>

ጣናን በተመለከተ የሚከተሉት የሁለት ታላላቅ ሰዎች አስተያየቶች ሰሚ አካል ይሻሉ፡፡ (የዶ/ር ይሁኔ አየለ እና የ‹ጃኖ› መንግሥቱ ዘገዬ)

‹‹ጣናን ለማየት ሦስተኛ ዓይን ያስፈልጋል››
(ይሁኔ አየለ (PhD))
tana-haykጣና ችግር ተደቅኖበታል፡፡ እንደ ችግሩ አሳሳቢነት ጠንከር ያሉ እርምጃዎች መወሰድ ነበረባቸው፡፡
የችግሩ ጥልቀት ለምን አልታየንም?
በጣና ጉዳይ ላይ የእይታ ችግር ያለ ይመስለኛል፡፡ ችግሩን ሳጤነው ጣናን የሚያይ ሦስተኛውን ዓይን ያለመታደል ችግር ይመስለኛል፡፡ ችግሩን ለመፍተታት ሦስተኛው ዓይን ያላቸው ሰዎች ያስፈልጉናል፡፡
ጣናን የዕለት ጉርሱን የሚፈልግና የተፈጥሮ ተግዳሮቱን ለማስታገስ የሚባዝን ዓይን አያየውም፤ ጣናን ትርፍ ሀብት ለማጋበስ የሚዋትት ዓይን አያየውም፤ ጣናን ስልጣንን የሚያማትር ዓይን አያየውም፤ ጣናን በፍርሀት የተሸበበ ዓይን አያየውም፤ ጣናን የኃይማኖት መጽሐፍትን ሸምድዶ የሚያነበንብ ዓይን አያየውም፡፡ ባጠቃላይ በተራውና በተፈጥሮው ዓይን ጣና አይታይም፤ ጣና ረቂቅ ነው፡፡
ትውልድን አሻግሮ የሚያይ ዓይን ጣናን ማየት ይችላል፤ ተፈጥሮን ማየት የሚችል ዓይን ጣናን ማየት ይችላል፤ የመንፈሳዊነት መገለጥ(spiritual imagination) ባለቤት የሆነ ዓይን ጣናን ማየት ይችላል፤ ደፋርና እውነትን የሚያማትር ዓይን ጣናን ማየት ይችላል፡፡ በአጠቃላይ ጣናን ለማየት ሦስተኛው ዓይን ያስፈልግል፡፡
የጣና ችግር ላይ መውደቅ ተጠያቂነትን ይዞ የሚመጣ ይመስለኛል፡፡ በዚህ ጉዳይ ሁሉም ተጠያቂ ነው፡፡ የተጠያቂነቱ መጠን ግን ሚለያይ ይመስለኛል፡፡ አንደኛው ተጠያቂ ክልሉን የሚያስተዳድረው መንግስት፤ ሁለተኛ የፌደራሉ መንግስት፤ ሶስተኛ እኔና እኔን መሰሎች፤ አራተኛ የክልሉ ህዝብ እና የመጨረሻው የኢትጵያ ህዝብ፡፡
ለምንድን ነው የክልሉ ህዝብ በዘመቻ እየወጣ ችግሩን ለመቅረፍ እርብርቦሽ የማያደርገው?
ከአቅሙ በላይ ከሆነ ሌሎች ወገኖቹን እርዳታ ይጠይቅ፡፡ ተመራማሪዎች ቅብጥሴ የሚባለው ነገር ችግሩን በቶሎ ይቀርፋል የሚል እምነት የለኝም፤ በዚህ ወቅት ምርምር ታእምረኛ ጥይት ያመጣል የሚል ካለ የዋህ መሆን አለበት፡፡ የምርምር ውጤት በተፈጥሮው ዘገምተኛ ነው፡፡ ምርምሩ ውጤት አስኪያመጣ ድረስ ጣና ሙሉ በሙሉ ሊሸፈን ይችላል፡፡
ለእኔ የሚታየኝ በዘመቻ ወጥቶ በእጅና በመሳሪያ መታገል ነው፡፡ የሰው ትብብር እቦጭን ይቅርና የግብጽ ፒራሚዶችን እንዳነፀና የአክሱምን ሀውልት ቀርጾ አጓጉዞ ማቆም እንደቻለ አይተናል፡፡ ሰው ከተባበረ የሚሳነው የለም፡፡ ለምን መተባበር አቃተን?
——//—–
የክተት ዘመቻ ይታወጅልን! !!!!
(መንግሥቱ ዘገዬ – Mengistu Zegeye)
ወቅቱ ክረምት ነው ። ተማሪው እረፍት ያገኛል ። እምቦጭን በተባበረ ክንድ ለማውደም ጊዜው ምቹ ነው ። የግድ ቴክኖሎጂ እስኪመጣ አንጠብቅም ። የክልሉ መንግስት የክተት ዘመቻ ያውጅልን ። አረሙን ለማውደም አፋጣኙ ሰውኛ መፍትሄው መንቀል ከሆነ ይኸ የከተማ ጮርናቄ ያወዛው መዳፍ ሁሉ መፈተኛው አሁን ነው ። ደጉ ባላገሩ ፤ ከተማ ለምኔ ፤ ትዝ አለኝ እርሻችን የሚል የጮሌ ዘፈን ከተማ መሃል እያሸረገዱ በገበሬው ስም ፈረንካ ማፈስና የገበሬው የመከራ ቀን ሲገለጥ ወደ ማጀት ገብቶ መሸጎጥ ዘመናዊ ማውደልደል ይባላል ። የገበሬውን ህመምና ስቃይ በክሊፕ ሙዚቃ ሳይሆን ከቅብቅቡና ከእርሻው ድረስ ዘልቆ መጋፈጥ ግድ ይላል ። ዝርዝር ፕሮግራም ይውጣ ። የዘመቻው አጋፋሪዎች የሰራዊቱን ብዛት ይንገሩንና ከወደ ወሎ በኩል የሚዘምተውን የሰራዊት ብዛት ያሳውቁን ። ከወሎ ምድር ብዙ እንደሚጠበቅብን እናምናለን ። ወሎ በረሃብ ጎኑ በተጎዳ ጊዜ እባክህ ናልኝ ብሎ ከጎኑ መሬት እየሰጠ ያን ክፉ ቀን እንዲያሳልፍ የወንድም አደራውን የተወጣውን አርማጫው ጎጄ ዛሬ መጤና ድንገቴ አረማሞ ደጁ ድረስ መጥቶ እንቧ ከረዩ ሲልበት ወሎዬ እሱን አይዞህ ማለት ከረሳን ቀኛችን ትርሳን! !!! ክተት ብለን ጊዮን ምድሩን በእጃችንና በእግራችን ቧጥጠን ከእምቦጭ ወረራ እንታደገዋለን ።
ክተት ይታወጅ! !!!!
—/›
እኔም እላለሁ… የጣናን እምቦጭ አረም ነቃቅሎ በመጣል ቢያንስ ጊዜያዊ መፍትሔ ለማምጣት ወገን መንገዱን ያመቻችና ሁላችንም እንዝመት፡፡ እኔ በግሌ የዓመት ረፍቴን በሙሉ ለዚህ ዘመቻ እጠቀመዋለሁ፡፡

Filed in: Amharic