>
4:01 pm - Saturday September 29, 2249

አክሱም ጽዮን ተመልካች አጥታለች !

አርክቴክት ዮሃንስ መኮንን

በኢትዮጵያ ታሪክ ለቤተ መንግስትም ሆነ ለቤተ ክህነት ቀደምት ማዕከል የሆነችው አክሱም ጽዮን ቤተክርስቲያን ለአደጋ ተጋልጣለች፡፡ ይህንን ያየሁት ሰሞኑን ለእረፍት ወደዚያው ባቀናሁበት ወቅት ሲሆን ሁለት ዋና ዋና ችግሮችን ታዝቤአለሁ፡፡

1ኛ) በግርማዊ ቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ የታነጸው ዋናው የአክሱም ጽዮን ቤተክርስቲያን ከውስጥ በኩል ዙሪያውን ያፈሳል፡፡ ባያያዝኩት ፎቶግራፍ ላይ እንደምትመለከቱት ካህናቱ ቢቸግራቸው ቤተመቅደሱ ውስጥ ፕላስቲክ አንጥፈው እና በርካታ ባልዲዎችን ደርድረው ፍሳሹን ለመከላከል ቢሞክሩም ችግሩ ግን ከዚያም የከፋ ሆኖ መቅደሱን ውሃ በውሃ አድርጎታል፡፡ ስለዚህ አፋጣኝ የሆነ በባለሙያ የታገዘ ጥናት አድርጎ መፍትሔ ካተበጀለት የሚሠርገው ውሃ የመዋቅር ብረቶቹን በማዛግ ከዚህም ወደከፋ የጉዳት ደረጃ እንዳያደርሳት ያሠጋል፡፡ ስለዚህ ይዋል ይደር ሳይባል አፋጣኝ መፍትሔ (አሁኑኑ) ያስፈልጋታል፡፡

2ኛ) በቂ ጥናት ያልተደረገባቸው አዳዲስ ግንባታዎች ታሪካዊቷን እና ጥንታዊቷን በተመቅደስ ከእይታ ጋርደዋታል፡፡ ግርማዋንም ክፉኛ ተገዳድረዋታል፡፡ አክሱም ጽዮን የአክሱም ከተማ እና ታሪክ እንብርት ብትሆንም አሁን ግን እነኚህ ግንባታዎች አደብዝዘዋታል፡፡ ከከተማዋም ነጥለዋታል፡፡ በተለይ! በተልይ! ለሙዝየምነት ታስቦ በዋናው ንገድ እና በቤተ መቅደሶቹ መካከል በኮንክሪት የተገነባው (በእኔ አመለካከት ቦታውንም አክሱምንም የማይመጥን) ባለ 4 ፎቅ ህንጻ ታካዊ ስህተት ይመስለኛል፡፡ እናንተው ምስሉን ዓይታችሁ ፍረዱ፡፡

በአክሱም ጽዮን ስም በሚመጣ የቱሪዝም ገቢ ኑሮን አደላድሎ መንፈሳዊውን እና ታሪካዊውን እሴት በዚህ መጠን ችላ ማለት አያስወቅስም? ከእግዚአብሔር ለሙሴ የተሰጠቸው ሰማያዊቷ ጽላት ማደሪያ፣ የቅዱስ ያሬድ መነሻ፣ የተሰዓቱ (ዘጠኙ) ቅዱሳን በኣት፣ የኢትዮጵ ቤተክርስቲን ፓትርያርክ መንበር፣ የንቡረ እዱ መቀመጫ እና የበርካታ ሊቃውንት መፍለቂያ አክሱም ጽዮን ይህን ያህል ተመልካች አጥታለች ማለት ነው?

Filed in: Amharic