>
5:13 pm - Wednesday April 19, 3933

የህወሃት ደህንነቶች በሌሎች የደህንነት አባላት ላይ እርምጃ መውሰድ ጀመሩ [ኢሳት]

ኢሳት ዜና–ነሐሴ 23/2009 ዓም በአገሪቱ ውስጥ የሚታየው ህዝባዊ የለውጥ እንቅስቃሴ ስጋት ላይ የጣለው ኢህአዴግ፣ ጥልቅ ተሃድሶ በሚል የዘረጋው አጀንዳ በህዝቡ ዘንድ ተቀባይነት እንዳላስገኘለት ከተረዳ በሁዋላ፣ አዲስ የቀረጸው የሙስና አጀንዳ በምን መልኩ ይተግበር በሚለው ላይ የድርጅቱ አመራሮች ግልጽ አቋም መያዝ ተስኖአቸው በሚገኝበት በዚህ ወቅት፣ የህወሃት የደህንነት አባላት ምርመራውን በሚያካሂዱና ሚስጢር ያውቃሉ በሚሉዋቸው የደህንነት ሰራተኞች ላይ እርምጃ መውሰድ መጀመራቸውን የደህንነት ምንጮች ገልጸዋል።
ለወራት ከፍተኛ ባለስልጣናቱን እያወዛገበ የሚገኘው የሙስና አጀንዳ ወደ ስልጣን ፉክክር እየተለወጠ መምጣቱን የሚገልጹት ምንጮች፣ በቅርቡ የታሰሩ በዝቅተኛ ደረጃ የሚገኙ ባለስልጣናትንና ባለሀብቶችን የሚመረምሩ የፌደራል ፖሊስ አባላት ሳይቀር በይፋ ራሳቸውን በማይገልጹ ቡድኖች ማስፈራሪያ እየደረሳቸው ነው።
መጀመሪያ በታቀደው መሰረት በሙስና የተጠረጠሩ ባለስልጣናትንና ባለሀብቶችን እንዲመረምሩ ከተመረጡት ደህንነቶች መካከል እስካሁን አንድ የደህንነት አባል መገደሉን ምንጮች ገልጸዋል። ሶሚ በሚል ቅጽል ስም የሚታወቀው የደህነነት አባሉ የኦሮሞ ተወላጅ ሲሆን፣ ከፌደራል ፖሊስ አባላት ጋር በመቀናጀት በመርምራው ንቁ ተሳተፎ ያደርግ ነበር። ግድያው ከመፈጸሙ በፊት 4 ግለሰቦች ወደ ደህንነቱ ቤት በመሄድ ባለቤቱን ማነጋገራቸው ታውቋል። ሟቹ የደህንነት አባል የኦሮሞ ብሄር ተወላጅ ሲሆን፣ በምርመራው ላይ በስፋት ይሳተፍ ነበር ተብሎአል። ሌላ የደህንነት አባልም እንዲሁ ማስፈራሪያ እንደደረሰውና ተሳትፎውን የማያቆም ከሆነ እርምጃ እንደሚወሰድበት ተዝቶበታል።
በህወሃት ውስጥ የሚገኙ አንዳንድ የደህንነት ሰራተኞች፣ ከህወሃት ባለስልጣናት በሚሰጥ ትዕዛዝ መርማሪዎችን እና መረጃዎችን እንዲሰበስቡ በተመደቡ የደህንነት ሰራተኞች ላይ እያደረሱት ያለው ማስፈራሪያ ከትግራይ ውጭ ያሉ የደህንነት አባላት ስጋት ውስጥ እንዲወድቁና አለመተማመኑ እንዲጨምር እንዳደረገው ምንጮች ይገልጻሉ።
የፌደራል ፖሊስ መርማሪ አባላት ሳይቀር በተወሰኑ ባለስልጣናት ዙሪያ እርስ በርስ መከፋፈላቸውን ምንጮች ይናገራሉ። በእስር ላይ የሚገኙ አንዳንድ ባለሀብቶች ከነባሩ የህወሃት መሪ አባይ ጸሃዬ ጋር ስላላችሁ ግንኙነት ተናገሩ ሲባሉ፣ የተወሰኑ መርማሪዎች ጥያቄው እንዲነሳ ፍላጎት እንዳልነበራቸው ምንጮች ገልጸዋል።
በእስር ላይ የሚገኙት የአዲስ ቪው ሆቴል ባለቤት አቶ ዓብይ አበራ በምርምራ ወቅት ሆቴሉ የአቶ አዲሱ ለገሰ መሆኑን እንዲሁም ከተለያዩ ባለስልጣናት ጋር ግንኙነት እንዳላቸው ቢናገሩም፣ አንደኛው ወገን ምርምራውን የመግፋት አዝማሚያ ሲያሳይ ሌላው ገን ግን ጉዳዩ ተራ ስም ማጥፋትና ምርምራው እንዲደናቀፍ ሆን ተብሎ የታቀደ ነው በማለት በከፍተኛ አመራሩ ላይ የሚደረገው ምርምራ እንዳይቀጥል እየታገለ ነው።
አቃቢ ህግ ለፍርድ ቤቱ ስለ አቶ አብይ ሲናገር፣ ባለሃብቱ የተለያዩ የመንግስት አመራሮችን ስም እየጠሩ ምርመራውን እያደናቀፉ መሆኑን፣ ምርመራውም እየተወሳሰበ መምጣቱን፣ ከእርሳቸው ጋር በተያያዘም አንዳንድ ከፍተኛ የመንግስት አመራሮች እጃቸው እንዳለበት መረጃ እያገኘን ነው በማለት ተናግሮ ነበር።
የጸረ-ሙስና ትግሉ ህዝባዊ ድጋፍ በማስገኘት የኢህአዴግን ህልውና ለማራዘም ብቸኛ መፍትሄ ተደርጎ ቢቀመጠም፣ “ማን ይከሰስ፣ ማን አይከሰስ” የሚለው ጥያቄ ኢህአዴግን በመሰረቱት አራት ድርጅቶች ውስጥ መከፋፈል እየፈጠረ በመምጣቱ በከፍተኛ አመራሮች ላይ የሚደረገው ዘመቻ ሊቀር እንደሚችል ፍንጮች እየታዩ ነው። በተለይ የህወሃት ደህንነቶች ምርምራ እንዲያካሂዱ እና መረጃ እንዲሰበስቡ በተመረጡ አንዳንድ የሌሎች ብሄር ተወላጆች ላይ እየወሰዱት ያለው እርምጃ በድርጅቱ ላይ ያልተጠበቀ አደጋ ይዞ እየመጣ መሆኑን ምንጮች ይገልጻሉ

Filed in: Amharic