>

27 ኢትዮጵያውያን ሳውዲ አረቢያ ውስጥ ታሰሩ! (ዶይቸ ቬለ)

by-nebiyu-sirak-29082017

ሳውዲ አረቢያ ውስጥ 14 ሴቶችን ጨምሮ 27 ኢትዮጵያውያንን በቁጥጥር ስር ማመሏ የ ዋዲ አል-ዳዋሲር ክልል የጸጥታ ኃይል አስታወቀ። የአካባቢው የመገናኛ ብዙኃን ዛሬ እንደዘገቡት፣ በቁጥጥር ስር የዋሉት ኢትዮጵያውያን የመኖሪያ እና የስራ ፍቃድ የላቸውም።

ሳዑዲ አረብያ የመኖሪያ ፈቃድ የሌላቸው የውጭ ዜጎች ከሀገርዋ እንዲወጡ ከጥቂት ወራት በፊት ያስቀመጠችው የመጀመሪያው የ90 ቀናት ቀነ ገደብ ተጠናቋል። ከዚህ ከተጠናቀቀው የምህረት አዋጅ ጋር ግንኙነት ይሩነው አይኑረው በግልጽ ባይታወቅም አረብ ኒውስ የተባለው የድረ ገጽ ፓርታል እንደዘገበው፣ ከሳውዲ አረቢያ መዲና ሪያድ በስተ ሰሜን በሚገኝ አንድ ከተማ ውስጥ 13 ወንዶች እና 14 ሴቶች ፣ በጠቅላላ 27 ኢትዮጵያውያን ሰሞኑን በቁጥጥር ስር ውለዋል። ኢትዮጵያውያኑ የታሰሩት የጸጥታ ኃይላት ዋዲ አል-ዳዋሲር በተባለው አካባቢ አንድ እርሻን በተቆጣጠሩበት ወቅት መሆኑ ተገልጿል። ሳውዲ አረቢያ የሚገኘው ጋዜጠኛ ነብዩ ሲራክ እንደገለፀልን፣ አካባቢው ለበርካታ ፍቃድ የሌላቸው ኢትዮጵያውያን መዳረሻ ነው። አብዘኞቹም በእረኝነት እና እርሻ ላይ ይሰራሉ።

ሳውዲ አረብያ እነዚህን ህገ ወጥ እንደሆኑ የተነገረላቸውን እና አሁን በቁጥጥር ስር የዋሉትን 27 ኢትዮጵያውያን ፍርድ ቤት ታቅርባቸው ወይስ አስጠርዛ ወደ ኢትዮጵያ ትላካቸው አትላካቸው በግልፅ የሚታወቅ ነገር የለም። ይህ ዜና በምህረት አዋጁ ተጠቅመው እስካሁን ሳውዲን ለቀው ያልወጡትን ኢትዮጵያውያን ጨርሶ አላደናገጠም። « በርሃ እና ስቃይ አሳልፈን ስለሆነ እዚህ የደረስነው ሆዳችን አይሸበርም» ይላሉ በባህር ሳውዲ አረቢያ እንደገቡ የገለፁልን ኢትዮጵያዊ ። ይሁንና፣ ሳውዲ አረቢያ የምህረት አዋጁን እንዳወጣች እሳቸውም ወደ ኢትዮጵያ ለመመለስ ሞክረው ነበር። በረመዳን ወቅት አስቀድሞ የሄደው ወንድማቸው ግን እዛው እንዲቀሩ መክሯቸው ቀርተዋል።

ህጋዊ የመኖርያ እና የስራ ፈቃድ የሌላቸው ኢትዮጵያውያን የሳውዲ መንግሥት ከወትሮው የተለየ ርምጃ ሲወስድ ባለመታዘባቸው አሁንም የመጣው ይምጣ በሚል በሳውዲ አረቢያ መቆየት እንደመረጡ ይናገራሉ። ጋዜጠኛ ነብዩ ሲራክም የሚለን ይህንኑ ነው። «የሳውዲ መንግሥት በትላልቅ ከተሞች ድሮ ከሚታወቀው ውጪ የተለየ ርምጃ እየወሰደ አይደለም»

ጊዜያዊው ሁኔታ ባያሰጋቸውም ተራዘመ የተባለውን የምህረት አዋጅ ተጠቅመው ሀገሪቷን ባለፈው አንድ ወራት ለመልቀቅ ለፈለጉ ኢትዮጵያውያንም ነገሮች እንደሚገው አለመስተካካላቸውን ገልጸውልናል። የምህረት አዋጁ ለሁለተኛ ጊዜ ተራዝሟል አልተራዘመም የሚለው ጉዳይ በራሱ ትልቅ ጥያቄ አስነስቷል ይላል ነብዩ። ሳውዲ አረቢያ የሚገኙት የኢትዮጵያ ኤምባሲ እና ቆንስላ ለዶይቸ ቬለ ዛሬም በስልክ አልተገኙም። በዛም ሆነ በዚህ የሳውዲ አረቢያ መንግስት ሕገ-ወጥ ያላቸዉ የዉጪ ዜጎች ሐገሩን እንዲለቁ አውጥቶት የነበረው የጊዜ ገደብ በአሁኑ ሰዓት አብቅቷል።

ልደት አበበ
አርያም ተክሌ

27 ኢትዮጵያውያን
Filed in: Amharic