>

· መንግስትን፤ “ኢትዮጵያዊነታችንን” መልስልን...ብለን ብንከሰውስ?

“ኢትዮጵያ”-የታለች?
· “የቴዲ አፍሮ ኢትዮጵያ”?– “የዶ/ር ነጋሶ ኢትዮጵያ”?—”የደርግ ኢትዮጵያ”???
· መንግስትን፤ “ኢትዮጵያዊነታችንን” መልስልን —-ብለን ብንከሰውስ ?

አያችሁልኝ … “የከፍታ ዘመን” በምኞት ብቻ እንደማይመጣ! አዲሱ ዓመት ገና ከመጥባቱ ከወደ ኦሮሚያና የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል የሰማናው ድንበር ተኮር ግጭት ያሳፍራል፡፡ የሚያሳፍረው ከወትሮው በተለየ በክልሎቹ ታጣቂ ሃይሎች ድጋፍ፣ የተጫረና የተቀጣጠለ “እሳት” መሆኑ ነው፡፡ (አማጺ ኃይል ወይም ተቃዋሚ ፓርቲ ቢሆን የአባት ነበር!) እንዴ ከጎረቤት አገር ጋር ጦርነት የገጠምን እኮ ነው የመሰለው – ወይም የሁለቱ ክልሎቹ የመንግስት ቃል አቀባዮች ያስመሰሉት።
ኢህአዴግ መራሹ መንግስት፤በውጭ የሚገኙ ዳያስፖራ ኢትዮጵያውያንን፣ በማህበራዊ ሚዲያ ህዝብን ወደ ግጭት እንዲገባ እየገፋፉ ነው ብሎ በተደጋጋሚ ሲወነጅል ሰምተናል፡፡ (በኒውዮርክ ስብሰባ ጭምር ለዓለም መንግስታት አቤት ብሏል!) ሰሞኑን ግን በሚያስገርም ሁኔታ ማህበራዊ ሚዲያውን ለእርስ በእርስ ግጭት የተጠቀመው ራሱ ኢህአዴግ ነው፡፡(መንግስት አማን አይደለም ልበል?)
በድንበር ግጭቱ ሰበብ በርካቶች ለሞት መዳረጋቸው ሳያንስ ብዙ ሺዎች ከመኖሪያ ቀዬአቸው መፈናቀላቸው በእጅጉ ያሳዝናል፡፡ ይሄ የሆነው ደግሞ ከ25 ዓመት የፌዴራሊዝም ሥርዓት ተሞክሮ በኋላ መሆኑ ግርም ድንቅ ይላል!! ከኛ አልፎ በቅርቡ የተረጋጋ መንግስት ለመመስረት ቀና ደፋ ለምትለው ሶማሊያ በሞዴልነት የቀረበው የፌደራሊዝም ሥርዓታችን፤ከሩብ ክፍለ ዘመን በኋላም ለድንበር ግጭቶች መፍትሄ አልባ መሆኑ ወይም መሆናችን እርግማን ነው፡፡ የኋላቀርነት ማህተም እንጂ የሥልጣኔ አርማ አይደለም፡፡ በኪሳራ የተሞላ እንጂ አንዳችም ትርፍ የለውም፡፡
ኪሳራው ደግሞ የኢትዮጵያ ሶማሌ ወይም የኦሮሚያ ክልል ብቻ አይደለም፡፡ ኪሳራው የኢህአዴግ ብቻም አይደለም፡፡ የመላ ኢትዮጵያውያን ኪሳራ ነው፡፡ የአገር ኪሳራ!! ይሄ ደግሞ አዲስ ዓመት መባቻ ላይ በየዋህነት የተመኘነውን “የከፍታ ዘመን” በአፍጢሙ ይደፋዋል፡፡
አንድ ጥያቄ አለኝ፡፡ (ለጊዜው ነው እንጂ ጥያቄዎቼስ ሺ ናቸው!!) እናላችሁ —- የኢህአዴግ የሥልጣን እኩያ ከሆነው የፌደራሊዝም ሥርአታችን ምን አተረፍን? (ሃቀኛ ጥያቄ እንጂ ስላቅ አይደለም!) እውነት “በልዩነት ውስጥ አንድነት” ተፈጥሯል? (ማስረጃው ምንድን ነው?) በእርግጥስ “ልዩነታችን ውበታችን” ሆኗል? የአገራችን ብሔር ብሔረሰቦች፣ በራሳቸው ጉዳይ ራሳቸው መወሰን ችለዋል? በየክልሎቹ የዜጎች መብትና ነጻነት ሰፍኗል? በመላው አገሪቱ የህግ የበላይነት ተረጋግጧል? (እንዴት ብሎ?) ለፌደራል ሥርዓቱ ውጤታማነት ቁልፍ ሚና የሚጫወተው “ዲሞክራሲ” በቅጡ ተገንብቷል? (ከየት መጥቶ?) ህዝቦች በወደዱትና በመረጡት መንግስት እየተመሩ ነው ወይስ በሚወዳቸውና በመረጣቸው መንግስት? (የሚወደን ብናገኝማ መታደል ነው!) ባለፉት 25 ዓመታት በብሄርና በጎሳ ታፍነን፣ በመንደርና በጎጥ ታጥረን —– ምን አተረፍን? ምንስ አጎደልን? (የምን ትርፍ?)
አይገርምም—- ይሄን ሁሉ ጥያቄ ደርድሬም ገና ብዙ– ብዙ ይቀረኛል፡፡ (የ25 ዓመት ውዝፍ እኮ ነው!) ውድ አንባቢዎቼን እንዳላሰለች ግን (እንደ ኢህአዴግ ካድሬ!) ለጊዜውም ቢሆን ጥያቄዎቼን ላሳርፋቸው። በእነዚህ ሁሉ ጥያቄዎች መሃል ግን እኔም እናንተም (ኢህአዴግም ጭምር!) የምናውቀው አንድ የጋራ እውነት አለን፡፡ ብሄራዊ እውነት፡፡ የማይበጀን ቀፋፊ እውነት። ግን ደግሞ የማንክደው፣ ያፈጠጠ እውነት፡፡ ምን መሰላችሁ? “ኢትዮጵያዊነት”ን አጥተነዋል፡፡ ተዘርፈን ወይም ተነጥቀን አይደለም፡፡ ራሳችን ጦርነት ከፍተንበት ነው፡፡ (በኢህአዴግ አዝማችነት!) ጎሳና ብሔር ላይ የሙጥኝ ብለን (ጥቅምና ጉዳቱን ሳናሰላ!) ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት “ኢትዮጵያዊነት”ን በእጅጉ ሸርሽረነዋል፡፡ “ኢትዮጵያዊ አንድነት” ላይ እንደ ባላንጣ ዘምተንበታል፡፡ (በራሱ ላይ የዘመተ ታሪካዊ ህዝብ ነን!!)
ክፋቱ ደግሞ፣ ኢትዮጵያዊነት ላይ መዝመታችን መዘዙ መጥፎ ነው፡፡ ብሔር ብሔር ብለን “ኢትዮጵያዊነትን” ፊት መንሳታችን ለፈተና ዳርጎናል፤ ለማንወጣው መከራ። ኢህአዴግ ሁሌም ሳይሰራ ለነገ የሚያሳድራቸው የቤት ሥራዎች (በመልካም አስተዳደር ችግር፣ በቸልተኝነት፣ በፖለቲካ ቁማር፣ በጥበብ ማነስ ወዘተ…ወዘተ) ውሎ አድሮ ዋጋ እያስከፈለን መሆኑን ደጋግመን አይተነዋል – በጠራራ ፀሃይ!! (ያውም በዜጎች ውድ ህይወት!) 

ምንጭ

 

Filed in: Amharic