>

''...የህወሃት አገዛዝ ዕድሜ በማሳጠር የነጻነት ቀን ለማፋጠን የሚያስችል ውሳኔ ከዚህ ጉባኤ ይጠበቃል!''

[ከህዝባችን ጎን ቆመን ለመፋለምና የህወሃት አገዛዝ ዕድሜ በማሳጠር የነጻነት ቀን ለማፋጠን የሚያስችል ውሳኔ ከዚህ ጉባኤ ይጠበቃል]
 አርበኛ ታጋይ ፕሮፈሰር ብርሃኑ ነጋ 
(የአርበኞች ግንቦት 7 ድምፅ ሬዲዮ).

የአርበኞች ግንቦት 7 ለአንድነትና ዲሞክራሲ ንቅናቄ የመጀመሪያውን አጠቃላይ ጉባኤ በማካሄድ ላይ ይገኛል።
ጥር 2 ቀን 2007 አመተ ምህረት በቀድሞ የኢትዮጵያ ህዝብ አርበኞች ግንባር እና የግንቦት 7 የፍትህ ፡ የነጻነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ውህደት የተመሠረተው የአርበኞች ግንቦት 7 ንቅናቄ የመጀመሪያ ጉባኤውን ከትናንት በስቲያ ረቡዕ ጵጉሜ 1 ቀን 2009 ዓመተ ምህረት ምሽት ጀምሮ ኤርትራ ውስጥ በማካሄድ ላይ እንደሚገኝ ታውቋል።
ንቅናቄው በማካሄድ ላይ በሚገኘው በዚህ የመጀመሪያ ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ ከተለያዩ ክፍለ አለማት የመጡ የንቅናቄው አባላት ተሳታፊ ሲሆኑ ኤርትራ በረሀ ውስጥ የሚገኙ የንቅናቄው ሰራዊት አባላት ተወካዮችም መገኘታቸው ተሰምቷል።
ረቡዕ ማታ የተጀመረውን የንቅናቄውን ጉባኤ በንግግር የከፈቱት ሊቀመንበሩ አርበኛ ታጋይ ፕሮፈሰር ብርሃኑ ነጋ ሲሆኑ ፕሮፌሰሩ ባቀረቡት የመክፈቻ ንግግር ላይም ሁለቱ ድርጅቶች ከተዋሃዱ ወዲህ ላለፈው ሁለት አመት ከስምንት ወራት ንቅናቄው የተጓዘባቸውን ሂደቶችና የገጠሙትን ተግዳሮቶች በአጭሩ አብራርተዋል። አርበኛ ታጋይ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በተለይ አጽንዖት ሰጥተው ያተኮሩበት ዋና ነጥብ አገራችን ውስጥ ለእኩልነትና ለፍትህ እየተካሄደ ባለው ህዝባዊ እምቢተኝነት ላይ ሲሆን ይህ ህዝባዊ እንቅስቃሴም የደረሰበትን ምዕራፍ በማስረዳት ከህዝባችን ጎን ቆመን ለመፋለምና የህወሃት አገዛዝ ዕድሜ በማሳጠር የነጻነት ቀን ለማፋጠን የሚያስችል ውሳኔ ከዚህ ጉባኤ እንደሚጠበቅ አሳስበዋል።
አርበኞች ግንቦት 7 ከተዋሃደ ወዲህ በአገራችን ኢትዮጵያም ሆነ በድርጅታቸው ውስጥ በርካታ ክስተቶች ተፈጥረው እንደነበር በመግቢያ ንግግራቸው የገለጹት ፕሮፈሰር ብርሃኑ ነጋ ፤ በኦሮሚያ ፤ በአማራ ፤ በጋምቤላ ፤ በኮንሶ ፤በሃመር፤ በጉጂ፤ በኦጋዴን እና በሌሎች የአገራችን ክፍሎች ህወሃት ሥልጣን ከተቆጣጠረ ወዲህ ሲደረጉ ከነበሩ የትግል አይነቶች በአይነትም ሆነ በመጠን የተለየ ሁኔታ መመዝገቡን ገልጸዋል። በዚህም የተነሳ አገዛዙ በተለመደው መንገድ መግዛት ተስኖት በምዕራባዊያን ወዳጆቹ ፊት ጭምር የነበረውን ግርማና ሞገስ የናደ እርምጃ ብቻ ሳይሆን በጠመንጃ ሃይል ካልሆነ በቀር ህዝባችንን ለማስተዳደር ምንም አይነት ህዝባዊ መሠረት እንደሌለው የሚያጋልጥ እርምጃ በመውሰድ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እስከማወጅ ደርሶ እንደነበርና ህዝባችን ለለውጥ ያለው ቁርጠኝነት የተፈለገውን ውጤት ሊያስገኝለት እንዳልቻለም አስረድተዋል።
በመጨረሻም ይህ ጉባኤ በንቅናቄው ውስጥ የተከሰቱትንና ትግሉን በቁርጠኝነት ለመግፋት እንቅፋት የሆኑትን ችግሮች በሚገባ መርምሮ የማስተካከያ እርምጃ በመውሰድና በአገራችን ችግሮች ላይ ተነጋግሮ በአጭር ጊዜ ውስጥ ትግሉን ለመቋጨት የሚያስችል ውሳኔዎችን በማስተላለፍ የተጣለበትን ታሪካዊ ሃላፊነቱን እንዲወጣ አሳስበዋል።

በዚህ የአርበኞች ግንቦት 7 የመጀመሪያ ጉባኤ ምሽት ላይ ከተገኙ እንግዶች መካከል የትግራይ ህዝብ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ ሊቀመንበር ታጋይ መኮንን ተስፋዬና ሌሎች ከኤርትራ መንግስት የተወከሉ ባለስልጣናትም በቦታው መገኘታቸው ታውቋል።
የትህዴኑ ሊቀመንበር ታጋይ መኮንን ተስፋዬ ጉባኤው የተሳካ እንዲሆን በድርጅታቸው አባላትና አመራር ሥም መልካም ምኞታቸውን ከገለጹ በኋላ ድርጅታቸው ከአርበኞች ግንቦት 7 እና ለዲሞክራሲ ከሚታገሉ ሌሎች ድርጅቶች ጋር ሆኖ የወያኔን ሥርዐት ለማስወገድ ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል። ቀጥለውም አገራችንንና ህዝባችንን ለውርደት ያበቃው የህወሃት አገዛዝ በምንም በኩል የትግራይ ህዝብ ተወካይ እንዳልሆነ ጉባኤውም ሆነ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ እንዲረዳም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ከመክፈቻ ንግግሮቹ በኋላ በአርበኞች ግንቦት 7 አደራ የኪነት ባህል ቡድን የተዘጋጀና ታዳሚውን በከፍተኛ ስሜት ያነሳሳ “የፍጻሜ ትግል” የተሰኘ መሳጭ የመድረክ ቴአትር የቀረበ ሲሆን በመቀጠልም ታዋቂው የኢትዮጲያ የቁርጥ ቀን ልጅ በመባል የሚታወቀው አርቲስት ሻምበል በላይነህ ቀስቃሽ የሆኑ ሙዚቃዎቹን በመጫወት ተሳታፊዉን በሞራልና በስሜት ሲያዝናና እንደነበር ተውቋል።በኪነት ቡድኑ አባል የተደረሰ የኦሮምኛ ቋንቋ ስነግጥምም መነበቡ ተገልጿል።
አርበኞች ግንቦት 7 ባለፈው ረቡዕ ምሽት ከጀመረው የመክፈቻ ዝግጅት በኋላ በጉባኤው መርሃ ግብር መሠረት ትናንት ሃሙስና ዛሬ አርብ ጳጉሜ 3 የሥራ አስፈጻሚውና የተለያዩ ዘርፎች ያቀረቡትን ሪፖርቶች በማዳመጥ በሪፖርቶቹ ላይ ሰፊ ውይይት አካሂዶአል። ጉባኤው በሚቀጥሉት ቀናት ውሎው የድርጅቱን መዋቅር፤ የትግል ስትራቴጂና መተዳደሪያ ደንቦችን ፈትሾ አስፈላጊውን ማሻሻያ በማድረግ የአመራሮች ምርጫ በማካሄድና የተለያዩ ውሳኔዎችን በማስተላለፍ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።

Filed in: Amharic