>

ለኢትዮጵያውያን ግርምትና ትዕንግርት የፈጠሩት 3ቱ ንስሮች (ጌጡ ተመስገን)

የመጀመሪያው አውሮፕላን በ1921 ዓ.ም. አዲስ አበባ መድረስ ለኢትዮጵያውን ከውጭው ዓለም ጋር ለመገናኘት አዲስ ምዕራፍ የተከፈተበት ቀን መሆኑ አስደስቷቸዋል፡፡

ለፈረንሳዮቹ ደግሞ በኢትዮጵያ አቪዬሽን ታሪክ ከሌሎች አገሮች በተለይ ዝግጅቱን አጠናቆ ከነበረው ጀርመን መቅደማቸው አስፈንድቋቸዋል፡፡ ለአብዛኛው ኢትዮጵያ ግን የአውሮፕላን መምጣት ግርምትና ትዕንግርት ፈጥሮበታል፡፡
‹‹ከቶ ምን አሳየኝ ይሠሩትን ያጡ
ጠንቀቅ በል ጌታዬ ወደ አንተም ጋር መጡ››
ብሎ እስኪዘምር ድረስ፡፡
መንገድ ሳይሠራለት፣ ሐዲድ ሳይነጠፍለት በአየር ላይ ተንሳፎ የመጣው ያን አውሮፕላን የአየር ባቡር የሚል ስም ወጣለት፡፡ በዚህ ሁኔታ ነበር የዛሬ 87 ዓመት በኢትዮጵያ የአቪዬሽን ታሪክ የተጀመረው፡፡

በኢትዮጵያ አቨየሽን የተጀመረው ንጉስ ተፈሪ በገዟቸው 3 ፈረንሳይ ስሪት ፖቴዝ አውሮፕላኖች ነው፡፡ አንደኛዋን ፈረንሳዊው ሙሴ አንድሬ ማዬ ከጅቡቲ በማብረር ነሀሴ 12 ቀን 1921 ዓ.ም “ስጋ ሜዳ” አውሮፕላን ማረፊያ ከቀኑ 7 ሰዓት ከ 10 ደቂቃ ላይ ባሳረፈበት ወቅት ነው፡፡ አውሮፕላኗም “ንስረ ተፈሪ” ተብላ ተሰየመች፡፡

ጅቡቲ ቀርተው የነበሩትን ሁለቱን ፖቴዝ አውሮፕላኖች አንዷን ካፕቴን ማዬ ፣ ሁለተኛዋን ደግሞ ጀርመናዊው ካውንት ሼዝበርግ እያበረሩ መስከረም 12 ቀን 1922 ዓ.ም ወደ አዲስ አበባ አመጧቸው፡፡ እነዚህ አይሮፕላኖች ከመጡ በኋላ “ንስረ አስፋወሰን” እና “ንስረ መኮንን” የሚል ስያሜ ተሰጥቷቸው ነበር፡፡

ከዚያም የፈረንሳይ ተፎካካሪ የነበረው የጀርመኑ ጀንከርስ (Junkers) አውሮፕላን በባሮን ሻን ኢግል አብራሪነት በከተማዋ ውስጥ ጃን ሜዳ አረፈ፡፡ በጃንሜዳ ውስጥ በማረፉ ከፈረንሳዩ አውሮፕላን የበለጠ በርካታ ተመልካች እንዲኖር አድርጐታል፡፡

የመጀመሪያ የአገር ውስጥ በረራ ጀንከርስ አውሮፕላን አዲስ አበባ ከደረሰ አንድ ወር በኋላ ነበር የአገር ውስጥ በረራውን የጀመረው፡፡ ያ ጉዞው የመጀመሪያው የአገር ውስጥ በረራ መሆኑ ነው፡፡ ያልተሳካው የመጀመሪያው በረራ ሊባልም ይችላል፡፡

ጀንከርስ የመጀመሪያ የአገር ውስጥ በረራው ወደ ጐሬ ሲሆን ተልዕኮውም የኢሊባቡር ጠቅላይ ገዥ የነበሩትን ራስ ናደውን ለማምጣት ነበር፡፡ ይህም አውሮፕላን በኢትዮጵያ ህመምተኞችን ለማጓጓዝ ሲበር የመጀመሪያው መሆኑ ነው፡፡

ራስ ናደው በጽኑ ታመው ነበርና የሚተኙበትን አልጋና ፍራሽ ጨምሮ ወደ ዋና ከተማቸው ጐሬ በረራውን ቀጠለ፡፡ ነገር ግን በአየር ሁኔታው አመቺ አለመሆን ምክንያት ተመልሶ እንድብር አካባቢ ለማረፍ ተገደደ፡፡ በማግስቱም ወደ አዲስ አበባ ተመለሰ፡፡

Filed in: Amharic