>

ግምገማ በአሰባሳቢ ማንነት መጽሓፍ ላይ (መሓመድ ኢድሪስ)

ኢትዮጵያዊነት፤ አሰባሳቢ ማንነት በአንድ አገር ልጅነት
(
ዩሱፍ ያሲን)

ato-yusuf-yasins-bookይህ ዛሬ ለመወያያነት ያቀረብኩትን የአቶ ዩሱፍ ያሲን ‘ኢትዮጵያዊነት፤ አሰባሳቢ ማንነት በአንድ አገር ልጅነት’ የሚለውን መፅሀፍ ማንበብ ከመጀመሬ በፊት የሽፋን ስዕሉና የርዕሱ መርዘም ብዙም እንዳልሳበኝ ለአንድ ወዳጄ ስነግረው እሱም ‘ርዕሱ ገና ከአሁኑ ምሁራዊ ስራ እንደማያስነብበን ይናገራል’ ነበር ያለኝ፡፡ በዚህ ስሜት ውስጥ በመሆን ስለደራሲው የተዘጋጀችውን አንድ አንቀፅ አነበብኩ፡- ደራሲው ከአፋር ቀይ ባሕር ዳርቻ የተገኙ፣ በጥላሁን ግዛው ይመራ የነበረው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ማሕበር ስራ አስፈፃሚ የነበሩ፣ ከአአዩ የህግ ትምህርታቸውን አቋርጠው ተሰደው በጀርመን አገር የፖለቲካል ሳይንስ የትምህርት ክፍል ምሩቅ መሆናቸው ለመፅሀፉ እንድጓጓ አደረገኝ፡፡ ከአበዮቱ በኋላ ከስደት ተመልሰው በብሔረሰቦች ጥናት ኢንስቲትዩት፣ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያቤት የአገር ውስጥ እና የውጭ ዲፕሎማሲ ኃላፊነቶች ላይ መስራታቸው ከሁሉም በላይ ደግሞ በጦቢያ መፅሔት ሐሰን ዑመር ዓብደላ በሚል ብዕር ስም የሚታወቁት በሳል ፀሀፊ መሆናቸውን ስረዳ ለመረጡት ርዕስ በበቂ ተሞክሮ የታሸ ስራ እንደሚያስነብቡን እርግጠኛ ሆንኩ፡፡ የመፅሀፉ መታሰቢያነት ‘ለለውጥ ፈላጊዎች’ መሆኑ ደግሞ እንደ አንድ በአገሩ ላይ ለውጥን እንደሚሻ ዜጋ ለኔ የተፃፈ እንደሆነ በመረዳት ገፅ ከገፅ እያገላበጥኩ ማንበቡን ተያያዝኩት፡፡

አቶ ዩሱፍ ያሲን የወደፊቱ አብሮነታችን በምን መልኩ ይደራጅ የሚለው ሀሳብ ሁሉንም ከእንቅልፉ የሚያባንን የስጋት ምንጭ መሆኑ ለመፅሀፉ መዘጋጀት እንደዋነኛ ምክንያት አድርገው ይጠቅሳሉ፡፡ ያለቀለት መፍትሄ ከግለሰብ እንደማይመጣም በመጠቆም አብሮ ለመኗኗር ለሚደረገው የፎርሙላ ፍለጋ የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣትና ያልተኳኳሉ እውነቶች ባሏቸው ነጥቦች ላይ የመወያያ ሀሳቦችን መሰንዘር እንደሆነ ያስቀምጣሉ፡፡ እኛም መፅሀፉ ላይ ውይይታችንን አሀዱ ብለን ጀምረናል፡፡ ቅኝታችን መፅሀፉ በተዘጋጀበት ቅደም ተከተል ሳይሆን ለመወያያነት በተመረጡ ርዕሶች ላይ በማተኮር እዛም እዚህም እያልን የምንጓዝ ይሆናል፡፡ በሚነሱት ነጥቦች ላይ የግል ትንተና አለመስጠቴ ይታወቅልኝ፡፡ ፅሁፉም መደበኛ የመፅሀፍ ዳሰሳ ሳይሆን ከመፅሀፉ ለመወያያነት የጠመረጡ ሀሳቦችን ብቻ ማንሻራሸር በመሆኑ በፀሀፊው የአፃፃፍ ዘይቤና የስነፅፍ መርሆዎች ዙሪያ የምለው አይኖርም፡፡ በተጨማሪም ከዚህ በፊት በመፅሀፉ ዙርያ የተሰሩ የምስክርነት ፅሁፎች ባልዳሰሷቸው ነጥቦች ላይ ለማተኮር እሞክራለሁ፡፡

በአንድ አገር ልጅነት አብሮ ለመኗኗር የመጀመሪያው እንቅፋት አንዳችን ስለሌላችን የያዝነው የእኛ እና እነሱ ምስል ነው ይሉናል ፀሀፊው፡፡ አስገራሚው ነገር ግን ኢትዮጵያውያን ስለራሳችን ምስል የቀረፅነው ከራሳችን ጥናት ላይ ተመስርተን ሳይሆን የውጭ አገር አሳሾች የጉዞ ማስታወሻዎች፣ ሚስዮናውያን፣ የውጭ አገር ፀሀፍት ስለኛ የነገሩንን አዎ እኛ እንደዚህ ነን ብለን በመቀበል እና አለፍ ሲልም በዘልማድ በአፍ ለአፍ ከተላለፉልን አስተሳሰቦች ላይ ተመስርተን ነው፡፡ ይህ መሆኑ ደግሞ እኛ እና እነሱ የሚባለው ልዩነት የማይገረሰስ ቋሚ ግድግዳ አድርገን እንዳንወስደው እድል የሚሰጠን ነው፡፡ ይህ ሲባል እንደ አባ ባሀሪ ድረሰት ያሉ ስራዎች በአገራችን የህዝቦች ምስል ቀረፃ ላይ የተጫወቱት ሚና የለም ማለት አይደለም፡፡ እንዲያውም የእኛ እና እነሱ ምስል እነሱን ለእኛ ስጋት አድርጎ እስከመውሰድም ማድረሱ አይካድም፡፡ ነገር ግን የምስል ቀረጻው ስር መሰረት የተጠና አለመሆኑ እና ተለዋዋጭ መሆኑ በአንድ አገር ልጅነት ለመኗኗር ቀመር ለመፈለግ በቁርጠኝነት ብንነሳ የሚያግደን አይሆንም፡፡ ለዚህም መፍትሄው ትኩረታችንን ከተረት ስጋት ወደ ስትራቴጂካዊ ስጋት ማዞር፣ ከተረት እና ተአምራዊ መፍትሄ ወደ ስትራቴጂካዊ መፍትሄ መሻገር ነው ይሉናል፡፡ እንደ አገር ምን ምን ያኮራናል ብለን ብንጠይቅ፣ ምን ምንስ ያሳፍረናል ብለን ብንጠይቅ ከተጠኑ እና እስትራቴጂካዊ ከሆኑ ኩራቶች ይልቅ ባዶ ፉከራዎች ይበዙታል፡፡ በትክክል እንደ አገር የሚያሸማቅቁንን ወደኋላ ትተን ጣት የምነቀስርበት መፈለግ ይቀለናል፡፡

ለማሳያነት ከሚጠቀሙት መካከል ድሮ ድሮ መቀመጫውን ሰሜን ምስራቅ ላደረገው ክፍል ደቡቡ እና ደቡብ ምስራቁ (ሙስሊሙ እና ኦሮሞው) ስጋት ተደርጎ ይሳል ነበር፡፡ ዛሬ ሁሉም የአንድ አገር ግዛቶች ሆነው ሳለ የስጋት አሳሳላችን ግን አልተቀየረም፡፡ ዛሬም በኦሮሞው እና በሙስሊሙ እናስፈራራለን፡፡ መስጋት ያለብን እንደ አገር ለተጠኑ እና ቢሰራባቸው ችግራችንን ለሚቀርፉ ስጋቶች መሆን ሲገባው ፕሮፌሰር ጌታቸው ‘የግራኝ አህመድ ወረራ’፣ ‘የኦሮሞ ወረራ’ እና ‘የጣልያን ወረራ’ ለኢትዮጵያ ኋላ መቅረት ዋነኛ ምክንያቶች ናቸው የሚሉትን ትርክት አሚን ብለን መቀበል መርጠናል፡፡ የጦርነት አውዳሚነት ምንም አጠያያቂ ካለመሆኑጋ ሌሎች ታሪካቸው ሆን ተብሎ እንደወደመባቸው የሚታወቁ እንደ ግብፅ ያሉ አገራት አኩሪ ታሪካቸውን ዳግም ማስጠበቅ እንደቻሉ እንዘነጋለን፡፡ እኛ የራሳችን ፊደል ያለን መሆናችን ታሪክ ሰንዶ ለማቆየት ለምን አልተጠቀምንበትም ብሎ ከመጠየቅ ለኋላ መቅረታችን ‘እነሱ’ የሚባሉ ጣት መጠቆሚያ መፈለግ ወደአንድነት ከማያመጡን ምክንያቶች ግንባር ቀደሙ ነው፡፡ ፀሀፊው ወደ ሙስሊሙ እና ኦሮሞውም የሚሰነዝሩት ጥያቄም አለ፡፡ የኦሮሞ ብሔርተኞች ሌሎች ስለኛ ፈጥረውታል የሚሉትን ምስል እነሱም ከመፍጠር ባልተቆጠቡበት ሁኔታ እራሳቸውን ንፁህ ማድረግ ይቻላቸዋል ወይ? ሙስሊሙ በአገሩ ጉዳይ ያገባኛል ባይነቱ መጨመሩ አንድ የለውጥ ሀይል ቢያደርገውም ሴኩላር የሆነ የመንግስት ስርዓት እየፈለግን ኢ-መደበኛ ‘አሚሮች’ እየመረጡ በመስጂድ በታጠረ እንቅስቃሴ እንዴት ነው የጋራ አገራዊ ማንነት መገንባት የሚቻለው? (በሙስሊሙ ጉዳይ ላይ በተናጠል ሌላ መወያያ ፅሁፍ ይኖረናል)፡፡

ከመፅሀፉ ያወያያል ብዬ የመረጥኩት ሁለተኛው ወሳኝ ነጥብ በኢትዮጵያ የሚነሳው የብሔር ጥያቄ ከብሄር ፅንሰ ሀሳብ እና ፖለቲካዊ የእድገት ደረጃ ጋር ተያይዞ የሚነሳ ሳይሆን ከአገር ምስረታ ጋር ተያይዞ የተፈጠረ የታሪክ ጥያቄ ነው የሚለው ነው፡፡ በአፄ ምኒልክ የተመራው የግዛት ማስፋፋትና የአገር ምስረታው ሂደት አሉታዊ ተፅእኖዎች እና የብሔር እንቅስቃሴን ማደበላለቃችን በአንድ አገር ልጅነት አብሮ የመኖር አቅማችንን እየተፈታተነው እንደሆነም ያስረዳሉ፡፡ በአገር ምስረታው ላይ የወል ታሪክ መፍጠር ብንችል ሌላው በሙሉ ግነት እና በቀላሉ መርገብ የሚችል ነው-ለአቶ የሱፍ፡፡ ወደዚህ ድምዳሜ ለመምጣት የብሔርተኛ እንቅስቃሴ በአውሮፓ ብሔርተኛ እንቅስቃሴዎች እንደታየው ዋነኛ አላማው የራስን መንግስት መመስረት ነው የሚል ትርጓሜ በመስጠት ይነሳሉ፡፡ ብሔርተኝነት ዋና አላማው የራስን መንግስት መመስረት ከሆነ ደግሞ የራሱን መንግስት ለመመስረት ብቁ የሆነው ብሔር የቱ ነው የሚለውን ጥያቄ ይወልዳል፡፡ እንደ ፖለቲካ ሀይል አንድ ስብስብ ብሔር ለመባል የሚበቃው ምን ሲሆን ነው የሚል ጥያቄም ያነሳል፡፡ የጆሴፍ ስታሊንን የብሔር አተረጓጎም በመውሰድም በሀገራችን ብሔር የሚባሉት በርግጥስ ብሔር የሚባለው ስብስብ ሊደርስ ከሚጠበቀብት የማህበረሰብ እድገት እርከን ላይ ደርሰዋል ወይ የሚል ጥያቄ አጭሮ በቂ መልስ ሳይሰጠው እንዳለፈው ይሰማኛል፡፡ የደርግ የኢትዮጵያ ብሔረሰቦች ጥናት ኢንስቲትዩት ሁሉንም ‘ብሔረሰብ’ ብሎ መጥራትና የኢፌዲሪ ህገመንግሰት ደግሞ ብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ለሚለው አገላለፁ ማን ብሔር፣ ማንስ ብሔረሰብ እንደሆነ ለይቶ አለማስቀመጡ በኢትዮጵያ ብሔር የሚለው ቃል የረጋ ፖለቲካዊ ትርጓሜ ላለመያዙ አስረጅ አድርጎ ያመጣዋል፡፡ የዚህ ወሳኙ ፖለቲካዊ እንድምታ ደግሞ የተማሪዎች እንቅስቃሴ ወቅት በዋለልኝ መኮንን የተነሳው ሀሳብ ፖለቲካዊ መልክ ያለው የብሔርተኛ እንቅስቃሴ ትክክለኛ መገለጫ ሳይሆን በአፄ ምኒልክ በተካሄደው የአገር ምስረታ ሂደት ላይ የተፈጠረ የታሪክ ጥያቄ ነው ሲል መደምደሙ ነው፡፡

ስለዚህ ለብዙ ችግሮቻችን ቁልፉን አፄ ምኒልክ ዘመን ላይ እንፈልገው ይሉናል፡፡ ሁሉንም ኢትዮጵያዊ በአንድ አገር ልጅነት አብሮ መያዝ የተሳካለት መሪ እንዳልነበረን በሰፊው ያስረዳሉ፡፡ ነገር ግን የአፄ ምኒልክን የማስገበር እንቅስቃሴ ከቀደሙ መሳፍንትም ሆነ ከቴዎድሮስ እና ዮሀንስ ጋር የሚወዳደር አለመሆኑን አፅንኦት ይሰጡታል፡፡ የአፄ ምኒልክ የአገር ምስረታ ሂደት በአንድ በኩል አገር ለመውለድ የተካሄደ የማይቀር የስቃይ ምጥ ሲሉት በሌላ በኩል ግን እንደ አገር አብረን መቀጠላችንን ጥያቄ ምልክት ውስጥ የከተተ የታሪክ አጋጣሚ ነው ይሉታል፡፡ ስለአፄ ምኒልክ ያለው ኦፊሴላዊ ታሪክ የታሪክ ተማራማሪዎችን ፍተሸ የማለፍ አቅም እንደሌላውና በአሸናፊዎች በመፃፉ ሀይል አንደተጫነው ማመን በሌላ በኩል በማህበራዊ ሳይንስ ላቦራቶሪ ውስጥ ካልሆነ በቀር ልቅም ክሽን ያለ ሂደት አሟልተው የተመሰረቱ አገሮች አለመኖራቸውን መረዳት ሁለት ፅንፎችን ወደመሀል ለማምጣት ወሳኝ ነው፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ለአቶ ዩሱፍ ኢትዮጵያውያን አብረን ለመኖር የተፈረደብን ህዝቦች ነን፡፡ እናም የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች በዋናነትም የኦሮሞ ብሔርተኛ እንቅስቃሴ መሪዎች ትልቁ ኃላፊነት በአንድ አገር ልጅነት አብሮ መኖር የማይቻልበት ምንም አይነት ፖለቲካዊ እና ታሪካዊ ማስረጃ ማቅረብ በማይቻልበት ሁኔታ ትኩረትና አቅማቸውን በአገር ምስረታው ታሪክ ሂደት ላይ እና መፃኢ የጋራ እድላችን ላይ አቀራራቢ ግንዛቤ መፍጠር ይሁን የሚል ነው፡፡

በአገር ምስረታው ሂደት ላይ መቀራረብ ስንችል ዜግነት የሚባለው በአንድ አገር ልጅነት የሚገኝ የሁሉም ኢትዮጵያውያን ማዕረግ መሆን ይጀምራል፡፡ ስለዜግነት ፅንሰ ሀሳብ ሰፊ ትኩረት ሰጥተው ይተነትናሉ አቶ ዩሱፍ በዚሁ ክፍልም የንደፈ ሀሳብና የተሞክሮ ሀብታም መሆናቸውን በተግባር ያሳዩናል፡፡ ዜግነትን ወደ ፓስፖርት ወረቀት ባለቤትነት አያወርዱትም፡፡ በዓለማችን በ38 አገሮች ውስጥ ከ 12 ሚሊዮን በላይ ሰዎች የየትኛውም አገር ፓስፖርት የላቸውም፡፡ እነዚህ ሰዎች ግን አገር አልባ፣ ዜግነት አልባ ናቸውን ሲሉ ይጠይቃሉ? ዜግነት የሚሰጥ ሳይሆን ግለሰቡ ለራሱ የሚሰጠው የሚወስደው ነው በሚል መንፈሳዊ አይነት ሀሳብ ያነሳሉ፡፡ በአንድ አገር ልጅነት አብሮ ሲኖርበአንዱ ላይ በተለየ መልኩ የሚጣሉ የመብት እቀባዎች ሌላው ቀርቶ እንደ አፄ ዮሀንስ ያልተጠመቀ አገር ጥሎ ይውጣ የሚለው ዜግነትን በህግ ደረጃ መንጠቅ የዜግነትን ስሜት ከግለሰቡ ላይ ሊወስደው አይችልም ሲሉ ይከራከራሉ፡፡ ሻገር ብለው ደግሞ በህግ መሰረት ላይ የቆመ የማዜግ (Naturalization
) አሰራር ኦባማን ከተራ ዜግነት አልፎ ለፕሬዝዳንትነት ሲያበቃ ኦባማ በአንዱ አረብ አገር ቢወለዱ ኖሮ ባለው የከፋላ ስርዓት ምክንያት ዜግነት አልባ ሆነው ይቀሩ ነበር ሲሉ ዜግነትን ከመንፈስነት ወደ ህጋዊ መሰረት ያለው አስተሳሳሪ ሀይልነት ያመጡታል፡፡

አገራዊነት እና አገራዊ ማንነትን መለየት አለመቻላችን የአገር ምስረታ ሂደትን እና የብሔር ፖለቲካን ማቀላቀላችን ያመጣብንን አይነት ችግር ውስጥ እንደከተተን ያምናሉ፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ባህል የተጫነው ኢትዮጵያዊ ማንነትን በአይዲዮሎጂ በደንብ የተፍታታ ኢትዮጵያዊነት አሸንፎ እስኪወጣ አገራዊ ማንነት አገራዊነትን ሳይቀር ወደማስተባበል ይወስደናልና፡፡ ስለዚህ ለአቶ ዩሱፍ ኢትዮጵያውያን የአብሮነት ቀመር ለማግኘት ብዙ እድሎች እንዳሉን በማመን ትልቁ ጉዳይ የህግ የበላይት እና ፍትሀዊ የስልጣን ክፍፍል ነው ሲሉ ሌላ ሰፊ ትንተና ውስጥ ይገባሉ፡፡

በቅድሚያ ዜጎች ከመንግስትጋ ያላቸው ግንኙነት በዜግነታቸው መሰረት እንጂ በሀይማታቸው እና በብሄራቸው መሆን ሲቆም አገራዊነት ከእስላማዊነት፣ ክርስያናዊነት፣ ኦሮሞነት..ወዘተ የሰፋ ቅርንጫፍ ማንነቶችን አሸንፎ የመውጣት አቅም ይኖረዋል፡፡ ሁሉም ዜጎች በህግ ፊት እኩል መሆን ሲጀምሩ ሌሎች ልዩነቶች ጌጦች ይሆናሉ፡፡ እያንዳንዱ ዜጋ መብቱ በህግ ፊት ከሌላው እኩል እንደሚጠበቅለት እርግጠኛ መሆን ሲችል ሌሎች ነገሮች ለመወያየት ፍቃደኛ ይሆናል፡፡ የዩጎዝላቪያ ተሞክሯቸውን እያነሱ የቀበሌ መታወቂያ ላይ ብሔረሰብ በሚለው ቦታ ላይ ትግሬ ብሎ መሙላት እና ኢትዮጵያዊ ብሎ መሙላት በህግ ፊት የመብት ጉዳይ እንጂ የልዩ ጥቅም ምንጭ ወይንም አንዱ ከአንዱ የበለጠ ኢትዮጵያዊ መሆን መልዕክት መያዙን ያቆማል፡፡ እናም ኢትዮጵያውያን ያልተሳካልን በህግ የበላይነት ላይ የፀና ሁሉንም ዜጎች እኩል የሚያይ የፖለቲካ ስርዓት ነው ሲሉ ዛሬ ላይ ትልቅ ራስ ምታት የሚመስለው ብሔር ተኮር ውጥረት መርገቢያው የህግ የበላይት ብቻና ብቻ ነው ይላሉ፡፡ የችግሮቻችን ሁሉ ምንጭ የገዢዎቻችን ያልተገደበ ስልጣን ፍላጎት እና እሱን ለማሳካት ዜጎችን መሳሪያ ማድረጋቸው ነው፡፡ በገዢዎች መካከል፣ በገዢዎችና በዜጎች እንዲሁም በዜጎች መካካል ያለውን ግንኙነት የሚወስነው የህግ የበላይነት ካልሆነ በስተቀር እጣ ፈንታችን እንደ ሶሪያ እና ሊቢያ እንዲያውም ከዚያ የከፋ እንደሆነ ስጋታቸውን እያጋሩ ጥያቄው የፍትህ እና የዴሞክራሲ ጥያቄ ነው ይሉናል፡፡ መፍትሄውም አንዱ ሌላውን በሀይለስላሴ ግዜ ይደረግ እንደነበረው የሀገር ፍቅርን እንዲያስተምር ማድረግ መሆኑ ቀርቶ፣፡ ወይንም የኦሮምያ ክልል የኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ በቅርቡ እንዳነሱት አንዱ ‘የተሸለ ኢትዮጵያዊነት’ ኖሮት ‘አነስተኛ ኢትዮጵያዊነት’ አላቸው ለሚላቸው አካላት ሊሰብክ የሚችልበት አግባብ መሰረቱን አጥቶ በህግ ማዕቀፍ ውስጥ የሚገለፅ በዜግነት ላይ የተመሰረተ አሰባሳቢ ማንነት እንፍጠር መፍጠርም እንችላለን ነው መልዕክታቸው፡፡ አጣልቶ የሚያፋቅር ትዳር በጣም ጠንካራ እንደሆነ ሁሉ ዳግም ያስታርቀን እያሉም ያጠቃልላሉ፡፡

በስተመጨረሻም
አቶ ጥላሁን አፈሳ ስለዚህ መፅፍ ባዘጋጁት ረዘም ያለ የምስክርነት ፅፍ “በዚህ አሳሳቢና ውስብስ የአገራችን ጥያቄ ላይ ከሰላሳ ዓመታት በላይ ስንጠብቀው የነበረው አንድ ሁነኛ መጽሃፍ ባገር ቋንቋ ፊደል ተለቅሞ ለአንባቢ መቅረቡ ስለታወቀኝ ከፍ ያለ ደስታ ተሰምቶኛል” ሲሉ ነበር የገለፁት

ሱለይ አደም በበኩሉ ስለዚህ መፅሀፍ የሰጠው ምስክርነት “እንደ ዳስ ካፒታል ደግሞ ደጋግሞ መነበብ ያለበት ስራ ነው” የሚል ሲሆን ሌላው የፌስ ቡክ ወዳጄ ይህን መፅፍ አንብበን ኢትዮጵያዊነታችንን እንፈትሽ ብሎናል፡፡ Hussen Kedir እንድናነበው ሲወተውተን መክረሙን አስታውሳለሁ

እናንተም መፅሀፉን እንድታነቡት የኔም ግብዣዬ ነው!

በዚሁ ላብቃ

Inbox

 

Filed in: Amharic