>

የተቃዋሚው መሪ ራይላ ኦዲንጋ የምርጫ ውጤቱን እንደማይቀበሉ ተናገሩ (ዮናስ ሃጎስ)

moamed-in-keniya-by-yonas-hagosጋዜጠኛውን ለፓርላማ የመረጠ ህዝብ

ይሄ ሰው መሐመድ ይባላል። ከተወሰኑ ዓመታት በፊት በዌስትጌት የናይሮቢ የገበያ ማዕከል ጥቃት በደረሰ ወቅት ሁኔታውን እንዲዘግቡ ከተላኩ ጋዜጠኞች አንዱ ነበረ። መሐመድ እንደሌሎቹ ጋዜጠኞች በቦታው የሽብሩን ጥቃት ለመከላከል የሄዱ ወታደሮችን ጀግንነት ለመዘገብ አልታደለም። ይልቅስ ሐቀኝነቱና ለእውነት የቆመ ጋዜጠኛ መሆኑ አስገደዱትና በወቅቱ የገበያ ማዕከሉን ከጥቃት እንዲከላከሉ የተላኩት ወታደሮች በጥቃቱ ሳቢያ ባለቤቶቻቸው ወይ የሞቱባቸው አሊያም የሸሹባቸው ሱቆችን ወርቅና ገንዘብ እያወጡ ሲዘርፉ እጅ ከፍንጅ በካሜራው ቀርፆ በቴሌቭዥን በይፋ ለቀቀው። በወቅቱ መሐመድ ከብዙ «የኬንያን ስም አበላሽቷል» ባዮች የመግደል ሙከራና ዛቻ ደርሶበት የነበረ ቢሆንም የሚሰራበት የቴሌቭዥን ጣቢያ ግን የስራውን ብቃት በማድነቅ የራሱን የሆነ የምርመራ ጋዜጠኝነት ስራውን የሚሰራበት ሳምንታዊ የዬሌቭዥን አየር ሰዓት ሰጡት።
•°•
ለአፍታ ያህል ይህ ሰው ኢትዮጵያ ውስጥ ያለ ጋዜጠኛ ቢሆን ሊደርስበት የሚችለውን መንገላታትና እስር እንዲሁም ግድያ በማሰብ የአንድ ደቂቃ የህሊና ፀሎት እናድርግ።
•°•
አስቡት በገበያ ማዕከሉ ላይ ጥቃቱን ያደረሰው አልሻባብ ነው። መሐመድ ደግሞ የሶማሊ ዝርያ ያለወወ ኬንያዊ ነው። መንግስታችን ቢሆን መሐመድን በቀላሉ በአልሻባብነት ፈርጆ በሽብር ሕጉ የመጨረሻው የተባለውን ፍርድ ያከናንበው እንደሆነ በፍፁም አያጠራጥርም።
•°•
ያው መሐመድ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለ ጋዜጠኛ አይደለምና ታሪኩ ቀጥሏል። የአየር ሰዓቱን ካገኘ በኋላ ብዙ የምርመራ ጋዜጠኝነት ዘገባዎችን በዚህ አየር ሰዓቱ ላይ ለእይታ አብቅቷል። ከነዛ ውስጥ በጣም ገንነው የወጡለት በናይሮቢ በሚገኙ ጠንቋዮች ላይ ራሱ ጠንቋይ ፈላጊ መስሎ ቦታው ድረስ ሄዶ የዘገበው፣ በፓስተር ኪኛሪ (አስታወሳችሁት ያንን አጭበርባሪ ፓስተር) ላይ የሰራው ዘገባና በቅርቡ ደግሞ ኬንያ ከአውሮፓ ያገኘችው ዩሮ ቦንድ ላይ ተሰራ የተባለውን ሙስና ያጋለጠ አንድ ሚንስትር (ሚንስትር ዲዔታ አላልኩም) ከስራ እንዲወገድ ያደረገ ዘገባ የሚጠቀሱ ናቸው።
•°•
ከቴሌቭዥን ጣቢያው በተጨማሪ የዛሬ ዓመት መንግስት የዓመቱ ምርጥ ጋዜጠኛ ሲል ያወደሰው ይኸው መሐመድ የሰፈሩ ሰዎች ደግሞ በሌላ መልኩ በትላንትናው ዕለት አወድሰውታል። ይኸውም ትላንት በተደረገው ምርጫ የቀድሞውን የፓርላማ ተወካያቸውን አሰናብተው ከመሐመድ በተሻለ ድምፃችንን ሊያሰማልን የሚችል ሌላ ሰው የለንም በማለት በሚደንቅ ሁኔታ የፓርላማ ተወካያቸው እንዲሆን ድምፃቸውን ሰጥተውታል።
•°•
እዚሁ አፍንጫችን ስር ያለች ሐገር ውስጥ መንግስትን ተቃውመህ በምትሰራው ዘገባ መንግስት የዓመቱ ምርጥ ጋዜጠኛ ብሎ ሲያወድስህና ሕዝቡ ደግሞ ለፓርላማ ክብር ሲያበቃህ እውነት እኛ ኢትዮጵያውያንን ለምን በሰው ሐገር ትቀናላችሁ ሊለን የሚቻለው አንድ ሰው ይኖራልን?
•°•
አቅጣጫውን ከመሐመድ ወደ ምርጫው መለስ ስናደርገው ከ36 ሺህ የምርጫ ጣቢያዎች የተሰበሰበው ድምፅ ፕሬዚዳንቱን ከተቃናቃኛቸው በአንድ ነጥብ ሶስት ሚልዮን ድምፅ ብልጫ እንዲገኙ አድርጓቸዋል። አጠቃላይ የምርጫ ጣቢያዎቹ ብዛት አርባ ሺህ በመሆኑ ከዚህ በኋላ አሸናፊውን ሊቀይር ይችላል ተብሎ የሚታሰብ ድምፅ እንደማይኖር ተረጋግጧል። የተቃዋሚው መሪ ራይላ ኦዲንጋ የምርጫ ውጤቱን እንደማይቀበሉ የተናገሩት ከሌሊቱ ዘጠኝ ሰዓት ላይ በጠሩት ጋዜጣዊ መግለጫ ነው። (ለመሆኑ ኢትዮጵያ ውስጥ ከሌሊቱ ዘጠኝ ሰዓት ተነስቶ መግለጫ ሊከታተል የሚሄድ ጋዜጠኛ ይኖር ይሆን? እዚህ እቴ ስራው 24 ሰዓት ነው። እንደዚህ ዓይነት ሕዝቡ በአትኩሮት የሚጠባበቀው ጉዳይ ሲኖር ደግሞ መረጃዎች የሚተላለፉት በደቂቃዎች ልዩነት ነው።
•°•
ለማንኛውም ሙሉ ውጤቱ ከተገለፀ በኋላ የኬንያ የመጪዎቹ ቀናቶች እጣ ፈንታ ይወሰናል። ባባ ኦዲንጋ አልቀበልም ባለው አምርሮ ደጋፊዎቹን ወደ አደባባይ ከጠራ… ያው ሰሞኑን ቤት ተቀምጠን በሶ እያፈረፈርን መብላት ነው። አይ ተሸንፌያለሁ! መልካም የስራ ዘመን! ብሎ ከተናገረ… ኑሮ ወደ ቀድሞዋ ሩጫ ትመለሳለች ማለት ነው። በጎውን ተመኙልን ወዳጆቼ! ከትላንትና ጠዋት ጀምሮ እንቅልፍ ባይናችን ሳይዞር ውጤት እየጠበቅን ነው…

Filed in: Amharic