>
5:13 pm - Sunday April 19, 8663

የዝምታየን ግድብ አስጣሰኝ (ታምራት ታረቀኝ)

ከተደጋጋሚ እስር በኋላ በቅረቡ ከተፈታው ወዳጄ ዳንኤል ሽበሺ ጋር ባለፈው ሳምንት በስልክ ተገናኘን፡፡ግንኑነታችን አንድም ከረዠም አመት በኋላ ሁለትም እሱ ከእስር በተፈታ ማግስት ቢሆንም በእንዴት ነህ አንዴት ነህ መጠያየቅ ብዙ አልቆየንም፡፡ አንዴ ተለክፈናልና ጭውውታችን ወደ ሀገር ጉዳይ ወደ ወቅታዊው የፖለቲካ ሁኔታ የገባው በደቂቃዎች ውስጥ ነበር፡፡ የአጠቃላይ የሀገራችን የፖለቲካ ሁኔታ ሲነሳም የፖለቲካ መድረኩ ተዋናይ ሆነው የሚታዩትን ግና መሆን ቀርቶ የተሰለፉበትን ገጸ ባህርይ መመሰልና ማስመሰል ያልቻሉት ፖለቲከኞችና ሀሳበ  መንገድም የሚመሩት ድርጅት መነሳቱ አይቀሬ ነው፡፡

እናም እኔ ወዳጄ በወፍ በረር ስንቃኝ እሱ እስር ቤት ባለበት ወቅት ነበርና ፓርቲው አንድነት እንዳይሆኑ የሆነው ስለ አንድነት የሚለውም የሚያደርገውም የለሌው ወዳጄ የሰማያዊ ፓርቲን ችግር ለማስወገድ ብዙ ጥሮ አንዳልተሳካለት ነገር ግን አሁንም ተስፋ አንዳልቆረጠና ሌሎች ሰዎችን በመያዝ ለማሸማገል፣ ለማገላገል፣ለማደራደር የሁለቱንም ወገን በር እያንኳኳ አንደሆነ ሲነግረኝ አእምሮዬ ፈጥኖ አንተስ የሚል ጥያቄ አጫረብኝ፡፡

ከዳንኤል በቀረበ ሁኔታ እኔ ስለ ሰማያዊ አውቃለሁ ብዬ አስባአለሁ፣ ማወቅ ብቻ አይደለም ከምስረታው ጀምሮ መንገራገጩ ከጓዳ አልፎ አደባባይ እስከበቃበት ግዜ ድረስ ያ እንዳይሆን ሰሚ ያላገኘ ጩኸት ጩኸት ጮኬአአለሁ፣ አንባቤ ያላገኘ አስተያየት ጽፌአለሁ ለውጤት ያልበቃ ጥረት አድርጌአለሁ፡፡ እኔ በዚህ ተስፋ ቆርጬ ዝምታን ስመርጥ ወዳጄ ዳንኤል ግን እስር እንግልቱ ተስፋ ሳያስቆርጠው ከእስር በወጣ ማግስት ሰማያዊዎችን ለመሸምገል ያደረገውን ጥረት መስማቴ ነው አንተስ የሚል ጥያቄ ያጫረብኝ፡፡ እናም የዝምታዬን ግድብ ጥሼ  ምን አልባት ለወዳጄ ችግር የመፍታት ጥረት ድጋፍ ሊሆን ከቻለ በሚል እገዛየ አንደማይለየው ለመግለጽ ጭምር  ነው ይህችን አስቴያየት መጻፌ፡፡

የኋላው ከሌለ የለም የፊቱ፡

ይልቃልና የሺዋስን ያስተዋወቀን አንድነት ፓርቲ ነው፡፡ ይልቃል በኢ/ር ግዛቸው ይመራ የበረው የድርጅት ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ጸሀፊ የሺዋስ ደግሞ በእኔ ይመራ የነበረው የወጣቶች ጉዳይ ምክትል ኃላፊ ነበሩ፡፡ ከዛ አልፎ ደግሞ ዝም አንልም መርህ ይከበር በሚለው አንቅስቃሴ ይበልጥ ተዋወቅን፡፡ ያንን ወቅት መለስ ብዬ ሳስበው አንዳንዶቹ ያኔ ይናገሩት የነበረውና ሰማያዊ ፓርቲን ከመሰረቱ በኋላ የሰሩትና የሚሰሩት ፈጽሞ የማይዛመድ መሆኑ ርህ ይከበር ብለው የጮሁና በዚሁ ምክንያት ከፓርቲ ለመለየት የበቁ የፓርቲ ህገ ደንብ የማያከብሩ ለመርህ የማይገዙ ሆነው ሳይ ፖለቲካችን ስር ነቀል ለውጥ እንደሚያስፈልገው ነው የገባኝ፡፡ የአስተሳሰብ ለውጥ፡፡ ለዚህ ሳያ የሚሆን ብዙ ማስረጃ ማቅረብ ቢቻልም የዚህ ጽሁፍ ዓማ ወዳጄ ዳንኤልና ሌሎች ለሚያደርጉት ውስጥ ችግርን በውስጥ ለመፍታት የመሞከር ጥረት እገዛ ማድረግ በመሆኑ ቢያንስ ለአሁን አስፈላጊ አይደለም፡፡ ነገር ግን ችግሩ ከሁለት በአንዱ ወይንም በሁለቱም ወገን ሻፈረኝ ባይነት እልባት አላገኝ ብሎ አካፋን አካፋ ማለት የግድ ከሆነ ማስታወሻየን ማየትና ማሳየት እጀምራለሁ፡፡

እህልን ከጥቅምት ልጅን ከጡት፣

የእንግሊዝ ጠቅላይ ምኒስትር የነበሩት ወ/ሮ ማርጋሪት ታቸር የፖለቲከ ስህተትና የሳንባ ነቀርሳ ጠንቆች የተመሳሳይነት ባህርይ አላቸው፡፡ ሁለቱም ችግሮች በለጋነታቸው ወቅት ከተነቃባቸው ችግሮቹን የማስወገድ ዕድል ከፍተኛ ነው፡፡ ችግሮቹ ሥር ከሰደዱ በኋላ የሚደረገው መሯሯጥ ግን ፈውስ የማስገኘቱ ሁኔታ አስቸጋሪ ብቻ ሳይሆን የማይቻልም ሊሆን ይችላል፡፡ ” በማለት መናገራቸው ይነገራል፡፡ ከሰማያዊ በፊት አራት ፓርቲዎችን በቅርብ አወቅ ነበርና ሰማያዊም ሌሎቹን ያጠቃው በሽታ ተጠቂ አንዳይሆን በማሰብ  በምስረታው ማግስት ነበር የአቅሜን ጥረት የጀመርኩት፡፡ የሰማያዊ ነገር ፍየል ከመድረሷ ቅጠል መበጠሷ አንዳይሆን በሚል ርእስ በጣፍኩትና ለስራ አስፈጻሚ አባላቱ በየግል በማድረስ የጀመረው ይህ ጥረቴ   ሊቀመንበሩን ይልቃልን ጨምሮ አብዛኛዎቹን የአመራር አባላት ከማነጋገር እስከ ለሥራ አስፈጻሚውም ለምክር ቤቱም ደብዳቤ እስከ መጻፍ ደርሶ የነበረው፡፡ ከዚህ አልፎም አንጃ የሚለው ቃል በይልቃል ወገን በነበሩ ሰዎች ተደጋግሞ ሲነገር በመስማቴ በዚህ ደረጃ ከተፈረጁት መካከል አራት ከስራ አስፈጻሚ አባላቱ ደግሞ ሊቀመንበሩን ጨምሮ አራት በጥቅሉ ሰምንት ሰዎችን በማገናኘት እንዲወያዩ፣ ለማድረግ ችየ ነበር፡፡ ቃል የእምነት እዳ ሳይሆን ቀረና የተነጋገሩትን ሁሉ ገደል ከተው ስምምነታቸውንም አፍርሰው በጀመሩት መንገድ ቀጠሉ እንጂ፡፡( ምንም እንኳን በጽሁፍ የሰፈረ ባይኖርም) አልሆነባቸውምና  የተነጋሩትን ሁሉ ገደል ከተው ሞክሬአለሁ የገቡት ቃል ባይከበርም፡፡ሌላም ሌላም መግለጽ ቢቻልም ፡፡በዚህ ሁኔታ ነገሮችን በጠዋት መፍታት ባለመቻሉ ነው ነገሩ ከሮ ይልቃል እና ተከታዮቹ የዝም አንልምን፣ የየሺዋስ ወገን ደግሞ የኢንጅነር ግዛቸውን ቦታ ለመያዝ የበቁት አሳፋሪ፡፡ እኛ ወጣቶች እያሉ ሲመጻደቁ ለነበሩ ሰዎች ይህ በጣም አሳፋሪ ነው፡፡ ሀፍረት ይሉ ነገር በወያኔ ሰፈር ብቻ ሳይሆን በአጠቃልይ በፖለቲካው መንደር የሌለ መሆኑ እንጂ፡፡

ከላይ በሰፈረው የወ/ሮ ማርጋሪት ንግግር ውስጥ ችግሮቹ ሥር ከሰደዱ በኋላ የሚደረገው መሯሯጥ ግን ፈውስ የማስገኘቱ ሁኔታ አስቸጋሪ ብቻ ሳይሆን የማይቻልም ሊሆን ይችላል፡፡ የሚል  ቢገኝም ቅንነቱ በተለይም ከራስ በላይ ማሰቡ ካለ የማይቻል ነገር አይኖርምና አባልና ደጋፊ የሚባለው ጎራ ለይቶ ከተያያዘው ጫጫታና ሁካታ ወጣ ብሎ ግለሰቦች ላይ ሳይሆን መሰረታዊው ጉዳይ ላይ ማተኮር ቢችል፣ ለኢትዮጵያ በጎ የሚያስቡ  አባልም ደጋፊም ያልሆኑ ወገኖች ደግሞ  ይመስለኛል የእነ ዳንኤልን ጥረት ማገዝ ቢችሉ መፍትሄው ቀላል ነው፡፡

የፖለቲካችን ችግር መፍትሄው የፓርቲ ወይንም የመሪ ግለሰቦች ለውጥ ሳይሆን የእያንዳንዱ ሰው የአስተሳሰብ ለውጥ ስለመሆኑ ሰማያዊ በቂ ማስረጃ ነው፡፡ከሽማግሌዎቼ ጋር መስራት ባለመቻላችን ወጣቶች አዲስ ፓርቲ መሰረትን ብለው ከሶስት አመት በላይ ሳይዘልቁ ውስጥ ለውስጥ ከመጎሻሸም አልፈው በአደባባይ ለመዘላለፍ መብቃታቸው በአምስተኛ አመታቸው በሁለት ጎራ ቆመው አንዱ ፓርቲ አንዱ ሸንጎ መባባላቸው ችግሩ ከአጠቃላይ የፖለቲካ ባህላችን የሚመነጭ ይመስለኛል፡፡ ከአንድነት የተለየነው ችግሮችን በውይይ መፍታት ልዩነትን በመከባበር ማስተናገድ ባለመቻሉ ነው ያሉን ሰዎች ዛሬ እነርሱ ከግል ፍላጎት ያልዘለለ ችግራቸውን መፍታት ተስኖአቸው እንዲህ ሲሆኑ ማየት በእውነቱ የሳዝናል ያሳፍራል፣፡እናም ለሰማያዊ የሚፈለገው መፍትሄ አጠቃላይ የፖለቲካ ባህላችንን ህመም የሚያክም ነው የሚሆነው፡፡  ስለሆነም እየተንከባለለ እኛ ዘንድ የደረሰው ይህ የመጠላፍና የሴራ የፖለቲካ ወደ ልጆቻችን እንዳይሸጋገር ሁላችንም ኃላፊነት አለብን፡፡ ይህ ሊሆን የሚችለው ደግሞ  እያንዳነዱ ሰው በራሱ ውስጥ የአስተሳሰብ ለውጥ ማድረግ ከቻለ ብቻ ነው፡፡ ሰው ራሱን መሆን ሲችል አፈ ጮሌዎች በሰሜት የሚቀሰቅሱት አለያም በተለያየ ሰበብና ምክንያት በአጃነት የሚያሰልፉት ጀሌ ስለማያገኙ እኔ ያልኩት ካልሆነ በማለት ካልባሁት ጭሬ ላፍሰው ተግባር ለመፈጸም አይቻላቸውም፡፡ እርቅ አይገፉም ከድርድር አያፈነግጡም፡፡ፓርቲ አይከፋፍሉም፣ለፍረጃና አሉባልታቸው ሰሚ አያገኙም፡፡

አባልና ተከታዩ፣

በዘመን አመጣሾቹ የመገናኛ ዘዴዎች በሚደረግ ጩኸት ፓርቲን ማዳን ይቻል ቢሆን ኖሮ አንድነት ባልሞተና በመቃብሩ ላይ ዳንኪራ ባልተረገጠ ነበር፡፡ ይህ እንደማይቻል ከደረሰባቸውም ካደረሱትም ማር ያልቻሉ ወይንም ያልፈለጉ ማህበራዊ መገናኛውን የጦርነት አውድ ሊደርጉት ሲዳዳቸው ማየት ከራሳቸው ፍላጎትና ጥቅም አልፈው የማያስቡ መሆናቸውን ነው የሚያረጋግጠው፡፡ እናም አባላትም ሆናችሁ ደጋፊዎች በውስጥም በውጪም የምትኖሩ ትንሽ ነገር ሲፈጠር ሮጦ ፌስ ቡክ ላይ መንጠልጠሉና አንዱን ደግፎ ሌላኝውን ነቅፎ ያዙኝ ልቀቁኝ ማለቱ እስከዛሬም አልበጀ ወደ ፊትም አይበጅም እና አንተወው፡፡ ከዚህ ይልቅ የምትደግፉት ወገን ለእርቅና ለድርድ ራሱን እንዲያስገዛ ህግና ደንብ አክብሮ እንዲሰራ አቅሙን አውቆ ልኩን ተረድቶ አንዲኖር መምከር ማገዙ ነው የሚበጀው ፡፡ አጉል ጭብጨባ አበው ልቤ አደገና ያለ ቁመቴ አላስገባ አለኝ የገዛ ቤት ለሚሉት አደጋ የዳጋቸው ብዙዎች የት ይደርሳሉ የተባሉ ሰዎችን አሳጥቶናል፡፡ ድጋፋችንም ሆነ ነቀፋችን በእውነት ላይ የተመሰረተ ከጎሳ ከሀይማኖት ከግልጥላቻና ፍቅር የጸዳ ይሁን፡፡አብልነታችሁም ሆነ ደጋፊነታችሁ ለፓርቲው እንጂ ለግለሰቦች አይሁን፡፡

ለይልቃልና ለየሺዋስ፣

የሺዋስ  የምክር ቤቱ ምክትል ሰብሳቤ ነበርክና ችግሮችን በምክር ቤት ደረጃ እንዴት መፍታት ይቻላል በሚል ከመታሰርህ ቀናቶች አስቀድሞ የተነጋገርነውንና ምክር ቤቱ በአንድ ኮሚቴ ውስጥ መድቦን ጀምረነው የነበርነውን ስራ የምትሰራው አይመስለኝም፡፡ በግል አንተን አስመልክቶ የተነጋገርነውንም እንዲሁ፡፡ ይልቃልም በተደጋጋሚ ቢሮህ እየመጣሁ ለብቻ በር እየዘጋን የተነጋገርናቸውን ትዘነጋለህ ብየ አላስብም፡፡ እንደውም እንደሌሎቹ ምስጋናና ውደሳ ሳይሆን ትችትና ነቀፋ በማብዛቴ ሚስተር አቃቂር የሚል ቅጽል ስም ሰጥተኸኝ እንደነበር ከዚህ አልፎም የሽማግሌ ባህርይ ይታይብሀል ያልከኝን የምትረሳው አይመስለኝም፡፡ ሌላም ሌላም፡፡ ይህን ማንሳቴ ስለ ራሴ የማውራት አባዜ ኖሮብኝ ሳይሆን የሰማያዊን በሽታ ምን ያህል ከጅምሩ እንደማውቅ ለመጠቆም ነው፡፡ በሽታውን ያላወቀ መድሀኒት የለውም ነው የሚባለው፡፡

የእርስ በእርስ እልሁን ተውትና ከምር ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ከሆነ ዓላማችሁ  ለለውጥ ከሆነ ትግላችሁ፣ በእምነት ከሆነ ወያኔን መቃወማችሁ እልሀችሁ ርስ በርስ ሳይሆን ከወያኔ ጋ ይሁን፡፡ አብሮ አደግነታችሁን ለአወኩሽ ናኩሽ ሳይሆን ለመተማመኛ መሰረት እስከ ቀራኒዮ አብሮ ለመዝለቅ ዋስትና አድርጉት፡፡ ተከታዮችም በግለሰቦች የምትነዱ ሳይሆን ፈጣሪ ከአንስሳት ሁሉ ለይቶ በሰጠን ጭንቅላት የምትመሩ እውነትን ከሀሰት የምትመረምሩ፣ የሚያብለጨልጭ ነገር ሁሉ ወርቅ አለመሆኑን የምትረዱ ሁኑ፡፡ በውጪ የምትኖሩ ኢትዮጵያውያንም ገንዘባችሁን የምታውሉበት የተቸገራችሁ ይመስል ሰዎች በረባ ባልረባ ተለያይተው ማዶና ማዶ ቆመው የነገር ጅራፍ ማጮኸ ሲጀምሩ፣ የመራረጅ አሉባልት ሲቆምሩ፣ ወገን ለይታችሁ በፕሮፓጋንዳ የምታግዙ በገንዘብም የምትረዱ ከመሆን ብትቆጠቡና እውነትን ፈላጊዎች የአንድነትን መሰረት አጥባቂዎች መሆን ብትችሉ መልካም ነው፡፡ ለማስታረቅ የዘንባባ ዘንጣፊ ይዛችሁ የምትቀርቡ እንጂ የእብድ ገላጋይ ሆናች ጠብ የምታባብሱ፣ በትንሽ እሳት ላይ ቤኒዚን እየጨመራችሁ የምታቀጣጥሉ ባትሆኑም እንዲሁ  መልካም ነው፡፡ ይህን ማድረጉ ደግሞ የተለየ እውቀት አይሻም፣ ገንዘብም ሆነ ጉልበት አያስወጣም፤ ሰው መሆን ብቻ በቂ ነው፡፡  እኔ ሰው የምለው ከትከሻው በላይ ጭንቅላቱ የከበደው ነው ያለው ማን ነበር !

የምንገኘው በአዲስ ዓመት ዋዜማ ላይ ነው፡፡የአዲስ ዓመት አዲስነቱ በእድሜአችን ላይ አንድ ቁጥር መጨመሩ ብቻ እየሆነ ይሄው ሀገራዊ ለውጥ ማምጣት ቀርቶ በየግል የአስተሳሰብ ለውጥ ማምጣት አልሆንላችሁ ብሎን ወይ ወደ ኋላ ወደ ቅድመ አያቶቻችን ስልጣኔ መመለስ ወይ ወደ ፊት አለም እየገሰገሰ ወደአለበት የዴሞክራሲ ምህዳር መሻገር ተስኖን አንድ ቦታ ቆመን አመት አንቆጥራለን፡ እስቲ ለየራሳችን ቃል እንግባና የመጣንበት መንገድ የትም አያደርሰንም፣ የያዝነው አስተሳሰብ ፍቅር አይመጣም አንድነትን አይፈጥርም የአንድ ሀገር ልጆችን በአንድነት ቀርቶ የአንድ ፓርቲ አባላትን በአብሮነት አያቆምም ይህን ደግሞ ባለፉት አመታት በደንብ ተረድቻለሁ በዚህ አስተሳሰብና መንገድ ዴሞክራሲን እውን ማድረግ እንደማይቻልም በበቂ ተምሬአለሁ ስለሆነም በዚህ አመት የአስተሳሰብ ለውጥ ለማምጣት ቃል እገባለሁ በሉ፡፡ ለማለት ሳይሆን ለመፈጸም ለፕሮፓጋንዳ ሳይሆን ለተግባር፡፡

ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለስላሴ ጥቅምት 23/1935 ዓ.ም ለፓርላማ አባላት ካሰሙት ንግግር የተወሰደ ተብሎ ከሚጠቅሳለቸው ውስጥ  “የሚመከረው ነገር በዝግታና በጥልቅ ታስቦ በለዘብታ ክርክር ተጣርቶ በትእግሥት እየተመላለሰ ተመክሮ የተቆረጠ ነገር እንዲሆን ነው፡፡” የሚል ዘመን ተሻጋሪ ምክር ይገኛል፡፡ ይህ ባለመሆኑ ነው ወያኔ ግዜ እየጠበቀ በሚሰጠን ኳስ እየተጫወትን፣ ሙቀት ትኩሳታችን እየለካ በሚለቅልን አጀንዳ እየተወራከብን፤ ብዙ ተባዙ የተባለው ለፓለቲከኞች ይመስል እንደ አሜባ መባዛት እንጂ መጠንከር አልሆንላችሁ ብሎን የኋላው ቢቀር  ሀያ ስድስት አመት አስቆጠርን፡፡ እልህ የለ ቁጭት የለ ማረር የለ ወሬ ብቻ! እስቲ ዛሬ አሁን በዚህ አዲስ አመት በሙሉው ቁጥር መጀመሪያ ችግራችን ይወገድ ሀጃችን ይሙላ ብለን ወደ ሌላው የምንቀስረውን ጣት ወደ ራሳችን ለማዞር የሚደፍር አቅምና ወኔ ለመፍጠር ቃል እንግባ!!

Filed in: Amharic