>

ኑ አብረን እንሙት - ገራሚ ግጥም !!!

ከናቲ ቪሎፒያ 

(ጋዜጠኛ ፣ ፀሃፊ እና ክሬቲቭ ዲዛይነር)
✍  ወንጌለ አርሴናል – ወንጌለ ማንቺስተር
ትንቢተ ቢዮንሴ – መፅሃፈ ቬንገር
ትምህርተ ሞሪኖህ – ህግጋተ ክላምፕ
መልእክተ ጄዚ – ሰቆቃወ ትራምፕ
ኦሪት ዘ አሜሪካ – ኦሪት ዘ ሆሊውድ
ምፅአተ እስራኤል – ትንቢተ ቦሊውድ
ራእየ ማዶና – መልእክተ ባይበር
ኦሪት ዘ ኦባማ – ወንጌለ መ’ሸበር
ምስጢረ ሮናልዶ – ዜና ባርሴሎና
ሆኗል ይህ ዘመን … ጌታችን ሆይ ና ና !

🌕   እስኪ አብረን እንሙት …. 🌕

✍ እንደ አሳ ኖሮ – ሲሙልጨለጭ ከርሞ
በዘመን ፌርማታ – ሲሽከረከር  ከስሞ
አቋም እና አቅም – የለውም አትግፋው
በብልት ማሰቢያው – ለፅናት አታልፋው
ዋ …
ተወው ይሙትበት – ኖረህ አታኑረው
የእስስት አመሉን – ደርሰህ ላትቀይረው !

🌕  እስኪ አብረን እንሙት …. 🌕

✍ ትዳር እና አዳር – በዝተው በመንደሩ
ተጋብተው ሲያበቁ – ተፋተው ለሚያድሩ
በልጆች ሜዳ ላይ –  ፍ …ቅርን አንጥፈው
ለፀብ ተማምለው – ለእርቁ ተኳርፈው
መኖርን ለሞቱት – ለነዛ ምስኪኖች
የዛሬ ትዳሮች – የነገ ጊንጥሎች
ዋ …
ተዋቸው ይሙቱ – አታብዛ ማስማማት
ወትሮም ሊፋቱ ነው – ማግባትን ያገቧት!

🌕   እስኪ  አብረን እንሙት …. 🌕

✍ ለዚህ ብኩን ትውልድ – ፋሽን ላንጋደደው
በማበድ እርካታ – ለሚጨማለቀው
ቡቱቱ እና ኮተት – ደርቦ ገላው ላይ
የውስጡን ውጥንቅጥ – አደባባይ ሲያሳይ
በሱሪው ቀዳዳ – በውስጡም ቀዳዳ
መሸከም ላመመው  – የህይወቱን ፍዳ
ዋ …
ከአንገት በታች ሆኖ  – የማሰቡ ርዝመት
“ስርአት” አትበለው – ተወው ይሙትበት !!!

🌕  እስኪ አብረን እንሙት …. 🌕

✍ የሃይማኖት አባት – ተብለው ሲያበቁ
ተዋቸው ይሙቱ – ሳይሸማቀቁ
መስበክ ቀላል ሆኖ – መኖር ሲከብዳቸው
አይተን እንዳላየን – ሆነን ስንቀርባቸው
ወንጌል ቁርአኑን – ተናግረው ሲያበቁ
በዘር እና ቅጥፈት – ተባልተው አለቁ
ዋ …
ኑሮ በዘዴ ነው – ሃይማኖትም የግል
በዝምታ እየው – አታብዛ ግልግል
ተዋቸው ይሙቱ – ፍቅርን እ’ያጣሉ
መሬት ሲኦል በዝቷል – ሄደው ይካፈሉ !

🌕   እስኪ አብረን እንሙት …. 🌕

✍ በተግባር ሜዳ ላይ – ለሚሰወርብህ
መንፃትን ቆሽሾ  – ለሚደሰኩርህ
ማመንን አንብቦ – አንተን ለሚመክርህ
ለዚህ ዘመን ምሁር – የሃይማኖት መሪ
ጥያቄ ማብዛት ነው – ትልቁ አስተማሪ !
ዋ …
ጠይቀው ጠይቀው – መንፈሱ እስኪጨንቀው
ያልኖረበት ህይወት – እስኪያጨማልቀው
አንብቦ እንዳይመልስ – የንባብ ጋጋታ
የጥያቄውን መልስ – ከምግባሩ ፍታ !

🌕   ኑ አብረን እንሙት …. 🌕

✍ በሶሻል ሚዲያው – መክሸፍ በበዛበት
የማንነት በሮች – በሚከፈቱበት
የስድብ ጋጋታን – የዝቅጠት ከፍታን
የዘር ጥንባጓሮን – የክፋት ሃተታን
ማንነቱን ቀብሮ – ለሚያለማምድህ
በአካል ምርጥ ሰው – ሆኖ ለኖረብህ
ዋ …
ተወው ይኑርበት – ተወው ይሙትበት
ወትሮም ጤነኛ ነው – መንገድ የጠፋበት!

🌕እናም እልሃለሁ ….. እደግምልሃለሁ ! 🌕

✍  ወንጌለ አርሴናል – ወንጌለ ማንቺስተር
ትንቢተ ቢዮንሴ – መፅሃፈ ቬንገር
ትምህርተ ሞሪኖህ – ህግጋተ ክላምፕ
መልእክተ ጄዚ – ሰቆቃወ ትራምፕ
ኦሪት ዘ አሜሪካ – ኦሪት ዘ ሆሊውድ
ምፅአተ እስራኤል – ትንቢተ ቦሊውድ
ራእየ ማዶና – መልእክተ ባይበር
ኦሪት ዘ ኦባማ – ወንጌለ መ’ሸበር
ምስጢረ ሮናልዶ – ዜና ባርሴሎና
ሆኗል ይህ ዘመን … ጌታችን ሆይ ና ና ….

✍ እስኪመጣ ጌታ – መምጣት ከቻለበት
አንተም በዚህ ፅና – መሆንን እይበት

ዋ …

ከቆሻሻ ገንዳ – ነጭ ጨርቅ አጠብቅ
ለእድፋም ዘመን – ሃሰትን አታርቅ
ደግሞስ ስትነፃ – ማን ያጨበጭባል ?
የሰው ሁሉ አይን – ስህተት ላይ ይሮጣል !

🌕  …. ቢሆንም …. ቢሆንም … 🌕

✍ በጠማማ ስሌት – ዘመንን አትለካ
ድሮም ሰካራም ነው – ዞሮበት ‘ሚያሽካካ
ከእውነት ተስማማ – አድፈህ አትሳቀቅ
ቆመህ አትባላ – ሞተህ አትታረቅ !!!

♦♦♦♦♦♦♦♦♦♦♦♦♦♦♦♦
© ከናቲ ቪሎፒያ 2009 ሰኔ
(ጋዜጠኛ ፣ ፀሃፊ እና ክሬቲቭ ዲዛይነር)

Filed in: Amharic