>

የማለዳው ወግ...በትንሳኤው ዋዜማ የልጅ አዋቂው አቀንቃኝ ብርቱ ምክር ! [ነቢዩ ሲራክ]

* ቢጎል እንደራው ከሞሰቡ እናት በሌላ ይቀየራል ወይም ? ”
* “ባልፍም ኖሬ ፣ ስል እናት ምድሬ ፣ እሷ ናት ክብሬ ፣ ኸረ እኔስ ሀገሬ“
* በርቱው የጥበብ ሰው ቴዲ አፍሮ ዛሬም ስለ ፍቅር፣ ህብረትና አንድነት ያቀነቅናል
* የልጅ አዋቂው Teddy Afro – ETHIOPIA – ኢትዮጵያ – [New! Official single 2017] ለገባንም ፣ ላልገባን ፣ እንዳይገባን ለምንፈልግም ይመክራል
* መካሪ ሽማግሌ በጠፋበት የሀገሬ ሰማይ ስር የልጅ አዋቂው በጽናት ቆሞ ይመክረናል

ማልጀ ለስራ ልወጣ ስዘገጃጅ ኮሽታ የሚቀሰቅሳቸው ዘኩና ማሀሌት ዛሬ የሉም ፤ የተንሳኤውን እና የፋሲካን ታላቅ በዓል ከአያቶቻቸው ጋር ለማክበር ወደ ሀገር ቤት ካቀኑ ገና የደፈኑት ሁለት ቀናት ቢሆንም ሁለቱ ቀናት የወራት ያህል ሩቅ ሆነውብኛል … እነዘኩ ከእንቅልፍ ነቅተው ከወዲያ ወዲህ ደክ ደክ እያሉ የምቀማምሰውን ቁርስ ማተረማመስም ሆነ በማለዳው መንፈስ በብላቴና ልጆቸ የታወደው የቤቴ ግርግር ድባብ ጸጥ ረጭ እንዳለ ነው … በጣም ይደብራል ፤ ያስፈራልም !ግን ህይዎት ነውና በምስጋና ቀኑን እጀምረዋለሁ !

የማለዳ መረጃዎችን ለማቃኘት ወደ መረጃ መረቡ ስቀርብ በውስጥ መስመር የደረሱኝን በርካታ መልዕክቶችን መካከለ ከብዙ ወዳጆቸ የደረሰኝ የ እንኳን አደረሰህ መልዕክት አብዛኛው የብርቱው ጥበበኛ የቴዲ አፍሮ አዲስ ዘፈን ማስፈንጠሪያ አለበት … የሀገሬ ህዝበ ክርስትያን የጸሎት ፤ ምህላው የህማማት የመጨረሻ ቀን ቢሆንም የፍቅር ህብረት ሰናኪውን ዘፈን መስማት ከሃጥያት ስርየቱ በዝቶብኝ ብቻ ሳይሆን የልጅ አዋቂውን ” ኢትዮጵያ “ የሚል አዲስ ዘፈን ለማዳመጥ ስጋዊ ህይዎቱ መንፈሳዊውን ማንነት ያሸነፈው መሰለኝና ለራሴ ተሸማቀቅኩ … በእርግጥም ሆኗል

ቴዲ ” ኢትዮጵያ “ የሚል ስም የተሰራጨው ጣዕመ ዜማ ” ደካማውን ማንነት ሸነፈበት ዋንኛ ምክንያት የኢትዮጵያ በመውደድ ድህነት መኖሩ አይደለም ፤ ኢትዮጵያን መውደድ የሚሉት የፍቅር አባዜ ግን አለ የሚያነሆልል … ” እንኳን ሰማይ ላይ ባንዴራሽን አይቶ ፤ ኢትዮጵያ ሲጠራ ማን ዝም ይላል ሰምቶ !“ ይለናል ቴዲ እማኝ ምስክርነቱን በሰጠበት የኢትዮጵያ ዜማው …

እውነት ነው ! ኢትዮጵያውያን ተለያይተንም እንኳ በልዩነት አምነን ፤ በሚያቀራርበን ተዋህደን ፤ ስለ አንዲት ባንዴራ ፤ ስለ አንዲት እናት ምድር እናት ሀገርና አንድ ህዝብ ትንሳኤ በህብረት እንቆም ዘንድ ሲመክር ሲዘክረን የባጀው አንደበተ ርቱዕና ድምጸ መረዋ ቴዎድሮስ ካሳሁን ዛሬም የደከመ መንፈስን ሽቅብ በሚያነቃቃ ጣዕመ ዜማን ይዞልን በፋሲካው የትንሳኤ ዋዜማ ተከስቷል !

በኢትዮጵያ ፍቅር የተነደፈው የልጅ አዋቂው ቴዲ በፍቅር ፣ በህብረትና አንድነት ሰባኪ መረዋ ድምጹ በኢትዮጵያዊነት ኩሩ መንገድ ስንጓዝ አበሳችን ለበዛ ፤ የጨለመ ተስፋውን ብርሃን እናይ ዘንድ ፣ በጭቆና የተንገላታ ማንነታችን ከድካሙ ያገግም ዘንድ ተስፈኞችን በእምነታችን እንድንጸና ዘንድሮም በረቀቀ የጥበብ ክህሎቱ እያዋዛ የእናት ፍቅሩን ጥልቅ ስሜት ያዘክረዋል ፤ የምናውቀው የምታውቁት ገሃድ እውነቱን ያስተምረናል … ቢጎል እንጀራው ከሞሰቡ እናት በሌላ ይቀየራል ወይም ?እያለም መካሪ ሽማግሌ በጠፋበት የሀገሬ ሰማይ ስር የልጅ አዋቂው በጽናት ቆሞ ይመክረናል !

በዘመነ ኖህ የውሃ ጥፋት ዘመን ለቀረው አለም በአንድ አምላክ የተገባውን ቃል ኪዳን ምልክት አረንጓዴ ቢጫና ቀይ ባንዴራ ሰንደቅ መለያዋ ያደረገች ሀገሩንና ጀግኖቿን የማይጠገበው መልክአ ምድሯንና አኩሪ ታሪኳን እነሆ ዛሬም ቴዲ በክብር ያወሳሳል ” እናት ክብር ሞገሴ ኢትዮጵያ እሷ ናት ” ሲል “በሰማዩ ላይ ቢታይ ቀለም ፣ የእሷ ነው እንጅ ሌላ አይደለም ” እያለ ለገባንም ፣ ላልገባንም ፣ እንዳይገባን ለምንፈልግም ደረቅ እውነቱን በዜማ ለውሶ በትንሳኤው ዋዜማ አቅርቦልናል …

ባለ መረዋ ድምጹ ቴዲ ጎድሎ የከፋንን ብዙሃንን ” በእምነታችሁ ጽኑ! ” በሚል መንፈስ ሲያጽናናንም ይመስላል ”…ተውኝ ይውጣልኝ ልጥራት ደጋግሜ ” …ይልና ሲቀጥል ” ቢጎል እንደራው ከሞሰቡ ላይ ፤ እናት በሌላ ይቀየራል ወይም ? ” ሲል ብርቱ ምክሩን ይለግሰናል …

” ባልፍልም ኖሬ ፣ ስለ እናት ምድሬ
እሷ ናት ክብሬ ፣ ኽረ እኔ አገሬ

ስንት የሞቱልሽ ለክብርሽ ዘብ አድረው
አልፈው ሲነኩሽ ባህርሽን ተሻግረው
የጀግኖቸ ሀገር ያዳም እግር አሻራ
ፈለገ ግዮን ያንች ስም ሲጠራ

እንኳን ሰማይ ላይ ባዴራሽን አይቶ
ስምሽ ሲጠራ ማን ዝም ይላል ሰምቶ

ቀስተ ደመና ሰማይ መቀነቱን ባንዴራሽን ታጥቆ
አርማሽ የታተመ እንኳን ባለም መዳፍ በአርያም ታውቆ

የተራሮች አናት ዘብ የቆሙልሽ ቤት ያክሱሟ ራስ ጦቢያ
የፍጥረት በር ነሽ የክብ አለም ምዕራፍ ዞሮ መጀመሪያ

በሰማዩ ላይ ቢታይ ቀለም
የእሷ ነው እንጅ ሌላ አይደለም

የመጭው ዘመን ፊት ናት መሪ
ዛሬ አለም ቢላት ኋላ ቀሪ

ተውኝ ይውጣልኝ ልጥራት ደጋግሜ
ኢትዮጵያ ማለት ለኔ አይደል ወይ ስሜ
ቢጎል እንጀራው ከመሶቡ ላይ
እናት በሌላ ይቀየራል ወይ?

ይዤ አላነሳም እጄን ከቀሚሷ
እናት እኮ ናት ተስፋ አልቆርጥ በሷ
የሷን ውለታ ከፍሎ ሳይጨርሰው
ኢትዮፕያ ሲባል አብሮ አይልም ወይ ሰው…

የሰሎሞን እፅ ነሽ ፣ የቅዱሳን እንባ ያበቀለሽ ቅጠል
ዛሬ አዲስ አይደለም በለኮሰው እሳት የነካሽ ሲቃጠል

ሳይወሰን ዝናሽ በቅርሶችሽ ድርሳን ባድባራት ታሪኩ
ነቢይ አይተው ከሩቅ ያሉልሽ በመጽሐፍ ኢትዮጵያን አትንኩ

ተውኝ ይውጣልኝ ልጥራት ደጋግሜ
ኢትዮጵያ ሀገሬ ፣ ባንች አይደል ወይ ክብሬ ”

ይለናል ብርቱው የጥበብ ሰው የኢትዮጵያ ልጅ ቴዲ አፍሮ

የትንሳኤው በዓል በተስፋ ደስታ መንፈስ እናከብረው ዘንድ ” ይዤ አላነሳም እጄን ከቀሚሷ ፣ እናት እኮ ናት ተስፋ አልቆርጥ በሷ … ” እያልን በተስፋ በዓሉን ስናከብር ኢትዮጵያ እንደማትጠፋ በዳግማዊ የቴዲ ምክር እቆዝም ዘንድ ” የሰሎሞን እፅ ነሽ ፣ የቅዱሳን እንባ ያበቀለሽ ቅጠል ፣ ዛሬ አዲስ አይደለም በለኮሰው እሳት የነካሽ ሲቃጠል ” በሚለው ዜማ ትንሳኤዋን በተስፋ መናፈቄ አልቀረም ! ” ሳይወሰን ዝናሽ በቅርሶችሽ ድርሳን ባድባራት ታሪኩ ፣ ነቢይ አይተው ከሩቅ ያሉልሽ በመጽሐፍ ኢትዮጵያን አትንኩ ! ” ብሎ ክብር ምስጥሯል እንደተቀኘላት ጉምቱ ባለጥበብ ” ከኢትዮጵያ አትጠፋም ” ወደ ” ኢትዮጵያን አትንኩ ከቁዘማው ወጥቸ በምሉዕ ተስፋ ልነቃቃ በመዘጋጀት ዋዜማውና ታላቁ የትንሳኤ በአል የሰላም ይሆንላችሁ ዘንድ ምኞቴን በማቅረብ ነው !

ነቢዩ ሲራክ
ሚያዝያ 7 ቀን 2009 ዓም

Filed in: Amharic