>

የኢትዮጵያዊነት አረዳድ ላይ የእኔ አስተያዬት (በፈቃዱ ዘ ኃይሉ)

(በኢንጂነር ይልቃል ጌትነት “ኢትዮጵያ ያለ ‹ኢትዮጵያዊነት› ልትኖር አይቻላትምን?” በሚል ለጻፍኩት ጽሑፍ የተሰጠ ምላሽ)

በመጀመሪያ ይህ ፅሁፍ በፍቃዱ ኃይሉ በፃፈው ፅሁፍ ላይ የቀረበ ትችት በመሆኑ በተነሱ ነጥቦች ላይ ተመጣጣኝና አጭር ለማድረግ ሲባል የፅሁፉ አወቃቀርና ብስለት በሚጠበቀው መልኩ የእኔን የፖለቲካ አረዳድና እይታ ለአንባቢ ለማቅረብ አይመችም፡፡ በመሆኑም አንባቢ በፅሁፍ ለቀረቡ የመከረከሪያ ነጥቦች የተሰነዘረ ብቻ አድርጎ እንዲገነዘብልኝ እጠይቃለሁ፡፡

በቅድሚያ በጽሑፉ የተገለጸው ሃሳብ የተወሰነ “የኅብረተሰብ ክፍልን” ማኅበራዊ ሥነ ልቦናን ስለሚወክል ሐሳቡ ለውይይት መቅረቡ ጥሩ ነው፡፡ በእኔ ግንዛቤ ፀሃፊው ለማስረዳት የሞከረው እሱ በተለምዶ ኢትዮጵያዊነት የሚለው የፖለቲካ አመለካከት ሁሉንም ኢትዮጵያውያን በእኩልነት ስለማያግባባና እሱም አጥብቆ የሚከራከርለት የዘውጌ ፖለቲካ በኢትዮጵያዊነት አመለካከት ተገቢውን ቦታ ባለማግኘቱ እሱ በተለምዶ ኢትዮጵያዊነት በሚለው አመለካከት ተለውጦ የዜግነት መብትን በማክበር ላይ ብቻ የተመሰረተ ማንነት እንዲሆነ ለማሳመን የተደረገ ሙከራ ሆኖ አግኝቸዋለሁ፡፡ ይህንን እይታውን ለማስረዳት የተጠቀመበት መከራከሪያና የደረሰበትን ድምዳሜ በእኔ ዕይታ የተሳሳተ ሁኖ ስላገኘሁት ይህንን የበኩሌን አስተያየት ሰንዝሬያለሁ፡፡ እነዚህን የተሳሳቱ ነጥቦች ከመጠቆሜ አስቀድሜ ግን ጸሐፊው የሌሎችን ስሜት ብቻ በማስተናገድ ዓይነት አተራረክ የሚከተለው አጻጻፍ ራሱን የት ላይ እንደቆመና እምነቱ ምን እንደሆነ ለመገምገም ዕድል እንዳይነፍገው ያለኝን ስጋት ለመጠቆም እወዳለሁ፡፡

1ኛ. ጸሐፊው ለዘውግ ፖለቲካ ወግኖ ኢትዮጵያዊነት ለዘውግ ፖለቲካ ተገቢውን ቦታና እኩልነት አልሰጠም የሚል አቋም ከወሰደ በኋላ ይህንን አቋሙን ለማስረዳት ሲል ከዚህም ከዛም የተቃረሙ ሃሳቦችን በአስረጅነት ለማቅረብ ሞክሯል፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ምንም ዓይነት የጋራ ስነ ልቦና መኖሩን አይገልፅም፡፡በኢትዮጵያ የሀገር ግንባታ ሂደት እና ማህበራዊ ልማት እንዲሁም የግዛት መጥበብና መስፋት በየትኛውም ዓለም ያለና የሚኖር ሁኖ እያለ ፀሃፊው ግን ይህንን የታሪክ ሀቅ የኢትዮጵያዊነት ድክመት አድርጎ ለማሳየት ይሞክራል፡፡ በየኢትጵያዊነት አተያይ በሰሜኑና በደቡብ ኢትዮጵያ ያለውን ልዩነት በመጠቆም በእኛ ሀገር ብቻ የተፈጠረ ጤናማ ያልሆነ ልዩ ነገር አድርጎ ያቀርበዋል፡፡ ከዚህ የተዛባ አረዳድ ለመዳን የፎከስ ኒውስ (FOX NEWS)ን እና ሲኤንኤን(CNNን) ወይም የትራምፕንና የኦባማን አሜሪካዊነት አረዳድ ምን ያህል እንደሚራራቅ ለማየት ቢሞክር በእኛ በኢትዮጵያውያን ላይ አለ ያለው የአተያይ ልዩነት በሁሉም ሀገር ያለና ሁሌም የሚኖር እንደሆነ ማዎቅ ይችል ነበር፡፡

2ኛ. ፀሃፊው የፈለገውን ሃሳብ ለማስረገጥ እንዲመቸው ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊነትን አንድ ትርጉም እንዳላቸው እያቀያየረ ይጠቀምባቸዋል፡፡ የጽሑፉ የመጀመሪያው አንቀጽ ላይ ኢትዮጵያ የሚለውን ቃል ብቻ ያስቀመጡ (ለምሳሌ “ኢትዮጵያለ ዘላለም በክብር ትኑር” የሚለውን መጥቀስ ይቻላል) መፈክሮችን ይጠቅስና ሁለተኛው አንቀጽ ላይ “እነዚህ ሁሉ በተለምዶ “ኢትዮጵያዊነት” የሚባለው የአንድነት ኃይሉ ፖለቲካዊ ንቅናቄ ማኅበራዊ መገለጫዎች ይመስላሉ” በማለት ለራሱ የሚመቸውን ድምዳሜ ሰጥቶ ትንታኔውን ይቀጥላል፡፡

3ኛ. ፀሃፊው ከኢትዮጵያዊነት መንፈስ እጅግ የራቀ አስተሳሰብ ያለው መሆኑን ለመገንዘብ የእኛን ኢትዮጵያዊነት ከእኛ አኗኗርና ስነ ልቦና ወስደው ለራሳቸው የነፃነት ትግል እንዲመች አድርገው ኢትዮጵያኒዝም የሚባል ንቅናቄ መስርተው ያደረጉትን ትግል በማድነቅ የመስራቾቹን አባቶቹን ሃሳብ እና የተግባር ህይወት ራሱ መርምሮ እንደማወቅ የእኛ ኢትዮጵያዊነት ከእነሱ ኢትዮጵያኒዝም በኋላ እንደመጣ አድርጎ ልዩነቱን ለማስረዳት ሲፍጨረጨር ይስተዋላል፡፡ በእኛ ተነቃቅተው እኛ ያደረግነውን ለማድረግ ከእኛ ኢትዮጵያዊነት ቀንጭበው የፈጠሩትን የኢትዮጵያዊነት ንቅናቄ ከሃሳቡና ከተግባሩ ባለቤቶች ጋር ማወዳደር በራሱ ከጤናማ ስሜት የሚመነጭ አይደለም፡፡ ሌላ ትርጉም ካልተሰጠው በስተቀር ይህ አስተሳሰብ ለክህደት የተጠጋ ኑፋቄ ነው፡፡

4ኛ. ጸሐፊው ኢትዮጵያዊነት በጎሳ መደራጀትን በተለየ ሁኔታ እንደሚፀየፍ እና ቁልቁል እንደሚያይ አድርጎ ለማሳየት ይሞክራል፡፡ እኔ እስከማውቀው ድረስ በጎሳ የፖለቲካ ፓርቲ ማቋቋም የተፈቀደው በኢትዮጵያ ብቻ ነው፡፡ ለምሳሌ የኬንያ ፖለቲካ በጎሰኝነት የተቃኘ ነው፤ ነገር ግን ፓርቲዎች በጎሳ መደራጀት በህግ የተከለከለ ነው፡፡ በዚያ ላይ “ኢትዮጵያዊነት አልተመቸኝም አውልቄ እጥለዋለሁ” የሚሉ ዜጎችን እናባብላቸው የሚል ፖለቲካ ያለውም እዚህ አገር ብቻ ነው፡፡ የትም አገር ቢሆን አሜሪካዊነትን አልፈልግም፣ ታንዛኒያዊነትን አልፈልግም የሚልን ዜጋ የየትኛቸውም አገር ፖለቲካ አይቀበለውም፡፡ “ኢትዮጵያዊነት እንዲህ ከሆነ አብረን ለመኖር እንቸገራለን” የሚል ማስፈራሪያ ማስቀመጥ በራሱ ሌላኛውን ወገን ተለማማጭ እንዲሆን የመበየን ያኛው ወገን “እኔም አብረን ለመኖር እቸገራለሁ” ማለት የማይችል ጥገኛ ያስመስለዋል፡፡ ስለዚህ መከራከሪያው ፍትሃዊነት የጎደለው ነው፡፡

5ኛ. ጸሐፊው የግድ ያስመሰለው “ኢትዮጵያዊነት ለሁሉም እንዲመች አድሮጎ እንደገና መበየን” በፖለቲካው ዓለም ውኃ የሚያነሳ ክርክር አይደለም፡፡ ተግባራዊ ለማድረግም ያስቸግራል፡፡ በታሪክ አረዳድም ይሁን በኢትዮጵያዊነት አረዳድ የተለያዩ አማራጭ አተያዮች ይኖራሉ እንጂ ሁሉንም የሚያግባባ አንድ ትርክት መያዝ አይቻልም፡፡ ይህ በየትኛውም ፖለቲካ ውስጥ ያለ እውነታ ነው፡፡ ለምሳሌ የአሜሪካን ፖለቲካ ብንወስድ የሪፐብሊካን (ሬድ) ስቴቶች የሚባሉት ለረዥም ግዜ ሪፐብሊካንን የሚመርጡ ስቴቶች እንደሆኑ ናቸው፡፡ የዴሞክራት (ብሉ) ስቴቶች የሚባሉት በፊትም አሁንም ከሞላ ጎደል አንድ ናቸው፡፡ የደጋፊዎቻቸው ካርታ እምብዛም አይቀየርም፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥም ቢሆን እሱ “በተለምዶ ኢትዮጵያዊነት” ለሚለው አዎንታዊ አመለካከት ያላቸው ሰሜነኞች፣ የደቡብ ክልል አካባቢ እና ከተማ ነዋሪዎች መሆናቸውን ከዚህ ለይቶ ጸሐፊው መመልከቱ ስህተት ነው፡፡ ለኢትዮጵያዊነት አማካይ ትርጉም ሊሰጠው ይገባል መባል የሌለበትም ከዚህ አንጻር ነው፡፡

6ኛ.ፀሃፊው አስቀድሞ በጭንቅላቱ የያዘውን የዘውጌ ሃሳብ ለማስረገጥ ሲል ከኢትዮጵያዊነት አልፎ ወዛደራዊ አለም አቀፋዊ ነኝ የሚለውን ደርግ ለጎሰኝነት ቦታ እንደነበረው የዘውግ ፖለቲካ በአዕምሮዓቸው የሌለውን ተፈሪ በንቲን እና አማን አንዶምን ወደ አመራር ማምጣቱ የዘውግ ጥያቄን ለማስታገስ እንደሆነ ይገልፃል፡፡ ይህንን ለማስረዳት “ዝንብ እንኳን አልገደልኩም” ያሉትን አረመኔውን መንግሰቱ ሃይለማሪያምን ለምስክርነት ጠርቷል፡፡ ሀቁ ግን ደርጎች ሐዲስ ዓለማየሁን ለርዕሰ ብሔርነት ጠይቀዋቸው እንደነበር እና አቶ ሐዲስ የራሳቸውን ቅድመ ሁኔታ በማቅረባቸው (ወታደራዊ ኮሚቴው ይፍረስ ማለትን ጨምሮ) እምቢ ብለው መቅረታቸውን ቢገልፀው እውነታው ከዘውግ ጋር ያልተገናኘ መሆኑን ግልጽ ያደርገዋል፡፡

7ኛ.ሌላው ጸሐፊው የዘውግ ፖለቲካ ቀድሞም እንደነበር ለማስረዳት የተጠቀመበት የነገሥታቱን አንዱ ካንዱ መጋባት ነው፡፡ ይሄ ግን ፍፁም የተሳሳተ አረዳድ እና እንዲያውም እንደ ሥልጣኔ ሊታይ የሚገባው ነገር ነበር፡፡ የጎጃሙ ንጉሥ ከሸዋው፣ የሸዋው ከትግሬው፣ ወዘተ መጋባታቸው በመሐከላቸው የመናናቅ መሠረት እና ድንበር እንዳልነበራቸው ማሳያ ነው፡፡ አንዱ ካንዱ መጋባታቸው ቅራኔን ለማርገብ፣ ሥልጣንን ለማንበር የሚጠቀሙበት ሥልጡን አካሔድ እንጂ እንዳሁኑ በዘውግ ተቧድኖ ደምና አጥንት እየለዩ ጎሳን የፖለቲካ መሰረት ጋር በእጅጉ የተራራቀና ላነሳው ሃሳብ በአስረጅነት ሳይሆን በአፍራሽነት ሊጠቀስ የሚገባው ነው፡፡

8ኛ. ለገጠሬ ዘውጌኝነትን ለከተሜ ኢትዮጵያዊነትን መስጠትም እንዲሁ በጥሞና የኢትዮጵያን ማህበረሰብ አደረጃጀት አለመረዳት ነው፡፡ ሀቁ ግን ገጠሬ አገርህ የትነው ሲባል የትውልድ መንደሩን ሲጠቅስ፣ ዘውግን የፖለቲካ አስተሳሰብ መሰረት አድርጎ ለፖለቲካል ኢኮኖሚ የበላይነት የሚሻኮተው ግን ተማርኩ የሚለውና ከተማ ቀመሱ ነው፡፡ ገጠሬው ብሔር ብሔረሰብ ከሚለው የዘውግ አመለካከት ጋር ትውውቅ የለውም፡፡ ሌላው የቀድሞ ጸሐፊዎች ዘ ብሔረ ቡልጋ፣ ዘ ብሔረ ዘጌ… እያሉ መጻፋቸው እንደ ዘውጌነት መታየቱ ትልቅ ስህተት ነው፡፡ እነዚህ የተጠቀሱት የቦታ ሥም ከመሆናቸው በስተቀር አሁን እንደሚባለው ኦሮሞ፣አማራ ፣ትግሬ ሲዳማ እንደሚባለው አይደለም፡፡ ከላይ እንደጠቀስኩት በገጠር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን መንደራቸውን ሀገራቸው አድርገው የሚያዩ ከመሆን አልፎ ከዘውገኝነት ጋር ምንም ግንኙነት የለውም፡፡

9ኛ. ጸሐፊው ኢትዮጵያዊነት እያበበ መሆኑን የሚያስረዱ ነገሮችን፣ ማለትም ሸቀጦች ሳይቀር ገበያ የሚያገኙት በኢትዮጵያዊነት ማስታወቂያ እንደሆነ ካስረዳ በኋላ ይሔ ሁሉ የዘውግ ፖለቲካ ማደግ ግብረ ምላሽ ነው በማለት ራሱ የሚመኘውን የግምት መልስ ይሰጣል፡፡ እውነታው ግን መጀመሪያውኑ የጠቀሰው የኢትዮጵያዊነት ፖለቲካ ተቀባይነት ለ26 ዓመታት በገዢው ፓርቲ የጎሰኝነት ፕሮጀክት ከተደረገበት ተፅዕኖ አለመዳከሙን ነው፡፡

10ኛ. ጸሐፊው “የ‘ኢትዮጵያዊነት’ አራማጆች የሚጠቁሙት ሦስት ዋና-ዋና መፍትሔዎች (ሀ) ፌዴራሊዝሙን አፍርሶ ማዋሐድ፣ (ለ) የዘውግ ፌዴራሊዝሙን አፍርሶ በመልክአ ምድር ደግሞ ማዋቀር፣ (ሐ) ፌዴራሊዝሙን እንዳለ በማኖር የክልሎችን ሥልጣን (በተለይ የመገንጠል መብትን) መቀነስ ናቸው” በሚል ያስቀመጣቸው በሙሉ ሦስቱም ከራሱ ጭንቅላት የፈለቁ ሆነው ነው ያገኘኋቸው፡፡ ቅንጅት፣ሰማያዊ እና መድረክን ጨምሮ የትኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ከእነዚህ አንዱን መፍትሔ ብለው አልጠቆሙም፡፡ ስለዚህ ጸሐፊው የራሱን ጥያቄ ጠይቆ፣ የራሱን መልስ የመስጠት ዝንባሌ ታይቶበታል፡፡

በአጠቃላይ ፀሃፊው እሱ ኢትዮጵያዊነት የሚለውን እና ለሌሎቹ ምቾት አይሰጥም ብሎ የሚያምንበትን ነገር ምክንያታዊ አድርጎ ለማቅረብ የሄደበት መንገድና ያቀረባቸው ማስረጃዎች ማለትም ጎሰኝነትን ከገጠሬነትና ከተሜነት በንፅፅር ያቀረበበት መንገድ፣ በኢትዮጵያ ስለነበረው የፖለቲካ ጋብቻ፣ ስለ ደርግ የስልጣን ተዋፅዎ፣ የኢትዮጵያዊነት የፌደራሊዝም አተያይ፣ የኢትዮጵያዊነትና ኢትዮጵያኒዝም ቅደም ተከተል እና ሌሎችም በቅንነትና በጥሞና ከተመለከተው የእሱን አስተያየት ከመደገፍ ይልቅ የሚያፈርሱ ናቸው፡፡ ይህ አይነቱ የተዛነፈ አስተሳሰብ የሚመነጨው አስቀድሞ አቋም ወስዶ የወሰዱትን አቋም ለማስረገጥ መረጃና ማስረጃ ለማግኘት ከመፈለግ የሚመጣ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ከምርምርና ከእውቀት ፍለጋ አመክንዖ ጋር በተቃርኖ የቆመ ስለሆነ ለመማርና ለመታረም እድል አይሰጥም፡፡ በመሆኑም ቢታሰብበት መልካም ነው እላለሁ፡፡

Filed in: Amharic