>

የኢትኖግራፊ ጉዞ ወደ ጎጃም (ክፍል ሁለት) [ጸሐፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ]

ጎጃምን ከሌሎች የቀድሞ ክፍለ ሀገሮቻችን ለየት የሚያደርገው ዙሪያውን በዐባይ ወንዝ የታጠረ መሆኑ ነው፡፡ ከጣና ሐይቅ በስተምዕራብ ራቅ ብሎ ካለው የግልገል ዐባይ መነሻና በሱዳን ድንበር መካከል ከሚገኘው ክፍት መሬት በስተቀር ክፍለ ሀገሩ በሙሉ በዐባይ የተከበበ ነው፡፡ እርግጥ በወንዝ የታጠሩ ሌሎች ክፍለ ሀገሮች አሉን፡፡ ለምሳሌ የቀድሞው የሀረርጌ ክፍለ ሀገር በምዕራብ በኩል በአዋሽና በዋቢ ሸበሌ ወንዞች የተከበበ ነው፡፡ ወለጋ ደግሞ በምሥራቅ በጊቤ ወንዝ፣ በሰሜን በዐባይ ወንዝ ይዋሰናል፡፡ ሌሎች የቀድሞ የኢትዮጵያ ክፍለ ሀገሮችም ከሁለት ወይም ከዚያ በላይ ከሚሆኑ ወንዞች ጋር የሚዋሰኑ ናቸው (በወንዝ ያልታጠረው የቀድሞ ክፍለ ሀገራችን ኢሉባቦር ብቻ ነው)፡፡ በአንድ ወንዝ የተቆለፈው ክፍለ ሀገር ግን ጎጃም ብቻ ነው፡፡ ይህም ዘወትር ይደንቀኛል፡፡

በሌላ በኩል ጎጃምን የከበበው ዐባይ ራሱ ይገርማል!! ስሙ የሰዎች መጠሪያ ሆኖ የሚያገለግለው ብቸኛ ወንዛችን እርሱ መሆኑን ልብ ብላችኋል? “አባይ”፣ “አባይነህ”፣ “አባይነሽ”፣ “አባይ-ወርቅ” በሚባሉ ስሞች የሚጠሩ ዜጎቻችን እልፍ አእላፍ ይሆናሉ፡፡ “አዋሽ”፣ “ጊቤ”፣ “ዋቢ ሸበሌ”፣ “ተከዜ” የሚባሉ ሰዎችስ ሰምታችሁ ታውቃላችሁ? በበኩሌ ገጥሞኝ አያውቅም፡፡ ከአማርኛ ስሞች በተጨማሪ ዐባይ በኦሮምኛ የሚጠራበት “Abbayya” የብዙ ሰዎች ስም ሆኖ እያገለገለ ነው፡፡ አሁን ከጠቀስኳቸው ሌላ “የአባይ-ሉል”፣ “የአባይ-እንቁ”፣ “የአባይ-ፈርጥ”፣ “የአባይ-አልማዝ” የሚሉ ስሞችም ሳይኖሩ ይቀራል? ለጊዜው አልታወቀም፡፡ ይህንን ዕድል ያገኘው ዐባይ ብቻ መሆኑ ግን ዓጃኢብ ያስብላል፡፡

ዐባይና ተረቶቻችንስ ምንና ምን ናቸው? እንደ ዐባይ በተረትና ምሳሌዎቻችን ውስጥ የሚመላለስ ወንዝ ይኖረን ይሆን? እስቲ ስለዐባይ ብቻ የተነገሩትን እንቁጠራቸው ጓዶች!

የዐባይን ልጅ ውሃ ጠማው፡፡
ዐባይ ማደሪያ የለው፣ ግንድ ይዞ ይዞራል፡፡
ዐባይን ያላየ ምንጭ ያመሰግናል፡፡
ዐባይን የደፈረ ጅረትን አይፈራም፡፡
ወዘተ…..ወዘተ….ወዘተ….

በዘፈኖቻችንስ ቢሆንስ የዐባይን ያህል ሰርጾ የገባ ወንዝ አለን? የሸክላ ማጫወቻ መጥቶ የኢትዮጵያ ሙዚቃ መቀረጽ ከተጀመረበት ዘመን አንስቶ እስከ አሁኗ ደቂቃ ድረስ ዐባይን የተንተራሰሱ ስንኞችን በዘፈኖቻን ውስጥ እየሰማን ነው፡፡ ለምሳሌ ድምጻዊ ሙሉቀን መለሰ ከሰላሳ ዓመት በፊት በአንዱ ዘፈን እንዲህ በማለት አዚሞ ነበር፡፡

የዐባይ ዳሩ ዳሩ ያበቅላል ጠንበለል
ዋጥ ላርጋትና አላየሁም ልበል፡፡

ከአንጋፋ አርቲስቶቻችን መካከል አንዱ የሆነው ዓለማየሁ እሸቴም ከሙሉቀን ቀደም ብሎ ለጎጃሟ ጉብል እንዲህ ብሎላታል፡፡

እሷስ እንኮይ ናት የዐባይ ዳር
እንኮይ ናት የዐባይ ዳር
የማትጠገብ የማትሰለች
እንኮይ ናት የዐባይ ዳር፡፡

በአማርኛ ዘፈኖች ውስጥ ለሚመላለሱት ዐባይ ተኮር ግጥሞች መሠረት የሆነው ከዐባይ ጋር ተላምዶ የሚኖረው አማርኛ ተናጋሪው የጎጃም ህዝብ ዐባይን በግጥሞቹና በቅኔዎቹ ውስጥ እያስገባ ልዩ ልዩ ስንኞችን የቋጥርበት ባሕል ነው፡፡ የጎጃም ሕዝብ ከዚህም አልፎ ዐባይን በሰውኛ ዘይቤ የሚያናግርበት ስነ-ቃል አዳብሯል፡፡ ታዲያ ከዐባይ በስተደቡብ የሚኖረው የወለጋ ኦሮሞም ዐባይን በመንተራሰስ ልዩ ልዩ ግጥሞችን መግጠምን ተክኖታል፡፡ ለምሳሌ በወለጋ የተወለደው ታዋቂው ድምጻዊ ተሾመ አሰግድ በጣም በሚታወቅበት የኦሮምኛ ዘፈኑ ለወደዳት ጉብል እንዲህ በማለት ዘፍኖላት ነበር፡፡

Bishaan Abbayyaa yaa taliila too
Bareedduu intalaa mucaa biyya koo
Sifudheen galaa koottu gara koo

ይህ የዘፈኑ አዝማች ነው፡፡ በቀላል አማርኛ እንዲህ ተብሎ ሊተረጎም ይችላል፡፡

እንደ አባይ ውሀ ንጹህ የሆንሽ
አንቺ ቆንጂቷ ሀገር ቤት ያለሽ
ነይልኝ ወደኔ ልግባ ወስጄሽ፡፡
—–
የዐባይ ወንዝ ለሰው ልጅ ስልጣኔ መወለድ ምክንያት ከሆኑት ሁለቱ ታላላቅ የዓለማችን ወንዞች አንዱ ነው፡፡ ከርሱ ጋር ይህንን ክብር የሚጋራው “ኤፍራጥስ” ነው፡፡ የኤፍራጥስ ወንዝ ለጥንቱ የሜሶጶጣሚያ እና የአሶሪያ ስልጣኔዎች መከሰት መንስኤ የሆነ ነው፡፡ የዐባይ ወንዝም ለአፍሪቃዊያኑ የግብጽና የኑቢያ ስልጣኔዎች መሠረት የሆነ ነው፡፡ ሎሬት ጸጋዬ ገብረ-መድኅን ለዐባይ በጻፉት ታዋቂ ግጥም ውስጥ ይህንን እውነታ እንደሚከተለው ገልጸውታል፡፡

ዐባይ የምድረ-ኩሽ መኩሪያ 
በቅድመ-ታሪክሽ ጥርጊያ
ከደምቢያ እስከ ኑቢያ
ከሜምፊስ እስከ ሜሮኤ
በስልጣኔሽ ትንሳኤ
ከዴልታሽ እስከ ዴር-ሱልጣን
ከኡሙ-ራህ እስከ ኡሙ-ዱርማን
(ባለቅኔው ዐባይን በእንስታይ ጾታ ነው ያናገሩት)

ይህ የዐባይ ወንዛችን ነው የሱዳን ዋና ከተማ በሆነችው ካርቱም ላይ ከማዕከላዊ አፍሪቃ ከሚነሳው ሌላኛው ወንዝ ጋር ተቀላቅሎ “ናይል”/ኒል” የሚባለውን የዓለማችን ረጅሙን ወንዝ የሚፈጥረው፡፡ ካርቱም የምትጠራበት ስም የፈለቀው ወንዞቹ በሚገናኙበት ቦታ የዝሆን ኩምቢ የመሰለ ቅርጽ ስለሚፈጥሩ ነው (በዐረብኛ ቋንቋ “ኹርጡም” ሲባል “የዝሆን ኩምቢ” ማለት ነው፡፡ አንዳንዴ ፍቺው ሰፋ ይልና “አፍንጫ” እንደማለትም ይሆናል፡፡ ይህንን “ኹርጡም” ነው ፈረንጆቹ ወደ “ካርቱም” የቀየሩት)፡፡

ከማዕከላዊ አፍሪቃ የሚነሳው “ነጩ ናይል” በርዝመቱ የኛውን ዐባይ ቢበልጠውም በውሀ ይዘቱ ግን እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡ በተጨማሪም ወንዙ በአብዛኛው በረግረጋማ ክልል ውስጥ ስለሚፈስ ከውሀው የሚበዛው እጅ በረግረጉ እየተዋጠ ይቀራል (“አስ-ሱድ” የሚባለው የዓለማችን ትልቁ ረግረግ የሚገኘው “ነጩ ናይል” በሚያቋርጣቸው ደቡብ ሱዳን እና የሱዳን ሪፐብሊክ መካከል ነው)፡፡ በመሆኑም የግብጽ ሕይወት ለመሆን ለበቃው የናይል ወንዝ እስትንፋሱ የኛው ዐባይ ነው፡፡

እውነት ነው! ናይልን “ናይል” ያደረገው የዐባይ ወንዝ ነው፡፡ ታዲያ ይህ መሆኑ እየታወቀ ፈረንጆች የ“ናይል መነሻ የቪክቶሪያ ሐይቅ ነው” የሚል ስላቅ ይደጋግማሉ፡፡ እነዚህ ፈረንጆች እንዲህ የሚሉት “የዐባይን መነሻ አገኘን” በማለት ቱማታ የነፉትን የ19ኛው ክፍለ ዘመን የአውሮጳ ሀገር አሳሾችን አባባል በመከተል ነው፡፡ የጥንት ዶክመንቶችን ስትመለከቱ ግን “ናይል” (በዐረብኛው ስሙ “ኒል”) እየተባለ ሲጠራ የኖረው የኛው ዐባይ ወንዝ ራሱ እንደሆነ ትገነዘባላችሁ፡፡

የዐባይ ወንዝ በናይል በኩል ወደ ግብጽ ከሚፈሰው ውሀ የሚበዛውን እጅ የሚሸፍን መሆኑ በመካከለኛ ዘመን የኢትዮጵያ ነገሥታትም ይታወቅ ነበር፡፡ በመሆኑም ነገሥታቱ ከግብጽ ሱልጣኖች ጋር በሚጣሉበት ወቅት “የዐባይ ወንዝን እይዘውና ወደ ሀገርህ እንዳይፈስ አደርገዋለሁ” በማለት ይዝቱ ነበር፡፡ ዐፄ ዓምደ ጽዮን እና ዐፄ ዘርአ ያዕቆብ ለግብጽ ሱልጣኖች በጻፏቸው ደብዳቤዎች ውስጥ እንዲህ ዓይነቱ ዛቻ ተጠቅሷል፡፡ እነዚያ ነገሥታት ወንዙን የሚገድቡበት ቴክኖሎጂም ሆነ አቅም አልነበራቸውም፡፡ ይሁንና የግብጽ ሱልጣኖች ደብዳቤዎቹ ሲደርሷቸው በጣም ይሸበሩ ነበር፡፡ የዚህ መንስኤ ደግሞ በቀደሙት ዘመናት በኢትዮጵያ ምድር ተከስተው በነበሩት ከሶስት ያላነሱ የድርቅ ወቅቶች ወደ ግብጽ የሚደርሰው የወንዙ ውሃ በጣም ቀንሶ ስለነበረና በተለይም በአንደኛው ወቅት “የኢትዮጵያ ንጉሥ (ከዛግዌ ነገሥታት አንዱ ይመስለኛል) ወንዙን ገድቦታል” ተብሎ ስለተወራ ነው፡፡

“ዐባይ” ወንዙ በአማርኛና በግዕዝ የሚጠራበት ስም ነው፡፡ ከላይ እንደገለጽኩትም የኦሮምኛ ስሙ “Abbayya” ነው (“የወንዙ የኦሮምኛ መጠሪያ ሞርሞር ነው” የሚሉ ሰዎች አሉ፡፡ ስሕተት ነው፡፡ ዝርዝሩን ስለባሌ በጻፍኩት ጽሑፍ ውስጥ አሳይቼአለሁ)፡፡ የጥንቱ የአዳል ሱልጣኔት ሕዝቦች ወንዙን “አባወይን” ይሉት እንደነበረስ አውቃችኋልን?

አዎን! በአዳል ምድር በተጠናቀሩ ጥንታዊ ሰነዶችም ሆነ ወደ አዳል ምድር መጥተው የነበሩ የዐረብ ደራሲዎች በጻፏቸው መጻሕፍት ውስጥ ወንዙ “አባወይን” ተብሎ ነው የተጠቀሰው፡፡ ለምሳሌ በ1526 ገደማ በሀረር ከተማ በተጻፈው “የወላስማ ሱልጣኖች ዜና መዋዕል” የተሰኘ የታሪክ ሰነድ ውስጥ “የኢፋት ሱልጣን የነበረው ቀዳማዊ ጀማሉዲን (1308-1322) በየዕለቱ ከአባወይን ወንዝ ውሀ የሚቀዳለት ፈጣን የሆነ የጂንኒ አገልጋይ ነበረው” የሚል ታሪክ ሰፍሯል፡፡

“ፉቱሕ አል- ሐበሻ” የሚባለውን የኢማም አሕመድ ኢብራሂም አል-ጛዚ ዜና መዋዕል የጻፈው ዐረብ ፈቂህ ደግሞ ወንዙን ሲገልጸው እንዲህ ብሎ ነበር፡፡

“ንጉሥ ወናግ ሰገድ (ዐፄ ልብነ ድንግል) ሊነጋጋ ሲል ከ“ዐባወይን” ወንዝ ራስጌ በኩል በአንድ ጠባብ መንገድ ወረደ። ወንዙ ከምስር ኒል (ናይል) ወንዝ ጋር የሚገናኝ ነው”
(ፉቱሕ አል-ሐበሽ፣ ቅጽ 2፣ ገጽ 215)

በነገራችን ላይ ኢማም አሕመድ ኢብራሂም ዐፄ ልብነ ድንግልን በሚያሳድድባቸው ቀዳሚ ዓመታት ሊገባበት ያልቻለው ክፍለ ሀገር ጎጃም ብቻ ነው፡፡ ምክንያቱ ደግሞ የዐባይ ወንዝ ጎጃምን እንደ ጥለት ሸፍኖት ከውጪ ከሚመጣበት ጥቃት ስለጋረደው ነው፡፡ ኢማሙ በዘመቻው ሂደት የአካባቢውን ጂኦግራፊ በትክክል ሲረዳ ግን ከጣና ሐይቅ በስተምዕራብ (በጎንደር ክፍለ ሀገር በሚገኙት ቋራ፣ ወገራና ጭልጋ በሚባሉት አውራጃዎች በኩል) ዞሮ ወደ ጎጃም ለመግባት ችሏል፡፡
——
የዐባይ ወንዝ “ግሽ ዐባይ” ከተባለው ቦታ ተነስቶ ወደ ጣና ሐይቅ ከገባ በኋላ ነው ትልቁ ወንዝ የሚፈጠረው፡፡ ይህ ጣና የሚባለው ሐይቅ ራሱን የቻለ ሌላ ዓለም ነው፡፡ ሐይቁ በልቤ ተጽፎ እንዲኖር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረገው ደግሞ በልጅነት ዘመኔ የገጠመኝ አንድ አደገኛ ዋናተኛ ነው፡፡

ኃይለ ማሪያም ይባላል፡፡ የባሕር ዳር ልጅ ነው፡፡ በዕድሜ በአንድ ወይም በሁለት ዓመት የምበልጠው ይመስለኛል፡፡ አባቱ በ1983 መግቢያ ላይ የሀብሮ አውራጃ አስተዳደር የአንዱ ዘርፍ ኃላፊ ሆነው ነበር ወደ ከተማችን የመጡት፡፡ በዚያ ዘመን ከነበሩን አስደሳች መዝናኛዎች መካከል ዋነኛው የውሃ ዋና ነው፡፡ በተለይም ቅዳሜ እና እሁድ ከገለምሶ ከተማ ግርጌ ያለውን የአው-ሰኢድ ወንዝ በቡድን ሆነን እንዋኝ ነበር፡፡ ታዲያ የሀረርጌ ልጆች ዋና በሌላው ሀገር ከሚታወቀው ዋና የተለየ ነው፡፡ ለምሳሌ እኛ ስንዋኝ ሁለቱንም እግሮቻችንን ከወንዙ እናወጣና ውሀውን “ዱፍ.. ዱፍ…ዱፍ…ዱፍ” በማድረግ እየደፈቅን እንሄዳለን፡፡ በዚህ ሳቢያም የውሃ ላይ ጉዞአችን የተንቀረፈፈ ነበር፡፡ በውሀው ውስጥ ለአምስት ደቂቃ ከቆየን በጣም እንደክማለን፡፡

ኃይለ ማሪያም ግን ከዚያ በፊት አይተነው የማናውቀውን የዋና ዓይነት አመጣብን፡፡ እግሮቹን ከወንዙ ሳያወጣ በእጆቹ ብቻ ውሀውን እየሳበው ሲጓዝ “አጃኢብ” አሰኘን፡፡ አግራሞታችን ከመብዛቱ የተነሳም ያለንበትን ቦታ ረሳነው፡፡ ልጁ ወንዙን አዳርሶ ሲወጣ በከፍተኛ በጭብጨባ ተቀበልነው፡፡ ሁላችንም ሮጠን ከበብነውና እንዲያ ዓይነቱን የዋና ዘዴ ከየት እንደተማረው እንዲነግረን አዋከብነው፡፡

“ጣና ላይ ነው የተማርኩት”
“ጣና ትልቁ ሐይቅ ወይስ ስለሌላ ጣና ነው የምታወራው?”
“ጣና ሐይቅ እያልኳችሁ ነው”
“እሱ እኮ ጎጃም ነው ያለው”
“አዎና! እኔም የባሕር ዳር ልጅ ነኝ”

ሳንወድ በግድ አመንነው፡፡ እናም ዋናውን እንዲደግምልን ለመንነው፡፡ ኃይለ ማሪያምም ወደ ወንዙ ገብቶ በዚያ ፍጥነቱ እየዋኘ በአጭር ጊዜ አዳረሰው፡፡ ይግረማችሁ ብሎም በመጣበት ኃይሉ ወደ ኋላው ተቀለበሰና ወንዙን እንደ ክሩዘር ጀልባ እየሰነጠቀው ተንፈላሰሰበት፡፡ በዚህን ጊዜ ታዲያ አድናቆታችን መልኩን ቀይሮ የቅናት መንፈስ ነፈሰብን፡፡ “እኔም ባሕር ዳር ብወለድ ኖሮ በጣና ሐይቅ ላይ እንዲህ እቀዝፍ ነበር አይደል?. ምነው ጣና ዳር ብወለድ ኖሮ!” እያልን በልባችን ታመምን፡፡

ከዚያን ዘመን ጀምሮ ጣናን ማየት ከህልሞቼ አንዱ ሆኖ ሰነበተ፡፡ ይሄው ሐይቁን ሳላየው ዕድሜዬ አለቀ፡፡ ደግሞም ዘመን ከፋና ጣና ራሱ በአረም ተጥለቀለቀ፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ በተከሰተው ነገር እያዘነ በሐዘን ደቀቀ፡፡ በተቃራኒው ደግሞ የሐይቁ ውልድ በሆነው የዐባይ ወንዝ ላይ የህዳሴው ግድብ እንደሚሰራ ከታወጀበት ዕለት አንስቶ ደስታ እና ፕሮፓጋንዳ ሀገር አደበላለቀ፡፡ የወሎው ሼኽ ሑሴን ጂብሪል የሚከተለውን ትንቢታዊ ግጥም የተቀኙት እንዲህ ዓይነት ዘመን እንደሚመጣ ስለታያቸው ይሆን?…

ዐባይ ደፈረሰ ጣናንም ያሙታል
እንዳትከተሉት ሙት ይዞ ይሞታል፡፡

(ይቀጥላል)
—-
አፈንዲ ሙተቂ
ሀምሌ 24/2009
አዳማ ከተማ ተጻፈ፡፡

Filed in: Amharic