>
5:13 pm - Thursday April 18, 4424

ከማዕከላዊ እስከ ዋሽንግተን ዲሲ (ሃብታሙ አያሌው)

መቼም ህወሓት መንፈሱን የተሸከሙ እርኩሳን አያልቁበት

እነዚያን መራር ቀናት ተሻግረን በህወሓት የታቀደብን ሳይሆን በኢትዮጵያ አምላክ (በፈጣሪ) የታሰበልን አሸንፎ ከየሺዋስ አሰፋ ጋር ዳግም ለመገናኘት አበቃን። ማዕከላዊ ለ4 ወራት በሲኦል መካከል አብረን አልፈናል። በቀዝቃዛው ግራውንድ ውስጥ ሰቆቃውን በዝማሬ ተሻግረናል። ወደ ማዕከላዊ ከመግባታችን በፊት በአካል የተገናኘነው አንድ ቀን ብቻ ነበር። ያውም ሁለታችንም አዲስ አበባ መስቀል አደባባይ ታክሲ ስንጠብቅ። ከዚህ ዘለግ ያለ ትውውቅ አልነበረንም፤ ሰላምታ የተለዋወጥነውም ሀብታሙነህ? የሺዋስ ነህ? በሚል የማረጋገጫ ጥያቄ ነበር። ከመስቀል አደባባዩ ድንገቴ ግንኙነት በኋላ አጋጣሚዎች አስተያይተውንም ሆነ አደዋውለውን አያውቁም። ዳግም ለመገናኘት ያበቃን የህወሓት የክስ መዝገብ ነበር።

“ህገ – መንግስቱን እና ህገ-መንግስታዊ ሥርዓቱን በኃይል ለመናድ አስበው በሀገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች የሽብር ተግባራትን ለመፈፀም፤ የልማት ተቋማትን ለማፈራረስና ለማውደም…በወንጀሉና ወንጀሉ በሚሰጠው ውጤት ሙሉ ተካፋይ በመሆን በፈፀሙት የሽብር ተግባር ለመፈፀም ማቀድ፤ ማሴር፤ መዘጋጀት፤ መነሳሳት ወንጀል ተከሰዋል” የሚል ነበር። ህወሓት ያንን ሁሉ ግፍ የፈፀመብን እንዲህ ባለ ክስ ነበር። በክስ መዝገቡ ከተዘረዘሩት በስልክም በአካልም የማውቀው የአንድነት ፓርቲ የድርጅት ጉዳይ ሀላፊ የነበረውን ዳንኤል ሺበሺን ብቻ ነበር። አብርሃ ደስታን በስም ሳውቀው ሌሎቹን በስምም አላውቃቸውም ነበር።

በስምም በአካልም የማንተዋወቅ ሰዎችን በአንድ ቀን በተመሳሳይ ሰዓት ከተማውን አሸብረው ከያለንበት በልዩ ኦፕሬሽን በቁጥጥር ስር አዋሉን። ከዚያም ከዚህ በታች የተዘረዘሩት ጮቤ እየረገጡ ተቀብለው ወደ ሲኦል አስገቡና ለጋንጩሮቹ አስረከቡን።
1. ዋና አዛዡ ኮማንደር ኮማንደር ተክላይ
2. የእስረኛ አስተዳደር ኃላፊው ኢንስፔክተር ገብሩ
3. የግቢ ዙሪያ ኃላፊ ም/ኮማንደር ብርሃነ
4. የጥበቃና ድልደላ ኃላፊ ኢንስፔክተር ወዲ ሃዲሱ
5. የሽፍት ኃላፊ ም/ኢን ብርሃነ እና ም/ ኢን ካህሳይ
6. የኤግዚቢት ክፍል ሃላፊ ኢንስፔክተር መለስ…ወ.ዘ.ተ

ጋንጩሮቹ መዓልት ወሌሊት ለአራት ወራት ጭካኔያቸውን አሳይተው ወደ ቂሊንጦ ወህኒ ቤት ሸኙን። መቼም ህወሓት መንፈሱን የተሸከሙ እርኩሳን አያልቁበት በዚያ ደግሞ እነ ሱፐር ኢንተንደንት እምባየ፤ መረሶ ፤ ገብረ መድህን፤ አጋዚ፤ በቅጥል ስሙ (ሻዕቢያ) የሚባል የጭካኔ አባት፤ የማነህ፤ አንገሶም፤ ኮለኔል ሃይሌ፤ ኮለኔል ካህሳይ፤ በቅጥል ስሙ(ጨርቆሴ) ወ.ዘ.ተ ተቀብለው ከነ ቤተሰቦቻችን እንደፈለጉ አንገላቱን።

የማንተዋወቀውን አስተዋወቁን፤ ሊያፈርሱ አስበው ሰሩን፤
ከማዕከላዊ ግፍ በኋላም በቅሊንጦ በህመም ክፉኛ ስሰቃይ የሺዋስ መከራዬን ተካፍሏል። ከወህኒቤት በኋላ በሆስፒታልም ከሆስፒታል በኋላም ከጎኔ ሆኖ የስቃዮን ልክ አይቶ አንብቷል። ዛሬ ደግሞ ሌላ ቀን ሆነ ትላንት ተስፋ የቆረጠበት ወንድሙ ቆሜ ዋሽንግተን ዲሲ ላይ አግኝቶኛል። ምስጋና የባህሪው የሆነ አምላካችን ይክበር ይመስገን !!

ከአሁኑ የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ከየሺዋስ አሰፋ ጋር ትላንት ማዕከላዊ ዛሬ ደግሞ ዋሽንግተን ዲሲ ተገናኝተናል። ስለኛ ያነባችሁ ውድ ኢትዮጵያውያን ዳግመኛ በአክብሮት እጅ እንነሳለን !!

Filed in: Amharic