>

የማለዳ ወግ ... ክፋት ድል ነስቶ ህዝብ ያለቅሳል - * ሀገር በአደገኛው መንገድ ...(ነቢዩ ሲራክ)

* በቆሸ ዳግም አደጋ ደረሰ …
* የኦሮሚያ፣ የሶማሊያ፣ የጎንደር ቅማንትና የኮንሶ ስጋት ..
* ሀገር በአደገኛው መንገድ …

ባሳለፍነው አመት መጋቢት 2009ዓ.ም አዲስ አበባ ቆሼ ተደርምዶ ባስከተለው አደጋ 75 ሰዎች ተቃትፈው ከ 300 በላይ ተፈናቅለዋል። የቆሸ መሪር ሀዘን ሳይወጣልን ዛሬ መስከረም 4 ቀን 2010 ዓም በአዲሱ አመት የመጀመሪያ ሳምንት ቆሸ በድጋሜ መደርመሱንና በአደጋው የሰው ህይወት ማለፉን እየሰማን ነው ፡(

በኦሮምያና ሶማሌ አዋሳኝ ድንበሮች የተቀሰቀሰው ሁከት በሁለቱም በኩል የንጹሃንን ደም ካስገበረ በኋላ ” ችግሩ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ተፈትቷል ” ትብለን የክልሉ መሪዎች መሳ ለመሳ ተቀምጠው ” አይደገምም ” ሲሉ በቁጭት መግለጫ አወጡ ። ይህ የሆነው ልክ የዛሬ ስድስት ወር አካባቢ ነው ። ዳሩ ግን ተፈታ የተባለው ችግር ስላለመፈታቱ በአዲሱ አመት የመንግስት መሰረቱ የተዛባ “የከፍታ ” ተራ ምኞት ከበርቻቻ ሳያከትም እውነቱ ተገለጠ 🙁

በኦሮሚያና ሶማሊያ ድንበር ከተሞች በተቀሰቀሰ ግጭት ከ50 በላይ የሰው ህይዎት ቀጥፎ ፣ የሀገር ሀብት እያወደመ ስለመገኘቱ መረጃው የኢሳት ፣ የጀርመን ወይም የአሜሪካ ራዲዮ ሳይሆን አተካራ የገጠሙት የሁለቱ ክልል ኮሚኒኬሽን ሃላፊዎች መግለጫ ነው ። የመንግሰት ተቋማት የሆኑት የሁለቱ ክልል ኮሚኒኬሽን ሃላፊዎች በፍጥጫ መድረክ ወጥተው አንዱ አንዱን ” ጸረ ሰላምና አሸባሪ ከሀዲ ” እየተባባሉ ሲወነጃጀሉ ከመስማት በላይ አሳፋሪ እውነት አላየሁም 🙁

ልክ የዛሬ ሁለት አመት በሀገሩ አንድነት ቀናኢ በሆነው የጎንደር ነዋሪ ላይ ክፉዎች ያጠመዱት የልዩነት ወጥመድ የተሰለፉት አማራና ቅማንት ብለው ለመለያየት ተነሱ። በጎንደሬው ላይ በተሸረበው ተንኮል ሰርቶ የልዩነቱ አንባጓሮ ቅማንቱን ከቀረው ጎንደሬ ጋር ደም ለማቃባት ተሞከረ ። የሰው ህይዎት ተቀጠፈ ። ንብረት ወደመ ሰው ተፈናቀለ 🙁
ዘንድሮ በያዝነው ሳምንት የቅማንትና የአማራ ጉዳይ ” በነዋሪው ምርጫ በህዝበ ውሳኔ ይፈታል !” ተብሎ ሊፈታ ቀናት ቀርተውታል። ውሳኔው ምን ይሁን ምን ለአንድነቱ ቀናኢ የሆነውን ህዝብ የመለያየት መግነጢሳዊ ሀይል የለውም ብልም የልዩነት ቅስቀሳ ቁርሾው ዋጋ እንዳያስከፍል ጎንደሬውን ኢትዮጵያዊ በከፋ ስጋት ላይ ጥሎታል 🙁

ልክ የዛሬ አንድ አመት የኮንሶ ነዋሪዎች ከልዩ ወረዳነት ወደ ወረዳ ወርደው በሰገን ዞን ስር እንዲጠቃለሉ መደረጋቸ ውን ተቃውመው ነበር ። የኮንሶ ነዋሪዎች አሁንም አምና ደም ያቃባ የውስጥ አስተዳደር ችግር የተፈታ ቢመስልም ፣ አሁንም ችግሩ የተዳፈነ ረመጥ እንጅ የተፈታ ችግር ነው ለማለት መረጃ ማስረጃ ማቅረብ የሚቻለው የለም ። ይህም በጥንቃቄ አልተያዘምና ውሎ ሲያድር የሚያስከፍለው ዋጋ ይኖራል 🙁

ወጌን ሳጠቃልል: 
… በብልሹ አስተዳደር ላይ የተገነባው የዘር ፖለቲካ ልዩነት አደጋውን እንታዘብ ዘንድ ክፋት ድል ነስቶ ሰላማዊ ህዝብ በሚኖርበት ቀየ በዘር ሀረጉ እየተነቀሰ እየወጣ ጥቃት እየደረሰበት ነው ። ይህ ደረቅ አሳዛኝ የማይካድ እውነት ነው 🙁 እውነት ለመሆኑ የቀደመው የአማሮች መፈናቀል ቢካድ እንኳ ሰሞነኛው የሶማሌና ኦሮሚያ ክልል የሚሰማ ሮሮ መሬት ላይ ያለውን እውነት ብቻ ነው …

ይህ አደገኛ አካሄድ ዜጎች በሁሉም ክልሎች ተንቀሳቅሰ ውና ሰርተው የመኖር መብታቸውን የሚፈታተን ያደርገዋል።! በየትኛውም ስሌት ከላይ የተመመከትናቸው አንኳር አንኳር እውነቶች ሀገር በአደገኛው መንገድ ላይ መሆኗን እንጅ በብሔር ብሔረሰብ ፍትሃዊ አደረጃጀት ከፍታ ላይ መሆኗን ነው ማለት አያስችለንም ! … ልብ ያለው ልብ ይበል !

ቸር ያሰማን

ነቢዩ ሲራክ 
መስከረም 4 ቀን 2010 ዓም

Filed in: Amharic