>

መስከረም ሳይጠባ እያንዣበበ ያለው አደጋ! (ኤርሚያስ ለገሰ ዋቅጅራ)

 በኦሮሚፋ የሚያስተምሩ ትምህርት ቤቶች ወይስ በሁሉም የመዲናይቱ ትምህርት ቤቶች ኦሮምኛ ማስተማር? ምን እየተደገሰ ነው?

” በአፋን ኦሮሞ አማካኝቶ ማስተር ፕላኑን በጓሮ በር!” በሚል ርዕስ ከዛሬ አንድ ወር በፊት አጭር መጣጥፍ አቅርቤ ነበር። ይሔንን መጣጥፍ በድጋሚ እንዳስታውስ ያደረገኝ ዛሬ የአዲስ አበባ ኢህአዴግ ፅህፈት ቤት ያቀረበውን ዜና ስመለከት የፈጠረብኝ አግራሞት ነው። የድርጅቱ ፅህፈት ቤት በድረገፁ ላይ ” በኦሮሚፋ የሚያስተምሩ ትምህርት ቤቶች በአዲሱ አመት ይከፈታሉ ” በሚል አርስተ ዜና በፎቶግራፍ የተደገፈ ዜና አቅርቧል። ትምህርት ቤቶቹ መጠናቀቃቸውን ፣ በመጪው አመት ስራ እንደሚጀምሩ ፣ የትምህርት ቤቶቹ ብዛትና የፈጁት ገንዘብ፣ ለትምህርቱ የሚያስፈልገው ቅድመ ዝግጅት መጠናቀቁ መግለጫ የሚሰጠው የኦሮሚያ ትምህርት ቢሮ ነው። ያስገረመኝ ይሄኛው ክፍል ነው።

የኦሮሚያ የትምህርት ቢሮው መግለጫ በዚህ አላበቃም። ይልቁንስ ለትምህርት ቤቶቹ ርዕሰ መምህራን ፣ የአስተዳደር ሠራተኞች ፣ የጥበቃ እና ፅዳት ሰራተኞች ተሟልተውላቸው ተማሪዎችን ለመመዝገብ መዘጋጀታቸውን ይፋ አድርገዋል። ከዚህ በተጨማሪም በቀጣይ ጊዜያቶች በተቀሩት ስድስት ክፍለ ከተሞች በኦሮሚያ ትምህርት ቢሮ እና በግል ባለሐብቶች ተሳትፎ በኦሮሚፋ የሚያስተምሩ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እንደሚገነቡ ተገልጿል። የትምህርት ቤቶቹ መገንባት በአዲስአበባ ከተማ እና በዙሪያዋ ያሉ የኦሮምኛ ቋንቋ ተናጋሪ ታዳጊዎች የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው እንዲከታተሉ እንደሚያደርግ በዘገባው ተመላክቷል።

እንደ እውነቱ ከሆነ ይሄ ዜና አግራሞትን ከመጫሩም በላይ በአገዛዙ ማእቀፍ ስር ሕጋዊ ጥያቄ የሚያስነሳ ነው። ከህጋዊነቱ ባልተናነሰ የአዲሳአባ የሚቀጥለው ጉዞ ካለፈው የሚከብድና የሚያስጨንቅ መሆኑን መገመት ይቻላል። አዲሳአባ ትከሻዋ ከሚችለው በላይ የችግር ጉድ ልትሸከም መዘጋጀቷን የሚያመላክት ነው። ዛሬ መዲናይቱ ላይ የነገሱትና በብቸኝነት የሚገዙት የትግራይ ነፃ አውጪዎች እና ተላላኪዎቻቸው ነዋሪውን እርስ በራስ ለማጨራረስ መዘጋጀታቸውን የሚጠቁም ነው። በመከባበርና በመፈቃቀር በአንድነት ተሰባስቦ ይኖር የነበረውን የአዲሳአባ ህዝብ በዘር ከፋፍሎ ለማጋደል በማሰብ የተጠነሰሰ ሴራ ነው። እርግጥም ሁኔታዎች እነሱ በፈለጉት መንገድ አልጋ በአልጋ ሆኖ ከቀጠለ የቀረበው ስጋት አየር ላይ የተንጠለጠለ ተራ ክስ ሳይሆን በቅርብ አመታት ውስጥ የሚከሰት ይሆናል።
በመጀመሪያ በእነሱ ማእቀፍ ውስጥ ሆነን ጥያቄዎች እናንሳ። የኦሮሚያ ትምህርት ቢሮ ምን አግብቶት በአዲሳአባ ላይ ስለተገነባ ትምህርት ቤት መግለጫ ይሰጣል። ምን አባቱ አግብቶት በአዲሳአባ ስለሚቀጠሩ ርዕሰ መምህራን፣ መምህራንና የትምህርት ቤት አስተዳደሮች ይናገራል። ምን አባቱ አግብቶት ስለ አስተዳደር ሰራተኞች ፣ የጥበቃና ፅዳት ሰራተኞች ቅጥር መግለጫ ይሰጣል። ወይንስ በመዲናይቱ ውስጥ የኦሮሚያ ክልል ባጠቃላይ የኦሮሚያ ትምህርት ቢሮ በልዩ ሁኔታ ስልጣን አለው?… ለመሆኑ ይሄ ሥልጣን ምኑ ላይ ነው የተገለፀው? በሕገመንግሥቱ ላይ ነው?… በቻርተሩ ላይ ነው? …በኦሮሚያ ህገ መንግስት ላይ ነው?…በሕውኃት ማኒፌስቶ ላይ ነው?…በአባይ ፀሐዬ መዳፍ ላይ ነው?
ከሕጋዊ ጥያቄዎቹ ሳልወጣ የኦሮሚያ ትምህርት ቢሮ ” የትምህርት ቤቶቹ መገንባት በአዲሳአባና በዙሪያዋ ያሉ የኦሮምኛ ቋንቋ ተናጋሪ ታዳጊዎች የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው እንዲከታተሉ” በማሰብ እንደሆነ ይገልፃል። ይሄ ማለት የትምህርት ቤቶቹ ተጠያቂነት ለአዲስ አበባ መስተዳድር እና ለኦሮሚያ ክልል ይሆናል ማለት ነው። የጋራ ተጠያቂነት። ይሄ ማለት ተማሪዎቹ በከተማው መስተዳድር እና በኦሮሚያ ልዩ ዞኖች የሚሰነድ ዶክመንት ይኖራቸዋል። መምህሩም፣ አስተዳደር ሰራተኛውም፣ ተላላኪውም ጥንድ ተጠያቂነት እንዲኖራቸው ያደርጋል። አንዱ የቀጠረውን ሌላው ሊያባርር ይችላል። አንዱ የሾመውን ሌላው ሊሽር ይችላል። ወይስ አይችልም? ወይስ ይችላል?
አሁንም ከሕጋዊ ጥያቄዎች ሳልወጣ ትምህርት ቤቶቹ ውስጥ ከፍተኛ ረብሻ፣ አመፅና ከባባድ ወንጀሎች ቢፈፀሙ የሚዳኙት የት ይሆናል። አይበለውና የአዲሳአባ ታዳጊዎች ከኦሮሚያ ልዩ ዞን ታዳጊዎች ጋር በኳስ ጨዋታ ውጤት ተጣልተው ተፈነካከቱ እንበል። ይሄ አይከሰትም አይባልም። በእኛ ዘመን የገመቹ ሰፈርና የቀራንዮ ልጆች ሲጫወቱ አምቧጋሮ ይነሳ ነበር። በታላቆቻችን ዘመን ደግሞ የቀርሳ ሰፈር ልጆች ከቀርሳ ሰፈር ልጆች ጋር የሚኖራቸው የኳስ ግጥሚያ የጦርነት ያህል ይፈራ ነበር። የአገር ሽማግሌዎች ለማስታረቅ ደቦ የተቀመጡበትን ጊዜም አስታውሳለሁ። የዞኑ አስተዳደር በነበርኩ ሰአት ደግሞ ከወረዳው ፓሊስ አዛዥ ኮማንደር ተስፋ ፈርሻ ጋር የማነብርሃን ትምህርት ቤት ለሁለት ተከታታይ ሳምንታት አፈርሳታ ተቀምጠናል። እናም በአዲሶቹ የጥምር ተጠያቂነት ባለባቸው ትምህርት ቤቶች ይሄ ችግር ሊፈጠር የሚችልበት እድል አለ።
ከዚህ ጋር ተያይዞ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በአካባቢ መገንባት በሚለው ፓሊሲ መሰረት በአዲሳአባ ዙሪያ ያሉ የኦሮሚያ ልዩ ዞኖች በራሳቸው ቀበሌ ለምን ተገንብቶላቸው እዛው አይማሩም የሚል ጥያቄም ምላሽ የሚፈልግ ነው። እንደሰማሁት ከሆነ የተገነቡት ትምህርት ቤቶች ከኦሮሚያ ልዩ ዞን ርቀት አላቸው። አንዳንዶቹም ወንዝ ያቋርጣሉ። ይሄ ከሆነ ዘንዳ ታዳጊዎቹ በአዳሪ ትምህርት ቤትነት አሊያም ቀለብ ተሰፍሮላቸውና የኦህዴድ ልጆች ሆነው የሚማሩ ናቸው። ልክ እንደ ቃላሚኖ?
በመጨረሻም ይሄ አካሄድ በመዲናይቱ የአፓርታይድ አይነት ስርአት በአጭር ጊዜ ውስጥ ሊዘረጋ እንደሚችል ሳልጠቁም አላልፍም። በሁለት ጐረቤቶች መካከል የኦህዴድ አባል የሆነው ድርጅታዊ ግዴታ ተጥሎበት ወደ ኦሮሚፋ ትምህርት ቤት ይሰዳል። የብአዴን አባሉና የተቀሩት አዲስአበቤዎች ወደ ሌሎች መደበኛ ትምህርት ቤቶች ይልካሉ። እያደር ታዳጊዎቹ በአስኳላ በሚማሩት የታሪክ ትምህርት እና በእለታዊ ውሎአቸው የተለያዩ ይሆናሉ። በጠላትነት ማፈላለግ ይጀምራሉ ። የተፈለገው ይሄ ባይሆን ኖሮ የአዲስ አበባን ህዝብ አሳምኖ በሁሉም የመዲናይቱ ትምህርት ቤቶች እንደ አንድ ትምህርት እስከ ሁለተኛ ደረጃ መስጠት በተቻለ ነበር።

Filed in: Amharic