>

ንቦቹ ተናደፉ (ዮናስ ሃጎስ-ኬኒያ ናይሮቢ)

የኬንያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሚያሰማው ዝርዝር ውሳኔዎችን የማንበብ ሂደት ከጠዋቱ አራት ሰዓት የጀመረ እስካሁን ድረስ እየተካሄደ ይገኛል። ፍርድ ቤቱ ውስጥ ዝርዝር ውሳኔው በዳኞቹ በሚነበብበት ሂደት ላይ ከፍርድ ቤቱ ውጭ ያልታሰበና አስደንጋጭ የሆነ ክስተት ተፈጥሮ የኬንያ መነጋገርያ ለመሆን በቅቷል።
***
ፖሊሶች ጠቅላይ ፍርድ ቤቱን በመክበብ ከጠዋት ጀምሮ ከተፈቀደላቸው ሰዎች በስተቀር ማንም ወደ ፍርድ ቤቱ እንዳይገባ የመከልከል ስራውን በአግባቡ እየተወጣ ነበረ። የመንግስት ደጋፊዎች የሆኑ ጥቂት ሰልፈኞች ደግሞ ፍርድ ቤቱ ዙርያ በመሆን በዳኛውና በፍርድ ቤቱ ላይ ያላቸውን ተቃውሞ እየገለፁ ነበረ። የሐገር ውስጥ እና የውጭ ጋዜጠኞችም የተለመደ ስራቸውን ለመስራት እዛው ተገኝተዋል።
***
በድንገት ከየት እንደመጣ ያልታወቀ የንብ መንጋ አካባቢውን በመውረር አንድ ሰው ሲያቆስል በአካባቢው የነበሩ ጋዜጠኞች፣ ተሰላፊዎችና ፖሊሶች በሩጫ አካባቢውን ለቅቀው ለመሄድ ተገድደዋል። ከብዙ ደቂቃዎች ረብሻና መንገላታት በኋላ ፖሊስ ረብሸኞች ከመጡ በሚል ያዘጋጀውን አስለቃሽ ጢስ ንቦቹ ላይ ለመርጨት ተገድዶ ንቦቹ አካባቢውን ለቅቀው ሊሄዱ ችለዋል።
***
ክስተቱ አጋጣሚ ይምስለ እንጂ የተቃዋሚው ደጋፊዎች አንጀታቸው ቅቤ እንደጠጣ በትዊተሩና ፊርስቡክ ላይ ካደረጓቸው ልጥፎች ለመረዳት የተቻለ ሲሆን ብዙዎቹ ከዚህ በፊት ተቃዋሚዎች ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ ሲነሳሱ በፖሊሶች ይደርስባቸው የነበረውን እንግልትና ትላንትና ዛሬ የምንግስት ደጋፊዎች ግን ፍርድ ቤቱን ተቃውመው ሲሰለፉ ከፖሊስ አንዳችም ትንኮሳ እንዳልደረሰባቸው በማነፃፀር የንቦቹን ወረራ ‹የእግዚአብሄር ስራ ነው› ሲሉ ተደምጠዋል። «እኛ ተሰልፈን ቢሆን ኖሮ ብዙ አስለቃሽ ጢስ እና ጥይት ይተኮስብን ነበረ። አሁን የጁፒሊ ደጋፊዎች ሲሰለፉ ግን ፖሊሶቹ አጅበዋቸው ይሄዳሉ። ይህ በትክክልም እግዚያብሔር የላከባቸው ቁጣ ነው!» ሲል አንድ የናሳ ደጋፊ ከታች ከምትመለከቱት ቪድዮ ጋር ለጥፏል።
***
ተቃዋሚውን ወክለው የፓርላማ መቀመጫ ያሸነፉት አቶ ባቡ ኦዊኖ (Babu Owino) የተባሉት ግለሰብ በትዊተር ገፃቸው ላይ «የጁፒሊ ደጋፊዎች አሁንም ከዛ ቦታ ብትበተኑ ይሻላችኋል፤ አለበለዚያ ከንቦቹ አስከትዬ ቸነፈር ነው የማወርድባችሁ!» ሲሉ ተሳልቀዋል።
***
የፍርድ ቤቱ ዝርዝ ውሳኔ ያላለቀ ቢሆንም እስካሁን ከተነበበው ለመረዳት እንደተቻለው ፍርድ ቤቱ የምርጫ ቦርዱን ለተፈጠረው ችግር ሙሉ በሙሉ ተጠያቂ አድርጎታል። እንግዲህ የሚጠበቀው ውሳኔ ምርጫ ቦርዱ ቀጣዩን ምርጫ እንዲያስፈፅም ይደረጋል ወይንስ አይደረግም በሚለው ጉዳይ ላይ ብቻ ነው።
Filed in: Amharic