>
5:13 pm - Tuesday April 18, 1302

«ምን ነክቶሃል» አልሺኝ? (ዘውድአለም ታደሰ)

«ምን ነክቶሃል» አልሺኝ?

Italy police using water cannon and batons clash with Ethiopian and Ertreanምን ያልነካኝ አለ?
የመጣ መከራ ሳይነካኝ መች ያልፋል
ሌባን’ኳ ባቅሙ፥
ጎረቤቴን ትቶ – የኔን ቤት ይዘርፋል!

ጀማሪ ቀስተኛ
ቀሽም ተኳሽ ሁሉ፣
ኢላማ ለመማር፣ 
ወደኔ አነጣጥሮ ፣ ሲተኩስ እያየሽ
ይሄን ሁሉ ችዬ፥
ዝም ስል ብታይኝ “ምን ነካህ” ትያለሽ?

ምን ያልነካኝ አለ?

ሐገሬ ብቀመጥ ፣
የነካሁት ሁሉ፣ ፈጀኝ እንደረመጥ
ሰው ሐገር ብሰደድ፣ ሀዘኔን ለመርሳት
እየ …. ተሳለቁ ለኮሱብኝ እሳት!
የዳሰሰኝ ሁሉ፣
ሊሰቅለኝ ቋመጠ
መስቀል ይሰራ ዘንድ – እልፍ ዛፍ ቆረጠ
በሞቴ ይመስል – የምትድን ነፍሳቸው
በህይወት መኖሬ – ለምን አመማቸው?
አዎ!
ቃል ከአፌ ነጥፎ ዝም ስል ብታይኝ
ቢያስፈራም ፀጥታው ፥ “ምን ነካህ?” አትበይኝ!

ምን ያልነካኝ አለ?

ስቃዬን እንደስንቅ
መከራን እንደትጥቅ
በጀርባዬ ይዤ
ከሲኦል ሸሸሁ ስል – ሲኦል እወድቃለሁ
ሺህ ግዜ እየሞትኩ – ሺ ግዜ ‘ነቃለሁ
እንዳሳ ነባሪ – ውሃ ነው ህይወቴ
አፈር እየናፈቅሁ – ባህር ላይ ነው ሞቴ
ወዲያ ብሄድ መስቀል፣
ከዚያ ብሸሽ ጅራፍ – በአበባ ፈንታ፣
እዚህ የሾህ አክሊል ፣ እዚያ ጎለጎታ
የረገጥሁት ሁሉ፣
እሾህ እያወጣ ሲወጋኝ እያየሽ
“ምን ነካህ” ትያለሽ?

ምን ያልነካኝ አለ?

 

Filed in: Amharic