>

የሕይወት ዋጋ [ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም]

profeser Mesfen Weldemariam Quateroበ2009 ዓ.ም. ቆሼ የሚባል ሰፈር ወይም መንደር ተፈጠረ፤ ቆሼ ማለት ቆሻሻን ማቆላመጫ ነው፤ ቆሻሽዬ ማለት ነው፤ ቆሼ የቆሻሻ ተራራ ነው፤ በዚያ የቆሻሻ ተራራ ዙሪያ መሄጃ የሌላቸው ሰፈሩበት፤ ጥንት ሴትዮዋ እንዳለችው፡-

እሾህ ብቻ ሆነ እግሬን ብዳብሰው
እንዴት መራመጃ መሄጃ ያጣል ሰው!

ሴትዮዋ ይህንን ያንጎራጎረችው ከብዙ ትውልዶች በፊት ነው፤ ጉልበተኞች የኢትዮጵያን ሰዓት ሰንገው ስለያዙት አይነቀነቅም! ባለህበት ሂድ! ነው፤ ዛሬም መሄጃ የለም፤ ቆሻሻንም የሙጢኝ ቢሉ ማምለጥ አይቻልም፡፡

እነዚህ አንድ መቶ አሥራ ሦስት ሟቾች በርግጥ ሰዎች ናቸው? በርግጥ ኢትዮጵያን ናቸው? የምናገረው ጠፍቶኛልና ጥያቄዎች ብቻ ልጠይቅ፡– ቤታቸውን ጉልበተኞች አፍርሰውባቸው፣ መሬታቸውን ሰማይ-ጠቀስ ወይም መንገድ ለመሥራት መሬታቸውን ወስደውባቸው የሚደርሱበት አጥተው፣ ባዶ ቦታ ፈልገው የፕላስቲክ መጠለያቸውን እየሠሩ ግፍን አሜን ብለው በሰላም ተቀብለው ኑሮ ካሉት መቃብር ይሞቃል እያሉ ቀኖችን ሲቆጥሩ ቆሻሻ መጣያው ደባል የሆነባቸው መቼ ነው? ወይስ ቆሻሻ መጣያው ቀድሞ እነሱ ደባል ሆነውት ነው? ጥያቄው ማን ቀደመ ሳይሆን ቆሻሻውና መጠለያ ፈላጊዎቹ አብረው አንዲኖሩ ፈቃድ የሰጣቸው ማን ነው የሚል ነው? የመጠለያ ፈላጊዎቹን ቤት ያፈረሰውና የቆሻሻውን ተራራ የሚክበው ጉልበተኛ ወይም ጉልበተኞች የተለያዩ ናቸው? ወይስ አንድ ነው? አንድ ከሆነ እውር-ደንቆሮ ሳይሆን አይቀርም፤ በማን-አለብኝነት ልባቸው ያበጠ ግዴለሾች ሳይሆኑ አይቀርም፡፡

አንድ መቶ አሥራ ሦስቱና ሌሎቹም ዜጎች ቢሆኑ፣ ማለት የአገሩን ባለቤትነት ከጉልበተኞች ጋር በእኩልነት የሚጋሩ ቢሆኑ፣ ሌሎች ዜጎች እነዚህ በቆሻሻ የተበሉት ወገኖቻቸው መሆናቸውን ቢገነዘቡ ቆሻሻና ዜግነት እንደተደባለቁ ማወቃቸው ይቀራል? ዋናው ችግራችንስ ይኸው ሳይሆን ይቀራል?
የሞቱትን ነፍሳቸውን ይማር ማለቱ አጉል ወግ ነው፤ አጥንታቸውን እሾህ ያርገው ማለቱ ሳይሻል አይቀርም!

Filed in: Amharic