>
5:13 pm - Tuesday April 19, 5510

የሕሊና ዳኝነት እና ቀጣዩ ፈተና (ኤርሚያስ ለገሰ)

Ermias Legesse

ክፍል አንድ

“ችግሩ ካልተፈታ የአማራ ህዝብ እና የኢትዮጵያ ህዝብ እንዲያውቅልን እናደርጋለን!” ይሄን የተናገረው የብአዴን ካባ ለብሶ አማራ ክልል ተብሎ የተፈጠረውን አስተዳደር ለረጅም ጊዜ የመራው አቶ አዲሱ ለገሰ አይደለም። ” ኦቦ አዲሱ!” ምን ጐድሎበት ይሄን ይላል። ” ላለፋት አስር አመታት አንድም አዲስ ማከፋፈያ አልተገነባ።” ይሄንንም ያለው የኢህአዴጉ ጐብልስ በረከት ስምኦን አይደለም። እሱስ ቢሆን ምን ጐድሎበት ። ” ያሉት 25 ሐይል ማከፋፈያ (substations) አብዛኛው በደርግ ጊዜ የተሰሩ ናቸው፣ አርጅተዋል፣ ቮልታቸው አነስተኛ ነው፣ እነዚህን ይዞ ፋብሪካ መገንባት አይቻልም፣ የተገነቡትም መስራት አልቻሉም፣ በክልሉ ባለሃብቶችን መጥታችሁ አልሙ የማለት ሞራል የለንም።” ይሄንንም የመሰከሩት ህውሓቶች እና የፌስ ቡክ ስኳዶቻቸው የቁርጥ ቀን ልጆቻችን የሚሏቸው ታጋይ ታደሰ ጥንቅሹ፣ ካሳ ሸሪፎ፣ ህላዌ ዬሴፍ አይደሉም። እድሜ ለአድርባይነት እነዚህ የብአዴን ሰዎች ሁሉ በእጅና ደጅ ሆኖላቸው እንዴት ይሄን የሚል የሞራል ልዕልና ያገኛሉ? … ኧረ በጭራሽ!…

ታዲያ ማነው ይሄን ያለው? ተስፋዬ ጌታቸው ይባላል። የአማራ ክልል የካቢኔ ፣ የብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ፣ የንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ ሐላፊ ነው። ሌላኛው ደግሞ የክልሉ ፕሬዝዳንት ልዩ አማካሪ “ማንትሴ” ጥሩነህ ይባላል። ከይቅርታ ጋር ” ማንትሴ” ያልኩት ስሙን ማንበብ ስላልቻልኩ ነው። ከላይ የተገለጠውን እውነታ ለኢትዮጵያ ህዝብ ያፍረጠረጡ ብአዴኖች ናቸው።

እነዚህ ብአዴኖች በሕውኃት እቅፍ ውስጥ ሆነው ይሄን መሬት የረገጠ እውነት ለመናገር መድፈራቸው ሊበረታታ ይገባል። እንደ እውነቱ ከሆነ ጋዜጠኛውን ጨምሮ አንዳች ሂሳብ ሳይሰሩ ግልጥልጥ አድርጐ ማሳየታቸው በአርአያነት ሊታይ የሚችል ነው።ከሩቅ ሆኖ ሊከፍሉ የተዘጋጁትን ዋጋ ከወዲሁ መገመት ይቻላል።

እርግጥ የህዝቡ እምቢተኝነትና የተዳፈነ ቁጭት ተናጋሪዎቹን ወደዚህ ውሳኔ እንዳመራቸው ከጥያቄ የሚገባ አይደለም። የተዳፈነ ህዝባዊ ቁጣ በበረታ ቁጥር ህውሓት `ብአዴን` በሚባል የልጥ ገመድ ያሰራቸው አማሮች ገመዱን መበጣጠሳቸው የማይቀር ሐቅ ነው።

እነዚህ ሁለት የብአዴን ካድሬዎች ያቀረቡት ማስረጃና ምሬት በጥሞና ለተከታተለው ብዙ ምላሾችን ይሰጣል። እንድምታዎቹም ብዙ ናቸው። የበላይ ባለስልጣናት እንደመሆናቸው መጠን የፌዴራሉ መሥሪያቤቶች መረጃ ይደርሳቸዋል። ለምሳሌ የመብራት ሐይል ባለሥልጣን ባለፋት አራት አመት ብቻ 92 ማከፋፈያ በኢትየጵያ ደረጃ ሰርቷል። እ•ኤ•አ• በ2015 ብቻ የተሰሩት ሃይል ማከፋፈያዎች 45 ያህል ይሆናሉ። ይሁን እንጂ የአማራ ንግድ ቢሮ ሐላፊው እንደገለፀው ላለፋት አስር አመታት በአማራ ክልል አንድም ማከፋፈያ አልተገነባም።ምን ማለት ነው?… የገዱ አንዳርጋቸው ልዩ አማካሪ እንደገለጠው ከሆነ ደግሞ የተሰሩት ማከፋፈያዎች በደርግ ጊዜ ተገንብተው ያረጁና ከጥቅም ውጭ የወጡ ናቸው። ጉድና ጅራት ከኋላ ነው እንዲሉ ይሄን እውነት በመጨረሻው ዘመናት መስማት በጣም ያሳፍራል።

ሁለቱ የብአዴን ከፍተኛ ባለስልጣናት የሚያውቁት ሌላም እውነት አለ። ህውሃት እድሜውን ለማራዘም እና የገባበትን የውጭ ምንዛሪ ማነቆ ለማስተንፈስ የአገሬውን ህዝብ በኤሌክትሪክ እጦት እያሰቃየ ለጅቡቲ፣ ሱዳን እና ግብፅ ከ3,300 ሜጋ ዋት በላይ ለመሸጥ ዉል ተፈራርሟል። ግብፅ ብቻ ከ2ሺህ በላይ ሜጋ ዋት ለመውሰድ አሰፍስፋ እየጠበቀች ነው። በሌላ በኩል አቶ አርከበ እቁባይን የፈረንጅ ላም ሆነው እያገለገሉ ያሉትና የኢንዱስትሪ ፓርክ የሚል ስያሜ የተሰጣቸው ቁምሳጥኖች የኤሌክትሪክ ያለህ እያሉ ነው። ለአብነት ያህል የባህርዳሩ፣ የኮምቦልቻው እና የጐንደሩ ቁምሳጥኖች ከ934 ሜጋዋት በላይ እንደሚያስፈልጋቸው ለክልሉ መስተዳድርና ለኤሌክትሪክ ባለሥልጣን መስሪያቤት አቅርበዋል። እናም እነዚህ የክልል ባለስልጣናት ቢጨንቃቸው ለዘመናት ተሸክመው የኖሩትን እውነት አፍረጠረጡት። አይደለም የኢንዱስትሪ አብዬት የዩንቨርስቲ ተማሪዎችን ዳቦ ጋግሮ ለማብላት የሚያስችል ኮረንቲ እንደሌለ ይፋ አደረጉ። እንጅባራ እና ወልዲያ ዩንቨርስቲ ልጆቻቸውን የሚልኩ ቤተሰቦች ልጆቻቻቸው በጠኔ ሊጐዱ እንደሚችሉ በእጅ አዙር አሳወቁ። መቼስ ለወላጆች ይሄን መርዶ ከመስማት በላይ ጭንቀት የለም። ለብአዴኖቹ ባለስልጣናትም ቢሆን ይሄን መራር ሐቅ የኢትዩጵያ ህዝብ እንዲያውቅላቸው ከማድረግ ውጭ ጊዜያዊ አማራጭ የለም።

                         ~ክፍል ሁለት~
               “የትናንትናን በደል ለዛሬ በቀል”

ህውሃቶች ትናንት በትግራይ ላይ የተለየ በደል ተፈፅሟልና የዛሬው የኢኮኖሚ ኢፍትሐዊነት ትክክለኛው የአፀፋ ምላሽ ነው ብለው ያምናሉ። በሌላ በኩል የትግራይ ሕዝብና ትግራይን ትናንት የበደለ በማለት የሚወቅሱትን ዛሬ መበቀል እንደሚገባ የፀና እምነት አላቸው። ለዚህም ነው በአፈ ቀላጤያቸው ሐይለማሪያም ደሳለኝ አማካኝነት የትግራይን ብድራት ለመቶ አመት ከፍለን አንጨርሰውም በሚል አሳፋሪና አስቀያሚ በሆነ ይዘት እንዲገለጥ የተደረገው።

የሐይለማርያም የልብ ድንዛዜ፣ ከይሉኝታ መሰናበትና የኃፍረትን የመጨረሻ ድንበር መጣስ ወደ ጐን ትተን ለትግራይ የተደረገውን ብንመለከት ንግግሩ ወደ ተግባር መቀየሩን እንመለከታለን።ለዚህ አባባል አንድ ምሳሌ ብቻ ላንሳ ። ወጋችን ከኤሌክትሪክ ሐይል ጋር የተያያዘ በመሆኑ ምሳሌውም ከዛው ጋር ይዛመዳል። ወቅቱ ” በጦርነት ለተጐዱ ክልሎች ልዩ ጥቅም መስጠት” የሚል ግልፅ ፓሊሲ ተቀርጾ ወደ ስራ የተገባበት ነበር። ሁሉም የመንግስታዊም ሆነ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የሚቀርጿቸው ፕሮጀክቶች ማእከላዊ መገምገሚያ ምን ያህል በጦርነት የተጐዱ አካባቢዎችን በእቅዳቸው አማክለዋል የሚል ነበር። ከእነዚህ መንግስታዊ ድርጅቶች ውስጥ የኢትዮጵያ መብራት ሐይል ባለሥልጣን አንዱ ነበር።

እናም መብራት ሐይል ከቀረፃቸው ፕሮጀክቶች ውስጥ ” የትግራይ ክልል የሐይል ፕሮጀክት” የሚል ይገኝበታል። ፕሮጀክቱ መስመሩ ከየት ተነስቶ ፣ በየት አቋርጦ ፣ የት እንደሚደርስ በኤክስፐርቶች እና የባለስልጣኑ መስሪያቤት ሐላፊዎች በቴክኒክና ኢኮኖሚ አዋጭነት መስፈርት ተጠንቶ ቀረበ። ሙያተኞቹ መስመሩ ከባህርዳር ተነስቶ በጐንደር አድርጐ መቀሌ ቢዘልቅ ከቴክኒክ እና ኢኮኖሚ አዋጭነት አንፃር ይጠቅማል የሚል አስተያየት አቀረቡ።

ፕሮጀክቱ የቀረበለት አቶ መለስና የሕውሓት ፓሊት ቢሮ ተበሳጩ። ከህውሃቶች በላይ ህውሃት መምሰል የሚፈልገው ጠቅላይ ሚኒስትር ታምራት ላይኔ የበለጠ ተበሳጨ። የመብራት ሃይል ስራ አስኪያጅ የነበሩትን ዶክተር ወልደጊዮርጊስ ወልደገብርኤል ጨምሮ ሌሎች የባለስልጣን መስሪያቤቱ ሃላፊዎችን ጠራርገው አባረሩ። ” የትግራይ ክልል የሃይል ፕሮጀክት” በመባል የሚታወቀውን የግንባታ ፕሮግራም ስሙን ” የሰሜን ኢትዮጵያ ፓወር ትራንስሚሽን ፕሮጀክት” በሚል እንዲቀየር ተደረገ። ስሙን “ትግራይ” ከሚለው ወደ ” ሰሜን ኢትየጵያ ” መቀየር ያስፈለገው የፓለቲካ ኪሳራ እንዳያመጣ በማሰብ ነበር። በዛን ሰሞን መቀሌ በእቃ ብዛት ሰጠመች የሚባልበት ነበር። ከየቦታው ጄኔሬተሮች፣ የሆስፒታል አልጋዎች ፣ የዳቦ መጋገሪያ ማሽኖች፣ የመንግስት እርሻ የተለያዩ ማሽኖች፣ የቢሮ እቃዎች ተነቅለው የተወሰዱበት እንደነበር ይገለፃል።

መስመሩ ከየት ተነስቶ ፣ በየት አቋርጦ፣ የት ይድረስ የሚለው ተቀየረ። የጐንደር መንገድ በወሎ ወልዲያ እና ቆቦ ተተካ። መነሻውን ባህርዳር አድርጐ ወልዲያ፣ ከዛም ቆቦ፣ ከዛም መቀሌ ላይ ባላ እንዲሰራ ተደረገ። የመቀሌው አንደኛው ባላ ወደ አዲግራት ሲያዘግም፣ ሌላኛው ደግሞ አድዋ፣ አክሱም ፣ ውቅሮ፣ እንዳስላሴ አድርጐ እስከ ሽራሮ እንዲዘልቅ ተደረገ። የኢትዮጵያ ዋልታና ማገር የተባለችው ጐንደር በሕውኃት አይን የኤሌክትሪክ ምሶሶ መሸከም የማትችል ሆነች።
“ከትግራይ ክልል” ወደ “ሰሜን ኢትየጵያ” የተቀየረው ፕሮጀክት ያስመዘገበውን ውጤት ብንመለከት የስያሜው ለውጥ ፓለቲካዊ እንደነበረ በቀላሉ ማረጋገጥ ይቻላል።ለምሳሌ ከኃይል ፕሮጀክቶቹ ተጠቃሚ ከሆኑ 21 ከተሞች ውስጥ 17 ያህሉ የትግራይ ከተሞች ሆኑ። (አዲሱን የፕሮጀክት ካርታ እና የከተሞች ዝርዝር ለማየት አሌፍ መጽሔት ቅ3 ቁጥር 2 1986 ማየት ይችላል)።

በዚህ ” የሰሜን ኢትዬጲያ ፓወር ትራንስሚሽን” በሚለው የአፍሪካ ልማት ባንክ ብድር በተሰራው ፕሮጀክት ባስገኘው የኤሌክትሪክ ሃይል በመቀሌ ዛሬ 8 ቢሊዬን ብር ካፒታል ያለው መሶቦ ሲምንቶን፣ ከ6 ቢሊዬን ብር በላይ ያለው መስፍን ኢንዱስትሪያል ተገነባ። አዲግራት መዳኒት ፋብሪካውን ፣ አድዋ አልመዳ ጨርቃጨርቅን ፣ ውቅሮ ሳባ ቆዳ ፋብሪካን… ወዘተ ያለምንም ጭንቀት መገንባት ቻሉ።
እንግዲህ የአማራ ክልል የንግድ ቢሮውም ሆነ የፕሬዝዳንቱ አማካሪ የመጣው ይምጣ በማለት በሕይወታቸው ፈርደው እውነታውን ያፍረጠረጡት ከላይ የተገለፀውን ታሪካዊ በደል ስለሚያውቁ ይመስላል ። ትግራይ ደርሰው በመጡ ቁጥርና ከጓደኞቻቸው ጋር ልብ ለልብ ሲነጋገሩ የህዝባቸውን መቆርቆዝ፣ የብዝበዛና የጭቆና ኢላማ መሆን ሲመለከቱ አይናቸው ደም ስለሚቀላ ይሆናል ።

ሊወለድ የተቃረበው ህዝባዊ አመፅ እነሱንም እንዳይበላቸው በማሰብም ጭምር ሊሆን ይችላል። ከየትኛውም ጊዜ በባሰ የአማራ ህዝብ ከሌሎች ኢትዮጵያዊ ወንድም እና እህቶቹ ጋር ሆ! ብሎ ሊነሳ እንደሚችል የተገነዘቡ ይመስላል።ለዚህም ይሆናል “እየደረሰብን ያለው ኢፍትሐዊነት የኢትዮጵያ ህዝብ እንዲያውቅልን እናደርጋለን” እስከማለት የደረሱት።

Filed in: Amharic