>
5:13 pm - Sunday April 19, 4144

በኬንያው የ2017 ምርጫ የየትኛው ሐገር ስደተኞች ይበልጥ ለአደጋ ተጋላጭ ናቸው? (ዮናስ ሃጎስ)

 

በኬንያው የ2017 ምርጫ ላይ ሁለት ከተነሳ ከስደተኞች ውስጥ የየትኛው ሐገር ስደተኞች ይበልጥ ለአደጋ ተጋላጭ ናቸው?

keniya flagየኬንያ ምርጫ ከዛሬ 01/08/2017 ወዲህ ስምንት ቀናቶች ብቻ ይቀሩታል። ይህ ምርጫ እንደባለፈው ምርጫ ሰላማዊ በሆነ መንገድ ተከናውኖ እንደማያልፍ የሚያመላክቱ ነገሮች መፈጠር የጀመሩት ሰሞኑን ሳይሆን ከወራቶች በፊት ነው። በምዕራብ ኬንያ በድርቅ የተጎዱ ዜጎች እያሉ እንዲሁም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተከሰተው ውኃ ወለድ ኮሌራ በሽታ የተጎጂዎቹ ቁጥር እያሻቀበ በመጣበት ሁኔታ (አዎ የኬንያ መንግስት እንደ ዶፍተራችን ኮሌራን አተት ነው እያለ ላወዛግብ አይልም። ቢልም ነፃዎቹ ሚድያዎች መንገድ አይከፍቱለትም) የኡሁሩ ኬንያታ መንግስት ከፍተኛ በጀት በመመደብ አድማ በታኝ ቁሳቁሶችን ከውጭ ሐገራት ያስመጣው ያለምክንያት አይደለም። ከዚያም ባሻገር ባለፈው ፅሁፌ እንደገለፅኩት የሐገር ውስጥ ጉዳይ ሚንስትሩ ድንገተኛ ሕልፈት የዚሁ አይቀሬ ሁከት መንስዔ መሆኑን ብዙዎች ይስማሙበታል። ለተቃዋሚዎች ለስለስ ያለ ልቦና ያላቸው ንኪሳሪ ሞተው ሰዓታት ሳይቆጠሩ የገዢው ፓርቲ ቀንደኛ ወገን የሆኑት ማቲያንጊ ከትምህርት ሚንስትርነት ወደ ንኪሳሪ ቦታ መመደባቸው ብዙዎቹን መንግስት ምርጫውን ተከትሎ የሚነሱ ሁከቶችን በሐይል ለማስተናገድ መወሰኑን እንዲያረጋግጡ መንገድ ከፍቷል። ይህ ድራማ ሰሞኑንም እንደቀጠለ ነው።
°
ከትላንት በስቲያ የምክትል ፕሬዚዳንቱ ዊልያምስ ሩቶ መኖርያ ቤት ላይ የደረሰው ጥቃት የዚህ ድራማ ቀጣይ ክፍል ሆኖ ሲመዘገብ የምርጫ ቦርዱ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሐላፊ የሆነው ዊልያምስ ሙሳንዶ አሁን ከመሸ ሞቶ መገኘቱ ድራማው ትራዤዲ ቦታ ላይ መድረሱን አመላክቷል። ዊልያምስ ሩቶ ቤት ላይ «ተቃጥቷል» የተባለው ሙከራ የተቃዋሚ ኃይሎች እኛን ለመወንጀል በራሱ በምክትል ፕሬዚዳንቱ የተቀነባበረ ድራማ ሲሉ ያወገዙት ሲሆን የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂው ኃላፊ ሞቶ መገኘት በባለፈው ምርጫ ላይ ተደርጓል የተባለውን ማጭበርበር ዲጂታል በሆነ መንገድ በዚህኛውም ምርጫ እንዳይደገም ለማድረግ የነበረውን ተስፋ እንዳጨለመ ተቃዋሚዎች እየተናገሩ ይገኛሉ። ዊልያም ማሱንዶ የምርጫ ቦርዱን ሰርቨሮች እንደ መዳፋቸው ከሚያውቁት በጣት የሚቆጠሩ የምርጫ ቦርዱ ባለሙያዎች አንደኛው ሲሆን የመግደል ሙከራ ዛቻ እየደረሰው እንደሆነ በተደጋጋሚ ለኬንያ ፖሊስ ማመልከቱን መረጃዎች ያሳያሉ። ቅዳሜ ጠዋት ጀምሮ የደረሰበት ያልታወቀው ይኸው ግለሰብ ዛሬ አመሻሽ ላይ ሬሳው ተገኝቶ ለምርመራ ወደ ሆስፒታል ተወስዷል።
•°•
የተቃዋሚው መሪ ራይላ ኦዲንጋ በተለያዩ ጊዜያቶች በሰጧቸው መግለጫዎች ገዢው ፓርቲ ይህን ምርጫ ለማጭበርበር በመወሰኑ ከዚያ በኋላ ይነሳብኛል ብሎ ያሰበውን የሕዝብ ዓመፅ በሐይል ለማዳፈን ከፍተኛ እንቅስቃሴ እያደረገ ነው። በአሁኑ ጊዜ ወታደሮች፣ ፖሊሶችና የደህንነት ሐይሎች ከፍተኛ ስልጠና እየወሰዱ መሆኑንና ለተቃዋሚው ስስ ልብ አላቸው ተብለው የታመኑ ወታደራዊ አዛዦች ከቦታ ቦታ በዝውውር እንዲቀያየሩ እየተደረጉ ነው። በናይሮቢ ውስጥ በአሁኑ ሰዓት የንግድ እንቅስቃሴዎች ሁሉ እጅግ የተዳከሙ ሲሆን የተወሰኑ ቦታዎች ላይ ሰዎች ምርጫውን ለማሳለፍ ሲሉ ከመኖርያቸው ወደ ትውልድ ቦታቸው እየተንቀሳቀሱ ነው። ከፍተኛ የንግድ እንቅስቃሴዎች «ከምርጫው በኋላ) በሚል ባሉበት የቆሙ ሲሆን ሸማቹ ደግሞ ምናልባት ሁከት ከተነሳ ከቤት ያለመውጣት ነገር ሊፈጠር ይችላል በሚል ስጋት የእህል አስቤዛውን አጠናክሮ ተያይዞታል።
•°•
በኬንያ ብዙ ጊዜ ሁከት ሲፈጠር የመጀመሪያ ተጠቂ የሚሆኑት ስደተኞች ናቸው። ሆኖም ሁሉም ስደተኞች በእኩል ሁኔታ ጥቃት ይደርስባቸዋል ማለት አይደለም። ምክንያቱም ሁሉም ስደተኞች በእኩል ሁኔታ ላይ ያሉ አይደሉምና። በኬንያ ውስጥ የኢትዮጵያን፣ ሱዳን፣ ሶማሊያ፣ ኮንጎ፣ ሩዋንዳ፣ ኡጋንዳንና ሌሎችንም ዜጎች የያዙ የስደተኛ ማዕከላት አሉ። የብዙዎቹን ሐገራት ስደተኞች ሁኔታ ካየን ጠንካራ የሆነ ኮሚኒቲ አላቸው። ለምሳሌ የሱዳን ስደተኞች እጅግ በጣም የተጠናከረ ኮሚኒቲ ስላላቸውና ሰብሰብ ብለው ስለሚኖሩ በዚህ ሁከት የመጠቃት እድላቸው አናሳ ነው። የኮንጎ፣ ሩዋንዳና ኡጋንዳ ዜጎችም እንደ ሱዳኖቹ ሰብሰብ ብለው አይኑሩ እንጂ ኮሚኒቲያቸው እጅግ በጣም የተጠናከረና ብዙ ጊዜ ስደተኞቻቸው ላይ ለሚደርስ ጉዳት ፈጣን ምላሽ በመስጠት የሚታወቁ ናቸው። የሶማሊያን ስደተኞች ካስተዋልን ንግዱን በአብዛኛው ለመቆጣጠር የቻሉ ከመሆናቸው ጋር በኬንያ ውስጥ በሚልዮን የሚቆጠሩ የነርሱ ብሔር ተወላጆች መኖራቸውና እነርሱንም እንደሚደግፏቸው ሲታይ የነርሱም ጉዳት ያን ያህል ይሆናል ለማለት ይከብዳል።

እንግዲህ ማን ቀረ… አዎ መከረኞቹ የሚል ድርሰት የታተመልን እኛው ኢትዮጵያኖቹ ቀርተናል።
•°•
ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በናይሮቢና አጎራባች ከተሞች ተበታትነው የሚገኙ ሲሆን የራሳቸው የስደተኛው የሆነ ኮሚኒቲ የላቸውም። በ2015 ላይ አባል ሆኜበት አያያዙ አላምር ሲለኝ ዞር ያልኩበት በናይሮቢ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ ከኤምባሲ ሰራተኞች፣ ለተለያየ ጉዳይና ስራ ወደ ናይሮቢ መጥተው የሚኖሩ ስደተኛ ያልሆኑ ኢትዮጵያኖችንም ጭምር በአባልነት የሚመዘግብ ሲሆን ዓላማው ኢትዮጵያውያኑን ማቀራረብና ባሕል ልውውጥ ማድረግ ነው። ላለፉት 2 ዓመታት አንዳችም ነገር ያልሰራው ይህ ኮሚኒቲ ለስደተኞች መብታቸው እስከምን እንደሆነ፣ እንደዚህ ዓይነት ሁከት ሲነሳ እንዴት ራሳቸውን መጠበቅ እንደሚገባቸው የሚያስጨብጥ ግንዛቤ ለመስጠት ብቃቱ አለው ማለት በፍፁም አይቻልም። በዚህ ሁለት ዓመት ውስጥ እንኳ በመቶዎች የሚቆጠሩ በሕገ ወጥ አመላላሾች ከቦታ ቦታ ሲዘዋወሩ የነበሩ ሰዎችን ፖሊስ አግኝቶ ሲያስር ሌላው የሕግ ድጋፍ ቀርቶ በፍርድ ቤት የሚያስተረጉምላቸው አስተርጓሚ እንኳ ማቅረብ አልቻለም። ኢትዮጵያኖች በየቦታው ተበታትነው ከመኖራቸው፣ ጠንካራ የሚያስተሳስር ኮሚኒቲ ባለመፍጠራቸውና በፌስቡክ እንደሚታየው ዓይነት ብሔረሰባዊ ተኮር የኑሮ ዘይቤ ውስጥ መግባታቸው የቀጣዩ ምርጫ ዓይነት ሁከት ሲፈጠር ለአደጋ ተጋላጭነታቸው ከየትኛውም ሐገር ስደተኛ የከፋ አድርጎታል።

Filed in: Amharic