>
5:13 pm - Monday April 19, 6432

የኬንያ ምርጫ ለቀሪው የአፍሪካ ሐገሮች ምሳሌ መሆን በሚችልበት ሁኔታ ተጠናቅቋል (ዮናስ ሃጎስ)

kenya-electionአሁን ከመሸ በ KTN ቴሌቭዥን ጣቢያ ላይ ቀርቦ የምርጫ ቦርድ ማጭበርበሩንና በፎርም 34A ውጤት መሰረት አሸናፊ መሆኑን የገለፀው የተቃዋሚዎች መሪ ራይላ ኦዲንጋ ትክክለኛ ውጤት ነው ያለውን አቅርቦታል። ይህን መግለጫ ተከትሎ እንደ መቀዝቀዝ ብሎ የነበረው የኪቢራ ሁከት በድጋሚ አገርሽቶበት ቦታው በአድማ በታኝ ፖሊሶችና ወታደሮች ተከብቧል።
•°•
የምርጫ ቦርድ ከሁሉም የምርጫ ጣቢያዎች የሚመጣው የምርጫ ውጤት ዛሬ ተጠናቅቆ ይገባል የሚል ዕምነት ስላለው ውጤቱን ከነገ ጀምሮ እስከ ቀጣይ ሰኞ ባሉት ጊዜያት ድረስ የሚያሳውቅ ይሆናል። ኬንያኖች የምርጫውን ውጤት ራሳቸው አይተው አገናዝበው ይፈርዱ ዘንድ አሰራሬን ግልፅ ማድረግ እፈልጋለሁ ያለው የምርጫ ቦርድ ከሁሉም የምርጫ ጣቢያ የሚገኙትን ፎርም 34A ወረቀቶች ስካን አድርገው በዌብሳይቱ ላይ እንደሚለቁትና ማንኛውም ኬንያዊ ወደ ዌብሳይታቸው ጎራ ብሎ በየትኛው የምርጫ ጣቢያ ማን ምን ድምፅ እንዳገኘ መመልከት ይችላል ማለት ነው።
•°•
ከኬንያ የሂዩማን ራይት ቦዲ ውጭ ያሉ የኬንያ ምርጫ ዓለማቀፍ ታዛቢዎች ምርጫው ትክክለኛ እንደነበረ ግን ጥቃቅን የሚባሉ ስህተቶች እንደነበሩበት ዛሬ ከመሸ በሰጡት መግለጫ አሳውቀዋል። ታምቦ ምቤኪ የአፍሪካ ሕብረት ታዛቢ ቡድን ተወካይና ጂም ኬሪ የአሜሪካ ታዛቢ ቡድን ተወካይ እንዳሉት ከሆነ አንዳንድ በአሰራር ስህተት ምክንያት የተፈጠሩ ጉድለቶች ቢታዩበትም ቅሉ የኬንያ ምርጫ ለቀሪው የአፍሪካ ሐገሮች ምሳሌ መሆን በሚችልበት ሁኔታ ተጠናቅቋል ሲሉ ተናግረዋል።
•°•
የምርጫ ቦርዱ ውጤት የሚያሳየው የአሁኑ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ በ8 ሚልዮን ድምፅ እየመሩ መሆኑን ሲሆን የራይላ ኦዲንጋ «ትክክለኛ» የተባለው ውጤት ደግሞ ራይላ ራሱ በ8 ሚልዮን ድምፅ ማሸነፉን ያሳያል… የትኛው ትክክል ይሆን? ይሄ ሁለት የተለያዩ የምርጫ ውጤት በሐገሪቷ ላይ ምን ያመጣ ይሆን? አብረን በሂደት እናየዋለን።

ባለፉት ሁለት ቀናቶች (የምርጫው ቀን ከተቆጠረ ሶስት ቀናቶች) በናይሮቢና ሌሎች ዋና ዋና ከተሞች የንግድ ቤቶች ዝግ ሆነው ነው የሰነበተቱት። የመንግስት ሰራተኞችም ሁከቱን በመፍራት ከስራ ገበታቸው ላይ ሊገኙ አልቻሉም። ይህ ያሳሰበው የኬንያታ መንግስት ሁሉም የመንግስት ሰራተኞች በነገው ዕለት በስራ ገበታቸው ላይ መገኘት እንዳለባቸው የሚያስጠነቅቅ ሰርኩላር ከመሸ ወዲያ በሚድያዎች አስነግሯል። የመንግስት መ/ቤቶቹም በነገው እለት በስራ ገበታው ላይ ያልተገኘን ሰራተኛ ስም ዝርዝር ማቅረብ እንዳለባቸው ሰርኩላሩ ያዝዛል።
•°•
ጥያቄው የከተማዋ የትራንፖርት ሁኔታ በጣም በመነመነበትና ማምሻውን ናሳ እኛ ባለን ውጤት መሰረት አሸናፊ ነን ብለው ባወጁበት ሁኔታ ይሄ የመንግስት ትዕዛዝ ተግባራዊ ይሆናል ወይ የሚለው ነገር ነው።
°•
የምርጫ ቦርዱን ውጤት ለማየት የምትፈልጉ…https://forms.iebc.or.ke/ በመጎብኘት ውጤቱን በየምርጫ ጣቢያው ማየት ትችላላችሁ።
Filed in: Amharic