተታቸውን የነገሯቸውን የተቃዋሚ ፖለቲካ መሪዎች፣ ጋዜጠኞች፣ ጦማሪያን፣ የመብት ተሟጋቾች፣ …ወዘተ ለእስርና ስደት ዳርገዋቸዋል።

በግራ መጋባት ወደ እርስ-በእርስ ዕልቂት!

በአጠቃላይ፣ የኢህአዴግ መሪዎች “አያውቁም” እንዳይባል ሀገርና ሕዝብ ይመራሉ፣ “ያውቃሉ” እንዳይባል ደግሞ ራሳቸውን ለውድቀት የሚዳርግ ስህተት ይሰራሉ። በዚህ ምክንያት፣ የእርስ-በእርስ ግጭትና የመበታተን አደጋ ሀገሪቱና ሕዝቡ ላይ ተጋርጧል። ይሄንን ግራ-መጋባት ለመፍታት የኢህአዴግ መንግስት ከፍተኛ አመራሮችን ሃሳብ፣ ተግባራትና ስራዎችን እንደ ማሳያ እያነሱ መከራከር ይቻላል። ይህ ግን ከአንድ መቋጫ ላይ አንደርስም። ስለዚህ፣ ከሃሳብ ይልቅ አመለካከትን፣ ከተግባር ይልቅ መዋቅርን፣ ከሥራ ይልቅ አሰራርን፣… በአጠቃላይ ከፖለቲካዊ ስርዓቱ ይዘት (content) ይልቅ ቅርፁን (form) መመልከት ያስፈልጋል።

የኢህአዴግ መንግስት መስራቾችና ከፍተኛ አመራሮች፣ እንዲሁም ቀንደኛ ደጋፊዎች ሁሉንም ነገር የሚመለከቱት በብሔር ምንፅር ነው። ድጋፍና ተቃውሞ በብሔር ነው። ሥራቸውን የሚሰሩት በብሔር ነው። ሁሉም ሰው የሚሰራው በብሔር ይመስላቸዋል። ለምሳሌ፣ በኢትዮጲያ የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ፕረዜዳንቶች በሙሉ የአከባቢው ብሔር ተወላጆች ናቸው። ለዚህ ምክንያቱ “የአከባቢው ተወላጅ የሆነ ሰው ለአካባቢው ማህብረሰብ ተገቢ የሆነ የማህብረሰብ አገልግሎት ይሰጣል” የሚል ነው። ስለዚህ የአንድ ዩኒቨርሲቲ ፕረዜዳንት በትምህርት የቀሰመው በዓለም-አቀፋዊ እውነታ ላይ የተመሰረተ ዕውቀትና ክህሎት ከተወለደበት ማህብረሰብ ውጪ ፋይዳ-ቢስ ነው። አሁን በሀገራችን ያለው መንግስታዊ ስርዓት ዕውቀትና ክህሎትን ሳይቀር የሚመለከተው ከብሔር አንፃር ነው።

የኢህአዴግ መንግስት ከፍተኛ አመራሮችና ደጋፊዎች ሃሳብና አመለካከታቸው ሙሉ በሙሉ በብሔር ላይ የተመሰረተ ነው። እ.አ.አ. ከ1945 – 1980 ዓ.ም ዩጎዝላቪያን የመሩት “Tito” (Josip Broz) ለረጅም አመታት የሀገሪቱን የመሩት በሀገራዊ አንድነትና የወደፊት አብሮነት መርህ ነበር። የቀድሞ ጠ/ሚኒስትር መለስ ዜናዊን ጨምሮ አብዛኞቹ የህወሓት/ኢህአዴግ አመራሮች ሀገሪቷን እየመሩ ያሉት በብሔርተኝነትና የታሪክ ቁርሾን በመቆስቆስ ነው። ለምሳሌ፣ “Tito” በዩጎዝላቪያ ”Serbs” እና “Croats” ሕዝቦች መካከል በቀድሞ ዘመን በተካሄደው የእርስ-በእርስ ጦርነት አማካኝነት የተፈጠረውን ቂምና ጥላቻ በማስወገድ የእርቅ መንፈስ ለማስፈን ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል።

በተቃራኒው፣ የኢህአዴግ መንግስት ላለፈው ሩብ ክ/ዘመን በተለይ በአማራና ኦሮሞ ሕዝቦች መካከል ያለውን የታሪክ ልዩነትና ቁርሾ በመቆስቆስ ቂምና ጥላቻ ለማስፋፋት ጥረት አድርጓል። ቀደም ሲል ለመግለፅ እንደተሞከረው፣ የምሁራን ዕውቀትና አገልግሎት በብሔርና ቋንቋ የሚከፋፍል የፖለቲካ ቡድን ለስርዓቱ ስጋት የሆነ የብሔሮች ጥምረት ሲፈጠር የእርስ-በእርስ ግጭት እንደሚፈጥር ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ እንዲህ ያለ መንግስት አምሳያው ያለው ምስራቅ አውሮፓ ሳይሆን ደቡብ አፍሪካ ነው።

የሰቆቃ ልጆች እና የብሔር አፓርታይድ በሚሉ ተከታታይ ፅሁፎች በዝርዝር ለመግለፅ እንደሞከርኩት አሁን በሀገራችን ያለው መንግስታዊ ስርዓት እ.አ.አ. ከ1948 – 1994 ዓ.ም ድረስ በደቡብ አፍሪካ ከነበረው የአፓርታይድ ስርዓት ጋር ከአመሰራረቱ እስከ ውድቀቱ ድረስ ፍፁም ተመሳሳይ ነው። ብዙዎች በደቡብ አፍሪካ የነበረው የአፓርታይድ ስርዓት በዘር ላይ የተመሰረተ እንደሆነ ያስባሉ። ነገር ግን፣ ለአፓርታይድ ስርዓት መመስረት ዋና ምክንያቱ ዘረኝነት አይደለም። የአፓርታይድ መነሻ ምክንያቱ እ.አ.አ. ከ1899 – 1902 ዓ.ም በደቡብ አፍሪካ ነጭ ሰፋሪዎች እና በእንግሊዞች መካከል የተካሄደው ¨The Second Boers War” ነው። ይህ ጦርነት በነጮች መካከል የተካሄደ ጦርነት እንጂ በጥቁሮችና ነጮች መካከል የተካሄደ አልነበረም።

የአፓርታይድ ስርዓት የደቡብ አፍሪካን ሕዝብ በዘር ሀረግና በቆዳ ቀለም ነጮች፥ ጥቁሮች፥ ሕንዶችና ቅይጦች (colored) በማለት ለአራት ይከፍላቸዋል። ሆኖም ግን፣ የፀረ-አፓርታይድ ትግሉ ሲካሄድ የነበረው በዋናነት በጥቁሮችና በነጮች መካከል ነው። የአፓርታይድ ስርዓት መሰረታዊ ዓላማ ከሀገሪቱ ሕዝብ ውስጥ አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ነጮችን የፖለቲካ የበላይነት ማረጋገጥ ነው። ለዚህ ደግሞ በሀገሪቱ 70% የሚሆኑትን ጥቁሮች በጎሳና ብሔር መከፋፈል አለበት።

በዚህ መሰረት፣ የአፓርታይድ ስርዓት የደቡብ አፍሪካ ጥቁር ሕዝብን በጎሳና ብሔር ለአስር ክልሎች ከፋፍሏቸዋል። እያንዳንዱ ክልል ራሱን በራሱ የማስተዳደር ስልጣን አለው። ነገር ግን፣ የአንዱ ክልል ነዋሪ በሌላኛው ክልል ጉዳይ ጣልቃ እንዳይገቡ በሕግ የተከለከለ ነበር። ይህ የደቡብ አፍሪካ ጥቁሮች በሀገራዊ ጉዳይ ላይ የጋራ አጀንዳና የተቀናጀ እንቅስቃሴ እንዳይኖራቸው የታለመ ነው።

የአፓርታይድ ስርዓት የአነስተኛ ብሔርን የስልጣን የበላይነት ለማረጋገጥ አብላጫ ድምፅ ያላቸውን ሕዝቦች በጎሳና ብሔር በመከፋፈል ላይ የተመሰረተ ስርዓት ነው። አሁን በኢትዮጲያ ያለው ፖለቲካዊ ስርዓት በደቡብ አፍሪካ ከነበረው ጋር ፍፁም ተመሳሳይ ነው። የህወሓት/ትግራይ የበላይነትን ለማስቀጠል በሀገሪቱ አብላጫ ድምፅ ያላቸውን በተለይ የአማራና ኦሮሞ ሕዝቦች በመለያየት ላይ የተመሰረተ ነው።

ከዚህ በተጨማሪ፣ እ.አ.አ. ከ1984 ዓ.ም ጀምሮ የደቡብ አፍሪካ ጥቁሮች በመካከላቸው ያለውን ልዩነት ወደጎን በመተው የመብትና ነፃነት ጥያቄያቸውን በጋራ መጠየቅ ሲጀምሩ የአፓርታይድ መንግስት የወሰደው እርምጃ አሁን በሀገራችን ለሚስተዋለው የፖለቲካ ቀውስና አለመረጋጋት መንስዔን፣ እንዲሁም በሁለቱ ስርዓቶች መካከል ያለውን ተመሳሳይነት በግልፅ ይጠቁማል።

እ.አ.አ. በ1984 ዓ.ም በደቡብ አፍሪካ ከፍተኛ አመፅና ተቃውሞ ተቀሰቀሰ። ልክ ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ በተለያዩ የሀገራችን አከባቢዎች እንደታየው እ.አ.አ. በ1984 ዓ.ም በደቡብ አፍሪካ አመፅና ተቃውሞ ተቀስቅሶ ነበር። በሁለቱም አጋጣሚዎች የመንግስት እርምጃ አንድና ተመሳሳይ ነበር። የሕዝቡን የመብትና ነፃነት ጥያቄ በኃይል ለማዳፈን ያለማቋረጥ ጥረት ተደርጓል። በዚህ ምክንያት፣ የሕዝቡ ተቃውሞ ወደ ሁከትና ብጥብጥ እያመራ ሄደ።

ይህን ተከትሎ በደቡብ አፍሪካ የአፓርታይድ መሪ የነበሩት “Pieter Willem Botha” ልክ እንደ ጠ/ሚ ኃይለማሪያም ደሳለኝ ጥልቅ ተሃድሶ በማድረግ ለሕዝቡ ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት ጥረት እንደሚያደርጉ በተደጋጋሚ ቃል ገቡ። የጠ/ሚ ኃይለማሪያም ንግግር ለሁላችንም የቅርብ ግዜ ትዝታ ስለሆነ እዚህ መድገም አያስፈልግም። የአፓርታይዱ መሪ ንግግርና የተሃድሶ እንቅስቃሴ ግን “Stephen Ellis” የተባለው የዘርፉ ምሁር ባቀረበው በጥናታዊ ፅሁፍ እንዲህ ገልፆታል፡-

“…in a series of speeches, Botha seemed to try to direct the country into reformist paths and away from the racial “Apartheid”…. What is certain is that his idea of ‘healthy power sharing’ meant he would cling to ‘group rights’ as a means of maintaining White control, which he claimed was still in the best interests of South Africa….A changing and increasingly volatile South African society led to the civil insurrection of 1984 and its repercussions around the country. Botha’s response was the repression of activists and liberation movements under a state of emergency. The reform policy stagnated.…” The Historical Significance of South Africa’s Third Force, Journal of Southern African Studies, Vol. 24, No.2. (Jun., 1998), pp. 261-299.

ይሁን እንጂ የሁለቱም ሀገራት መንግስታት ስር ነቀል ተሃድሶ ማምጣት ተሳናቸው። ከዚያ ይልቅ፣ የሕዝቡን የመብትና ነፃነት ጥያቄ በኃይል ለማፈን ጥረት ማድረግ ቀጠሉ። ሆኖም ግን፣ የሁለቱም መንግስታት እርምጃ የሕዝቡን ቁጣና ተቃውሞን ይበልጥ እንዲባባስ አደረገው። በዚህ ምክንያት፣ እ.አ.አ. በ1986 በደቡብ አፍሪካ፣ ባለፈው የ2009 ዓ.ም ደግሞ በኢትዮጲያ የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ታወጀ።

በሌላ በኩል የአፓርታይድ ስርዓት የመከላከያና ድህንነት ኃላፊዎች በሕቡዕ ሦስተኛው ኃይል (The third Force) የተባለ ፀረ-አብዮታዊ ቡድን አቋቋሙ። ይህ ከክልል ሚሊሺያዎችና ልዩ ፖሊስ ኃይል የተወጣጣው ቡድን እንደ ዝምባብዌና ሞዛምቢክ ባሉ ጎረቤት ሀገራት የነበረውን የአማፂያን እንቅስቃሴ እንዲያውኩ የተቋቋሙ ነበሩ። የአሰቸኳይ ግዜው ከታወጀ በኋላ ግን በደቡብ አፍሪካ ጦር ወታደራዊ ስልጠና እና ትጥቅ ተሰጥቷቸው የፀረ-አፓርታይድ ትግሉን በማጨናገፍ ተግባር እንዲሰማሩ ተደረገ። የአፓርታይድ ስርዓት በተለይ በደቡብ አፍሪካ “KwaZulu Natal” በሚባለው ክልል የታየውና ዛሬ በሶማሊ ክልል እየታየ ያለው ፍፁም ተመሳሳይ ነው።

“In April 1986, the State Security Council had endorsed guidelines for a strategy for counter-revolutionary war which, among other things, emphasised that the forces of revolution should not be combatted by the security forces alone, but also by ‘anti-revolutionary groups such as Inkatha … as well as the ethnic factor in South African society’. In the following months, specifically ethnic organisations were armed and trained in KwaZulu and Ciskei, while anti-ANC groups in other places were encouraged and armed in the form of kitskonstabels or special policemen and vigilantes….  In effect, military units, which had carried out the destabilisation of neighbouring countries, were now implementing similar strategies at home, on the instructions of the State President, the State Security Council and the head of the [South Africa Defense Force]”  

Journal of Southern African Studies, Vol. 24, No.2. (Jun., 1998), pp. 261-299

በአጠቃላይ፣ በተለያዩ የደቡብ አፍሪካ ጎሳዎችና ብሔሮች መካከል የእርስ-በእርስ ግጭት ለመፍጠር የተደረገው ጥረት ዛሬ በአንዳንድ የአማራ፣ ኦሮሚያ፣ ሶማሊና ደቡብ ክልሎች እየታየ ካለው ጋር ተመሳሳይ ነው። ስለዚህ፣ የደቡብ አፍሪካ አፓርታይድ ስርዓት በተለያዩ ብሔሮች መካከል የአርስ-በእርስ ግጭት በመፍጠር የነጮች የበላይነትን ለማስቀጠል ካደረገው ጥረትና ካስከተለው ውጤት በመነሳት ሀገራችን ኢትዮጲያ ወደየት እየሄደች እንደሆነ መገመት ይቻላል።

በደቡብ አፍሪካ በተለይ እ.አ.አ. ከ1986 ዓ.ም ጀምሮ በተለያዩ የጥቁር ጎሳዎችና ብሔሮች መካከል የእርስ በእርስ ግጭት ለመፍጠር በሕቡዕ የተሰራው ስራ እ.አ.አ. ከ1990 – 1994 ዓ.ም ባሉት አራት አመታት ውስጥ ፍሬ አፈራ። በእርግጥ ከመርዛማ ዛፍ መልካም ፍሬ አይጠበቅም። በእነዚህ አራት አመታት ውስጥ ብቻ በተነሳ ሁከትና ብጥብጥ 14,000 ደቡብ አፍሪካዊያን ሕይወታቸውን አጥተዋል።  እ.አ.አ. ከ1948 ዓ.ም የአፓርታይድ ስርዓትን ለመጣል በተደረገው ትግል ከተገደሉት ሰዎች ከ1990 – 1994 ዓ.ም ባሉት አራት አመታት ውስጥ ብቻ የተገደሉት ይበልጣል። ሀገራችን ወደየት እያመራች እንደሆነ ለማወቅ ለሚሻ ከዚህ በላይ ጠቋሚ ማስረጃ አይገኝም። አዎ…ኢትዮጲያ ወደ እርስ-በእርስ ግጭትና ዕልቂት እያመራች ነው!

Filed in: Amharic