>

ከአድዋ ድል ባሻገር (ታምሩ ተመስገን)

1895 ዓ.ም አዲስ አበባ

ጣሊያን መስፋፋት ቀጥላ ኖሮ የታቦተ ጽዮን መቀመጫ የሆነችውን ቅድስቲቱን አክሱምን ወረረች፡፡ በኢትዮጲያ ታሪክ ያለፉ ነገስታት በሙሉ የማይደራደሩበት ነገር ቢኖር አክሱምን ለጠላት አሳልፎ መስጠትን ነበር፡፡ አፄ ምኒልክም ወራሪ ጦርን ይወጉ ዘንድ አገር አቀፍ ክተት አዋጅ ያስነገሩት ይሄኔ ነው ባዘቶ ደመና ከምድር በተወዳጁበት የወራቶች አጥቢያ በሆነው ወርሃ መስከረም ሺህ ስምንት መቶ ዘጠና አምስት አመተ-ምህረት፡፡
.
ጥቅምት 13 1896
ደብረ-ማርቆስ , አባ አስራት ገዳም
……ከቅዳሴ ውጭ በሆነ ጊዜ የገዳሙ አበመኔት አባ ይኩኑአምላክ በጉም የታፈነውን ጥሻ በመቋሚያቸው እየገላለጡ፡፡ ጤዛ ያዘለውን ሰርዶ እየተው በጠፍር ጫማቸው ጤዛ ያላዘለውን ሰርዶ እየረገጡ ሄደው ከቤታቸው ገቡና አንዳች ጥራጥሬ በእፍኛቸው ዘግነው ሲያበቁ ቁልቁል ከሾላው ዛፍ ግድም አዝግመው ሄዱና ከአንድ ወዛም ድንጊያ ላይ ተቀመጡ፡፡ ከፊታቸው እልፍ ብሎ የተሰየመው ገዳሙን እሁለት ቦታ ገምሶ የሚያልፈው ወንዝ ከድንጋዮች ጋር ሲላተም በውል ይሰማል፡፡ ጎጆአቸውን በገዳሙ ዙሪያ ከሚገኙ እድሜ ጠገብ ዛፎች ላይ የቀለሱት ወፎች የክረምቱ ቆፈን ሳይበግራቸው ከደጃፋቸው ተሰይመው ይዘምራሉ፡፡ የተለያዩ አይነት ዝማሬዎች እዚህም እዛም ይዘመራሉ፡፡ ወዲያ ደግሞ ማልደው የተነሱት ደቂቅ መነኮሳት ስልትናለዛን አዋህደው ትምህርተ ሀይማኖትን ከህሊናቸው ለመመዝገብ ጮክ ብለው በቃላቸው ሲወጡት ይሰማሉ፡፡ አልፎ አልፎም የገዳሙ ማዕጠንት ሲጤስ ይታያል፡፡ በቃ አባ አስራት ገዳም እንደዚህ ነው፡፡ ገነትን ባላውቀውም የገነት አይነት ለዛ ያለው ግን ምድር ላይ የሚገኝ የነፈስ መሻት፡፡ ስጋን ድል እየነሳ ነፍስን በውብ አበቦች እርሻ ላይ የሚያሰማራ አይነት ምትሀት የተቸረ፡፡ ታዲያ አባ ይኩኑአምላክ በዚህ ሁሉ በረከት ተከበው ሳለ ስለምን ተክዘው ተቀመጡ? አካላቸው እንጂ መንፈሳቸው ከሳቸው ጋር እንዳልሆነ እንዲሁ ትካዜአችውን አይቶ ማንም መረዳት ይችላል፡፡ ቅድም ከቤታቸው የዘገኑትን ጥራጥሬ ከመሬት ላይ በተኑት፡፡ የተሸረከተ በቆለ ነው፡፡ ከተወሰኑ ደቂቃዎች በኋላ በርከት ያሉ እርግቦች መጠው ጥራጥሬውን መለቃቀም ጀመሩ፡፡ ገብስማ እርግብ ፣ ነጭ እርግብ ፣ ጥቁር እርግብ ፣ በነጭ መደብ ጥቁር ጣል ጣል ያለባቸው እርግቦች….. ጀምበር ተጨንቃም ቢሆን በግፍ ከሸፈናት ዳመና ተላቃ ለመውጣት ምስክር ረጃጅም እግሮቿ መታየታቸው፡፡ ጤዛ ያዘሉት ሰርዶዎች ላይ ጨረሯ ሲያርፍ የሆነ ነፍስን የሚሰልብ ቀለም ያንፀባርቃል፡፡ በቃላት ለመግለፅ የሚቸግር አይነት ውብ ቀለም፡፡ አባ ይኩኑአምላክ ከጀርባቸው በኩል ወደሳቸው የሚመጣ የእግር ዳና በሰሙ ጊዜ ጀርባቸውን ሲገላመጡ ዳኘና ሚስቱ የዳርነሽ መሆናቸውን ተገነዘቡ፡፡ ዳኘ መናኛ ጠይም ቁምጣውን በአራፊ ካኔትራ ለብሶ በግራ እጁ ጋሻ በቀኝ እጁ ደግሞ ጦር ይዟል፡፡ መጫሚያ የለውም፡፡ እንዲሁ ንቃቃቱ ማርትሬዛ የሚሸጉጥ እግር ብቻ ነው ያለው፡፡ ራሱ ላይ ነጭ ቁራጭ ሸማ አስሯል፡፡ ድፍረት እና አትንኩኝ ባይነት ከአይኑ ይንቀለቀላሉ፡፡ የዳርነሽ ከጥጥ የተሰራ ጥለቱ አረንጓዴ ቢጫ ቀይ የሆነ ጉንፈ ሰፊ ሸማዋን ለብሳለቸው፡፡ በጀርባዋ ደግሞ በወደላ አገልግል ስንቅ ተሸክማለች፡፡ ሁለቱም ሸክማቸውን ከጎን ካሳርፉ በኋላ አባ አግር ላይ ተደፍተው “አባ ይፍቱን” አሉ፡፡ አባ ይኩኑአምላክም ከጉንፋቸው ውስጥ ሸሽገው አስቀምጠውት በነበረው የብር መስቀላቸው የዳኘንና የዳርነሽን ጀርባ አፈራርቀው እየዳሰሱ “እሱ መድሃኒአለም ይፍታችሁ፡፡ በሉ ተነሱ፡፡” አሏቸው፡፡ ሁለቱም የአባን መስቀል ሶስት ሶስት ቦታ ስመው ስመው ሰርዶው ላይ ቁጭ አሉ፡፡ “እንግዲህ ጓዝ አያያዛችሁ መወሰናችሁን እያረዳኝ ነው?” አባ በትካዜ ወንዙን አሻግረው እየተመለከቱ ጠየቁ፡፡ “አይ አባ በይህ በኩል ብንተወው በያ በኩል የማይተውን ጠላት ተደጅ ቀርቦ ሳለ እንዴት ጭጭ አንበል፡፡ ምነው አባ እኛስ በጀ ባንል የኣባቻችን አጥም ተነስቶ ደጋኑን ወድሮ ፍላፃውን አይስልም ብለው ነው? ጠላጥ ተፊት ቀርቦ የምን ማንቀላፋት ነው፡፡ ላፈሩም አይደለም እንዴ የተፈጠርነው!” አለ ዳኘ አደራየን አላስበላም በሚል ቃና፡፡ “እንደው ሌላ መላ አለ እንደሁስ አላሰባችሁም?” ጠየቁ አባ ይኩኑአምላክ፡፡ መለሿ የዳርነሽ ነበረች “እንደው በያሰሞን የእምየ መልዕክተኛ ክተት አዋጁን ታበሰረን በኋላ በጠና ስንዳክም ነበር፡፡ ግና ወዲህ የንጉስ ተክለሀይማኖት ጦር በብርቱ አሞተ መራራ ጀግና ያስፈልገዋል እየተባለ በቀያችን ሲናፈስ ጊዜ ለርሳቸው ልንገባ ወሰንን፡፡ ኧራ ከተክለ ሀይማኖት ተምንሸሽስ እንዲያው ያውሬ መጫወቻ ሆነን ብንቀር ይሻለናል፡፡” ስትናገር ጀግንነቷ በግንበሯ እና በአንገቷ ላይ በፈጠጡ ወፍራም የደም ስሮቿ ይገለጣል፡፡ “እንግዲህ ካላችሁ ዘንዳ ደግ፡፡ ታዲያ የበኩር ልጃችሁንስ ነገር መከራችሁበት?” “አባ እርሶም እግዜሩም በሚያውቀው ዘመዶቻችን በሙሉ እንዲያው አልቀዋል፡፡ ለልጃችን ተኛ በቀር ዘመድ የለውም፡፡ ቀዳሚ የለው ተከታይ የሌለው አንድያ ልጃችን ነው፡፡ ከክተቱ እስትንመለስ ድርስ መልካም ፈቃድዎ ሆኖ እርሶ ዘንድ ቢቀመጥ ብለን ወዲህ አምጥተነዋል፡፡” አለች የዳርነሽ እናትነቷ ሲገነፍል በእንባ እየራሰች፡፡ አባ ይኩኑአምላክ ትንሽ እንደማሰብ አደረጉና “ደግ! ቤት የፈጣሪ ነውና እንግዲህ ህጣኑ እኔ ጋር መቆየቱ መልካም ነው፡፡ ባይሆን የቤት ንብረት ነገራችሁን ነገር ለሌላ ሰው መልክ አስይዙት፡፡” ባልና ሚስት ተነስተው የአባን እጅ ሳሙ፡፡ “አይገባም አይገባም… እንግዲህ ወደ አድዋ መክተታችሁ አንድም ለሀገራችሁ አፈር አንድም ለሀይማኖት ማተባችሁ ነውና መድሃኒያለም በመንገዳችሁ ሁሉ ይቅደም፡፡ በድል ተመለሱ፡፡” አሉና አባ ይኩኑ አምላክ የዳኘን ጦርና ጋሻ የዳርነሽን ስንቅ ባርከው ሸኟቸው፡፡

የዳርነሽና ዳኘ ለንጉስ ተክለ ሀይማኖት አደሩ፡፡ አፈርና ማተባቸውን ለማፅናት ወደ አድዋም ዘመቱ፡፡
.
ጊዜያትም እንዲሁ እርስ በርስ እየተነካኩ አለፉ፡፡ የጣሊያንም ጦር ድል እንደሆነ በቀየው ተሰማ፡፡ ከንጉስ ተክለሃይማኖት ጋር ዘምተው ከሞት የተረፉት ወደየ ቀያቸው ተመለሱ፡፡ ዳኘና የዳርነሽ ግን ከእነርሱ መካከል እንደ አንደኛቸው አልነበሩም…

Filed in: Amharic