>

በመርህ ላይ ተመስርተህ መራሩን እውነት ተጋፈጥ! [ኤርሚያስ ለገሰ]

Jim collinsGood to great: why some companies make the leap and others not” በሚለው መጽሐፉ ” መራሩን ሀቅ ተጋፈጥ፣ ሆኖም ተስፋ አትቁረጥ” ይላል። ፀሐፊው እንደሚገልጠው ከሆነ ታላቅ አላማን ለማሳካት መራሩን እውነት መጋፈጥ ግድ ይላል። በሌላ በኩል ይሄንን ትልቅ ግብ ለማሳካት የሚደረገው ጉዞ በየጊዜው መውደቅና መነሳት ስለሚያጋጥመው ጨለምተኝነት እና ተስፋ መቁረጥ ውስጥ መግባት እንደማያስፈልግ ያስገነዝባል።

እርግጥም መራሩን ሐቅ በመርህ ላይ ተመስርቶ ለመጋፈጥ ቁርጠኝነት ይጠይቃል። ፊት ለፊት አገር አፍራሽ አደጋ እየታየ እንደ ሰጐን አንገት መቅበር የሚያዋጣ አይደለም። ዝሆኑ እቤት ውስጥ መኖሩን አምኖ በመቀበል መጋፈጥ ያስፈልጋል። ታዋቂው የአመራር ሳይንስ ምሁር Stephen covey ” The speed of TRUST” በሚለው መፅሐፉ እንዲህ ይለናል፣

“confront reality is about taking the tough issues head on. It’s about sharing the bad news as well as the good, naming the ‘ elephant in the room’ addressing the ‘ scared cows”, and discussing the ‘ undiscussables’. Address the tough stuff directly. Acknowledge the unsaid lead out courageously in conversation. Remove the ‘ sword from their hands’. Don’t skirt the real issues. Don’t bury your head in the sand.”

ከላይኛውም ሆነ ከዚህ አባባል መረዳት የሚቻለው ወሳኝ የሆኑ የሕልውና ጉዳዬች ላይ ግልፅ አቋምን ማሳየት ለድርድር የማይቀርብ መሆኑን ነው። ከዚህ በተጨማሪም በመርህና በአስተሳሰብ ደረጃ ግልፅ ልዩነት የሚታይባቸው አጀንዳዎችን ለመጋፈጥ ቁርጠኝነት ከምንም ነገር በላይ ወሳኝ መሆኑን ማየት ይቻላል።በመሆኑም እየተደረገ ያለው ትግል ማዕከላዊ አላማ ከፓለቲካ ፣ ከኢኮኖሚና መንፈሳዊ እስር ለመላቀቅ እንደመሆኑ መጠን የሕዝብ ቁጣና የመደፈር እልህ ያቃጠለው ወገን ሁሉ በመርሆዎች ላይ ሳይደራደር በጋራ መነሳት ይኖርበታል።

ወደ ገደለው ጉዳዬ ስገባ ሰሞኑን ከአዲስ አበባ ወቅታዊ የፓለቲካ ሁኔታ አንፃር በሚነሱት ቁምነገሮች ዙሪያ አስተያየቴን በተደጋጋሚ ሰጥቻለሁ። የደረሱኝ ግብረመልሶች የተለያዩ ናቸው። አንዳንዶቹ አቋሜን አጥላልተው በመተቸት የራሳቸውን አቋሞች ለመከላከል የሚመሩበትን ፅሁፍ አውጥተዋል። አንዳንዶቹ ደግሞ ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው ስድብ ያልተለየው አሉባልታዎች እና የመንደር ወሬዎችን በመለቃቀም ያቀረቡበት ነው። ያም ሆኖ ግን ግለሰቦቹ እየተሳደቡም፣ እያጉረመረሙም በመሰረታዊ ጉዳዬች ላይ ፍላጐታቸውን ግልፅ ለማድረግ የተገደዱበት ስለሆነ አንዳንድ አዎንታዊ ገጽታዎች እንዳሉት ለመታዘብ ችያለሁ።

እንደ እውነቱ ከሆነ በቀረቡት የመንደር ወሬዎች ላይ ለመተቸት አልፈልግም። በእኔ እምነት ለእነዚህ መልስ ለመስጠት መሞከር እነሱ እንደሚፈልጉት መሰረታዊ ጉዳዬችን ወደ ጐን ትቶ እዚህ ግባ በማይባል መናኛ ስድቦች ላይ እንካለ ሰላንቲያ በመግጠም ወደ እነሱ ደረጃ መውረድ ይሆናል። እርግጥ አንድ ታዋቂ የአሜሪካ ጋዜጠኛ ” የተፃራሪህ ጩኸት ፣ መሳደብ ፣ መራገጥ፣ ጫጫታ ሲያበዛብህ ጥሩ ስራ ሠርቻለሁ ብለህ መደሰት አለብህ። ለመልካም ሥራህ የተግባር መስፈርቱን ያ ነውና!” በማለት የገለጠውን በልቦናዬ ሳላስበው ቀርቼ አይደለም። የፃፍኩት መልካም ይሁን አይሁን ጊዜ የሚገልፀው ቢሆንም አቋሜ መሆኑን በቀይ እስክሪብቶ አሰምርበታለሁ።

በመሪ ርዕሴ ላይ ለማመላከት እንደሞከርኩት በሰሞኑ የአዲሳአባ ፓለቲካ ላይ የተለያዩ ሐይሎች ቆሜለታለሁ ከሚሉት ማህበረሰብ በመነሳትም ሆነ ግላዊ ፍላጐትን ለማሟላት በማሰብ የተለያዩ የማይታረቁ አቋሞችን በማራመድ ላይ ናቸው።

የመጀመሪያው የስርአቱ ባለቤት የሆነውና አጀንዳውን ለስልጣን ማራዘሚያ የሚጠቀምበት ህውሓት ይገኛል። ይሄ ሃይል ዶክተር መረራ ” የሕውሓት ዲቃላ” እያለ የሚጠራውን ኦህዴድ እንደ ትሮይ ፈረስ በመጠቀም አጀንዳውን የሚያስፈፅም ነው።

ሁለተኛው ሐይል የመዲናይቱን የባለቤትነት ፣ ተጠሪነትና ውክልና ጥያቄ የሚያነሳው ነው። በዚህ ፈርጅ ውስጥ የተለያዩ አመለካከቶች አሉ። አንዳንዶቹ አገዛዙ በወረቀት ደረጃ የፓለቲካ ፕሮግራሙ ማስፈፀሚያ ባደረገው ሕገ መንግስት አንቀፅ 49 የሰፈረውን ” የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ራሱን በራሱ የማስተዳደር ሙሉ ስልጣን ይኖረዋል ” የሚለውን የማይቀበሉ ናቸው። በሌላ በኩል በታሪካዊ ሁኔታና ባለቤትነት ጥያቄ ላይ ተመሳሳይ አመለካከት ያላቸው ግን ደግሞ የከተማው መስተዳድር በተሰመረለት የግዛት ወሰን ሙሉ/ የተሸራረፈ ስልጣን እንዲኖረው የሚፈልጉ ይገኙበታል። ይሄኛው ክፋይ በጥቅሉ ሲታይ በሁለቱ አስተዳደሮች ውስጥ ሊፈጠሩ የሚችሉትን ያለመግባባቶችና የጥቅም ግጭቶች ላይ በግልፅ የተቆጠሩ መፍትሔዎችን ማሳየት የቻለ አይመስለኝም።

የሶስተኛው አቋም የአዲሳአባ ነዋሪም ሆነ ዲሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ወደፊት የሚመረጠው የከተማው አስተዳደር ምንም አይነት መሸራረፍም ሆነ ተፅእኖ ሳይደርስበት ራሱን በራሱ የማስተዳደር ሙሉ ስልጣን ይኖረዋል የሚል ነው። ከዚህ ተጭማሪም አዲስ አበባ የአፍሪካ፣ የኢትዮጵያ እና የኦሮሚያ መቀመጫ ርዕሰ ከተማ መሆኗ ተገቢ መሆኑን እና ዲሞክራሲያዊ ስርአት ሲመጣ ለመዲናይቱ ትልቅ ፀጋ እንደሆነ እምነት ያለው ነው። የጥቅም ግጭቶች ቢከሰቱ እንኳን ስርአቱ ዲሞክራሲያዊ እስከሆነ ድረስ በውይይትና በጋራ አሸናፊነት የሚጠናቀቅ እንደሚሆን እምነት አለው።

ሌሎች ከላይ ከተጠቀሱት አቋሞች በተለየ የሚሰለፋ እንደሚኖሩ አውቃለሁ። መዘርዘርም የሚቻል ይመስለኛል። ለዚህ አጭር መጣጥፍ ከላይ በተጠቀሱት ላይ ብቻ ልሞርከዝና የግሌን ቦታ ልጠቁም። እኔ የምደግፈው የአዲስ አበባ ነዋሪና አስተዳደር በሚከለልለት ግዛት ላይ ምልዑ ሥልጣን ይኖረዋል የሚለውን ነው። በመሆኑም በተለያዩ ጊዜያቶች አዱገነትን በተመለከተ የማቀርባቸው አስተያየቶች ከዚህ እምነት የሚቀዱ ናቸው። የአዲስ አበባ ነዋሪና መስተዳድር ራሱን በራሱ የማስተዳደር ሙሉ ስልጣኑን ከሚጋፋ ሐይሎች ጋር በምንም መልኩ ስምምነት ሊኖረኝ አይችልም ። የዘወትር ፀሎቴም በቆምኩበት መሠረት ላይ ተመስርቼ ተቃራኒ አጀንዳዎችን ለመሻገር ቁርጠኝነት እንድላበስ ነው።

ወደ ሰሞኑ የመዲናይቱ አጀንዳ ስመለስ በሕውኃት ድብቅ ሴራ ፕሮፌሰር መረራ ” ዲቃላው እና የሕውሐት የፓለቲካ ቀዶ ጥገና ውጤት ” በማለት በሚጠራው ኦህዴድ አማካኝነት የኦሮሚያ ትምህርት ቢሮ የሚቆጣጠራቸውና የሚያስተዳድራቸው በኦሮምኛ የሚያስተምሩ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት መከፈታቸው የተገለፀበት ነበር። ይሄንን ውሳኔ ከላይ በጠቀስኩት መርህ ላይ በመመስረት ተቃውሞ አሰምቻለሁ።ለመድገም ያህል እርምጃው የአዲስ አበባ አስተዳደር ነዋሪዎቹን የማስተዳደር ሙሉ ሥልጣኑን እንደሚጋፋና አካሄዱ ነዋሪውን በመከፋፈል አደገኛ ሁኔታ ሊፈጥር እንደሚችል ግምቴን አስቀምጫለሁ። ሌላው ቀርቶ እየተሰራ ያለው ስራ አገዛዙ በቀጣይ ወራት አፀድቀዋለሁ ካለው አዋጅ በተፃራሪ መሆኑን በቀላሉ ማየት ይቻላል። ለምሳሌ ያህል ረቂቅ አዋጁን ለማስተዋወቅ የከተማው አስተዳደር ባወጣው ሰነድ ላይ የሚከተለውን አስፍሯል ፣

” …ልጆቻቸው በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ማስተማር ለሚፈልጉ ዜጐች የከተማው አስተዳደር በአፋን ኦሮሞ የመጀመሪያ ትምህርት ቤት ማደራጀት እንዳለበት አስቀምጧል።” ምንም እንኳን ከአዋጁ በፊት ቢተገበርም ሰነዱ ይሄን ይላል።

ለማጠቃለል ያህል ከኦሮምኛ ትምህርት በአዲስ አበባ/ ፊኒፊኔ ከመሰጠት አንፃር የሚከተሉትን እምነቶቼን መግለፅ እፈልጋለሁ ።

አንደኛ: የኦሮምኛ ትምህርት በሁሉም የአዲሳአባ ትምህርት ቤቶች ከመዋለ ህፃናት እስከ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እንደ አንድ የትምህርት አይነት መሰጠት አለበት። የትምህርት አመራሩም ሆና አስተዳደራዊ ጉዳዬች ባለቤቱ የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ሊሆን ይገባል። ለአፈፃፀም እንዲረዳ በትምህርት ቢሮው ስር ራሱን የቻለ መምሪያ (ዲያሮክቶሬት) ሊኖረው ይገባል።

ሁለተኛ: የኦሮምኛ ቋንቋ ዲሞክራሲያዊ ስርአት ሲመጣ የፌዴራሉ ተጨማሪ የስራ ቋንቋ መሆኑ ስለማይቀር የአዲሳአባን ተሞክሮ በመቀመር በመላው ኢትየጵያ ከአንደኛ ደረጃ እስከ ሁለተኛ ደረጃ እንደ አንድ የትምህርት አይነት የሚሰጥበትን ሁኔታ መፍጠር።

ሦስተኛ: ዜጐች ለትምህርቱ ልዩ ትኩረት እንዲሰጡና በባለቤትነት መንፈስ እንዲማሩት የተለያዩ ማትጊያ ስልቶችን መጠቀም መቻል። ለምሳሌ የዩኒቨርስቲ መግቢያ በቀድሞው ጊዜ ሂሳብና እንግሊዘኛን ትኩረት እንደሚያደርገው ኦሮምኛ እና አማርኛን ከግምት መክተት ይቻላል። በተራዘመ ሂደት የከተማው መንግስታዊ መስሪያቤቶች ወጣቶቹን ለመቅጠር ከሚያወጡት መመዘኛ 10%( የዘፈቀደ ቁጥር ነው) የኦሮምኛ ቋንቋ መሰረታዊ መግባቢያ የሚሆኑትን ማወቃቸውን ሊያካትት ይችላል።

ይሄ ሁሉ መሆን የሚችለው ግን አንድ ነገር ሲሟሏ ብቻ ነው።በዚህ አገዛዝ መቃብር ላይ ዲሞክራሲያዊ ስርአት ሲመጣ!!

Filed in: Amharic