>

አገር አልባ እየሆነ ያለው ህዝብ [ቬሮኒካ መላኩ]

By Veronicaከሁለት አመት በፊት የአፍሪካን ታሪክ ለማወቅ በጣም ፈለኩና በአንድ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም አንድ ኮርስ ብቻ ለመውሰድ ተመዘገብኩኝ ።
ቤኒናዊው ፕሮፌሰር ስለአፍሪካ እና አፍሪካውያን ብዙ አሰቃቂም አስደሳችም ታሪክ ሲነግረን ከረመ። አንድ ቀን አንድ ታሪካዊ ቪዲዮ ከፈተልን። ከ 15 ሚሊዮን በላይ አፍሪካውያን እንደት አገር አልባ እንደ ሆኑ የሚያሳይ ታሪካዊ ቪዲዮ ነው። ታሪካዊው ቪዲዮ ስለምእራብ አፍሪካ እና አፍሪካውያን አሰቃቂ የባርነት አመታት በተንቀሳቃሽ ምስል አስደግፎ ይተርካል።
ቤኒን የባሕር ወሽመጥ ጥግ ላይ የጎንደሩን ጃንተከል ዋርካ የሚመስል ተገትሯል ። አጠገቡም ሀውልት ተሰርቷል ።

“ዛፉ ምንድን ነው ? ” ብለን ጠየቅን ።

” የመርሳት ዛፍ ነው ። ” አለን ።

” ምን ይሆን የሚያስረሳው ?” አልን ።

” አገር አልባ የሚደረጉ አፍሪካውያንን አገራቸውን መልሰው እንዳያስታውሱ እና ወደ አገራቸው እንዳይመለሱ የአገር ትዝታ የሚያስረሳ ዛፍ ነው ። “አለ ።

ይሄን “የመርሳት ዛፍ’ አፍሪካውያንን ወንዶችን ዘጠኝ ጊዜ ሴቶቹ ደግሞ ሰባት ጊዜ እንዲዞሩ ይገደዱ ነበር ። አፍሪካውያን ይሄን የመርሳት ዛፍ ካዞሯቸው በኋላ ‘የማይመለሱበት በር’ በሚባል የመውጫ በር ለአንድየና ለመጨረሻ ጊዜ ይሸኟቸዋል ።
ይች በር አፍሪካውያን በአፍሪካ መሬት የሚኖራቸውን የመጨረሻ ቆይታ የሚያመለክት ነው።
አፍሪካውያን ዛፉን መዞራቸው የትውልድ አገራቸውን ትዝታ ከአእምሯቸው እንደሚያጠፋላቸውና ይህም ለማመፅ እንዳይነሳሱ እንደሚያደርጋቸው ይነገራቸው ነበር። በዚህ የተነሳ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ አፍሪካውያን አገር አልባ ሆኑ ።

ሌላው አገር አልባ ሆነው ለሺህ አመታት የኖሩት ህዝቦች እስራኤላውያን ናቸው። እስራኤላውያን የተበተኑት ከክርስቶስ ልደት በኋላ በ66-73 ዓ/ም በሮማውያን ላይ የዓመጽ ጦርነት ካደረጉ በኋላ ነው። በዚያን ጊዜ እስራኤልንን ጨምሮ በአብዛኛው ዓለምን ይገዙ የነበሩት ሮማውያን ነበሩ። ነገር ግን በይሁዳ ይገዛ የነበረው ሮማዊው ገዥ አይሁዶች ለቤተመቅደስ ይከፍሉት ከነበረው ቀረጥ ገንዘብ በኃይል ለመውሰድ ወደ ቤተመቅደሱ ወታደሮቹ እንዲገቡና ገንዘብ እንዲወስዱ ካደረገ በኋላ ነው።
በዚህ የመጀመሪያው የአይሁድ ዓመጽ ተብሎ በሚታወቀው ዓመጽ አይሁዳውያን ሮማውያንን ከይሁዳና ከገሊላ አባርረው ለጥቂት ዓመታትም ቢሆን ነጻ የሆኑበት ጊዜ ነበር። በኋላ ግን ሮማውያን መጥተው ጠቅላላ አይሁዳውያንን የማጥፋት ዘመቻ በማካሄድ አይሁዳውያንን ከይሁዳና ከኢየሩሳሌም በማባረርና ብዙዎችንም ባሪያ አድርገው በመውሰድ ትልቅ የአይሁድ ስደትን አስነስተዋል። እስራኤላውያን ከአገራቸው ተባርረውና እንደ ጨው በአለም ላይ ተበትነው ከ 6ሚሊዮን በላይ ህዝባቸውን በጅምላ ጭፍጨፋ ከአጡ በኋላና ለ 1ሺህ 9መቶ አመታት አገር አልባ ከሆኑ በኋላ ወደ አገራቸው ተመለሱ ።

ጎንደርን በአካል አላውቃትም። እነዚያ የጎንደርን የታሪክ ገድሎች ለዘላለም ላይጠፉና እንዳይረሱ ሆነው በወርቅ ቀለም የተፃፈባቸውን ታሪካዊ ቤተ መንግስቶች እድል ገጥሞኝ እግሬ ረግጧቸው አያውቅም። ያችን ከ 400 አመታት በላይ የአፄዎችና የንጉሰ ነገስታት መናገሻና መናሃሪያ የነበረች አገር በአይኔ በብረቱ አይቻት አላውቅም ። ያችን የ 44 ታቦታት አገር እና የጥንታዊ መስጊድ መናሃሪያ የሆነችውን አገር አጠገቧም ደርሼ አላውቅም። ጎንደር ከ400 አመታት በፊት ከፖርቱጋል ጋር አምባሳደር ተለዋውጣ ነበር። ይሄ ምናልባትም በጥቁሩ የአፍሪካ አህጉር ውስጥ የመጀመሪያው በአቻነት የአምባሳደር ልውውጥ ያደረገች ከተማ ያደርጋት ይሆናል።
በአለም አስደናቂነታቸው ከሚታወቁት አንዱ የሆነውን የእቴጌ ምንትዋብ አትክልት ስፍራ ፣ የነግስታቱ መዋኛ ስፍራ ፣ የጉግስ መጫዎቻ ሜዳ ፣ የችሎት ማስቻያ አደባባዮች ለማየት እድል አላገኘሁም።

ጎንደር በአካል ባልገኝም ፣ ከምናቤ ውስጥ ወጥታ አታውቅም ። ስለጎንደር ጀምስ ብሩስ ፣ ፖንሴንት ፣ ሚሼል ዲባዲ እና ሌሎች ፀሃፍት በምትሀተኛ ብእራቸው ጓዳ ጎድጓዳዋን እንዳውቅ አድርገውኛል። ያችን የአለም ቁሳዊና መንፈሳዊ የስልጣኔ ምንጭ የሆነች አገር ጎንደርን በአይኔ ባልመለከታትም እያንዳንዷን ቀበሌና መንደር በመንፈሴ አውቃቸዋለሁኝ። ይች ገናና አገር የተጋረጠባትን አደጋ እና ሴራ ሳስብ እንቅልፍ አጣለሁኝ ፣ ሸለብም ካደረገኝ በደረቀ ሌሊት እቃዣለሁኝ ። ብዙዎች ግን ይሄ አደጋ የታያቸው አይመስለኝም። ሳሩን እንጅ ገደሉን የማናይበት ሴራ የነገሰብን ይመስለኛል።

ከላይ የዚህን ፅሁፍ ርእስ ” አገር አልባ ” ስል እንዳጋነንኩት የሚያስቡ ሊኖሩ ይችላሉ። በአለም ላይ አገር አልባ የሆኑት ህዝቦች እንደዚህ እንደ እኛ ቀስ በቀስ እየተነቀሉ ነው የጠፉት ። እስኪ የእኛንም የአገር አልባነት ጉዞ አስታውሱት ።መጀመሪያ ወልቃይትን ከጎንደር ተነጠቅን ። ከወሎ ራያን በመውሰድ አገር አልባ አደረጉን አሁን ደሞ ያችው ገናናዋ ጎንደር እንቅልፍ ነስታቸው እየሸነሸኗት ነው ።ህውሃት ፋሽስታዊ ሸፍጡን ጭኖ ከደደቢት ከመጣበት ጊዜ ጀምሮ አማራ አገር አልባ እየተደረገ ነው።

የእኛን መኖር ማሳወቂያው ጊዜ አሁን ነው። ከላይ ፅሁፌን ስጀምር ምእራብ አፍሪካዊቷ ቤኒን ውስጥ ቅኝ ገዥዎች አፍሪካውያንን “የመርሳት ዛፍን ” 9 ኝ ጊዜ አዙረውና በሰንሰለት አስረው አትላንቲክን በማሻገር አገር አልባ እንዳደረጓቸው እኛንም “ጃን ተከል ዋርካን” 11 ጊዜ አዙረው አገር አልባ አድርገው እስኪያስቀሩን ድረስ መጠበቅ የለብንም ።
ድሮም ቢሆን አደገኛ ጠላት ከሩቅ የሚመጣ ሳይሆን በቅርብ የሚገኝ ፣ ውጭ ያለ ሳይሆን ውስጥ የሚኖር ነው። በውጭ ካለው ትልቅ ጠላት ይልቅ ለትልቅ ጠላት ስፍራ የሚሰጥ በውስጥ ያለ የወዳጅ ጠላት የከፋ ነው።

አሁን ውሽንፍርና ማእበል እያላጋን ነው ። ከውሽንፍር በኋላ ፀጥታ አለ። እርግጥ በአማራ ፖለቲካ ውስጥ የለውጥ ነፋስ እየነፈሰ ነው። ወደድንም ጠላንም ይህ እያደገ የመጣው የአማራ የብሄርተኝነት አስተሳሰብ አገር አልባ እየሆነ የመጣውን አማራን የመታደጊያው እና የማዳኛው የፖለቲካ ክኒን ነው። ሁላችንም ይሄን ያፈጠጠ ሀቅ ልንቀበለው ይገባል።

በመጨረሻ ይሄ የንጉስ ዳዊት መዝሙር ለጎንደር መታሰቢያ ይሁንልኝ።
“ከዚያ በባቢሎን ወንዞች ተቀምጠን ፅዮንን ባሰብናት ጊዜ አለቀስን።
መሰንቋችንን በውስጥዋ ባለው ህያ ዛፍ ሰቀልን።
ከዚያም የማረኩን ከፅዮን ቅኔ አንዲቱን ተቀኙልን አሉን ።………
የሩሳሌም ሆይ ረስቼሽ እንደሆነ ቀኜ ትርሳኝ ።
ያላሰብሁሽም እንደሆነ ምላሴ በትናጋዬ ይጣበቅ ። ”
መዝሙር 137: 1 _ 66
እኔም ጎንደር ሆይ ረስቼሽ እንደሆነ ቀኜ ትርሳኝ። ያላሰብሁሽ እንደሆነ ምላሴ በትናጋዬ ይጣበቅ ።

Filed in: Amharic