>

በርማ (ዮናስ ሃጎስ)

የሐገሪቷ መጠርያ ስም Republic of the Union of Myanmar ሲሆን በብዛት የምትታወቀው በርማ በሚለው መጠርያዋ ነው። ባንግላዴሽ፣ ላኦስ፣ ታይዋንና ቻይና ያዋስኗታል። 51 ሚልዮን ሕዝቦች ይኖሩባታል። ከነዚህ ውስጥም የዛሬ አጀንዳችን የሆኑት የሮሂንግያ ሙስሊሞች ነዋሪዎች ብዛት 1.1 ሚልዮን ነው።
***
የሮሂንግያ ሙስሊሞች ከብዙ ዘመናት በፊት ከአረቦችና ፋርስ ባሕረ ሰላጤ በኩል ወደ አሁኒቷ ምያንማር ግዛት የፈለሱ እንደሆነ የሚታመን ሲሆን በአብዛኛው የምያንማር ነዋሪዎች ዘንድ የሚታዩት እንደ መጤ ማሕበረሰብ ነው። በዚህም ሳቢያ እስካሁን ድረስ የምያንማር ዜግነትን ያላገኙ stateless ነዋሪዎች በመሆናቸው ለማንኛውም ዜጋ የተፈቀደውን የሕክምና፣ ትምህርትና የስራ እድል የመሳሰሉ ነገሮችን የማግኘት መብት የላቸውም። ይህን መብታቸውን ለማስከበር ጫካ የገቡ የሮሂንግያ ታጣቂዎች ከባለፈው ዓመት ጥቅምት ወር ጀምሮ ከመንግስት ሐይሎች ጋር ውግያ በማድረግ ላይ መሆናቸው ይታወቃል።
***

የሰሞኑ ውዝግብ የተጀመረው የሮሂንግያ ታጣቂዎች Arakan Rohingya Salvation Army (ARSA) የመንግስትን ሐይሎች ባለፈው ነሐሴ 25/2017 ላይ ጥቃት በመክፈታቸው ነው። ታጣቂዎቹ በከፈቱት ጥቃት 71 ሰዎች ሲገደሉ ከነዚህ ውስጥ የመንግስት ወታደሮች 11 ብቻ ነበሩ። (60ዎቹ) ንፁሃን ዜጎች መሆናቸው ነው) በርምጃው የቤተሰብ አባላታቸውን ያጡ አንድ የአካባቢው ነዋሪ ለዘጋርድያን በሰጡት ቃለ መጠይቅ ታጣቂዎቹ ከሰዓት በሁዋላ ዘጠኝ ሰዓት አካባቢ በድንገት ወደ መንደራቸው እንደመጡባቸውና ያለ ቅድመ ማስጠንቀቂያ ተኩስ እንደከፈቱባቸው ነው የሚናገሩት። በመንደሪቷ ላይ በደረሰው ጥቃት የተደናገጡት አብዛኞቹ የቡድሒዝም ተከታይ የሆኑ የመንደሪቷ ነዋሪዎች ወደ አቅራቢያቸው የሚገኝ ከተማ በመሸሽ በፖሊስ ጣቢያው በመጠለል ነፍሳቸውን ለማትረፍ ችለዋል።
***
ይህንን ጥቃት ተከትሎ የመንግስት ሐይሎች በነሐሴ ወር መጨረሻና በመስከረም 2/2017 በወሰዱት እርምጃ ከ1000 የማያንሱ የሮሂንግያ ሙስሊሞች የሞቱ ሲሆን ወደ መቶ ሺህ የሚደርሱ ደግሞ ቤት ንብረታቸውን ጥለው ለመሰደድ በቅተዋል። እርምጃው ትላንትናና ዛሬ ጋብ ያለ ቢሆንም በዚህ ይቆማል ተብሎ እንደማይታሰብ ነው ዓለማቀፍ ዘጋቢዎች የሚናገሩት። የሮሂንግያ ታጣቂዎጭ አሁንም ድረስ ትጥቅ ያልፈቱ ሲሆን የመንግስት ሐይሎችም የሚወስዱት እርምጃ ከታጣቂዎችም አልፎ ሰላማዊ ዜጎች ላይ ያነጣጠረ መሆኑ በዓለማቀፉ ማሕበረሰብ ሐገሪቷን እንድትወገዝ አድርጓታል።
***
በሐገራችን በነፃነት ታግይነቷ ብዙዎቹ ምሳሌ የሚያደርጓት Aung San Suu Kyi የበርማ ተወላጅ ስትሆን በ1991 ለሰላም ባደረገችው ጥረት የኖቤል ተሸላሚ እንደሆነች ይታወቃል። ይሁንና ሰሞኑን የተሰጣትን ኖቤል መነጠቅ እንደሚገባት የሚናገሩ ድምፆች እየበረከቱ ሲሆን ለዚህም ዋንኛው ምክንያት በጠንካራ አክቲቪስትነቷና መንግስትን በሰላ ትችት በማጥቃት የምትታወቀው የኖቤል ተሸላሚ በሰሞኑ የመንግስት በሮሂንግያ ሙስሊሞች ላይ እየወሰደው ባለው ገደብ የለሽ እርምጃ አንዲትም ቃል ባለመተንፈሷ ይመስላል። Aung San በ2007 የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በሮሒንግያ ሙስሊሞች ጉዳይ ላይ ጣልቃ በመግባት ዘላቂ መፍትሔ እንዲፈጥር ጥያቄ አቅርባ የነበረ ቢሆንም ሰሞኑን መንግስት የሮሒንግያ ታጣቂዎች ላደረሱት ጉዳት በምላሹ እየወሰደ ያለውን ጭካኔ የተሞላበት የብቀላ እርምጃ አለመቃወሟ በርምጃው ከመንግስት ጎን መቆሟን ያሳያል የሚል አመለካከት እንዲፈጠር ምክንያት ሆኗል።
***
በየመን የሚገኘው የአልቃኢዳ ቅርንጫፍና የታሊባን ሐይሎች በምያንማር ላይ እርምጃ እንደሚወስዱ እየዛቱ ሲገኝ ዓለማቀፍ የቋማት ምያንማር የሙስሊሞቹን ጉዳይ ዘላቂ የሆነ መፍትሔ በመስጠት እንድትቋጨው ከፍተኛ ግፊት እያደረጉ ይገኛሉ። የካቶሊኩ ፓፓስ ፖፕ ፍራንሲስም ሙስሊሞቹ የዜግነት መብት ተሰጥቷቸው እንደማንኛውም ዜጋ ሊታዩ እንደሚገባ ባለፈው ሳምንት አሳስበዋል።
***
ሁለት ነገሮችን ለመጨመር ያህል…
1) በበርማ ሙስሊሞች የተሰማንን ሐዘን ለመግለፅ ሲባል ምንም ከጉዳዩ ጋር ግንኙነት የሌላቸውን ምስሎች በስህተት ከመለጠፍ እንቆጠብ።
2) የበርማ ጉዳይ ችላ ተብሏል አሊያም በዝምታ ታልፏል የሚለው አባባል ትክክል አይደለም። ከራሽያ ጀምሮ በተለያዩ ሐገራት የተቃውሞ ሰልፎች ተካሂዷል። ለሮሒንግያ ሙስሊሞች ዜግነት እንዲሰጥ የሚጠይቅ ፔቲሽን እየተሰባሰበ ነው። አለማቀፍ መንግስታት በርማ ይህን ቀውስ መግታት ካልቻለች ከኢኮኖሚ ማዕቀብ ጀምሮ ብዙ ቅጣቶች እንደሚጠብቋት አስጠንቅቀዋታል። እንደገናም ችግሩ ያለው በሁለቱም ወገኖች ዘንዳ ነው። የሙስሊሞቹም ታጣቂዎች ሰዎችን ገድለዋል። አሁንም እየተዋጉ ነው። የመንግስትም ታጣቂዎች ገደብ የለሽ እርምጃ ወስደዋል።
***
በርማ ለሮሒንግያ ሙስሊሞች ዜግነት በመስጠት ጉዳዩን ሰላማዊ በሆነ መንገድ እንደምትቋጨው ምኞት እያደረግን ዘገባዬን እዚህ ላይ ላብቃ…
Filed in: Amharic