>

እየመረጡ በሁለት ሚዛን የመለካት አባዜ (በውብሸት ሙላት)

(ዐፄ ዘርዓያዕቆብን በማሰብ የተጻፈ)

በኢትዮጵያ ታሪክና ፖለቲካ ድርጊትና ሰዉ እየመረጡ በአባይ ሚዛን መሥፈርን ዐቢይ ተግባራቸው ያደረጉ ቡድኖች በርካታ ናቸው፡፡ ከድርጊት አንጻር፣ ከአገሪቱ አንድነት ጋር የሚገናኙትን በመምዘዝ፣ ከሰዎች ደግሞ ለአገሪቱ አንድነት ወደር የለሽ ተግባር የፈጸሙት ላይ ይገንናል፡፡ ድርጊቶቹን እንተውና መሪዎችን እንመልከት፡፡ መሪዎች ላይ ሲሆን ደግሞ ዐፄ ምኒልክና ዐፄ ዘርዓያዕቆብ ላይ የሚደርሰው በአባይ ሚዛን የመለካት ተግባር የበረታ ነው፡፡ የዛሬው ትኩረት ግን ዐፄዘርዓ ያዕቆብ ነው፡፡

በጽሑፍ እንደደረሰን፣ የታሪክ ባለሙያዎች እንደተነተኑት፣ ተቋማቱም እስካሁን በመቀጠል ምስክር እንደሆኑት ዐፄ ዘርዓያዕቆብ ገናና እና ታላቅ መሪ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ፣ ወቃሾቹና በአባይ ሚዛን ሰፋሪዎቹ፣ አገሪቱን ለሁለት ሊከፍል የነበረውን የሃይማኖት ክፍፍል እጅግ በሠለጠነ እና አሁንም ቢሆን ተምሳሌት ሊሆን በሚችል መንገድ መፍታቱን ማስታወስ አይፈለጉም፡፡

በተለይም ከዐፄ አምደጽዮን ጀምሮ መመለስ የጀመረውን የሥነ ጽሑፍ ሁኔታ ማንሳትማ በጭራሽ፡፡ እስከ ጎጃምና አንጎት (በአሁኑ አጠራር አብዝኃኛው ሰሜን ወሎ) ድረስ ማስገበር ጀምሮ የነበረውን መሠረቱ ዘይላ ላይ ከነበረው ከአዳል መንግሥት ጋር ተዋግቶ ያደረገውን ድል ማንም መዘከር አይፈለግም፡፡

በአባቱ ዘመን ተጀምሮ የነበረውን ማዕከላዊ የንጉሥ ጦር እና በየአካባቢው ያለውን ሰላም የሚያስጠብቅም በክፉ ጊዜም አብሮ ከማዕከላዊው መንግሥት ጋር የሚዘምት ከባሌ እስከ አሁኗ ኤርትራ፣ አፋር፣ ጎጃም፣ ጎንደር፣ ወላይታና ሲዳሞ አካባቢ ቋሚ የጨዋ ሠራዊት መመሥረቱን ማንሳት አይፈለግም፡፡ በቤተ ክርሥቲያን ላይ እስካሁን ድረስ የዘለቀ ማሻሻያ ማድረጉን ማስታወስ አይፈለግም፡፡ ሕግና ሥርዓት ለማስፈን የተጋውን ማንሳትም አይፈለግም፡፡ ሌሎችም በርካታ በጎ ተግባራቱን መዘርዘር ይቻላል፡፡

ዐፄ ዘርዓያዕቆብ እንደነገሠ በሕዝቡ ዘንድ ድንጋጤ መፈጠሩን የዜና መዋዕሉ ጸሐፊ ሳይቀር ነግሮናል፡፡ ለሕዝቡ የድንጋጤ ምንጭ የሆኑት ደግሞ ያስተላለፋቸው ቅጣቶች እንደሆኑም ጨምሮ ጽፏል፡፡ ዐፄ ዘርዓ ያዕቆብ ካስተላለፋቸው ቅጣቶች በብዙ መልኩ የሚጮኸው ‹‹ደቂቀ እስጢፋኖሶች›› ላይ የወሰደው ርምጃ ነው፡፡

ዐፄ ዘርዓ ያዕቆብ ግን ከደቂቀ እስጢፋኖሶቹ የበለጠ የጭካኔ ተግባር የፈጸመው በራሱ ልጆች ላይ ነው፡፡ ለዚያውም ሰይጣንና ጣኦት ማምለክ እንዲቀር በአገሪቱ ያሳለፈውን አዋጅ በመጣሳቸው በተሰጠ ቅጣት፡፡ በቅጣቱም ልጆቹ ሕይወታቸውን አጥተዋል፡፡ ይሄንኑም ለሕዝቡ በአደባባይ አሳውቋል፡፡ ልጆቹን መግደሉን ማንም አያሳዝነውም፡፡

የወራሴ መንግሥቱ የበእደ ማርያም እናት ‹‹ሥልጣን ለመገልበጥ አሲራለች፣ ተመካክራለች››ብሎ አስገርፏታል፤ ሞታለች፡፡ የእሷን ሞት ማንም አያስታውስም፡፡ የደቂቀ እስጢፋኖሶቹን ብቻ እንጂ፡፡
የልጆቹ ባሎች በዘመኑ እንደተለመደው ንጉሡን ሊያስገድሉ ተመሳጥረዋል ተብለው ተገርፈዋል፣ታስረዋል፤ የሞቱም አሉ፡፡ አባ ኖብም ጭምር ተቀጥተዋል፤ሞተዋልም፡፡ የእነዚህን ሞትና ቅጣት ማንም አያስታውስም፡፡ ሌሎች ምሳሌዎችንም መጨመር ይቻላል፡፡

እስኪ ዐፄ ዘርዓ ያዕቆብን ከሌሎች ነገሥታት ጋር እናነጻጽረው፡፡ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ በርካታ ቅዱሳን የጻድቅነትም የቅዱስነትም ማእረግ የተሰጣቸው በንጉሥ የተቀጡ፣ የተገረፉና የተገደሉ ናቸው፡፡ ቤተ ክርስቲያን የሞቱትን ‹‹ሰማዕታት›› ብላ ስትጠራ ነገሥታቱን ግን ጭራቅ አድርጋ በመሳል አይደለም፡፡ ይህ ዓይነት ወግ አልተለመደም፤ ኢትዮጵያዊም አይደለም፡፡

በኢትዮጵያ ታሪክ በተለይም ከዐፄ ይኩኖ አምላክ እስከ ዐፄ ልብነ ድንግል ድረስ በርካታ ቅዱሳን እና ሰማእታት ተብለው የተቆጠሩ ሰዎች የተከሠቱት በዐፄ ዓምደጽዮን ዘመን ነው፡፡ ዐፄ ዓምደጽዮን ምናልባትም ከአሁኗ ኢትዮጵያን ግዛት በላይ ባይሆን እንኳን የሚስተካከል አካባቢን አካሏል፡፡ አረማዊ የነበረውን የኅብረተሰብ ክፍል ሃይማኖታዊ እንዲሆን የማይተካ ሚና ፈጽሟል፡፡ ቢሆንም ደግሞ እነ አቡነ አኖሬዎስን፣ ፊሊጶስን ሌሎችም በከተማው አካላቸው እንዲጎተት ሁሉ አድርጓል፡፡

ይሁን እንጂ፣ አምደጽዮንን በማናቸውም መልኩ በክፉ አይነሳም፡፡
ለነገሩ እሱ አገሪቱን ባያስፋፋ ቅዱሳኑም ክርስትና የሚስፋፉበት ቦታም አልነበረም፡፡ እሱ ባያስገርፋቸውም ለእኛም ሰማእታት አይሆኑንም ነበር፡፡ ባስተማሩባቸውም ቦታ እንደቅዱስ ተቆጥረው ያስተማሩት ትምህርት ላይቀጥል ይችል ነበር፡፡ ሌሎችንም ምክንያቶች መዘርዘር ይቻላል፡፡ እናም፣ ዐፄ ዓምደጽዮንም እጅግ ታላቁ ንጉሣችን ነው፡፡ ሰማእትነት የተቀበሉትም እንዲሁ፡፡ የሁለቱም ጥምረት ነው አገር የመሠረተው፡፡ እንኳንስ ቤተ ክርስቲያኗ በይፋ ይቅርና እኛም ተራው ዜጋ ዐፄ አምደጽዮንን አንወቅስም፡፡ ገናናው ንጉሣችን ነው፡፡

እንዲህ ዓይነት ድርጊቶችን የፈጸሙ ነገሥታት በርካታ ናቸው፡፡ በገናናነታቸው ከሚጠቀሱት ውስጥ ዐፄ ፋሲለደስና ዐፄ ቴዎድሮስ ዳግማዊን ማንሳት እንችላለን፡፡ እጅግ የምንኮራባቸው መሪዎቻችን ናቸው፡፡ ሰዉ ስላልገደሉ አይደለም፡፡ በድምሩ ስለፈጸሙት ድርጊትና ለአገራችን ስላበረከቱት እንጂ! ምናልባት እነዚህ ሁለት ነገሥታት በገደሉት ሰዉ ከሆነ ከዐፄ ዘርዓያዕቆብ ጋር ሲነጻጸር በማናቸውም መለኪያ አይወዳደሩም፡፡ ነገር ግን ወቀሳው ደግሞ የሰማይና መሬት ያህል ይራራቃል፡፡ እነሱ የቀጧቸው ደቂቀ እስጢፋኖሶች ስላልሆኑ ነውን?

በመግደልማ የመጽሐፍ ቅዱሱ ሙሴና ዳዊትም ገድለዋል፡፡ ነገር ግን ነብያትም ነገሥታትም ናቸው፡፡ በተለይ ደግሞ ንጉሥ ዳዊት ፈጣሪም “እንደልቤ” ነው ያለው፡፡ ግን ኦርዮንን ሳይቀር ለቤርሳቤህ ሲል ጦር ሜዳ በመላክ ያስገደለ፡፡ ቅዱስ ዳዊት ግን ቅዱሳችን ነው፤ ስላልገደለ ወይንም ስላላስገደለ ግን አይደለም፡፡ ዐፄ ዘርዓያዕቆብ ላይ ቅንጣት ታክል ለመረዳት ፍላጎት የማያሳዩት ከእሱ የባሰ ብዙ ሰው የቀጡትን ግን ‹‹ቅዱስ›› ብለው ሲጠሩ በደስታ ነው፡፡ ለእሱ ሲሆን ሚዛናቸው ሌላ ነው፡፡

ምንም ጥርጥር የሌለው ነገር ቢኖር ደቂቀ እስጢፋኖሶቹ ተቀጥተዋል፡፡ ይሁን እንጂ፣ እነ አባ እስጢፋኖስ በትግራይ ከሚገኙ ገዳማት ሸሽተው ወደ ጎጃም እና ጎንደር ተሰደው እንደነበር ገድላቸው ይናገራል፡፡ ቀድመው የነበሩባቸው ገዳማት አበምኔቶች “ምህረት አድርገንላችኋል” በማለት ጠርተው ኋላ ገረፈዋቸዋል፣ ወደ ንጉሡም ከሰዋቸዋል፡፡ ስለከሳሾቹ ግን ማንም አያነሳም፡፡ ንጉሡ ያወጀውን፣ ቀድሞ የጨረሠውን አገር የሚከፋፍል እንቅስቃሴ መፍትሔ ካበጀ በኋላ እንደገና ሌላ ቡድን በመሆን መነሳታቸውን ማስታወስ አይፈለግም፡፡
ከተፈረደባቸውም በኋላ፣ የሞት ፍርዱን ወደ ዕድሜ ልክ እስራት ቀይሮላቸዋል፡፡ ይሁን እንጂ፣ ቅጣቱን እንደ ፍርዱ ለመፈጸም አልፈለጉም፡፡ ቅጣቱን ወደጎን በመተው የቀደመ ድርጊታቸውን ቀጥለዋል፡፡ ንጉሡ በወቅቱ ያጋጠመውን ሁኔታ ምናልባት ከፕሮፌሰር ታደሰ ታምራትና ከቤተ ክርስቲያኒቱ ውጭ የተረዳውና ለመረዳትም የፈለገ ያለ አይመስልም፡፡

ቤተ ክርስቲያኗ እነ አባ እስጢፋኖስንም ‹‹ቅዱስ›› እንደሆኑ በመቁጠር ገዳማትም ተገድሞላቸዋል፡፡ ደብረ ገሪዛን የዚህ ማሳያ ነው፡፡ ዐፄ ዘርዓያዕቆብም እንደ ሌሎች ሁሉ ቅዱስ ባይባልም ጻድቅ እንደሆነ ተቆጥሮ ስሙ ስንክሳር ላይ ገብቶ በጸሎት ይታሰባል፡፡

በአጠቃላይ ዘርዓ ያዕቆብ ላይ የሚሰነዘረው ዘመቻ ልክ እንደ ዐፄ ምኒልክ ሁሉ ሚዛኑ የተለየ፣ ለሌሎች የሚጠቀሙበትን በመተው ነጠላ ዘሃ በመምዘዝ ሚዛን በመስቀል የሚደረገው የሚያስተዛዝብ ነው፡፡

እኛ ግን ዋኖቻችን እንንቅ ዘንድ፣ እናዋርድ ዘንድ ‘ከዝሙት አልተወለድንም’፡፡ ‘ንሕነሰ ኢተወለድነ እምዝሙት’ በማለት አለቃ ኤስድሮስን አላግባብ ለመተቸት ተማሪዎቹ የተጠቀሙበትን አገላለጽ ተጠቅመናል፡፡ ነገሥታቱም፣ የተገረፉትም ደቂቀ እስጢፋኖሶቹንም ጨምሮ ሁሉም ለእኛም ለአገሪቱ ዋኖቻችን ናቸው፡፡

Filed in: Amharic